ከኤሊያስ
ቤት ለማግኘት ትዳር እየፈረሰ ነው (ግን ፌክ ነው!)
አንዲት የሥራ ባልደረባዬ እህት አለች - ነገር የምታውቅ፡፡ (ነገረኛ አልወጣኝም!) ጨዋታ አዋቂ፣ ተረበኛ፣ ቀልድና ፌዝ መፍጠር የሚሆንላት ማለቴ ነው። ፈረንጆቹ humorist እንደሚሉት፡፡ እናላችሁ… በሳምንት አንድ “የሰቀለ” ቀልድ ወይም ተረብ አታጣም - እቺ የባልደረባዬ እህት፡፡ አንዳንዱ ደሙን የሚያመርትበትን ጉዳይ እሷ ቀልዳ ትዝናናበታለች፡፡ ለራሷ መዝናናት ብቻ ሳይሆን ለሰውም ትተርፋለች። የሳቅና የጨዋታ ምንጭ ናት - በአጭሩ፡፡ ይሄንን ችሎታ ለማን እንደተመኘሁት ታውቃላችሁ? ለአገሬ ፖለቲከኞች - ለገዢውም ለተቃዋሚውም፤ ለወጣቱም ለአዛውንቱም፤ ለገጠሩም ለከተሜውም፤ ለአገር ቤቱም ለዳያስፖራውም፤ ለምሁሩም ለተማሪውም በቃ ሁሉም ቀልድ አዋቂና ተጫዋች ቢሆን እንዴት ይመቸኝ ነበር መሰላችሁ! እኔማ እነኢህአዴግ ብቻ ሳይሆኑ ራሱ መንግስትም (ኢህአዴግና መንግስት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው እንዳትሉኝ!) ቀልድ አዋቂና ተጫዋች ቢሆን ደስታውን አልችለውም! (ለራሱም ደስታ እኮ ነው) ዲስኩር አበዛሁ አይደል… አሁን ወደቁም ነገሩ፡፡
ያቺ የባልደረባዬ እህት ሰሞኑን ምን አለች መሰላችሁ? “የኢህአዴግ ሰልፍ ከእሁዱ የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ በለጠ እኮ!” ግራ ገባኝ፡፡ ኢህአዴግ መቼ ነው ሰልፍ የጠራው - ለራሴ ያቀረብኩት ጥያቄ ነበር፡፡ ሌላው ቢቀር በኢቴቪ አይዘገብም እንዴ? እንኳን የ”ገዢያችን” ሰልፍ የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ ተዘግቧል እኮ (አንዳንዶች “ተንኮል ታስቦ ነው” ቢሉም) ነገርየው እንዳልገባኝ ተናገርኩ - ኢህአዴግ ስላደረገው ሰልፍ አላውቅም በማለት (ከ2002 ምርጫ በኋላ ማለቴ ነው!) ለካስ እሷ የምትለው ሌላ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ደብተር ለመክፈት የተሰለፈውን ህዝብ ማለቷ ነው - ቤት ፈላጊውን፡፡
በእርግጥ ይሄኛውም ሰላማዊ ሰልፍ ነው “የመኖሪያ ቤት ብሶት የወለደው የአዲስ አበባ ነዋሪ” ቤት ለማግኘት ያደረገው ሰልፍ!! ሁለቱም ሰልፎች እኮ አንድ ናቸው - የኢህአዴግም የሰማያዊ ፓርቲም፡፡ እንዴት አትሉም? ሁለቱም የመብት ጥያቄ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ልዩነታቸው ምን መሰላችሁ? አንዱ በተቃውሞ፣ ሌላው በድጋፍ መደረጋቸው ነው፡፡ (የባንኩን እንደ ድጋፍ ሰልፍ ቁጠሩት) ግን እኮ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሰልፍ መውጣት ከጀመረ ከረምረም ብሏል፡፡ ቆይ መቼ ነው ለታክሲ መሰለፍ የተጀመረው? እውነቴን እኮ ነው…የትራንስፖርት ወረፋም እኮ ሰላማዊ ሰልፍ ነው - በውዴታ ሳይሆን በግዳጅ የሚደረግ፡፡ (ዕድሜ ለኢህአዴግ!) እኔ የምለው ግን… በቃ ባቡሩ ሥራ ካልጀመረ የትራንስፖርት ችግር ላይፈታ ነው!፡ ትንሽ ተስፋ ያደረግሁት ምን ነበር መሰላችሁ? ከአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ጋር ተያይዞ የታክሲ ወረፋ እልባት ያገኛል ብዬ ገምቼ ነበር፡፡
