Monday, July 22, 2013

ይድረስ ለክቡር ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም

በዘውገ ፋንታ
Seattle, U.S.A
በዚህ ሐምሌ ወር (2005 ዓ/ም) የጻፉትን እንደተለመደው በጉጉት ማንበብ ጀምሬ በመንሰፍሰፍ ጨርሻለሁ። መልዕክቶችዎ ብዙ ዘመን የሸፈናቸውን ትዝታዎች እንዳስታውስና ብዙ ትውስቶችን እንዳሰላስል አድርጎኛል። ብዙ ሆድ የሚያባቡ ሃሳቦች ነበሩ። የአብዘኽኘው ሰው ስሜት እንዴት እንደሆነ ባላውቅም፣ ሁላችንም ያለንበት ጀልባ አንድ፣ ያለንበት ባሕር አንድ፣ ጉዞአችንና አቅጣቻችን እንዲሁ አንድ ነው ብየ ስለማምን ያንዱ ስሜት የጋራ ነው ብዬ ገምቻለሁ። ሆኖም በዚያ የተነሳ ይህን ጽሑፍ ስጽፍ የግል ስሜቴ እንዳይለውጠው ጥንቃቄ አድርጌአለሁ። የቀረ እንክርዳድ ሃሳብ ምንጊዜም ስለማይጠፋ፣ ስለሱ አስቀድሜ አንባቢን ይቅርታ እጠይቃለሁ። በ”መንሰፍሰፍ” ያልኩት ቃል ለየት ያለ ይመስል ይሆናል። ክቡርነትዎ ያስተላለፏቸው መልዕክቶች የሚያስፈሩ፣ የሚያባቡና የሚያርበተብቱ ይሁኑ አይሁኑ ለይቸ ለማወቅ ተስኖኛል። ፍራቻና መባባቱም ቅጥ አጥቷል። ሆኖም ግን፣ አሜርካ ውስጥ ስለምኖር በዕርግጥ ፍራቻ አላውቅም። ስለ ሀገራችን መውደቅና መጥፋት ሳስብ የምለውና የማስበው ዝብርቅርቅ ያለ ይሆናል። ለሞት ስንቅ ቢኖረው የኔንና የሌላውን ከምሬ ነበር።

የክቡርነትዎ ጽሑፍ ብዙ አሮጌ ዐመቶች የሽፈኗቸውን የጥንት አጋጣሚዎች አስታውሶኛል። ከታወሱኝ መካከል  አንዱ ጎልቶ የታወሰኝ ይህ ነበር። በእንግሊዝ ሀገር ስኖር፣ በለንደን ከተማ ወጣ ባለች ቤተመንግሥት የልዑል መሥፍን አለማየሁ ቴዎድሮስ አፅም የተቀመጠበትን ቦታ እንድጎበኝ አንድ እንግሊዛዊ ሰው ወሰደኝ። በዚያን ጊዜ የተሰማኝን ደስታ በትክክል ለመግለጽ ቃል ያጥረኛል። ከዚያ በፊት አባቱ አፄ ቴዎድሮስ የቆሙባትን ቦታ መቅደላን አይቸ ነበር። ንጉሡ በተንጓለሉበት ቦታ ላይ ቁሜ በታሪክ ያነበብኩትን እያስታወስኩ ሳስብ የተሰማኝ ስሜትና የልጃቸው አፅም ባረፈበት ቦታ ላይ ቆሜ  ሳሰላስል የተሰማኝ ስሜት እጅግ የተለያየ ነበር። የልዑል መሥፍን አለማየሁ ፎትግራፍ በእንግሊዝ ነገሥታት ፎቶግራፎች መካከል ተቀምጦ ሳይ የተሰማኝ ኩራት ወደር የሌለው ነበር። ፎቶግራፉን አይቸ የማልጠግበው እንደሆነብኝ ትዝ ይለኛል። ደስታየን እንድካፈል እንደኔ የሚሰማው ኢትዮጵያዊ ባጠገቤ ባለመኖሩ አወራጭቶኝ ነበር። ልዑል መሥፍን አለማየሁ አድጎ ምን እንደሚመስል ማወቄ እራሱ ጉድ ታሪክ ሆነብኝ። ግን ብዙ ሳልቆይ እበሳጭ ጀመርኩ። ስለ እሱ የተጻፉትን ታሪኮች እየተጠያየኩ መሰብሰብ ጀመርኩ። የታላቁ ንጉሥ ልጅ አፅም በባዕድ ሀገር መኖሩ ጥያቄ አሳደረብኝ። እስከመቸስ በባዕድ ሀገር ተቀብሮ ይኖራል እያልኩ ለረጅም ጊዜ ሳሰላስል ቆይቻለሁ። የልዑል መሥፍን አለማየሁን ብዙ ውጣ ውረድ፣ መንገላታት፣ ብቸኝነትና በመጨረሻም አሟሟቱን አንብቦ የማያለቅስ፣ የማይጸጸትና የማይበሳጭ ኢትዮጵያ ይኖራል ብዬ አላምንም። እንዲህ ማለቴ ከአርባ ዓመት በፊት በነበረው የኢትዮጵያ ሰው ልቦና አንጻር ነው።  