Thursday, June 20, 2013

የአባይ ማደሪያው የት ነው?

አባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል የሚል ብሂላዊ አነጋገር …. እርግጥ አባይ በሐበሻይቱ ምድር ጦቢያ ማደሪያ አልባ ሆኖዋል፤ 

መንግስታት ምናልባት ከአስራ ሶስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እና ከዚያም በፊት ለአብነት በእነአጼ ዳዊት ዘመነ መንግስት አባይን አስመልክቶ ከግብጽ ጋር ጉንጭ አልፋ ውሃ ያልቋጠረ ክርክር እና ሙግት ብሽሽቅም አካሂዱ ነበር። የሐበሹቹ መሪዎች አባይን እንገድባለን ሲሉ በግብጽ በኩልም ፓትሪያርክ አንልክላችሁን እየተባባሉ ከአንድ መንግስት ወደሌላ መንግስት የዘለቀ ክርክር ...እና ሙግል.. ከዚህም አልፈው ጦር እስከመማዘዝ ድረስ ደርሰዋል። 

ኢትዮጵያዊ የመጀመሪያዋን ፓትሪያርክ በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት መርጣ ስርዓተ ሾመት ስታካሄድ ግብጻዊያን የአቡኑን መመረጥ ልክ እንደ ትልቅ ክህደት በመቁጠር አቡዋራ በወቅቱ አስነስተዋል በወቅቱ የሃይለ ስላሴ መንግስት ተደማጭነት ብርታቱ ለግብፆች ስለከበዳቸው ብዙም ቢፈራገጡም ሰሚ አልባ ጩኸት ብቻ ነበር በወቅቱ የተረፋቸው።


የአባይ ተፈላጊነቱ እና ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ በኢትዮጵያ ምድር እና በግብጽ የተወሰነ ብቻ አልነበረም፤ አባይ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ በጣሊያን፣ በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ፣ በእስራኤል፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በመላው የአረብ ምድር፣ ኤርትራ፣ በኮንጎ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በብሩንዲ፣ በሩዋንዳ በአገራት ደረጃ አወያይቶዋል፣ ሁሉን አከራክሮዋል፣ ገና ወደፊትም ያነታርካል፤ ብዙ ልዮ ክስተት ያሳየናል። በአለምችን ውዝግብ እና ተጽዕኖ በመፍጠር ረገድ የኢየሩሳሌም ከተማ፣ የሰለሞን ቤተ መቅደስ፣ የአላስካ መስጊድ፣ የፓልስታይን መንግስትነት፣ የኢራን ወደ ሃያል ጉልበተኛነት ሙከራ፣ የቻይና ፍልስፍና እና ዕድገት፣ እንዲሁም የናይል ወንዝ ከፍተኛ ደረጃ እና ስፍራ ላይ ይገኛሉ። 

ከላይ ከዘረዘርኳቸው አገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ይልቅ በአባይ የቤት ስራቸውን ለረጅም ዘመን ሲሰሩ የከረሙት ግብጾች ናቸው። ግብጾች የአባይን ውሃ ሙላት ተነተርሶ ዋፋ ኢል ናይል የተሰኘ ዓመታዉ ክብረ በዓል ሁልጊዜ ነሐሴ መጀመሪያ ላይ አላቸው፤ በዚህ ወር የናይል ወንዝ የውሃው ሙላት በግብጽ ከፍተኛ ደረጃ የሚደርስበት ወቅት ሲሆን የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በነሐሴ ወር በኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ መዝነቡ ነው።ነገር ግን በጥንት ጊዜ ግብጻዊያን በየዓመቱ ከፍተኛ ዝናብ የሚዘንበበት ምክንያት ጣኦታቸው የሆነችው ኢሲስ ለሞተባት ባልዋ ለኦሲሪስ በየአመቱ አምርራ ስለምታለቅስ ነው ብለውም ያምኑ ነበር። (ድንቅ እና መሰረት ያለው እምነት ነው ….እንደ እኔ እምነት ኢትዮጵያ እያለቀሰች መስሎ ተሰምቶኛል ….ለካ ለዘመናት ስናለቅስ ኖረናል።)