(ለእንግዶቹ ሲባል የማንሆነው የለም ብዬ እኮ ነው!) ሆኖም ግምቴ ግምት ሆኖ ቀረ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ምን ወሬ እንደሰማሁ ታውቃላችሁ? ከአዲስ የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ጋር በተገናኘ ውልና ማስረጃ ቢሮ በፍቺ ማመልከቻ ተጨናንቋል አሉ (የጋብቻ ፍቺ እኮ ነው!) ወይ ጉድ! ቤቱ ሲገኝ ጋብቻው ፈረሰ ማለት እኮ ነው! ፍቺው ግን የምር አይደለም አሉ፡፡ “ፌክ” ፍቺ ነው! ፍቺውን የሚፈጽሙት ቤት ለማግኘት ነው፡፡ ባልም ሚስትም በነፍስ ወከፍ አንድ አንድ ኮንዶሚኒየም እጃቸው ለማስገባት ህጋዊ ትዳራቸውን ይቀዳሉ (ጊዜው ከፍቷል!) ግን እኮ ህጋዊ ያልሆነ ትዳር ይቀጥላል! በዲቪ አሜሪካ ለመሄድ ስንቱ “ፌክ” ጋብቻ እየፈፀመ የተሳካለትም ጉድ የሆነም እንዳለ እናውቃለን፡፡ አሁን ደግሞ “ፌክ” ፍቺ መጣ እየተባለ ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ መስተዳድሩ በአዲሱ የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ “ህገወጦችን ለጠቆመ 15 በመቶ ወሮታ ይከፈለዋል” ብሏል፡፡ ህገወጦችን ጠቁሞ ገንዘብ ማግኘት እኮ ክፋት የለውም፡፡ እኔን ያሳሰበኝ ምን መሰላችሁ … ነገርየው እንደ ዋና መተዳደርያ እንዳይቆጠር ነው! (የፖሊስ ስራ መስሎኝ!) እኔ የምላችሁ … የህዳሴው ግድብ ጉድ አፈላ አይደለ! (እዚህ ሳይሆን ካይሮ!) እውነት ግን ምንድነው ግብፆቹ የሚሉት? (በ21ኛው ክ/ዘመን ጦርነት ማሰብ እኮ “ሼም” ነው!) ከሁሉም ደግሞ ምን ገረመኝ መሰላችሁ?
ለአደባባይ መብቃት የሌለበት ውይይት (ውይይት ሳይሆን ሴራ እኮ ነው!) በስህተት በቲቪ ላይቭ ተላለፈ መባሉ ነው! ቅድም የጠቀስኩላችሁ የባልደረባዬ እህት፤ የግብፅ ተቃዋሚዎች በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈት መመካከራቸውን ስትሰማ፤ እንደ አብዛኞቻችን “ዘራፍ” ለማለት አልቃጣትም። የግድቡ ጉዳይ እንደሚመለከታት የገለፀችው “ከህዳሴው ጋር እኮ ቦንድ አለኝ!” በማለት ነው። (ቅኔ እኮ ነው!) እንግዲህ ሰሙ የገዛቸውን ቦንድ የሚጠቁም ነው፡፡ (ባለ 50 ሺ ወይም ባለ 100ሺ ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል) ወርቁ ደግሞ Bond ከሚለው የእንግሊዝኛው ቃል ይመዘዛል - ትስስር፣ ቁርኝት፣ እትብት፣ ደም፣ እናት አገር… እንደ ማለት ነው፡፡ አንዱ ወዳጄ ደግሞ “የዋህ ናቸው” አለ - የኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሸፈቱ አማፂያንን ለመደገፍ በምስጢር ተመካክረዋል የተባሉትን የግብፅ ተቃዋሚዎች፡፡ “እነዚህ ምን የዋህ ናቸው … አደጋ እንጂ!” አልኩኝ - ድንገት ወኔዬ ተነስቶብኝ፡፡