ልዑል መሥፍን አለማየሁ ብዙ ነገሮችን ናፍቆና አምሮት እንደሞተ ግልጽ ነበር። ስለ እሱ የተጻፉት ታሪኮች አንድንዶቹ የዕውነቱ-ደበና ቢሆኑም አለመታደሉን ያስረዳሉ። የሀገሩ እሸት፣ ቋንጣ፣ ቆሎ፣ ዳቦ፣ ፍትፍቱ፣ ቅራሪና ብርዙ፣ የለመደው ምግብና መጠጥ ሁሉ ናፍቆት መሞቱ አያጠራጥርም። ከዚያም በላይ መጫወቻ ግቢው፣ ሜዳው፣ አየሩ፣ እንስሳው፣ መንደሩን እና ያገሩን ሰው እየናፈቀ እንደሞተ ወይም ናፍቆት እንደገደለው ለመረዳት አይከብድም። በልዑል መሥፍን አለማየሁ ቴዎድሮስ ከደረሰው ግፍ፣ በኢትዮጵያኖች ላይ አሁን ባለንበት ወቅት ባገራቸውና በባዕድ አገሮችም እየተካሄደ እንደሆነ እያንዳንዳችን ምስክር ነን።
ሌላው ትዝታ ብዙ ነገሮችን ያፈራርቃል። ክቡርነትዎ ደሴ መጥተው የሁለተኛ ደረጃ ማለፊያ ፈተና ሲያካሂዱ አንዱ ተፈታኝ ነበርኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርስዎን አውቄአለሁ። ከዚያም ካርታ ድርጅት ሰሰራ፣ ወዳጆችዎ፣ ክቡር አምባሳደር ኃይሉ ወልደማርያምና ክቡር አቶ ታየ ረታ፣ “መስፍን ካርታዎች ይፈልጋልና ሂድህ የሚፈልገውን ጠይቅና ሰርተህ ስጠው” እየተባልኩ፣ ከእርስዎ ቢሮ እየመጣሁ ብዙ የተለያዩ ካርታዎች በተለያዩ ጊዜ እያዘጋጀሁ ሰጥቸዎታለሁ። ቢሮዎንም አስታውሳለሁ። እንደተባለው በር ይኑርና አይኑረው የማይታወቅና ዝው ተብሎ የሚገባበት ነበር። እርስዎን በውስጧ ላላየ ሰው፣ የዕርስዎን ቢሮ (አዕምሮ እንደሚገምተው አይነት) ሲፈልግ ውሎ ይመሻል እንጂ አያገኛትም ነበር። የት ነው ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ግን መልሱ “ምን ሁነሀል? ወደዚያ ሂድ፣ ታገኘዋለህ!” የሚል ነበር። መጽሐፉና የተጠቀለለው ወረቀት መደርደሪያውዎቹን ሞልቶ በዕግርዎ ስር ተከምሮ ነበር። ይኽ በጥንት ጊዜ ከአርባ ዓመት በፊት የነበረውን የሚገልጽ እንጂ ከዚያ በኋላ ትንሽ ቤተመንግሥት የሆነውን የሚያመለክት አይደለም።  የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ከተማ በብዙ ቀለም የተሰራ ካርታ አሳትሜ ስለነበር ለእርስዎና ከእርስዎ ቢሮ ብዙ ጊዜ ቆመው ለማያቸው ፕሮፌሰር (ስማቸውን ዘነጋሁ) ስሰጣችሁ፣ ሁለታችሁም አድንቃችሁ በጣም ጥሩ በርታ ብላችሁኝ ነበር። ከዚያ በኋል አላየሆትም፤ ተቻኩየ አገር ጥየ ወጣሁ።
