Friday, July 5, 2013

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ በመንግስት ጥያቄ መሰረት የጎንደርን ሰላማዊ ሰልፍ ለሐምሌ ሰባት አዘዋውረናል አለ

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

አንድነት ፓርቲ የሶስት ወራት ህዝባዊ ንቅናቄ የትግል ስልት በመንደፍ የመጀመሪያውን የአደባባይ ላይ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ሰኔ 30/10/2005 በጎንደር ከተማ እንደሚያደርግ ማሳወቁ የሚታወስ ነው፡፡ ሁልጊዜም የሀገሪቱን ህግ ጠብቆ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሰው ፓርቲያችን የአገሪቱ ህገ መንግስት አንቀፅ 30 የሰላማዊ ሰልፍ አዋጅ 50 ዓመት ቁጥር 4 በሚደነግገው መሰረትም ከህዝቡ ጋር የሚያደርገውን ሰላማዊ ሰልፍ በጎንደር ከተማ ማወቅ ለሚገባው አካልና ለዞኑ አስተዳደር አሳውቆ ወደ ቅስቀሳ በመግባት 80 በላይ በራሪ ወረቀቶችን በማሳተም 20 በላይ በራሪ ወረቀቶችን በጎንደር ከተማ አሰራጭቷል፡፡ በመዋቅራችን አማካኝነትም የቤት ለቤት ቅስቀሳ በማድረግ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምፁን እንዲያሰማ እያደረግን ባለንበት ወቅት በክልሉ መንግስት የማደናቀፍና የማሰር ርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡

በክልሉ መንግስት አባሎቻችን ላይና አመራሮቻችን ላይ በሕገ ወጥ መንገድ ህገ መንግስታዊ መብታቸው እየተገፈፈ፤ ሰብዓዊ ክብራቸውን በመጣስ ላይ ነው፡፡ በሰሜን ጎንደር ዞን በምዕራብ አርማጭሆ አብርሃ ጅራ ከተማ የፓርቲያችን አባላት የሆኑት አቶ አለልኝ አባይ፣ አቶ እንግዳው ዋኘው፣ አቶ አብርሃም ልጃለምና አቶ አንጋው ተገኝ የፓርቲውን የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ለምን በተናችሁ ተብለው ከሰኔ 22 ቀን 2005 . ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በጎንደር ከተማ አቶ ማሩ አሻገረ ከሰኔ 26 ቀን 2005 . ጀምሮ፣ አቶ አምደማሪያም እዝራ እና አቶ ስማቸው ዝምቤ ከሰኔ 25 ቀን 2005 . ጀምሮ በእስር ላይ ናቸው፡፡ እንዲሁም በወገራ አቶ ጀጃው ቡላዴ ሰኔ 25 ቀን 2005 . ታስሮ ተለቋል፡፡ አቶ ጋሻው ዘውዱ ላይ ጥይት በመተኮስ የመግደል ሙከራ የተደረገ ሲሆን ሮጦ ለማምለጥ ችሏል፡፡ በአልፋ ጣቁሳ ወረዳ መምህር አዋጁ ስዩም ከሰኔ 26 ቀን 2005 . ጀምሮ በእስር ላይ ሲሆን ሁሉም የታሰሩት ለምን ቀሰቀሳችሁና ወረቀት አሰራጫችሁ በሚል ነው፡፡ ፓርቲያችንም የዞኑን መስተዳድር አፋኝነትና ህገወጥነትን እያወገዘ የታሰሩ አባሎቻችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ በፅኑ እንጠይቃለን፡፡ የታሰሩ አባሎቻችንም ህገወጥ እስሩን በመቃወም ከትናንት ጀምሮ የርሀብ አድማ ላይ ናቸው፡፡

የዞኑ አስተዳደርና የከተማው /ከንቲባ በአንድ በኩል ሰላማዊ ሰልፋችንን ለማፈን ርምጃ እየወሰዱ በሌላ በኩል የህዝቡ ሰላማዊ ትግል ወዳድነት ስላስደነገጣቸው የእንነጋገር ጥሪ 25/10/2005 . አቀረቡ፡፡
በተለይም የከተማው /ከንቲባ የሆኑት አቶ ጌትነት አማረ ከሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች ጋር 27/10/2005 . 2 ሰዓት የፈጀ ድርድር ካደረጉ በኋላ ሰላማዊ ሰልፉ በሚደረግበት ዕለት በጎንደር የተማሪዎች ምረቃ ስላለና የመንገድ ምረቃ ስላለ እንዲሁም ፖሊስ ግምገማና ስልጠና ላይ በመሆኑ በቂ የጥበቃ ኃይል አይኖረንም በሚል ቀኑን አዘዋውሩልን የሚል ጥያቄ በማቅረባቸውና ይህም ጥያቄ ተገቢ ሆኖ ስላገኘነው በጎንደር የሚደረገውን ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ከሰኔ 30 ቀን 2005 . ወደ እሁድ ሐምሌ 7 ቀን 2005 . ተዘዋውሮ እንዲደረግ ፓርቲያችን ወስኗል፡፡

በዚህም መሰረት ህዝባዊ ንቅናቄያችን የቆመለትን ዓላማ በምንም ህገ-ወጥነት የማይቀለበስ መሆኑን እየገለፅን ሰላማዊ ትግላችንን አጠናክረን እንደምንቀጥል እናረጋግጣለን፡፡ ሰላማዊ ትግል የሚያስከፍለውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል የቆምንለት ክቡር አላማ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህንን በመረዳት አሁንም እንደበፊቱ ሁሉ በቁርጠኝነት ከጎናችን እንዲቆም ጥሪያችንን በድጋሚ እናቀርባለን፡፡ የጎንደርና አካባቢው ሕዝብም ይህንን አፋኝ ስርዓት በማውገዝ ከጎናችን በመቆም ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሀገራዊ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡

የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት!!!

UDJ 

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

ሰኔ 28 ቀን 2005 .

አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment