የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ግብፃዊያን ከሰሞኑ በቴሌቭዥን ቀጥታ ስርጭት ላይ ኢትዮጵያንና የሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ የሚናገሩት ነገር ትክክል አለመሆኑን እና እርሳቸውንም ጉዳዩ እንዳሳዘናቸው ተናገሩ። ግብፃዊያን እየተከተሉ ያሉት መንገድ እንደማያዋጣቸው ገልፀዋል።
ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ከትናንት በስትያ በራዲሰን ብሉ ሆቴል የአፍሪካ ሕብረት 50ኛ ዓመት ክብረ-በዓልን በሚዘክረው “JUBILEE” በተሰኘው መፅሔት የምረቃ ስነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። እንደ እርሳቸው ንግግር ከሆነ ግብፆች አሁን እያደረጉ ያሉት ነገር ትክክል አይደለም። በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ነገሮችን ማወጅ እንደማያዋጣቸውና እንደማይጠቅማቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ መለስ ዜናዊን ጠቅሰው እንዳወሱት፣ ኢትዮጵያ እና ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ተጠቃሚዎች እንጂ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች ሆኖ የሚኖርበት ዘመን ማብቃቱን ጠቁመዋል። ይልቅስ የተፋሰሱ ሀገሮች በጋራ የሚጠቀሙበትን አግባብ መኖር ነው ያለበት እንጂ ሁልጊዜ ግብፆች የበላይ ሌላው የበታች ሆኖ መቀጠል እንደማይቻል ከንግግራቸው መረዳት ይቻላል።
ከሰሞኑ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ከግብፅ ሀገር የተላለፈው ዘገባ እንደሚያሳየው፣ ፕሬዚዳንት ሙርሲ ካቢኔዎቻቸውን ሰብስበው በማወያየት ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመፈፀም ታጥቀው መነሳታቸውን ያስረዳል። ከፕሬዝዳንት ሙርሲ ጋር የተሰባሰቡት የግብፅ ባለስልጣን እንደሚናገሩት ከሆነ ኢትዮጵያን በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ማጥቃት እንደሚገባ አብዛኛዎቹ በሙሉ ስሜታቸው ሲናገሩ ታይተዋል። ኢትዮጵያን ማጥቃት መንገድ ብለው ከያዟቸው አቅጣጫዎች መካከል በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሱትን መደገፍ፣ የኤርትራን መንግስትን መርዳት፣ ሱማሊያ ውስጥ ያለውን አልሸባብን ማስታጠቅ እና ሌሎም ተጠቅሰዋል።
ይህ የግብጻዊያን እብሪትና ትዕቢት ያናደዳቸው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ይህ የግብፃዊያን እስትራቴጂ ፈፅሞ ልክ ያልሆነ፣ የአንዲትን ሉአላዊ ሀገር መረጋጋት ለመረበሽ መጣር ለክፍለ አህጉሩ አለመረጋጋት የሚያጋልጥ አካሔድ መሆኑን ጠቁመዋል። ከዚህ ሌላም የእነዚህ የግብፃዊያን አካሔድ ወደ ተሳሳተ መንገድ የሚመራቸው በመሆኑ ሊመከሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በአዳራሹ ውስጥ ለታደሙት የኢትዮጵያ ምሁራን እና ለአፍሪካዊያንም መልዕክት አስተላልፈዋል። ምሁራኑም በዚህ በፀረ ኢትዮጵያዊ በሆነ መንገድ የሚጓዙን ግብጻዊያን የሚመክርና እውነታውን የሚያስረዱ ጥናቶችና የምርምር ስራዎችን እንዲሁም ፅሁፎችን እንዲያቀርቡ መክረዋል።
No comments:
Post a Comment