ቀጥየ፣ እርስዎ የሚጽፉትን፣ የሚናገሩትንና ስለእርስዎ የሚነገረውን የኢትዮጵያ ታሪክ አካል የሆነውን በታላቅ ስሜት እከታተል እንደነበር ለማመልከት እፈልጋለሁ። በዚያን ወቅት በተማሪዎችና በሰራተኞች ደምቀውና ጎልተው ከሚዘወተሩት ቡና ቤቶች አካባቢ የሚነፍሱ ብዙ ፌዞች ነበሩ። አንድ ድርጊት ሲፈጠር፣ በሚቀጥሉት ቀኖችና ወሮች ጉዳዩ መሰረቱን ስቶና ተለውጦ በአስቂኝ ፌዝ ተደለባብሶ ይነገራል። አሁን ሳስበው፣ አዲስ አበባ የዓለም ፌዝ  መናገሻ መባል ይገባት ነበር እላለሁ። ለፌዘኞች የሹም-ሽረት ወቅት ትልቅ ዓመትበዐላቸው ነበር። በአንድ ሹም-ሽረት ወቅት፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ለምን ፕ/ር መስፍንን የአንዱ ምንስትሪ ምንስትር አልሆኑም እያለ ይጠይቅና ያወሳ ነበር። በ’ሹም-ሽረት” ዋዜማ ሕዝብ የሚሾመውንና የሚሻረውን አስቀድሞ(የራሱን ምርጫ ይሆናል)ማናፈስ ይጀምራል። ብዙው ትችት የፖለቲካ ‘አሳስኔሽን’(ግድያ) ቢባል ተገቢ ነበር። በማግስቱ ደግሞ“ተሻረ” ወይም “ተሾመ” የተባለው ሳይሆን “ተረሳ” ወይም “ተረሱ” የተባሉት ሰዎች ስም ነበር የሚወሳው። በዚያ ጉዳይ ቆሽታቸው የተነካ ወይም የቆሰለውን የሚያውቁ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሁም በዲ.ሲ ከተማ በህይዎት እንዳሉ እገምታለሁ። ኢትዮጵያኖች ንጉሡ ለምን ፕ/ር መስፍንን የትምሕርት ምንስትር ወይም ሌላ ከፍተኛ ስልጣን አልሰጧቸውም እያሉ የሚጠይቁ ብዙ ቅን ሰዎች ነበሩ። ለዚያ ጥያቄ መልስ የሚነገረው ብዙ ነበር። አንድ መጥቀስ የምሻው አለኝ። እሱም ስለ አማርኛ ቋንቋ ጥልቀትና የአዲስ አበባን ሰው እንደ አቅሙ አቻችሎ ያኖረ የምንግሥቱ ሕጎች ሳይሆኑ የአማርኛ ቋንቋ ነብር ብዬ አምናለሁ። አሁኑ ተበልዞ ጣዕሙን ያጣውን ደረቅ ዐይነት አይደለም። ስገምተው አሁን ሕዝብ መግባቢያ ቃሎቹ “እምቢ! አላውቅም!እንጃ! እንደፈለግህ!” ይመስሉኛል። በዚያን ጊዜ የሚነገረው አማርኛ፣ ሕዝብ እንዲሳሳቅ፣ አንዱ ሌላውን እንዲያስገርም፣ ሰለልተኛው እንዲነቃና እንዲያሰላስል የሚያደርግ ነበር ብየ ብናገር፣ በዚያን ጊዜ የነበረው ትውልድ ምስክሬ ይሆናል ብዬ  እተማመናለሁ። ክቡርነትዎ ለምን እንዳልተሾሙ ይወራ የነበረው ምክንያት ከጥሩ አፍ እንደሰማሁት፣ እርስዎን ለማሾም ንጉሡ ፈቃዳቸው እንዲሆን ሲጠየቁ፣ ንጉሡ “እኛ እሱን አንሾምም!” በማለት እምቢ ስላሉ ነው ተብሏል። “ባይሆን የትምህርት ምንስትር  እንዲሆኑ ግርማዊነትዎ ይፍቀዱ” ብለው ሲማለዱ፣ ንጉሡ “ለሱ ሹመት ወይስ ሽረት? የቱን አስባችሁ ነው?” የሚል መልስ ሰጧቸው ይባላል። በምንሊክ ቤ/መ  አካባቢ በይበልጥ በአንዳንድ ቦታዎች የሚነገር እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህን የሚያውቁ ወይም የሰሙ “አዎ፣ ተብሏል” የሚሉ ከዚህ በዲ.