አባይን አስመልክቶ ብዙ ፍላጎቶች እና ምኞቶች ባለፉት ምዕተ አመታት ተስተናግዶዋል። የተለያዮም ስምምነቶች እና ውሎች ተፈርመዋል። አብዛኛዎቹ ውሎች ለግብጽ እና ግብጽን በቅኝ ለገዙዋት ያደላ እና የወገኑ ውሎችም ነበሩ። 

በዚህ ጽሑፌ ላትት የምወደው አባይን አስመልክቶ ስለነበሩ ውሎች እና አገራችን ላይ ስላላቸው እንድምታ ነው።

ውሎቹን ለመጻፍ እንዲያመቸኝ በሶስት ከፍያቸዋልሁኝ እርግጥ ሶስተኛው የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ መደምደሚያ አይነት ነው።

1. የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች

2. ከቅኝ ግዛት በሃላ የተደረጉት ውሎች

3. ኢትዮጵያ የተስማማችባቸው ውሎች


1. የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች


. ሚያዚያ 15 1891 የአንግሎ ጣሊያን ፕሮቶኮል ሲሰኝ፤ በስምምነቱ አንቀጽ ሶስት ላይ የጣሊያን መንግስት አታባር ወንዝ ላይ ምንም አይነት ግንባታ እንደማያካሄድ ሲከለክል፤ በስምምነቱም ላይ አታባራ ወንዝ ላይ የሚደረግ መስኖንም በተመለከተ አወዛጋቢ ቋንቋ ሲኖረው ወደ ናይል የሚፈሰውን ውሃ ፍሰት የማይቀንስበትን ሁኔታ አትኩሮት የሰጠ ውል እና ስምምነት ነበር። በዚህም ውሃውን የመጠቀም መብትን አስመልክቶ እንዲሁም የውሃው ባለቤት ወይንም የማን ንብረት እንደሆነ በሚያሻማ ቋንቋ የተለወሰ ስምምነትም ነው።

. ግንቦት 17 1902 ይህ ስምምነት በታላቁዋ ብሪታኒያ እና ኢትዮጵያ መካከል የተፈረመ ስምምነት ነው።

በዚህ ስምምነት አንቀጽ ሶስት ላይ ሚኒሊክ ሁለተኛ ንጉሰ ነገስት ኢትዮጵያ ከታላቋ ብሪታኒያ መንግስት እና ከሱዳን መንግስታት ጋር ሳትስማማ የውሃውን ፍሰት የሚያጉዋድል በአባይ ላይ፣ በአሶባ እና በጣና ሐይቅ ላይ ምንም አይነት ግንባታ እንዳያካሄዱ እና ለማንኛውም አካልም ግንባታ እንዳያፈቅዱ ተስማምተዋል ይላል። እርግጥ የዚህ ስምምነት የእንግዚዝኛው እና አማሪኛው ቅጂ ተመሳሳይ አይደለም።

. ግንቦት 9 1906 ይህ ስምምነት በታላቂዋን ብሪታኒያን እና በወቅቱ ነጻ በነበረችውን የኮንጎ ግዛትጋር የተደረገ ስምምነት ነው።

በአንቀጽ ሶስት ላይ ነጻይቷ የኮንጎ ግዛት በሰሚሊክ ወይንም ኢሳንጎ ወንዝ አቅረቢያ ወደ አልበርት ሐይቅ የሚፈሰውን የውሃ መጠን የሚቀንስ ማናቸውንም አይነት ግንባታ ያለ ሱዳን መንግስት ፈቃድ እናታደርግ እንዲሁም ለሌላ ወገን ግንባታውን እንዳትፈቅድ የሚከለክል አንቀጽ ሲሆን ይህንን ስምምነትነጻይቷን ኮንጎወክሎ የቤልጅየም መንግስት ፈርሞዋል። 

