Saturday, July 20, 2013

አቡነ ጢሞቴዎስ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊነት ተገለሉ፤ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ኮሌጁን በጊዜያዊ ሓላፊነት እንዲመሩ ተመድበዋል

  • አቡነ ጢሞቴዎስ ጉዳያቸው ከሚታይበት ስብሰባ ላለመውጣት ሲለመኑ ውለዋል
  • ፓትርያሪኩ ስለ አቡነ ጢሞቴዎስ ብዙ ከመናገር ተጠንቅቀዋል፤ ተቆጥበዋል
  • ደቀ መዛሙርቱና መምህራኑ ደስታቸውን በቅኔ፣ ወረብና መዝሙር እየገለጹ ነው
  • የአጣሪ ኮሚቴው የመፍትሔ ሐሳቦች እንዲተገበሩ ቅ/ሲኖዶሱ መመሪያ ሰጥቷል
  • የንቡረ እድ ኤልያስ ምደባ ከሚያስነሣው ግዙፍ ጥያቄ ጋራ የምረቃው ቅድመ ዝግጅት ይቀጥላል..
His Grace Abune Timothy
ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ጢሞቴዎስ
ላለፉት 14 ዓመታት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን በበላይ ሓላፊነት ሲመሩ የቆዩት ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ጢሞቴዎስ ከሥልጣናቸው እንዲገለሉ ቅዱስ ሲኖዶስ መስማማቱ ተገለጸ፡፡

ቅ/ሲኖዶሱ ዛሬ፣ ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በደረሰበት ስምምነት መሠረት÷ በኮሌጁ ደቀ መዛሙርት እና መምህራን ከፍተኛ ተቃውሞ የተነሣባቸው ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ በበላይ ሓላፊነት ከያዙት ሥልጣን ይገለላሉ፤ ለኮሌጁ አዲስ ሊቀ ጳጳስ እስከሚመድብ ድረስም የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ‹‹የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ›› ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በጊዜያዊ ሓላፊነት እየሠሩ እንዲቆዩ ተመድበዋል፡፡
በቀን መደበኛ ደቀ መዛሙርት እና በኮሌጁ አስተዳደር መካከል በተፈጠረውና ላለፉት ስድስት ወራት ሲባባስ ለቆየው አለመግባባት እልባት ለመስጠት በተጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ከ18 ያላነሱ የቅ/ሲኖዶስ አባላት ተገኝተዋል፡፡ ተሰብሳቢዎቹ የኮሌጁን አስተዳደራዊ እና አካዳሚያዊ ኹኔታ፣ የቦርዱን አሠራር፣ የመምህራኑንና ደቀ መዛሙርቱን አያያዝ በተመለከተ የተፈጸሙ ስሕተቶችን በመዘርዘር የበላይ ሓላፊው ችግሩን ለመፍታት የተከተሉትን አካሄድ ተችተዋል፡፡ አቡነ ጢሞቴዎስ ከሚገኙበት የዕርግናና የጤንነት አቋም በመነሣት የችግሩ አያያዛቸው ሊቀ ጳጳሱንና በዙሪያቸው የተሰለፉ ግለሰቦችን ከመጥቀም በቀር የኮሌጁን መብት የማያስጠብቅ፣ ሀብቱን ለብክነት የሚዳርግና ተቋማዊ ተልእኮ የሚያሰናክል እንደኾነ በመግለጽ ለውዝግቡ መባባስ የበላይ ሓላፊውን ዋነኛ ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
በስብሰባው የተወሱት ጉዳዮች አለመግባባቱን ያጣራው ኮሚቴ በ18 ገጾችና በስምንት ዋና ዋና ክፍሎች ካቀረበው ሪፖርት ጋራ ተቀራራቢ እንደኾነ የገለጹት የስብሰባው ምንጮች መፍትሔውም ኮሚቴው ከአጭርና ከረጅም ጊዜ አንጻር በመከፋፈል ባቀረባቸው የማስተካከያ ርምጃዎች መሠረት ተፈጻሚ እንዲኾን ከስምምነት ላይ መደረሱ ተዘግቧል፡፡ ስለኾነም በቀደመው ዜና ብሥራታችን እንደገለጽነው፣ የኮሌጁ የቀን መርሐ ግብር ሓላፊ ዘላለም ረድኤት ከኮሌጅ ሓላፊነቱ ከመነሣቱም በላይ ከኮሌጁ ይወገዳል፤ አካዳሚክ ዲኑ መ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝ ከአካዳሚክ ምክትል ዲን ሓላፊነታቸው ተነሥተው የያዟቸው ተደራራቢ ኮርሶች ተቀንሰው በማስተማር ሥራ ብቻ ይወሰናሉ፡፡
