እኔ አማልሰጣችሁ ፣ እናንተ እማትወስዱት….
ያለስም፣ ስም – ስጡኝ
ቅጡኝ፣ አስቀጡኝ፤
አግዙኝ፣ ወርውሩኝ፣ … በማጎሪያችሁ
እሰሩት… እጀን፣ … በካቴናችሁ
‘ጠንዙት’ እግሬን፣ …. በእግር ብረታችሁ
ቸንክሩት፣ ገንዙት፣ … ይደንዝዝላችሁ
ሽባ ሆኘ ልቅር፣ ‘’ልሰንከልላችሁ’’:: …
እንካችሁ …. ጀርባዬን
መጫሚያ፣ መዳፌን፤
ግረፉት፣ አቃጥሉት፣ …. በኮረንቲ ገመድ
የሰራ አከላቴ፣ ይክሰል፣ ይሁን ዓመድ:: …
ዝረፉት … ሀብቴን
ቤትና ንብረቴን፣ በምድር ያለኝን፤
ሰብስቡ፣ አከማቹት፣ ለዓለም ይሁናችሁ
ለማይጠረቃው፣ ለከርስ ዓላማችሁ
ለማፍረስ፣ ለመናድ፣ ለጥፋት ግባችሁ:: …
እንካችሁ…… ደረቴን
እንካችሁ…… ግ’ባሬን፤
ለታንክ፣ ለመትረጊስ፣ ለጥይታችሁ
አፍስሱት ደሜን፣……. እስኪከረፋችሁ
አድቅቁት አጥንቴን፣……. እስኪወጋችሁ::…
እንካችሁ……… እንካችሁ
ሥጋ – ሰውነቴን፣ ለጉድጓዳችሁ
ለመቃብራችሁ::…
እንካችሁ…… እንካችሁ
ሁሉንም …… እንካችሁ፤……
….. ግን “የእፍኝት ልጆች”…
…. የሀገር እስስቶች …
…… እናንተ እኩያኖች፤…
ምድር ሰማይ ሆኖ፣ ሰማይ ቢሆን ምድር፣ ቢፋለስ ተፈጥሮ
በጨረቃ ቦታ፣ ብትወጣ ጸሀይ፣ ዘመን ተቀይሮ፤
ቢተባበራችሁ፣ የዓለም ኃይል በአንድነት
እኔ እማልሰጣችሁ፣ እናንተ እማትወስዱት፤……
የሰው ልጅነቴን፣ ኢትዮጵያዊነቴን!
አረንጓዴ – ቢጫ – ቀይ፣ ሰንደቅ ዓላማዬን!
ከዓምላክ ያገኘሁት፣ ፍጹም ነጻነቴን!
—–//—-
ፊልጶስ/ 2005
No comments:
Post a Comment