“የኢትዮጵያን ታሪክ ባያውቁ ነው!” “እንዴት ማለት … እነሱ እኮ ሃሳባቸው አማፂያንን እያስታጠቁ ኢትዮጵያን ሰላም ሊነሱ ነው!” “የሚታጠቅላቸው ሲያገኙ አይደል …” “ቆይ ምን እያልክ ነው … አማፂያን እንደግፋችሁ ሲባሉ እምቢ ይላሉ ነው የምትለው?” ጠየቅሁት፤ ግራ ገብቶኝ “ዓላማቸው የህዳሴው ግድብ እንዳይሰራ መሆኑን እያወቀ ከእነሱ ጋር የሚያብር ኢትዮጵያዊ የለም!” አለኝ ፍርጥም ብሎ፡፡ “መንግስት በትጥቅ ትግል እንጂ በሰላም እሺ አይልም ብለው የሸፈቱትስ?” በጥርጣሬ የተጠቀለለ ጥያቄ ሰነዘርኩኝ፡፡ “በመንግስት ላይ የሸፈተ እኮ በአገሩ ላይ ሸፈተ ማለት አይደለም … ኢትዮጵያዊ በአገሩ ጉዳይ ቀልድ አያቅም … አንድ ነው!” አለኝ በእልህ ተሞልቶ፡፡ (እንደ አፍህ ያድርገው አልኩት - በልቤ!) እስቲ ከአባይ ጉዳይ ወጥተን ደግሞ ወደ ሰላማዊ ሰልፍ እንግባ (እንሰለፍ አልወጣኝም!) ቅድም የጠቀስኩት፣ የሰማያዊ ፓርቲ የተቃውሞ ሰልፍ ጉዳይ ማለቴ ነው፡፡
ጠዋት ላይ የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ኢህአዴግ ማታ በኢቴቪ ተቃወመው አይደል! (ተቃውሞን በተቃውሞ ማለት እኮ ነው!) ይሄውላችሁ … ኢህአዴግ ለምን ሰልፉን ተቃወመ እያልኩ አይደለም (ህገመንግስታዊ መብቱ ነው!) እኔ ማንሳት የፈለግሁት ሰማያዊ ፓርት ጉዳያቸው በፍ/ቤት የተያዘ ተከሳሾችን “ይፈቱ” ሲል መጠየቁ በህግ ስርዓቱ ላይ ጫና ለማድረስ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ እንዳለው የሚያሳይ ነው በማለት “ህገ መንግስት ጥሷል” … ሲል መወንጀሉን በተመለከተ ነው፡፡ እንግዲህ የተከሰሱና በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ ሰዎችን ጉዳይ ማንሳት (በበጐም በክፉም!) ህገ መንግስት መጣስ ነው ከተባለ … ግለሰቦቹ እንደተያዙ ኢቴቪ ያስተላለፈው ዶክመንታሪ ፊልም ጉዳይም እንዳይረሳ ለማለት ያህል ነው፡፡ (ጉዳያቸው በፍ/ቤት ውሳኔ ሳያገኝ እኮ ነው ያሰራጨው!) እኔ ግን ለጦቢያ ምን እንደምመኝ ታውቃላችሁ? ህገ መንግስት መጣስና አለመጣሱን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ (እቅጯን) የሚናገር ዘመናዊ መሳሪያ ማሰራት! እንዴ … ከብዙ ውዝግብ እኮ ነው የሚያወጣን!! አያችሁ… መሳሪያው ከተሰራ ተጠርጣሪውን ይዞ ደሙን ወይም ሽንቱን መመርመር ብቻ እኮ ነው ወይም ሌላ የምርመራ ዘዴ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዛ በኋላ ማን ህገ መንግስቱን አክብሮ ይንቀሳቀሳል፣ ማንስ ይጥሳል የሚለውን በደንብ እንለያለን! (መሆንና መምሰል እኮ ይለያያል!) እናላችሁ … የዓለም የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ሌላ ዲስኩራቸውን ትተው ይሄን መሳሪያ ቢፈለስፉ ትልቅ ባለውለታችን ይሆኑ ነበር፡፡ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ!
No comments:
Post a Comment