እውነታውና በተግባር ሲተረጎም መልሱ እስር፣ድብደባ፣ከአገር መሰደድ,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,
በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት አንቀፅ 29 ላይ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ያለገደብ
ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም በጋዜጠኛ ተመስገን ክስ ላይ የመከላከያ ቃላቸውን ሰጡ
ህዝብን ለአመፅ የሚቀሰቅሱ ጽሁፎች ፅፎ አሰራጭቷል ሲል የፌዴራሉ አቃቤ ህግ ክስ በመሰረተበት፤ የቀድሞዋ ፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ጉዳይ በተመለከተ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያምና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ፋካሊቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ያሬድ ለገሰ የተከሳሽ የመከላከያ ምስክር ሆነው በትናንትናው ዕለት ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል።የፌዴራሉ አቃቤ ህግ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ሶስት ክሶችን የመሰረተ ሲሆን፤
በ1ኛ ክሱ ጋዜጠኛው በቀድሞዋ “ፍትህ” ጋዜጣ ላይ “ሞትን የማይፈሩ ወጣቶች” በሚል ርዕስ ስር “ለምን እንፈራለን” የሚል ቀስቃሽ ጽሁፍ ፅፏል ሲል፤ በሁለተኛ ክሱ ላይ ደግሞ “
የሁለተኛ ዜግነት ኑሮ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ስር የመንግስትን ስም አጉድፏል ያለ ሲሆን፤
በሶስተኛው ክሱ ደግሞ “ሲኖዶሱና መጅሊሱ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማጥመቂያዎች” በሚል ርዕስ ስር የሁለቱም ሃይማኖት መሪዎች ካድሬዎች ናቸው ሲል ስማቸውን አጉድፏል ሲል ክሱን ይዘረዝራል።
ይህን በተመለከተ የተከሳሹ ጠበቆች፤ ጋዜጠኛው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ህጋዊ መብቱን ተጠቅሞ የፃፈው ነው ብለው የመከራከሪያ ሀሳብ በማንሳታቸው ፍርድ ቤቱ የመከላከያ ምስክሮችን ቃል ለመስማት ቀጠሮ ይዞ እንደነበር ይታወሳል።
በዚሁም መሰረት ህዝብን ለማሸበር ሞክሯል፤ ፅሁፉን ባዘጋጀበት ወቅት የነበረውን የወቅቱን የአረብ አብዮት ተገን አድርጎ አመፅ ቀስቃሽ ፅሁፎችን ጽፏል የተባለው ጋዜጠኛ ተመስገንን ለመከላከል ምስክር ሆነው የቀረቡት ፕሮፌሰር መስፍን፤ “የተፃፈው እውነት ነው። እውነት ደግሞ ምንጊዜም ቢፃፍ ለኛም ቢሆን ጥሩ ነው” ብለዋል። ምክንያት ካልሆነበት በስተቀር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የፃፈው ነገር እውነት ነው ብዬ አምንበታለሁ” ሲሉም አክለው የምስክርነት ቃላቸውን ለችሎቱ ሰጥተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተባባሪ የህግ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ያሬድ ለገሰ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸውን እና አለማቀፋዊ ስምምነት የተሰጣቸውን ህጎች እያጣቀሱ ጋዜጠኛው ፅፏቸዋል ተብለው በተጠቀሱት “አመፅ ቀስቃሽ” ፅሁፎች ላይ ሙያዊ ትንታኔያቸውን ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል። ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት አንቀፅ 29 ላይ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ያለገደብ የተቀመጠ ቢሆንም ከጋዜጠኝነት ሙያ አኳያም ቢሆን ጋዜጠኛ ተመስገን “አመፅ ሊቀሰቅስ” የሚችል ፅሁፍ ፅፏል ለማለት እንደማይደፍሩ አስረግጠው ተናግረዋል። የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት በዚሁ መዝገብ ስር ሶስተኛውንና ቀሪውን የሙያ መከላከያ ምስክር ከጋዜጠኝነት አንፃር ለመመልከት እና የባለሙያውን ቃል ለማድመጥ ለሐምሌ 23 ቀን 2005 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
No comments:
Post a Comment