ይህን እንድል ያስገደደኝ ለረዢም ጊዜ ውስጤ ሲብሰለሰል የቆየና አሁንም እንዲያገረሽብኝ ምክንያት የሆነው አንዳንድ ሰዎች በሚሰጡት አስተያት ነው፡፡ በጣም የሚገርመኝ በስመ ተቃዋሚ እዚሁ አገር ቤትም ተቀምጠው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሆነው ለዚህ አላማቸው ቀን ከሌት የሚሰሩ አሉ፡፡ ሊታወቅ የሚገባው ነገር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተደረጉ መልካምም ሆነ መጥፎ ነገሮች የኢትዮጵያ ታሪክ ሆነው ማለፋቸውን ነው፡፡ እኔን አብዝቶ የሚገርመኝ በታሪክ ስህተቶችን ብቻ እያነሱ እንዲህ ሁነናል እንዲህ ተደርገናል የሚባለው ነገር ነው፡፡ ይሄን ማለት በራሱ መፍትሄ አይሆንም፡፡ መሆን ያለበት እንዴት ከስህተታችን እንማር እንዴት ወደፊት እንሂድ የሚለው ነበር መሆን ያለበት፡፡
ኢህአዴግ የሚመራበት ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም ለዚህ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል፡፡ በርግጥ ለኢህአዴግ ይሄ ከፋፍለህ ግዛ ህልውናው ነው፡፡ እንደዛ ባይሆንማ እግርና እጅ በሌለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለ22 አመታት ስልጣን ላይ አይቆይም ነበር፡፡ እናም ከኢህአዴግ እንደነዚህ አይነት ማለትም ሃይማኖትን፣ ቋንቋን ፣ ብሄርን የመሳሰሉት ላይ አተኩሮ ቢሰራ አይገርመንም ምክንያቱም ሲነሳ የጀመረው ከፋፍለህ ግዛ ስለሆነ፡፡ እነዚህንም ነገሮች በደንብ አድርገው ተጠቅመውበታልም፡፡ ዝርዝር ጉዳይ አያስፈልገውም፡፡ ላለፉት 22 አመታት ያየናቸው ናቸው፡፡ የዚህን ሴራ ልዩ የሚያደርገው በተቃዋሚውም ጎራ ተሰልፈው ይህንን ተግባራቸውን የሚያከናውኑ ግለሰቦች ፣ፓርቲዎች መኖራቸው ነው፡፡
ሊታወቅ የሚገባው ግን ይህ ትውልድ ሂሳብ እንደማያወራርድ ነው፡፡ እርግጥ ነው በታሪካችን ውስጥ መልካምም ሆነ ስህተት ነገሮች ተሰርተው ይሆናል፡፡ አሁን ያለው ወጣት በዚህ ጊዜ እንዲህ ተደረገ ፣ እንዲህ ሆነ በሚል አሉታዊ ነገር ብቻ ተለጥፎ ወደፊት እንዳይራመድ የሚደረገው የገዢው ፓርቲና የአንዳንድ ተቃዋሚ ተብዬዎች ሴራን ይህ ትውልድ ተቀብሎ ተግባራዊ ያደርጋል ማለት ዘበት ነው፡፡ ወጣቱ ሊያደርግ የሚችለው በታሪካችን ውስጥ ያለፉትን በጎ ነገሮች በመቀበል ፤ በሌላው አንፃር ደግሞ ጥሩ የማይባሉትን እያስተካከልን ወደፊት መሄድ እንጂ ገዢዎቻችን እንደሚፈልጉት ትላንት ላይ ተለጥፈን የጎሪጥ እየተያየን ምጣችንን ማርዘም አይደለም፡፡
አሁን እያየን ያለነው የመብት ረገጣ እራሱ ለዚህ ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ ዛሬ ያለው ነገ አልፎ ታሪክ የሚሆን ነው፡፡ ዛሬ ማንም መብቱን የጠየቀ፣ እንዲሁም ከአምባገነኑ ኢህአዴግ ስርዐት በተቃርኖ የቆመ ሁላ ሃገር ከሃዲ፣ አሸባሪ ተብሎ ዘብጥያ ይወርዳል፡፡ ለዚህም ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ እስክንድር ነጋ፣ ርዐዮት አለሙ፣ ውብሸት ታዬ ፣ አንዷለም አራጌ፣ኦልባና ሌሊሳ፣ናትናኤል መኮንን ወ.ዘ.ተ በፈጠራ ክስ ተፈርዶባቸው በእስር ይገኛሉ፡፡
