Wednesday, July 17, 2013

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተማሪዎቹን ጥያቄ ሳይመልስ እንዲዘጋ ተወሰነ

በመስከረም አያሌው


የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎቹ በተደጋጋሚ ያነሱትን የአስተዳደር መሻሻል ጥያቄ ሳይመልስ እስከ መጪው መስከረም አጋማሽ ድረስ እንዲዘጋ የአመራር ቦርዱ ወሰነ።
የኮሌጁ ተማሪዎች ያነሷቸውን የተለያዩ ጥያቄዎች ይዘው ወደ ፓትሪያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት ከትናትና በስቲያ ያመሩ ቢሆንም የስራ አመራር ቦርዱ ያለው ችግር እስኪጣራ ድረስ ኮሌጁ እንዲዘጋ መወሰኑን እና ተማሪዎችም ከሐምሌ 8 ቀን እስከ ሐምሌ 9 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ኮሌጁን ለቀው እንዲወጡ በደብዳቤ አሳውቋል።
ተማሪዎቹ ከትናንት በስቲያ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንግበው ወደ መንበረ ፓትሪያሪክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ያቀኑ ሲሆን፤ ተማሪዎቹን የሚያነጋግራቸው እንኳን ሳያገኙ ወደ ኮሌጃቸው ተመልሰዋል። ተማሪዎቹ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ የተለያዩ ጥያቄዎችን ይዘው መሄዳቸውን የተማሪ መማክርት ሰብሳቢ የሆነው ዲያቆን ታምርአየሁ አጥናፌ ገልጾልናል። እንደ ዲያቆን ታምርአየሁ ገለፃ ከሆነ ተማሪዎቹ ይዘዋቸው የቀረቡት ጥያቄዎች ከስድስት ወር በፊት ጀምሮ ሲያነሷቸው የነበሩ ጥያቄዎች ናቸው። ከጥያቄዎቹ መካከልም በኮሌጁ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ስርዓት ይወገድ፤ ሙሰኞች ከስልጣን ይውረዱ፤ ደረጃውን የጠበቀ የመማሪያ እና የማደሪያ ህንፃ ይሰጠን የሚሉት ይገኙበታል።
“ላለፉት አምስት አመታት ሙሉ አንድም ቀን ያለ ብጥብጥ፣ ያለ ችግር እና ንትርክ አሳልፈን አናውቅም። አሁን ያሉት ሰዎች መልስ እንዲሰጡንና በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀን ነበር” ያለው ሰብሳቢው፤ ሆኖም ግን ማንም ሊያነጋግራቸው ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልጿል። በመሆኑም ተማሪዎቹ አጠቃላይ አስተዳደራዊ ለውጥ እንዲደረግ ጠይቀዋል። በእድሜ የገፉ እና ስራቸውን በአግባቡ እየሰሩ ያልሆኑ ሰዎች በሌላ ይተኩልን የሚል ጥያቄም አንስተዋል። “ዘንድሮ ጠቅለል ባለ መልኩ አጠቃላይ አስተዳደራዊ ለውጥ እንዲደረግልን ነው የጠየቅነው። የኮሌጁ የበላይ ዲን በእድሜ የገፉ እና አይናቸው፣ እጃቸው እና ጆሯቸው የደከመ ስለሆነ በሌላ እንዲተኩ ጠይቀናል። ሌላ ዲን ተሹሞ አካዳሚክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ካሪኩለም የሚያወጣ ሀሳቦችን በማስፈፀም ላይ ጠንካራ የሆነ አመራር እንዲኖር ጠይቀናል። ከሁሉም በላይ ቅጥሩ ደግሞ የዘመድ አዝማድ ሳይሆን መስፈርት ወጥቶ መምህራንም ሆኑ የአስተዳደር ሰራተኞች በህጋዊ መንገድ እንዲቀጠሩ የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበናል” ብሏል ዲያቆን ታምርአየሁ።
ሌላው ተማሪዎቹ ያነሱት ጥያቄ የመሰረተ ልማት ጥያቄ ነው። ይኸውም በኮሌጁ ውስጥ ያሉት የመማሪያ ክፍሎች፣ መመገቢያ ክፍሎች እና የመኝታ ክፍሎች ብዙ አመታትን ያስቆጠሩ እና ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆናቸው በተደጋጋሚ እንዲታደስ መጠየቃቸውን፤ ሆኖም ግን እየተደረገ ያለው ነገር የተለየ መሆኑን ተማሪዎቹ ገልፀዋል። “ኮሌጅ ነው ተብሎ የተገነባው ህንፃ ለንግድ ተከራየ እንጂ ተማሪዎች ልንጠቀምበት አልቻልንም” ሲል ዲያቆን ታምርአየሁ ይናገራል።
እነዚህን ጥያቄዎች ይዘው በተደጋጋሚ ወደ ቤተክርስቲያን አባቶች ማምራታቸውን የገለፁት ተማሪዎቹ ሆኖም ግን ምንም አይነት ምላሽ ማግኘት አልቻሉም። ቅዱስ ፓትሪያሪኩ ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን እንዲያጣራ ወስነዋል። አጣሪ ኮሚቴው ጉዳዩን አጣርቶ የጨረሰ ቢሆንም ተማሪዎቹ ውጤቱ ይነገረን ቢሉም ሊነገራቸው እንዳልቻለ ነው የገለፁት። “እኛ እየጠየቅን ያለነው የአጣሪ ኮሚቴው ውጤት እንዲነገረን ነው። ውጤቱ ይነገረን ስንል ደግሞ ምንም ሊነግረን የሚችሉት ነገር የለም። ከዚያ ይልቅ እኛን ካፍቴሪያ እየዘጉ በረሀብ መቅጣትን ነው የያዙት ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ እስከ ዛሬ (ሰኞ) ድረስ እየተራብን ነው ያለነው። ከአሁን በኋላም ምን ሊሆን እንደሚችል አናውቅም” ሲሉም ተማሪዎቹ ስላሉበት ሁኔታ ይናገራሉ።
ተማሪዎቹ ከተማሪዎች መማክርት ጀምሮ በየደረጃው ላሉ ለኮሌጁ አስተዳደር፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ እና ለፓትሪያሪኩ ጭምር ጥያቄያቸውን እንዳቀረቡ የገለፁ ሲሆን ነገር ግን እነዚህ አካላት ጉዳዩ ይጣራል የሚል ተስፋ ከመስጠት ውጪ ምንም አይነት መፍትሔ ሳይሰጧቸው መቅረታቸውን ገልፀዋል። ጉዳዩን ተመልክቶ ከተሳሳትን እንኳ ተሳስታችኋል የሚለን አካል ማግኘት አልቻልንም ያሉት ተማሪዎቹ እንዲያውም ጥያቄያችን ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው እየተባልን ነው ብለዋል። “አብዛኞቻችን ከየክፍለ ሀገሩ መምጣታችን እና ገንዘብና ዘመድ እንደሌለን እየታወቀ ሆን ተብሎ በረሀብ እየቀጡ አማሮ ማባረር ነው የታሰበው” ያሉት ተማሪዎቹ፣ ጥያቄው ትክክል እስከሆነ ድረስ ከመጠየቅ ወደ ኋላ እንደማይሉ ገልጸዋል።
የኮሌጁ መምህራን በበኩላቸው ችግሩን ተነጋግሮ መፍታት ሲቻል ፖሊስና ደህንነት በመምጣቱ ቅሬታ እንዳላቸው ገልፀዋል። በኮሌጁ በሀዲሳትና ትርጓሜ መምህርነት ለ41ዓመታት ያስተማሩት መምህር ሀዲስ አለም እንደገለፁት፤ ተማሪዎቹ ምግብ እንዳይመገቡ መመገቢያ ክፍሎች ተዘግተውባቸው ልመና እስከመውጣት ደርሰዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ተማሪዎቹ አንዴ ትምህርት ተቋርጧል ውጡ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከፍተናል ግቡ እየተባሉ መቆየታቸውን ገልፀዋል።
“በአንድ በኩል ጉዳያችሁን እናይላችኋለን ይሏቸዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በቶሎ ውጡ የሚል ነገር አለ። እኛም ተናግረናል። ይሄ ኮሌጅ የግለሰብ እንጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ቤተክርስቲያን ሀብት አይመስልም። ሲፈልጉ ይዘጉታል ሲፈልጉ ይከፍቱታል። ዝም ብሎ ውጡ ግቡ ብቻ ነው። ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እንኳ በህግ ሲመራ ይህ ኮሌጅ ግን በግለሰብ ነው የሚመራው” ሲሉ ያለውን ሁኔታ መምህር ደጉ ይገልፃሉ።
በአሁኑ ወቅትም ተማሪዎቹ ለፅድቅ ያሉ ሰዎች የሚሰጧቸውን እየተመገቡ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው የሚመጣውን ነገር በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ መምህራኑ ገልጸዋል። ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም የፓትሪያሪኩ ልዩ ፀሐፊ ስልክ ሊያነሱልን አልቻሉም።

No comments:

Post a Comment