ሲ በአዲስ አበባም እንደ አሉ አምናለሁ፤ እግዜአብሔር ያቆያቸውና ይመሰክራሉ። የንጉሡ ንግግር አስተርጓሚ ወይም ማብራሪያ በተለይ ለቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንደሚያስፈልጋቸው ይነገር ነበር። ንጉሡ “እኛ እሱን አንሾምም!” ያሉበትን ምክንያት አዋቂዎች ሲያብራሩት፣ የርስዎ ቢሮ ያልተደነገገችና መስፈርት ያልተደረገላት ስልጣን ናት ማለታቸው ነበር ተብሏል። ቀጥለውም ነጉሡ “ሹመት ወይስ ሽረት?” በማለት የጠየቁት ስለኢትዮጵያ ጉዳይ የነበርዎትን ሰፊ ስልጣን አሰመልክቶ ነው ተብሏል። የተባለውን ቃል በቃል ለማንጸባረቅ ጥሬአለሁ። በሌላ መስካሪዎች ቃሎቹ ተሻሽለው ቢቀርቡ አሚን ብየ እቀበላለሁ።
መጀመሪያ አዲስ አበባ ስመጣ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነበርኩ፣ ብዙ ያስደንቁኝን ሁሉ ከዚህ ባላሰፍርም፣ ትቂት አስገራሚ ሆነው የታዩኝን ለመግለጽ፣ የአቡነ ጴጥሮስና የምንሊክ ኃውልቶች ዋናዎቹ ነበሩ። ቀኑን ሙሉ ከሀውልቱ ግርጌ ቁጭ ብየ እያንጋጠጥኩ እያየሁ ብውል የምጠግበው አልነበረም። የአዲስ አበባ የሰፈር ስም ብዛት እያስገረመኝ እንደ ኢትዮጵያ ‘ጂዖግራፊ’ ማጥናት ጀምሬ ነበር። የአዲስ አበባን ካርታ ስሰራ ያጠናኋቸው ስሞች ረድተውኛል ብል ትክክል ነው። ኋውልቶቹ፣ የመንገዶቹ፣ የአደባባዩና የሰፈሮቹ ስሞች በኢትዮጵያ ታላላቅ ጀግኖችና ንጉሦች ስመ የተሰየሙ ስለሆኑ፣ አዲስ አበባ የታሪክ ገጾች ሆኖ ትታየኝ ነበር። ወደር የማይገኝላቸው የነዚያ ታላላቅ ጀግኖችና ሰማዕታት ስምና ታሪክ አብሮን የሚኖር በየቀኑ የሚታወሱ አድርጓቸዋል ቢባል ከዕውነት የራቀ አይሆንም። የሁሉም ጀግኖች ኃውልቶች በየሰፈሩና አደባባዮች ቁመው ቢታዩ የአዲስ አበባ ገጽ እንዴት በይበልጥ ባማረ! የኢትዮጵያን ሕዝብ ነጻነቱን መልሶ ሲቀዳጅና መንበረ መንግሥቱን በእጁ ሲይዝ ለጀግኖቹ ውለታ ብቻ ሳይሆን፣ ለራሱ ክብር ሲል ማስታወሻ ኃውልታቸውን እንደሚያዎም አልጠራጠርም።
በኢትዮጵያኖች ላይ የደረሰው ግፍ፣ በማናቸውም ሕዝብ በቀላሉ ሊፈጸም የማይችል ነው። የዓለም ሕዝብ ሊቀበለው የምይችል፣ ለዚያም በላይ ለሰብዐዊ መብት ሲል ተገዶ የሚወስደው ዕርምጃ ነበር። አለመሆኑ፣ “ልጁ ቀማኛ አባቱ ዳኛ” የሚባለውን እስስር ሁኔታ በግልጽ አሳይቶናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በማያውቀው ረቂቅ ሴራ ወራሪን የሚቋቋምለትንና ከተገዥነት የሚያድነውን አካል