መደማመጥ ነው ቁም ነገሩ፡፡ መልዕክቱን በማስተላለፍ ሕዝብ እንዲያዳምጠውና እንዲቀበለው የሚፈልግ መንግሥት፣ ከሁሉም በፊት የሕዝብን ብሶትና ቅሬታ የሚያዳምጥና አዳምጦ መፍትሔ ለመስጠት የሚንቀሳቀስ መሆን አለበት፡፡
ያዳመጠ መንግሥት ይደመጣል፤ የማያዳምጥ መንግሥት አይደመጥምና፡፡
ስለሆነም የአመራር ጥበብ መጀመሪያ ሕዝብን ማዳመጥ ነው፡፡
በአዎንታዊ መንፈስ የሚታዩ በርካታ ስብሰባዎች በመንግሥት በኩል እየተካሄዱ ናቸው፡፡ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች ሚኒስትሮች የተገኙበት ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፡፡ የነጋዴውን ችግር ለማዳመጥ የተጠራ ስብሰባ ነበር፡፡ ነጋዴውም ከሞላ ጎደል ችግሩን ተናግሯል፡፡ የመንግሥት አዕምሮና ልብም እዚያው ነበር ጆሮውም ጭምር፡፡ ዋናው ጥያቄ መንግሥት አዳምጧል ወይ? ነው፡፡
አዳመጠ ስንል ቃላትን ሰማ ወይ? ማለታችን አይደለም፡፡ ቃላትማ ይሰማሉ፡፡ ቁም ነገሩ ግን ማዳመጡ ላይ ነው፡፡ ችግሩ ምንድን ነው? ጥልቀቱስ? ስፋቱስ? እያስከተለው ያለው ቀውስስ? በአገር ኢኮኖሚና ቢዝነስ ያለው ጫናስ? ከድህነት ለመላቀቅ በሚደረገው ሙከራ ላይ የሚያሳድረው ጉዳትስ? እየተባለና እየተስተዋለ፣ እየተመዘነና ስለመፍትሔው እየታሰበ ከልብ ማዳመጡ ላይ ነው ቁም ነገሩ፡፡
መንግሥት ከልብ ካዳመጠ ችግሩን ለመፍታት አያስቸግረውም፡፡ የማይፈታ ችግር አይደለምና፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትና የብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ከፍተኛ ኃላፊዎችም ከፕሬሱ ጋር ተገናኝተው በተከታታይ ሲወያዩ ፕሬሱ ያለበትን ችግር ዘርዝሮ አስቀምጧል፡፡ በግሉ ፕሬስ ላይ እየደረሰ ያለው የሕግ ጫና፣ የማተሚያ ቤት ችግር፣ የምዝገባና ዕድሳት እንቅፋቶች፣ የፋይናንስ አቅም፣ ወዘተ ተዘርዝሮ ተቀመጠ፡፡ የመፍትሔ ሐሳብ የተባለውም በዝርዝር ተደርድሯል፡፡
መንግሥት ችግሩን በግልጽና በዝርዝር ስለተቀመጠለት አልሰማሁም አላወቅኩም ሊል አይችልም፡፡ አላወቅኩም ሊል የሚችለው ቃላቱን ሰምቶ ቁም ነገሩን ያላዳመጠ እንደሆነ ነው፡፡ መንግሥት አዳምጦ ችግሩን ለመፍታት ከተንቀሳቀሰና የፕሬሱን ችግር ከፈታ የፕሬስ ነፃነትን እውን ለማድረግ ይዘጋጃል፡፡ ፕሬሱ ከተደመጠ መንግሥትን ያዳምጣል፡፡ መንግሥት ካላዳመጠ ግን ፕሬሱም አያዳምጥም፡፡
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንም ግብር ከፋዩን ኅብረተሰብ ሰብስቦ አነጋግሮ ነበር፡፡ ዜጎች ችግራቸውን በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡ ጥያቄው መንግሥት አዳምጧል ወይ? የሚል ነው፡፡
ሲቪል ማኅበረሰቡም ስብሰባ ተጠርቶ ችግሩን ዘርዝሯል፡፡ መንግሥት አዳምጧል ወይ? በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩትም ስብሰባ ተጠርተው ችግራቸውን ዘርዝረው አስረድተዋል፡፡ መንግሥት አዳምጧል ወይ?
በኤክስፖርት መስክ ያለውን ችግር ለመወያየት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት ሰሞኑን የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በኤክስፖርት መስክ ያሉት አመቺ ሁኔታዎችና አስቸጋሪ ጉዳዮች መፍትሔያቸው በሚያስገርም ሁኔታ በዝርዝር ቀርቧል፡፡ በአኀዝና በማስረጃ በማስደገፍ፡፡ ይህን ችግርና ይህን መፍትሔ መንግሥት ያዳምጠዋል ወይ? ይቀበለዋል ወይ?
