ከ ኤልያስ
ምቀኞች ቢበዙልን እኮ ባለ3 ዲጂት እድገት እናስመዘግብ ነበር !
አንዳንዴ የአባቶችን ተረትና ምሳሌ እንዲሁም ብሂል ዝም ብሎ ማጣጣል “ፌር” አይመስለኝም። አንዳንድ ቀለም የዘለቃቸው የጦቢያ ምሁሮችና ዘመናይ ነን ባዮች ግን እነዚህን ሥነ ቃሎች ለድህነታችንና ኋላ ቀርነታችን ሰበብ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ አላወቁም እንጂ ጦቢያችን ከእነመንግስቷ ቆማ የምትሄደው በእነዚህ ወርቃማ አባባሎች እኮ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር---ከእነዚህ ምሁር ነን ባዮች እኮ የጥንቶቹ አባቶቻችን በብዙ ነገር ሺ ጊዜ ይበልጧቸዋል፡፡ እናም “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” እላቸዋለሁ - የአባቶቻችንን ብሂሎች የሚተቹትን የጦቢያ ምሁሮች፡፡ ይሄን ግሳፄ የምሰነዝረው ግን ዝም ብዬ አይደለም፡፡
ብሂሎቹ ለጦቢያ የህልውና መሠረት መሆናቸውን ስለደረስኩበት ነው፡፡ ለዛሬ ልዩ ትኩረት አድርገን የምንፈትሸው ከጥንት የአባቶች አባባል ከወረስናቸው ሥነቃሎች መካከል “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለውን ወርቃማ ብሂል ነው፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ --- የጦቢያችን ህልውና የተመሰረተው ሙሉ በሙሉ በእዚህ ብሂል ላይ ነው፡፡ ብታምኑኝም ባታምኑኝም “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለው ሥነ ቃል ባይኖር ጦቢያችን አትኖርም ነበር፡፡ ጥናቴ እንደሚጠቁመው፤ የአበሻ ዘር ምቀኛ ያጣ ዕለት መኖር ያቆማል (አሳዛኝ ቢመስልም ሃቅ ነው!) በአጠቃላይ የዕድገታችን በሉት የስልጣኔያችን ወይም በኢህአዴግ ቋንቋ የህዳሴያችን መሰረቱ “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለው መሪ ሥነ ቃል ነው፡፡ አበሻ ሲፀልይ “ምቀኛ አታሳጣኝ” ይላል ሲባል አልሰማችሁም? ቀልድ ከመሰላችሁ እንደኔ ተሸውዳችኋል፡፡ ፈፅሞ የማያጠራጥር ሃቅ መሆኑን እኔ ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ - በመረጃም በማስረጃም፡፡ እንኳን ዜጐች ራሳቸው ፖለቲከኞችም ከዚህ ሌላ ፀሎት እንደሌላቸው በአሉባልታ ሳይሆን በሁነኛ መረጃ ደርሼበታለሁ፡፡
ለነገሩ “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለው ብሂል የጦቢያ የህልውና መሰረት የሆነው በኢህአዴግ ዘመን አይደለም፡፡ ከጃንሆይ ዘመን ጀምሮ ነው ይላል - የጥናት ውጤቴ፡፡ እስቲ ማስረጃዎችን እየመዘዝን ሃቁን እንፈትሽ፡፡ ከዚያ በፊት ግን ሰሞኑን በኢቴቪ “ሰው ለሰው” በተሰኘው ዝነኛ ድራማ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች ግራ ያጋባኝን ላጋራችሁ (አስተያየቱ ሰውኛ አይመስልም እኮ!) እንደ መሰለኝ “ሰው ለሰው” ወደ ቀጣዩ ሲዝን የመሸጋገሪያ አስተያየቶችን እያስተናገደ ነው፡፡ ባለፈው ረቡዕ ዕለት አስተያየት ከሰጡት ተመልካቾች መካከል ይበልጥ ትኩረቴን የሳበው አንድ ታዋቂ ኮሜድያን ነበር፡፡ በነገራችሁ ላይ ይሄ ኮሜድያን ሰዓሊና የዱር እንስሳት መብት ተሟጋች (Activist) መሆኑንም የሰማሁ መሰለኝ - በEBS የ“ጆሲ ቶክ ሾው” ላይ፡፡ እናላችሁ --- ስለ “ሰው ለሰው” ድራማ በሰጠው አስተያየት ኮሜዲ የሚመስል ደረቅ ቀልድ ለመፍጠር ሞክሯል (ህይወትና ኮሜዲ ተደበላልቆበታል ልበል?!) መጀመርያ ላይ እንዲህ አለ፡- “ሰው ለሰውን የማየው ባገኘሁበት ቦታ ነው፤ ቴሌቪዥን በሌለበትም አያለሁ” (ኮሜዲም ከሆነ ቱርጁማን ያስፈልገዋል) ቀጥሎ ደግሞ “ሰው ለሰውን የማየው በዓይኔ ነው” አለና አረፈው (በአፍንጫው ሊያይ አስቦ ነበር?) ከዚያም ከድራማው መወገድ አለባቸው የምላቸው (የፀረ-አብዮት እርምጃ መሰለው እንዴ!) አለና የገፀባህርያቱን ስም ይዘረዝር ገባ፡፡
በመጨረሻም “ሁሉም ገፀ ባህርያት ቢወገዱ ፊልሙ የበለጠ አሪፍ ይሆናል” ብሎ ቅጥአምባሩ የጠፋ ነገር ተናግሮ ሄደ፡፡ እኔ የምላችሁ … ድንገት በብሔራዊ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ ዘባርቆ መሰወር ይቻላል እንዴ? ቤታችን ድረስ መጥቶ ግራ አጋብቶን እኮ ነው ላጥ ያለው፡፡ ምናልባት ሁሉ ነገሬ የተሰራው ከኮሜዲ ነው ሊለን አስቦ ይሆን? (ለዛሬ አልተሳካልህም ብለነዋል!) ከሁሉም የገረሙኝ ደግሞ “የሰው ለሰው” ፕሮዱዩሰሮች ናቸው፡፡ ይሄንን በፌዝ የተሞላ “ፉገራ” ያቀረቡት ምን ይፈይድልናል ብለው ነው? ምናልባት ሊያዝናኑን አስበው ይሆን? (እነሱም አልተሳካላቸውም!) አሁን በቀጥታ የምናመራው “ምቀኛ አታሳጣኝ” ወደሚለው የጦቢያችን የዘወትር ፀሎት ነው፡፡ በዚህ ወጋችን ይሄ ብሂል የቱን ያህል ከማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወታችን ጋር በእጅጉ እንደተቆራኘ እንቃኛለን - ከሦስት መንግስታት አብነቶችን እየነቀስን፡፡ (ጥናቱ የንጉሱ፣ የደርግንና የኢህአዴግ መራሹን መንግስታት ያካትታል!) በሉ ከጃንሆይ ዘመን እንጀምር፡፡ በእጄ ላይ በገባው መረጃ መሰረት፤ ንጉሱ ትልቁን ጊዮን ሆቴል (ገዢ ያጣውን ማለቴ ነው!) እና ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትን አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አሰርተው ያጠናቀቁት “ምቀኛ አታሳጣኝ” በሚለው ብሂል ላይ ተመስርተው ነው፡፡ እንዴት ሆነ መሰላችሁ? የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫውን በኢትዮጵያ እንዲያደርግ ሃሳብ ሲቀርብ ብዙ የአፍሪካ አገራት ተመቅኝተውን ነበር - እማኞች እንደሚናገሩት፡፡