ሌላው ደግሞ በሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ በሆኑት ዜጎች ላይ ያየነው የፈጠራ ክስ ነው፡፡ የሃይማኖት ጥያቄ ነው የጠየቁት፡፡ በተቃራኒው ለስርዐቱ ከፋፍለህ ግዛ የተመቹ ባለመሆናቸው ከነሱም ጋር ፀብ ውስጥ ተገባ፡፡ በመጀመሪያም አህባሽ ይወገድልን ያለፈቃዳችን ተጭኖብናል ብለው ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀመሩ፡፡ ከዛም የሃይኖት መሪዎቻችንን መምረጥ አለብን፣ መሪዎቻችንንም በመስጂድ እንጂ በቀበሌ አይደለም የምንመርጠው ሲሉ ስርዐቱ በሃይል በቀበሌ እንዲሆን አደረገው፡፡ ይህም ልዩነቱን አስፍቶት አሁን ካለበት ደረጃ አደረሰው፡፡ ትግሉም ድምፃችን ይሰማ በሚል ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ትላንት የመፍትሄ አፈላላጊ የነበሩት ዜጎች ዛሬ በግፍ በእስር ይገኛሉ፡፡ ከዛም የእነዚህ ዜጎች ፍፁም ሰላማዊ የሆነውን የሐይማኖት ጥያቄ ጥላሸት ለመቀባት ‹‹ጀሃዳዊ ሃረካት ›› የሚል የፈጠራ ዶክመንተሪ አሰርተው አሰራጩ፡፡ ይህም በመብት ታጋዮቹ እና በፖለቲካ አመራሮች ላይ ከተሰራው አኬልዳማ ከተሰኘ ድራማ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
በመጁሊሱ ላይ ያየናቸው የስርአቱ ጣልቃ ገብነት በሲኖዶሱ ውስጥም ታይተዋል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ለሁለት ተከፍላ ላለፉት 22 አመታት መቆየቷ ሳያንስ፤ በስርዐቱ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ውጭ ካለው ሲኖዶስ ጋር እተደረገ የነበረው እርቀ ሰላም እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ የእርቁ መንገድም በገዢው ፓርቲ ሴራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ዛሬም ምእመኑና ሲኖዶሱ ልብ ለልብ አይደሉም፡፡ በዋልድባ ያየነውም የስርዐቱ ጣልቃገብነትን ያየነው ነው፡፡ ዛሬም የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው፡፡ የሚሰማቸው ያለ ግን አይመስልም፡፡ ነገ እነዚህ ተማሪዎች አሸባሪዎች ተብለው ወይም ሌላ ስም ተሰጥቷቸው ዘብጥያ እንደማይወርዱ ምንም ዋስትና የለም፡፡ ይህ የሚያሳየን ምንድን ነው? ማንም ጥያቄ የጠየቀ እንዲሁም ከገዢው መንግስት በተቃርኖ የቆመ አሸባሪ ነው፡፡ከሃዲ ነው፡፡ ሌላም ሌላም ስም ሊሰጠው ይችላል፡፡ እና መሆን ያለበት እንዴት ከዚህ አይነት አፈና እንውጣ ነው?