ቀድሞ እንደተጠበቀው የዛሬው አስቸኳይ ስብሰባ ያሰማን ዐቢይ ውሳኔ፣ የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ከሥልጣናቸው ገለል እንዲሉ መደረጋቸው ነው፡፡ ስብሰባው የተጀመረው ሌሎች ወቅታዊ አጀንዳዎችን በመመልከት እንደነበር የተገለጸ ሲኾን በኮሌጁ ዙሪያ መወያየቱን ለመቀጠል በሕገ ቤተ ክርስቲያን በተደነገገው መሠረት የብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ከስብሰባው መውጣት የግድ ነበር፤ ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ አባላትየተደነገገው የሕጉ አንቀጽ ፰ ንኡስ አንቀጽ ፯ እንደሚሠራው፣ አንድ የሲኖዶስ አባል ስለራሱ ጉዳይ በሚታይበት ስብሰባ ላይ በአባልነት መገኘት አይችልምና፡፡
የሕጉን የስብሰባ ሥርዐት በመጥቀስ ጭምር ከስብሰባው እንዲወጡ የተጠየቁት ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ግን ፈቃደኛ ባለመኾናቸው በተሳታፊዎቹ ሲለመኑ ውለዋል፤ ከዚህም አልፈው ቅ/ሲኖዶስ የኮሌጁን ወቅታዊ ኹኔታ አጀንዳ በማድረግ ለአስቸኳይ ስብሰባ መቀመጡን ሳይቀር ነቅፈዋል፤ ስብሰባውንም ‹‹ሕገ ወጥ ነው›› ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ ቅ/ሲኖዶሱ ‹‹አስኬማዬን ይረከበኝ›› ሲሉም አሻፈረኝ ብለዋል፡፡ ምንጮቹ እንደገለጹት ልመናው በመጨረሻ ሠምሮ ስብሰባው ባለጉዳዩ በሌሉበት የቀጠለው የጉባኤው ርእሰ መንበር ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ሲጨመሩበት ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጣዊ ጉዳይ የማይመለከታቸው ወገኖች ሁሉ እጃቸውን በችግሩ ሰበብ እንዲያስገቡ ምክንያት መኾኑን ያወሱት ርእሰ መንበሩ፣ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ብዙኀን መገናኛ ርእሰ ጉዳይ እየተደረገች መተቸቷ እንዳሳዘናቸው በመግለጽ ጉባኤው መፍትሔ እንዲሰጠው ጠይቀዋል፤ ከዚህ በቀር አቡነ ጢሞቴዎስን በሚመለከት ሌሎች ተሰብሳቢዎች በሰፊው ከተናገሩት በአንጻሩ ጥንቃቄና ቁጥብነት መርጠው መታየታቸው ተስተውሏል፡፡ እንዲያውም ቤቱ በጉዳዩ ላይ መሠረታዊ አቋም እየያዘ መሄዱ ሲረጋገጥ ‹‹ይህን ሁሉ ነገር መኖሩን መች ዐወቅኁትና!›› በሚል ጸጸትና በእምባ ስሜታቸውን መግለጻቸው ነው የተሰማው፡
አቡነ ጢሞቴዎስ በሌሉበት ውይይቱ ቀጠለ፡፡ በቀደሙት ቀናት መምህራኑና የደቀ መዛሙርቱ መማክርት አመራሮች በቋሚ ሲኖዶሱ ፊት በየራሳቸው ቀርበው አስረድተው ነበር፡፡ በዛሬው ስብሰባ ደግሞ በቅ/ሲኖዶሱ የተጠሩት አቡነ ጢሞቴዎስ የሚመኩባቸው የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ነበሩ፡፡ ኮሌጁ እንዲዘጋ ደቀ መዛሙርቱም ለቀው እንዲወጡ ለፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት የውሳኔ መነሻ ሰጥተዋል የተባሉት የቦርድ አባላት በቅ/ሲኖዶሱ ፊት የሰጡት ምስክርነት ግን እንደወትሮው አቡነ ጢሞቴዎስን የሚደግፍ አልያም ድክመታቸውን የሚሸፍን አልነበረም፡፡