በእግር ኳስ ፌዴሬሽን የተነሳ በደረሰው ችግር ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳንሆን ፊፋም ይኼው ይህ ችግር አለባችሁ ብሎናል፡፡ ከፌዴሬሽኑ አመራሮች የተገኘው ምላሽ ግን አለማዳመጡን ያሳያል፡፡ እንደምንም ጊዜያዊ ችግሩን አድበስብሶ ለማለፍና ለማረጋጋት ያለመ እንጂ፣ ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጥ ዕርምጃ አልተወሰደም፡፡ ብሶትንና ችግርን ከልብ የሚያዳምጥ አልተገኘም፡፡
የወጣቶች አትሌቶቻችን ለሽያጭ መቅረብ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በዜጎች ላይ በስደት እያደረሰ ያለውን አሳፋሪና አሳዛኝ ችግር ሕዝብ ለመንግሥት አቅርቧል፡፡ መንግሥት ሰምቷል፡፡ ግን አዳምጧል ወይ? ጆሮ፣ ልብና አዕምሮ በጋራ ችግሩን ተወያይተውበታል ወይ? የመንግሥት ጆሮ፣ ልብና አዕምሮ ማለታችን ነው፡፡
ሕዝብ ለመንግሥት ችግሩን የሚናገረው በስብሰባ ብቻ አይደለም፡፡ በየቀበሌው፣ በየክፍለ ከተማው፣ በየከተማ አስተዳደር እርከኖች፣ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በየክልሉ፣ ወዘተ በማመልከቻ፣ በቃልና በጽሑፍ በየደቂቃውና በየሰኮንዱ አቤት እያለ ነው፡፡ የሰሚ ያለህ እያለ እየጮኸ ነው፡፡ መብቴ ተረገጠ፣ ንብረቴ ተቀማ፣ ጉቦ ካልሰጠህ ችግርህ አይፈታልህም ተባልኩ፣ አድልዎ ተፈጸመብኝ፣ ወዘተ እያለ ነው፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ የሚያዳምጠው እያገኘ ነው ወይ?
ምናልባት መንግሥት የእከሌን ማመልከቻና አቤቱታ ሰምቼ መፍትሔ ሰጥቼ የለም ወይ ሊል ይችል ይሆናል፡፡ በኔትወርክ፣ በጉቦ፣ በወዳጅነትና በሕገወጥ ግንኙነቶች ላይ በተመሠረተ መንገድ ስለሚሰጥ መፍትሔ አይደለም የምንነጋገረው፡፡ እንደ ዜጋ ከሕግና ከመብት አንፃር ስለሚቀርብ አቤቱታና ስለሚሰጥ ምላሽ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያም ሕዝብ መንግሥት ለምን አያዳምጥም እያለ እያለቀሰ ነው፡፡
እዚህ ላይ ሁለት ዓበይት ቁም ነገሮችን መጥቀስ እንፈልጋለን፡፡
1.
ሕዝብን ማዳጥ የመንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነው
መንግሥት ያዳምጥ ስንል እባክህ ሩህሩህ፣ አዛኝና ሰው አክባሪ ሁን እያልን እየተማፀንን አይደለም፡፡ የሕዝብን እሮሮና ብሶት ማዳመጥ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታህ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ የተቀመጥከው ለዚህ ነው፡፡ ሕዝብን ካላዳመጥክ በሕግ ተጠያቂ ትሆናለህ ማለታችን ነው፡፡
2.
የማያዳምጥ መንግሥት የማይደመጥ መንግሥት ይሆናል
መንግሥት ሕዝብን የሚያዳምጠው በሕገ መንግሥቱ ስለሚገደድ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የሕዝብ ወገን ነኝ የሚል ሥልጣን የያዘ ፓርቲና መንግሥት፣ ሕዝብን ምረጠኝ የሚል ፓርቲና መንግሥት፣ የሕዝብ ከበሬታና አመኔታ ሊያገኝና ዓላማውን በተግባር ላይ ሊያውል የሚችለው ሕዝብን ሲያዳምጥ ብቻ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ የሚቆየው ሕዝብን ሲያዳምጥ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ ለራስ ተብሎም መደረግ ያለበት ነው፡፡ የማያዳምጥ መንግሥት የማይደመጥ መንግሥት ይሆናልና፡፡
No comments:
Post a Comment