ሌላው ዜጎችን ከቀያቸው ማባረር ሌላው ምሳሌ ነው ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንዳየነው ዜጎች ሃብት ንብረት ካፈሩበት ባዶ እጃቸውን ተባረዋል፡፡ ለዚህ ማስረጃ በቤንች ማጂዋ ጉራ ፈርዳ እና በቤንሻንጉል ያየነው ምሳሌ ነው፡፡ ሌላው ዜጎችን ሽብርተኛ ተብለው ከተፈረጁት ፓርቲዎች ጋር እያያዙ ብዙ ንፁሃን ዜጎች ታስረዋል፣ ተገለዋል፣ ተሰደዋል፡፡ ይህ የዜጎችን ማንነት ተገን ተደርጎ የሚካሄድ አይመስለኝም፡፡ ነውም ብዬ አላምንም፡፡ ይሀ ለኔ የስርአቱ ባህርይ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት ሁሉንም እሺ ብሎ የሚቀበል ካልሆነ በስተቀር ማንም የስርዐቱ ሰለባ ይሆናል፡፡ ዜጎችን በህግ ሽፋን ማሰረ ማሰቃየት ስራዬ ብሎ ለያዘ ስርዐት ማድረግ ያለብን ባንድነት መታገል ነው፡፡
ሌላው ከዚህ በኋላ ወጣቱ ሊታገሰው የማይችለው ነገር ቢኖር በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር የሚያካሂዱትን ብልጣብልጥነት የተሞላባቸውን ተግባራት ነው፡፡ ይህም በተለያየ የስራ መስክ ተሰማርተው አንዳንዶችም ድርጅት መስርተው ያሉ ምን እንደሚሰሩ ያየነው ነው፡፡ ከዚህ ቦኋላ ግን ይህ ብልጣብልጥነት የትም የማያደርስ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ይህን የሚሸከም ትከሻ እንደማይኖረን ነው፡፡ ይህም ከምንሰራቸው ስራዎች አንዱ ነው፡፡ ከፋፍለህ ግዛን ብቻ ብናስወግድ ዋጋ የለውም፡፡ መሰተካከል ያለባቸው ተቋሞችም ጭምር ናቸው፡፡
አሁን ባለንበት ክፍለ ዘመን የገዢው ፓርቲና የየብሄራቸው ልሂቃን ነን የሚሉትን ግለሰቦች አካሄዳቸው እንደማይመጥነን፤ ከፋፍለህ ግዛን እንደማንደግፍ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ብሔር በሉት፣ሐማኖት በሉት፣ ቋንቋ በሉት ይህ ወጣት ትውልድ በነዚህ ነገሮች ታጥሮ የተቀመጠ አለመሆኑን ነው፡፡ ወደፊትም በኢትዮጵያዊነታችን እንደምንገፋበት ሊታወቅ ይገባል፡፡ እንደ ዜጋ ሰው መሆን እና በሰው ልጆች ላይ የሚደርስን ማንኛውንም አይነት የመብት ረገጣ እንቃወማለን፡፡ እከሌ ብሄሩ አማራ ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ ወ.ዘ.ተ የምንል ሳይሆን ያለምንም ልዩነት ሰው መሆኑን አምነን የምንቀበል ነን፡፡ ስለዚህ የምናካሂደው ትግል ሁላችንንም በእኩልነት የሚያስተናግድ ስርአት እንዲፈጠር እንጂ አንዱ አምባገነን ሄዶ ሌላው እንዲመጣ አይደለም፡፡ ግለሰቦች አንዲቀየሩ ብቻ ሳይሆን የምንፈልገው ለዴሞክራሲና ለመልካም አስተዳድር ግንባታ ወሳኝ የሆኑት ተቋማትም አብረው እንዲቀየሩ ነው፡፡ ይሄ ሲሆን ነው ከበፊት ስህተቶቻችን እየተማርን ወደፊት መጓዝ የምንችለው፡፡ አለም ከደረሰበትም ለመድረስ የምንችለው በዚህ ነው፡፡ በትላንት ላይ ተለጥፈን ብቻ የጎሪጥ የምንተያይ ከሆነማ ለከፋፍለህ ግዛ የተመቸን ሆንን ማለት ነው፡፡ ይህም ምጣችንን ከማርዘም በቀር ምንም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ይህ በዚህ ሁኔታ እንዳይቀጥልና የአምባገነኖች ቤተ ሙከራ እንዳንሆን በአንድነት መታገል የግድ ይላል፡፡
No comments:
Post a Comment