እንዲያጣ ተደረገ። የሀገርና የሕዝብ ሰንሰለቶች በረቀቀ የሴራ ስልት ተበጣጠሱ። ከታች እስክላይ የነበረው የአስተዳደር ድርብርብ በዘዴ ተናደ። የተረፈው ዳግም እንዳይነሳ በተቀደደለት በር ወደ ውጭ ጎርፎ እንዲወጣ ተደረገ። ለማዳን ከተባለ ይሁን። እስራኤልም የተፎከረበትን የአማራ ሰው ለማዳን ጎትታ አውጥታለች። ኢትዮጵያ ወገኗን በህይዎት ልትጠበቅ ስላልቻለች፣ የቀረው ለመኖር ሲል በዓለም ዙሪያ ተሰደደ። ያረገጠው ምድር የለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የዘመኑ እስራኤሎች (አይሁዶች) ሆነዋል። ምክንያቱና መነሻው አንድና ተመሳሳይ ነው። የተሰደዱት ኢትዮጵያኖች ባረፉበት ምድር ሁሉ ሌላ ፈተና እንደሚገጥማቸው ግልጽ ነበር። ገዳይን ቢሸሹ ከሌላ መከራ አራቁም። ብዙዎቹ ለአስከፊ ግፍ ተዳርገዋል። በውጭ የሚኖርቱ ከናት ሀገራቸው ጋር ያለውን  የባህል፣ የቋንቋና የኃይማኖት እስስር እንዳይቋረጥ በያሉበት በአላቸው አቅም እየሞክሩ ነው። ግን፣ በሄዱበት ተከትሎ የሚሄድ ጣጣ አለ፣ ከዚያም በላይ ኢትዮጵያን የሚገዛው ጨቋኝ ኃይል፣ ስደተኞችን እየተከታተለ ባሉበት ሀገር ኑሮአቸው እንዲናጋ ለማድረግ የሚፈጽመው ሴራ ሊላ እጅግ አስጊ ሁኔታ ፈጥሯል። ብዙ የተንገላታ ሰው በቆየ ህመም በድንገተኛ ሞት እየተቀጨ የሚያልቀው ቁጥር ብዙ ነው። አንድ ሰው የዕድሜውን መጨረሻ ሲረዳ፣ አገሩ እንዲቀበር ምኞቱን ይገልጻል። ወይም ወዳጆችና ጎደኞች አስበው ሬሳው በውድ ሀገሩ እንዲያርፍ ያደርጋሉ። ሆኖም በአረፈበት ሀገር መቅበር እየተለመደ ነው። ኢትዮጵያኖች ሲሰደዱ በወንዝና በባህር ውስጥ ሰምጠው፣ በበርሃ ሲጓዙ ተርበው፣ ተጠምተው፣ ታመውና በአውሬ ተበልተው ያለቁ መቃብር ቀርቶ ያልተለቀሰላቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ናቸው። የጠፉት ሰወች አባቶች/እናቶችና አያቶች በቆረቆሯቸው ከተሞች ውስጥ እንዳይኖሩ ሲባረሩ፣  የአረመኔዎቹ መሪ ይህ በማይባል ልቅሶና ዳንኪራ ተቀብሯል። የት? ከአያቶቻቸው ጎን! እንደውም በዚችው መናገሻ ከተማ ኃውልቱ እንዲቆም ታስቧል!
ክቡር ፕ/ር መስፍን፣ ሸሽተናል፣ ሀገር ጥለን ሄደናል። ሆኖም በህይዎት ወደ ሀገሩ ተመልሶ ለመኖር የማይመኝ ሰው ካለ ጣት ይቁጠረው። በውጭ የሚኖር ሰው ሬሳው በሀግሩ እንዲያርፍ መጠየቁ ይህን ምኞቱን ያመለክታል። ሕዝብ ታሪክ የሆነውን ምግባርና ድርጊት አመዛዝኖ ያውቃል። አንድ ሰው የራሱን ኑሮና ህይወት ሰውቶ ለወገኑና ለሀገሩ ጥቅም ታላቅ ምግባር ሲፈጽም፣ ሕዝብ በበኩሉ ለታሪክና ለትውልድ ጥቅም ሲል የጀግኖችን ስምና ታሪክ ወርሶ የሀገሪቱ ቅርስ ያደርጋል።

No comments:

Post a Comment