Monday, July 22, 2013

ይድረስ ለተገፋው ወገኔ !

“ህገ መንግስት ተጥሷል!” ካልክ ድምጽህን በሰላማዊ ተቃውሞ አሰማ !
ይድረስ ትናንተም ሆነ ዛሬ ግፍ በነገሰባት ምድር ኑሮን በመከራ ለምትገፋው ወገኔ ! ይድረስ መልካም አስተዳደር ጠፍቶ በደል ለተጫነብህ ፣ ፍትህ ርትዕ ተዛብቶ የአስተዳደር ሚዛኑ ኑሮህን ላጨለመው ወገኔ ! ይድረስ ከዲስኩር  ባላለፈ  ”የእድገት ስልጣኔ መንገድ እየተጓዝክ ነው ” ለሚሉህ ፣ ይድረስ ግልጽነት በጎደለው “መልካም አስተዳደር” ለምትረገጠው ታጋሽ ወገን፣ ይድረስ ትናንትም ሆነ ዛሬ ከአብራክህ ወጥተው አንተን ያልሆኑ ፣ ህመምህ የማያማቸው፣ በደልህ በማይገባቸው የመንግስት ምስለኔ ልጆችህ እየተሰቃየህ ላለህው ! ይድረስ የግፍ በደል ቀንበር ከትከሻህ ላልወረደልህ፣ ስቃይ መከራው ላላባራልህ ይድረስ ለከልታማው ወገኔ! ይድረስ የአንድ ጎልማሳ እድሜን በጭቆና መግፋቱ እያመመህም ቢሆን ለቻለከው፣ በቁጣ አመጻን ከመግለጽ ተገትተህ ጎስቋላ ኑሮን በዝምታ፣ በይሁንታ እየገፋህ ላለህው ወገኔ! በኮራህ በደላህበት፣ አክብረህ በተከበርክበት ቅየ ያ ክፉ ቀን አለፈ ስትል፣ ዛሬም ክፉው ቀን ተከትሎ  አበሳህን እያሳየህ ለምትገኘው ተገፊ ወገኔ!