ይልቁንም እንደ ቦርድ የመሥራትና የመወሰን ነጻነት እንደሌላቸውና ኮሌጁን እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመምራት እንዳልቻሉ አጋለጡ፤ በተለይ በየ15 ቀኑ እየተገናኘ ሻይ ቡና ጠጥቶ፣ አበሉን ሰብስቦ ብቻ ከመለያየት በቀር መምህራኑን ይኹን ደቀ መዛሙርቱን አናግሮ እንደማያውቅ በተተቸው የቦርዱ ስብሰባ ላይ አዘውትረው ይገኛሉ የሚባሉት ዶ/ር ተጠምቀ መሐሪ ኮሌጁ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው የሚያሰኝ አስተዳደራዊና አካዳሚያዊ ቁመና ይኹን የተሟላ ሎጅስትክ እንደሌለው በአጽንዖት ተናገሩ፡፡
በአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት ገጽ 4 እና 5 ላይ በተመዘገበው ቃላቸው አራት የሥራ አመራር ቦርዱ አባላት የጠቀሷቸው ችግሮችም ይህንኑ የሚያብራሩ ናቸው፡-
  • የኮሌጁ ቦርድ ከሌሎች ተመሳሳይ ቦርዶች የተለየ መኾኑ፤ ማለትም ለኮሌጁ የሚጠቅሙ ፖሊሲዎችንና ስትራተጅዎችን በማውጣት ሳይኾን በየዐሥራ አምስት ቀኑ እየተገናኘን የኮሌጁ አስተዳደር ሊሠራ የሚገባውን እየሠራ መኾኑን ይህንንም እንዲያደርግ ደንቡ የሚደነግግ መኾኑን፣
  • የኮሌጁ አስተዳደር የአመራር ድክመት ያለበት መኾኑ፣
  • የደቀ መዛሙርቱ አመላመልና አቀባበል ችግር እንዳለበት፣
  • የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የኾኑት በተለይም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በስብሰባው ላይ አዘውትረው አለመገኘት፤ በመደበኛ ስብሰባ የሚገኙት ከምእመናን የተመረጡ አባላት ሲኾኑ ስብሰባውን የሚመሩትም ም/ሰብሳቢው ዶ/ር ተጠምቀ መሐሪ ናቸው፡፡ ይህም ሃይማኖት ነክ የኾኑ ጉዳዮች በአጀንዳነት ሲቀርቡ ለመወሰን እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌ በተከለሰው ሥርዐተ ትምህርት የአምስት ዓመቱ የዲግሪ መርሐ ግብር ወደ አራት ዓመት ሲቀየር የብሉይ እና የሐዲስ ኮዳን ትምህርቶች ተገቢው ትኩረት አልተሰጣቸውም ተብሎ በመምህራኑ ለቀረበው ጥያቄ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ይህ ካሪኩለም ሲጸድቅ ቢገኙ ኑሮ ቅሬታ ላይፈጠር ይችል እንደነበር ተናግረዋል፡፡
  • ኮሌጁ የበጀት ችግር ያለበት መኾኑ፤ ምንም እንኳን የኮሌጁን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ በኮሌጁ ግቢ ግዙፍ ሕንጻ ቢገነባም በሕንጻው ገቢ ኮሌጁ እንደማይጠቀም፣ በባለሞያ ተጠንቶ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚቀርበው በጀት እየተቀነሰ በየዓመቱ ተመሳሳይ በጀት መላኩ፤
  • ለኮሌጁ መምህራን፣ ደቀ መዛሙርትና አስተዳደር የወጡ ደንቦች ክፍተት ያለባቸው መኾኑ፤ ለምሳሌ የኮሌጁ አካዳሚክ ኮሚሽን አባላት እና አስተዳደር አባላት ተመሳሳይ ኾኖ እንዲዋቀር ደንቡ መፍቀዱ አንዱ ያጠፋውን ሌላው እንዲያርም መንገድ አለመመቻቸቱ የሚሉ ሐሳቦች ይገኙበታል፡፡
ለእኒህ ችግሮች የቦርዱ አባላት የሰጧቸው ተነጻጻሪ የመፍትሔ ሐሳቦች እንደሚከተለው ሰፍረዋል፡-
  • የኮሌጁ በጀት ለይቶና ተስተካክሎ እንዲሁም ተመጥኖ እንዲሰጠው ቢደረግ፣
  • ከውስጥ ገቢ ማለትም ከካፌ፣ ከመማሪያ ክፍሎች፣ ከአዳራሽ ኪራዮች፣ ከማታ፣ ከማስተርስና ከርቀት ትምህርት ፕሮግራም የሚገኘው ገቢ በትክክል ታውቆ ቀሪው ከቤተ ክህነት የሚሸፈንበት መንገድ ቢመቻች ወይም ከሕንጻው ገቢ ላይ ተጠንቶ የተወሰነ ፐርሰንት ለኮሌጁ ቢሰጥ፤
  • ደቀ መዛሙርቱ በኮሌጁ ውስጥ በወጣላቸው መተዳደሪያ ደንብ እንዲተዳደሩ ቢደረግ፤