ምቀኝነታቸው ግን በበቂ ምክንያት ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ኢትዮጽያ በቂ ሆቴል እንደሌላት፣ አውሮፕላን ማረፍያ እንዳልገነባች፣ መንገድ እንዳልሰራችና ንፅህና እንደሚጐድላትም በዝርዝር አስረዱ። (ምቀኞቹ! ) ንጉሱና ሚኒስትሮቻቸው ይሄ ሁሉ ሃሰት መሆኑን ለማሳየት ነው በእልህና በቁርጠኝነት መትጋት የጀመሩት፡፡ ደግሞም ተሳካላቸው፡፡ በ9 ወር ውስጥ ጊዮን ሆቴል ተገነባ፡፡ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላንም ተሰራ፡፡ እኒያ ምቀኞች “ኩም” አሉ። የአፍሪካ አገራቱ ባይመቀኙንስ ኖሮ? ጊዮንም ኤርፖርትም መቼ እንደሚሰሩ ለማወቅ ይቸግራል፡፡ በነገራችሁ ላይ በአዲስ አበባ የቴሌቪዥን ስርጭት የተስፋፋውም ከዚሁ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጋር ተያይዞ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለው ብሂላችን ቀላል ጠቀመን! ወታራዊው የደርግ መንግስት እንዲያ በጦርነት ውስጥ ተመስጐ እንኳ ከአፍሪካ ግዙፉን የጦር ሰራዊት የገነባው እንዴትና ለምን ይመስላችኋል? መቼም ለአፍሪካ ሰላምን ለማስፈን ብሎ እንዳልነበር ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይልቁንም ከሶማሊያ ጀምሮ የጦቢያ ጥንካሬ የማያስደስታቸው የአፍሪካና የአረብ አገራት እንዳሉ ስለሚያውቅ ነው፡፡ እናም “ምቀኛ አታሳጠኝ” እያለ ራሱን በጦር ሃይል በደንብ አድርጐ አደረጀ (የማታ ማታ በኢህአዴግ ቢፈረካከስም!) ወደ ኢህአዴግ መራሹ መንግስትም ስንመጣ ነገሩ ተመሳሳይ ነው፡፡
ቀደም ሲል እንዳልኳችሁ ኢህአዴግም “ምቀኛ አታሳጣኝ” በሚል ፍልስፍናዊ ብሂል ነው የሚመራው (የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍናስ--እንዳትሉኝ) አሁን ለምሳሌ የኢትዮጵያን ህዝብ ከዳር እስከዳር አንቀሳቅሷል የተባለው የህዳሴ ግድብ ምቀኛ ባይኖርብን ይታሰብ ነበር? (የማይሆነውን!) ግብፆች- ኢትዮጵያ ለግድቡ ሥራ ከለጋሽ አገራት ብድር እንዳታገኝ ዘመቻ በመጀመራቸው እኮ ነው “መሃንዲሶቹ እኛው፣ ግንበኞቹ እኛው፣ የፋይናንስ ምንጮች እኛው---” ብለን ከኪሳችን አውጥተን ልንገነባ የተነሳነው። ለእልሃችንና ለቁርጠኝነታችን ሃይል የሆነን ምንድነው ከተባለ--- ያለ ምንም ጥርጥር የግብፆች ምቀኝነት ነው፡፡ እናላችሁ --- ግብፆቹ በዚያው ምቀኝነታቸው ቢቀጥሉልን በበለጠ ፍጥነት ግድቡን አጠናቀን ዓለምን ጉድ ያሰኘ የሪከርድ ባለቤት እንሆን ነበር (ጥቅሙ የጋራ ነው ብዬ እኮ ነው!) ሌላ የቅርብ ጊዜ መረጃም ልሰጣችሁ እችላለሁ። የቦሌ አዲሱ መንገድ በምን ያህል ፍጥነት ተሰርቶ እንደተጠናቀቀ ሳትታዘቡ አትቀሩም፡፡ (ኢህአዴግ አስማት የጀመረ የመሰላቸው አልጠፉም) ምናልባት የአፍሪካ ህብረት ምስረታ የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ባይኖር ኖሮ ስንት ዓመት እንደሚሟዘዝ መገመት ይቸግራል፡፡ አያችሁ ---ለበዓሉ ከመጡት መሪዎች መካከል የአፍሪካ ህብረት ከአዲስ አበባ ወደሌላ አፍሪካ አገር እንዲዛወር የሚሹ ምቀኞች እንዳሉ ኢህአዴግ “ነቄ” ነበር።