ኑሮ ሳይደላህ አመጻን አለመምረጥህ እና በደልን በዝምታ ቁዘማ ማሳለፍን የመምረጥ ምክንያትህን ከቀየው የወጣሁ ነኝና አውቀዋለሁ ! ጎንደሬውም ሆንክ ወሎየው እንደቀረው ኢትዮጵያዊ በጨካኙ ወታደራዊ ጁንታ አገዛዝ ከአብራክህበወጡ ጨካኝ ልጆችህ የጋለ ብረት አለሎ ተቀጥቅጠሃል። ልጆችህ ታስረው ርህራሄ በሌላቸው የአገዛዙ አቀንቃኞች ቁም ስቅላቸውን እያዩ ተገርፈዋል። በግፍ የተገደሉ ልጆችህን አስከሬን በወጉ እንዳትቀብር ተደርገሃል። መሽቶ እስኪነጋ በጨካኞች አረመኔያዊ የቀይ ነጭ ሽብር ዘመቻ ባሩድ የተረሸኑ ልጆችህ ደም ጉራንጉሩን፣አውራ ጎዳናዎችና አደባባዩን አጨቅይቶት የከፋ የሽብር ጊዜ አሳልፈሃል፣ አይገፋ የለም ቁጣህን አምቀህ ክፉውን ቀን በሆደ ሰፊነት  ገፍተሃል! በዚያ ክፉ ዘመን የስጋ ክፋይ ወንድሞቸን ፣ “የት ይደርሳሉ!” የተባሉ የዘመድ አዝማድ ጎረቤት ትንታግ ወጣቶችን በግፈኛው አገዛዝ የተነጠቁ ወገኖች አካል ነኝ ። ስለዚያ ዘመን የወላድ መከራ የማውቀው ጥቂት ባይባልም፣ ሰለነበረው ስርአት አስከፊነት የታሪክ መዛግብት አገላብጫለሁ ፣ የአይን እማኞችን “አህ” ብየ አድምጫለሁ! ከሁሉም በላይ የልጆቻቸውን የሞት መርዶ ለመስማት ብርቅ ሆኖ ሳይሳካላቸው ከቀሩት እናቶች መካከል ልጅ ብሆንም ያኔ የእኔዋን እናት እንባ አልረሳውም! በድህነት ቤት ልጅ ወልደው ፣አሳድገው በሞት ሲነጠቁ ለመቅበር ሳይታደሉ የቀሩት እናቶችን ቤት ይቁጠረው። ማቅ ለብሰው ማቅ መስለው አመታትን የገፉ እናቶች አብራክ ውጤት ነኝና የዘመኑን ስርአት ክፋት ጭነት አውቀዋለሁ። በዚያ የግፍ ዘመን በቀሩት የሃገሪቱ ክፍል እንደሆነው ሁሉ በጎንደር በጎጃም እና በወሎ ዋና ከተሞች ያለተወሰነው የግፍ እርምጃ በገጠር የወረዳና የአውራጃ ከተሞች በወጣቱ ደም የጨቀዩበተት ዘመን ፍጹም አይረሳም ።
ወገኔ ሆይ ! እዚህ ባደረሰህ መንገድ ለጋ ወጣት ልጆችህን ገብረሃልና የዛሬው ዝምታህ አይደንቀኝም ። በግፍ ጭቆናው ዘመን የሌሊቱ ጥይት እሩምታ በረድ ሲል የማለዳው ደሮ ሲጮህ ሬሳ የመፈለጉ አሰቃቂ የታሪክ ሂደት እንደ ቀረው የኢትዮጵያ ወገንህ ምሬት ሃዘንክን ጠባሳ ጥሎብሃልና ዛሬ አንገት መድፋት መቆዘምህ አያስደንቀኝም። ዛሬም ዘመን ከፍቶህ ዳግም ትንታግ ልጆችህን አንዳታጣ ስጋት ሆኖብህ ዝም በማለትህ “ሃሞትህ ፈሰሰ!” እያልኩ ላሳብቅብህ የረከሰ  ሰብዕናን አውርሰህ አላሳደግከኝምና ፣ በቁዘማ ዝምታህ አልፈርድም ። በከተማ ባሩድ እና ባልጠቀመን የእርስ በርስ ጦርነት የአብራክህን ክፋይ ልጆችህን በጆፊ አሞራ የተነጠቅክ የህብረተሰብ ክፍል ነህና ህመምህ ህምሜ በመሆኑ ይገባኛል። እናም የዛሬ ህመም ስጋትክን አሳምሬ አውቀዋለሁ ! እናም ” ለምን ግፍ ሲጫኑህ  በዝምታ ትቆዝማለህ? “ለማለት አይዳዳኝም! ያኔ! ያ ክፉ የደርግ ስርአት ያከትም ዘንድ ሃዘንክን ሃዘን አድርገህ በአገዛዙ ላይ አኮረፍክ ፣ ዳሩ ግን ልክ እንደ ዛሬው በዝምታ ቁዘማ አንገትክን ደፍተህ ግን አልተቀመጥክም ። ለምስክር የተረፉ ልጆችህ ለመስዋዕት በማዘጋጀት መርቀህ ወደ መራራው ትግል መርቀህ ላክካቸው ፣ እኒያ አንበሶች ተራራ ቋጥኝ ቧጠው ፣ ሸንተረር ወንዙን ተጋፍተው ተሻግረው ብሩህ በመከባበር የተገነባች ኢትዮጵያን ይፈጥሩ ዘንድ ነበር ።