  • በኮሌጁ ውስጥ ጠንካራና ውሳኔ የሚሰጡ የአስተዳደር ሰዎች ቢኖሩ፡፡ በዚህ ውስጥ የኮሌጁ ደንብ እንደሚያስረዳው፣ ኮሌጁአንድ ዋና ዲንና በሥሩ የአካዳሚክና የአስተዳደር ም/ዲኖች እንደሚኖሩ ቢገለጽም ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ጢሞቴዎስ የኮሌጁ ዋና ዲን ወይስ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ መኾናቸው በግልጽ አለመታወቁ እና ዶ/ር አባ ኀይለ ማርያም መለሰ በሌለ መዋቅር ም/ዋና ዲን ተብለው መመደብ ከዚህም የተነሣ የአስተዳደር ም/ዲን የሚባለው መዋቅር በሥራ አለመዋሉ ናቸው፡፡
  • ኮሌጁ የተሟሉ የቦርድ አባላት ቢኖሩት፤ በተለይ ለቦርዱ አባልነት የተመደቡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በስብሰባ ላይ እንዲገኙ ቢደረግ፤ በቦርድ አባልነትም የትምህርተ መለኰት ዕውቀት ያላቸው የቤተ ክርስቲያን ምሁራን እንዲሳተፉ ቢደረግ፤


በዚህና በመሳሰለው መልክ የቀረበው የቦርዱ አባላት ምስክርነት የእውነታው ማረጋጋጫ ኾኖ ቅ/ሲኖዶሱን ወደ አንድ ውሳኔ አደረሰው – ላለፉት 14 ዓመታት ኮሌጁን በበላይ ሓላፊነት ሲመሩ የነበሩት አቡነ ጢሞቴዎስ ከበላይ ሓላፊነታቸው እንዲገለሉ፣ በአስተዳደሩ ጣልቃ እንዳይገቡና ምናልባትም እስከ መጪው ዓመት ጥቅምት ድረስ በበላይ ጠባቂነት እንዲቆዩ!
እንደ ስብሰባው ምንጮች መረጃ ግን ይህን የቅ/ሲኖዶሱን የስምምነት ውሳኔ ባለጉዳዩ አቡነ ጢሞቴዎስ ባሉበት ለማሳወቅ ጭንቅ ኾኖ ነበር፡፡ ከመምህራኑ፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤቱ እና በተለይም እንደ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ካሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ በ‹‹እንተያያለን›› እልክ ተጋብተው የሰነበቱት አቡነ ጢሞቴዎስ ውሳኔውን እንዲቀበሉት ለማግባባት በወዳጅነታቸው የሚጠቀሱት አቶ(ኣቦይ) ስብሐት ነጋ ሚና እንደተጫወቱ በስፋት እየተወራ ቢኾንም መረጃውን ከገለልተኛ ምንጭ ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
የአቡነ ጢሞቴዎስ ከሥልጣን መገለል እንደተሰማ መምህራኑና ደቀ መዛሙርቱ በአንድነት በኮሌጁ ቅጽር ተሰብስበው ደስታቸውን በቅኔ፣ ወረብና መዝሙር የገለጹ ሲኾን ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ሰዓት ሐሤት ማድረጉ ቀጥሎ እስከ መንፈቀ ሌሊት ዘልቋል፡፡
NebureEd Elias Abreha
ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ
ንቡረ እድ ኤልያስ በጊዜያዊ ሓላፊነት የሚቆዩበት ምደባ እስከ ቀጣይ ዓመት ጥቅምት ወር እንደሚቆይ የተገለጸ ሲኾን ኮሌጁ አዲስ ሊቀ ጳጳስ እስኪመደብለት፣ አስተዳደሩና ቦርዱ በአዲስ መልክ እስኪዋቀር ድረስ ከድጋፍ ሰጭ ሠራተኞችና መምህራን ጋራ እየተመካከሩ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ንቡረ እዱ ለአጭር ጊዜ የኮሌጁ የአስተዳደር ዲን ኾነው መሥራታቸውን ያስታወሱ ወገኖች የአሁኑ አለመግባባት በተባባሰበት ስድስት ወራት በፊት ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ጽ/ቤት ከነበራቸው ቅርበት አንጻር የተጫወቱት ሚና ገንቢ እንዳልነበር ተችተዋል፡፡ ቀደም ባሉት ዘገባዎቻችን ሲገለጹ ከቆዩት የከፋ የሙሰኝነት፣ ቡድንተኝነትና ጎጠኝነት ችግሮቻቸውም በመነሣት በአንጋፋው የትምህርት ተቋም መመደባቸው አርኣያነት ይጎድለዋል፤ ከተቋሙ ተልእኮም አንጻር የሚደቅናቸው ስጋቶች አሉት፡፡
haratewahido.wordpress.com

No comments:

Post a Comment