እናም ቻይናዎችን ከጉድ አውጡኝ ብሎ በጥቂት ወራት ውስጥ አስፋልቱን አስማት በሚመስል ፍጥነት አዘረጋው፡፡ አያችሁልኝ-- የምቀኛን ፓወር! ከማጂክ እኮ ይበልጣል! “ምቀኛ አታሳጠን” የጦቢያ የህልውና መሰረት ነው የምላችሁ ለዚህ እኮ ነው፡፡ በነገራችሁ ላይ በዚሁ የአፍሪካ ህብረት በዓል ላይ እንግዶቹ መጥተው እስኪሄዱ ድረስ ውሃና መብራት እንዳይጠፋ የተቻለው ሁሉ ጥረት ይደረጋል ተብለን እንደነበር ትዝ ይለኛል (አልተሳካም እንጂ!) እኛ እኮ እንዲህ ከተባልን 21 ዓመት ሊሞላን ምን ቀረን፡፡ ግን እድሜ ለምቀኛ! በአፍም ቢሆን ከስንት ዓመት በኋላ ቃል ተገባልን፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ--- ምቀኛ ባይኖረን ኖሮ ባለሁለት ዲጂት እድገት የለም ነበር፡፡ ምቀኛ ባይኖረን ኖሮ ቀለበት መንገድ አይኖርም ነበር። ምቀኛ ባይኖረን ኖሮ የግል ፕሬስ አይታሰብም ነበር (አሁንስ የታለ እንዳትሉኝ) ምቀኛ ባይኖር ኖሮ ምርጫ የሚባል ነገር አይኖርም ነበር (አሁንስ የታለ ብትሉኝ ጆሮ የለኝም) ብቻ --- ሁሉነገራችን የተቃኘው “ምቀኛ አታሳጣኝ” በሚል የአበሻ ብሂል ነው፡፡ ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ የመንግስት መ/ቤቶችም በራቸውን ከርችመው ይከርሙና ምቀኛ ሲነሳባቸው መረጃ ለመስጠት ቁጭ ብድግ ይላሉ፡፡
ይሄ ብሂል የጦቢያ መንግስታት ፀሎት ብቻ ግን እንዳይመስላችሁ፡፡ የሰፊው የአበሻ ልጅ ፀሎት ነው (መንግስት እኮ ከህብረተሰቡ አብራክ ነው የወጣው!) አዲስ አበባ ላይ ድንገት የበቀሉ የሚመስሉት ባለመስተዋት ፎቆችም በምቀኛ አታሳጣኝ ብሂል የተሰሩ ይመስሉኛል (ጥናት ባላደርግም) የጦቢያ ነጋዴን ታውቁት የለ! ገንዘብ ከባንክ ተበድሮ የጓደኛው ዓይነት ባለስንት ሚሊዮን ብር አውቶሞቢል የሚገዛ ጀግና እኮ ነው! አንዳንድ ከውጭ አገር መጥተው የበጐ አድራጐት ድርጅት ወይም ደግሞ ቢዝነስ ያቋቋሙ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን የሚሰጡትን ኢንተርቪው ታዝባችሁ ከሆነ አንድ ነገር ትረዳላችሁ፡፡ የሰሩትን ነገር የሰሩት ምቀኛን ኩም ለማድረግ መሆኑን፡፡ ምን ይላሉ መሰላችሁ? “ነጮቹ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ከድርቅና ከረሃብ ጋር ነው የሚያያይዙት። የአቅሜን በማበርከት ይሄን ክፉ ገጽታ ለመቀየር ነው ወደ አገሬ ተመልሼ ኢንቨስት ያደረግሁት…” ምቀኛ ባይኖር እኮ በጦቢያ ምድር እግሩን የሚያነሳ አይኖርም ነበር ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው የጥንት አባቶቻችንን ማመስገን አለብን የምለው፡፡ እነሱ “ምቀኛ አታሳጣን” የሚለውን ብሂል ባይፈጥሩልን ኖሮ ጦቢያ አትኖርም ነበር ማለት እኮ ነው፡፡ ጦቢያ ከሌለች ደግሞ የአበሻ ዘር የለም ማለት ነው፡፡ ይሄውላችሁ … እዚህች አገር ላይ ብዙ መልካም ነገሮች የሚሰሩት ለእኛ ተብለው ሳይሆን ምቀኞቻችንን ኩም ለማድረግ እንደሆነ የፖለቲካ በፈገግታ ጥናት ይጠቁማል፡፡ እንደውም አንድ ሃሳቤን የሚያጠናክርልኝ ማስረጃ ትዝ አለኝ፡፡
የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከአዲስ አበባ እንዲነሳ ምቀኝነት ቢጤ የተቀነቀነበት ጊዜ ትዝ አይላችሁም- በኢህአዴግ ዘመን፡፡ ያኔ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ (ነፍሳቸውን ይማረውና) የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር፣ ንጉሱንና መንጌን ለአፍሪካ ህብረት ባበረከቱት አስተዋጽኦ ሰማይ ላይ ሰቀሏቸው፡፡ ይሄ እንግዲህ በኢህአዴግ ታሪክ የቀድሞ መንግስታት በበጐ ሲነሱ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው - “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለው ብሂል ያለውን ፓወር እኔ አልነግራችሁም!! እናም ጦቢያ በሁሉም ዘርፍ መጠነሰፊ ዕድገት ማስመዝገብ ትችል ዘንድ ምቀኞች በብዛት ያስፈልጓታል ባይ ነኝ፡፡ የጦቢያ መንግስት፣ የጦቢያ ፓርቲዎች፣ የጦቢያ ነጋዴዎች፣ የጦቢያ ምሁሮች፣ የጦቢያ አርቲስቶች ወዘተ ሁሉም የሚንቀሳቀሱት “ምቀኛ አታሳጣኝ” በሚል ብሂል ነው፡፡ ቆይ ቆይ --- ሰሞኑን የተመረቀውን ድንቅ የስፖርት አካዳሚ አይታችሁልኛል? (ቱቱቱ…በሉበት) እኔማ ምን አልኩ መሰላችሁ… “ከየትኛው አቅጣጫ የተነሳ ምቀኛ ይሆን አካዳሚውን እንድንሰራ እልህ ውስጥ የከተተን?” በነገራችሁ ላይ በባህርዳር፣ በትግራይ፣ በአዋሳና በኦሮምያ ክልል ትልልቅ ስቴዲየሞች ተጀምረው በእንጥልጥል ቀርተዋል፡፡ እናላችሁ --- እነዚህን ስቴዲየሞች ለማስጨረስ እንደሌላው ጊዜ ቴሌቶን ይዘጋጅ የሚል ሃሳብ አላቀርብም፡፡ (አሁንማ ምስጢሩን ደርሼበታለሁ!) ስቴዲየሞቹን በፍጥነት ለማጠናቀቅ “ጠብደል” ያሉ ምቀኞች ብቻ ነው የምንፈልገው - ከአፍሪካ ወይም ከእስያ አሊያም ደግሞ ከምዕራብ አገራት!! ለአገራችን ዕድገት እንቅፋት ሆኗል የተባለውን ሙስናን ጠራርጐ ለማጥፋትም ብቸኛው መፍትሔ ምቀኛ መፈለግ ነው፡፡
አገራችን በሙስና መጠቃቷን የሚለፍፍ ምቀኛ ካገኘን፣ ከጦቢያ ምድር ሙስና ውልቅ ብሎ ይጠፋል - እንደኩፍኝ!! ሰብዓዊ መብት እንዲከበርም ከምቀኛ የተሻለ መፍትሔ የለንም (ቢያንስ ለጊዜው) ሂዩማን ራይትስ ዎች አንድ ጊዜ ደህና አድርጎ ቢያብጠለጥለን እኮ ከእንቅልፋችን እንነቃ ነበር - “ምቀኛ አታሳጣኝ” በሚል ብሂል። በየጊዜው እየተዳፈነ ለመጣው የፕሬስ ነፃነትም መፍትሔ ሌላ ሳይሆን አስተማማኝ ምቀኛ ነው። ይሄውላችሁ --- የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ጦቢያ የፕሬስና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ነፃነት በቅጡ የሚከበርባት አገር አይደለችም የሚል የምቀኝነት ጉርጉርምታ ቢያሰሙ ሁሉነገር መስተካከሉ ምንም አያጠራጥርም፡፡ ኢህአዴግን የሚያነቃው ምቀኛ ነው ብያችሁ የለም! በነገራችሁ ላይ እኔም ይሄን አምድ የበለጠ ማራኪና ተነባቢ ለማድረግ ስላቀድኩ፣ ዕቅዴን ወደተግባር ለመለወጥ የሚያነሳሳኝ ደህና ምቀኛ በማፈላለግ ላይ ነኝ። “ምቀኛ አታሳጣኝ” እያልኩ የዛሬውን ወጌን ቋጨሁ!!
No comments:
Post a Comment