መራራው መስዋዕትነት በደም ተከፍሎ ያገኘህውን ውጤት ቢያሳዝንም ለሰላም ሲባል ይሁንታህን ሰጠህ ! ዲሞክራሲ ተሰብኮ እንለይ ያሉት ተለይተው፣ሃገሬው በቋንቋ ሲደለደል ሌላ መከራ ለመምጣቱ ምልክቶች ቢታዩም ይህንንም ይሁን አልክ! ለሰላም ለእድገት ሲባል! የሰቆጣ አላማጣው ፣ የሁመራና የወልቃይት ጠገዴውን ክፍፍልም ሳትመርጥ ፣ ሳትወድ የተጫነብህ ቢሆንም ይህንንም በዝምታ ቁጭት አለፍከው ! ያልቻልከውን ህመም የመጣብህ ፣ ከአመታት በፊት ከሱዳን የሚዋሰነው ድንግሉ የሃገርህ መሬት ከፍትህ ርትህ ውጭ ሃገሬው እየተፈናቀለ ለሱዳን እንዲሰጥ መደረጉ ነበር። ይህ አስቆጭቶ ቢያንገበግብህም ዝምታ ቁዘማህ ዛሬም ትዕግስት መሆኑን የሚረዱ ምስለኔዎችን አልታደልክም!
እናም የደም ክፋይ ነኝና ምክሬን ትሰማ እማጸንሃለሁ ! የተሰጠህን ዲሞክራሲያዊ መብት ተጠቀምበት ! ዝምታ ቁዘማውን ፣ ቁጭት ንዴት አቤቱታህን በሰላማዊ ተቃውሞዎች ሁሉ ተሰልፈህ ጥያቄዎችህን ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድምጽህን ከፍ አድርገህ በማሰማት ዝምታህን ትሰብር ዘንድ እመክርሃለሁ!
ኑሮህ ከድጡ ወደ ማጡ የመሆኑን ግራ አጋቢ እንቆቅልሽ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ እያለ ፣ ድህነት እና ስራ አጥነት በሃገር ነግሰው ፣ ኢኮኖሚ የሚሉት “አደገ !” ይሉናል ። ለእድገቱ ዋቢ ደግሞ በኑሮውን ጣራ መንካት የተደቆስውን ያንተን  ጓዳ የማያውቁት የአለም ገንዘብ ድርጅት እና ከአመት አመት የሚሰጠው የእድገት ቁጥር ከፍ ማለት ብቻ ነው ። ምድር ላይ ያለውን እውነታ ግን ከሚባለው የተለየ ነው! የኢኮኖሚው ብቻውን ማደግ ከመንገድና ከፎቅ ግንባታ ያለፈ ላለመሆኑ ብዙ ማለት ይቻላል ። የኢኮኖሚው ማደግ በአንተ በዜጋው የለት ተለት ኑሮ ላይ የማይታይ የማይዳሰስ ለመሆኑ ለማንም የተደበቀ አይደለም ። በኑሮው ጣራ መንካት ፣ በድህነቱ፣ በመልካም አስተዳደር እጦትና በስራ አጥነት ምክንያት እኔ ወዳለሁበት አረብ ሃገር ብቻ ያለ ህጋዊ ማዕቀፍ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ እድሜያቸው ለአቅመ አዳም ያለደረሱት ዜጎች በህጋዊ ኮንትራት ስም ተሰደዋል። እኒህ አብዛኛው ከገጠሩ የሃገራችን ክፍሎች በደላላ ተግዘው የመጡት አብዛኛው ሴት እህቶች እድሜያቸውን ቆልለው ሲሰደዱ እንኳ ከልካይ የለም። ይህ ብቻ አይደለም ። ለስራ ወደ ስለሚሔዱበት ሃገርም ሆነ ሰለሚሰሩት ስራ በቂ መረጃ አይሰጣቸውም! ችግር ቢገጥማቸው ለማን አቤት አንደሚሉና ወዴት እንደ ሚሄዱ አያውቁም! የመልካም አስተዳደሩ እና የመንግስት ተቀቋማት ግልጽነት ብሎም ተጠያቂነት አለመኖር ድህነት እንዳሸሸው ዜጋ ድንበር ለመሻገሩ ብዙ አመላካች መረጃዎችን ማቅረብ እችላለሁ ! በዋናነት የሚነሳው ዜጎች ከሃገር በስራ ኮንትራት ከመላካቸው አስቀድሞ በሃገሮች መካከል ግልጽ ስምምነት አለመደረጉ ነው። በዚህ ሁኔታ የተሰደዱትም ቢሆን የመብት ጥሰት ሲገጥማቸው አቤት ብለው ወደ ፍትህ የሚያቀርባቸው የተዳራጁ ሚስዮኖች አሉ ከማለት የሉም ማለት ይቀላል !
ወገኔ ሆይ! የዜጎች የከፋ ስደትና የመብት ጥበቃ ጉድለት መፍትሔ ያገኝ ዘንድ ለመንግስት ያለመታከት ተናግሬ ፣ መክሬ ፣ ዘክሬ የሰማኝ የለም! እናም ይህ በአብራክህ ክፋዮች ላይ እየደረሰ ላለው በደል በማናቸውም ስብሰባም ሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ተሳትፎ በማድረግ ድምጽህን እንድታሰማ እመክርሃለሁ! አማጸንሃለሁ!  የህዝብን ድምጽ የሚሰማ መንግስት ይስጠን!
ከሰላምታ ጋር
ነቢዩ ሲራክ
ሃምሌ 2005 ዓም ሳውዲ አረቢያ

No comments:

Post a Comment