. ታህሳስ 13 1906 የብሪታኒያ- ፈረንሳይ- ጣሊያን ሶሰትዮሽ ስምምነት ተፈርሞዋል። ዚህ ስምምነት አንቀጽ አራት ላይ ሶስቱ አገራት አንድነት የናይልን ተፋሰስ አስመልክቶ ብሪታኒያን እና ግብጽን ፍለላጎት በጋራ ለመጠበቅ እና አንድነት ለመቆም ተስማምተዋል።

. 1925 ብሪታኒያ እና ጣሊያን ጣናን አስመልክቶ የተለዋወጡት መረጃዎች እንደሚጠቁመው ጣሊያን የጣናንም ሆነ አባይን ውሃ አስመልክቶ ግብጽ እና ሱዳን ከማንም አገር በላይ ቅድሚያ ባለመብቶች እንደሆኑ ትቀበላለች ይላል በዚህም በአባይ እና በነጩ ናይል እንዲሁም በገባሮቻቸው ላይ ውሃውን ፍሰት የሚቀንስ ማናቸውንም ግንባታ ይቃረናል።

ኢትዮጵያ ይህንን ስምምነት አስመልክታ ተቃውሞዋን ለሁለቱም መንግስታት አስአውቃለች። ሁለቱም መንግስታት ሊግ ኦፍ ኔሽን ስለጉዳዮ አስመልክቶ ሲተየቁ የኢትዮጵያን ልዑአላዊነት እንዳልነኩም ከክደዋል። ነገር ግን ይህ ስምምነት በጣሊያን እና ባኢንግሊዞች ልከልልህ እከክልኝ አይነቱ መንገድ ነበር፤ ሁለቱም የገዛ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እና ያለምንም ዴንታ ኢትዮጵያን ጥቅም የደፈጠጠም ነበር።

. የግንቦት ሰባት 1929 . ስምምነት ደግሞ በግብጽ እና በሱዳን መካከል የተደረገ ስምምነት ሲሆን ይህ ስምምነት ለግብጽ የሚከተሉትን መብት ያጎናጽፋታል።

1. የናይልን ውሃ ግብጽ 48 ሱዳን ደግሞ 4 ቢሊዮን ሜትር ኩዮቢክ በየአመቱ ለመጠቀም ተስማምተዋል፤


2. ከደረቁ ማለለትም ከጥር እስከ ሐምሌ ድረስ የሚፈሰው አባይ ወሃን በተመለከተ ግብጻዊያን እንዲጠቀሙበት ለግብጻዊያን እንዲሆን ተስማምተዋል፣ 


3. ግብጽ ከላይኞቹ አገራት የሚፈሰውን የውሃ ፍሰት እንድትቆጣጠር ተስማምተዋል። 


4. ግብጽ የላይኞቹን አገራት ሳታማክር ያሻትን ፕሮጀክት በናይል ላይ እንድታከናውንም ይፈቅዳል።


5. ግብጽ ፍላጎቱዋን የሚነካ በናይል ላይ የሚደረግን ማንኛውም ግንባታ የማቀብ እና የማስቆምም መብት ይሰጣታል። 


ይህንን ስምምነት ኢትዮጵያ አጥብቃ ተቃውማቃለች።

በሚቀጥለው ጽሑፌ ደግሞ 

2. ከቅኝ ግዛት በሃላ የተደረጉት ውሎች

3. ኢትዮጵያ የተስማማችባቸው ውሎች እና የታላቁ ግድብ ዕጣ ፋንታን በተመለከተ ያዘጋጀሁትን ጽሑፍ አቀርበለሁኝ። 


ሰላም 

ቢንያም ሰለሞን 

ሰኔ 2005 .

No comments:

Post a Comment