ከነስረዲን ዑስማን
የሰሞኑ የድር አምባው ማኅበረሰብ መነጋገሪያ በሆነው የጀዋር መሐመድ ንግግር መነሻነት ለተሰጡ አሉታዊ አስተያየቶች ምላሽ እንዲሆን በዑባህ አብዱሰላም የተሰጠውን አፀፋ አስተያየት አነበብሁ፡፡ በዑባህ የአፀፋ አስተያየት ላይ የአባ ሳሙኤል አንድ መጽሐፍ እና “ተዓምረ ማርያም” ተጠቅሰው አንብቤአለሁ፡፡ በጀዋር ንግግር ላይ የተሰጡ አሉታዊ አስተያየቶችን በሙሉ አንብቤአለሁ ለማለት አልችልም፡፡ የውዝግቡን ሂደት ሳየው ግን በንግግሩ መነሻነት የሚካሄዱት እሰጥ አገባዎች በጣም ፈር እየለቀቁ፣ በስሜታዊነት፣ በወገንተኝነት እና ከግራም ከቀኝም በጭፍንነት እየተናጡ ያሉ ይመስለኛል፡፡ … ይህን በመሰለ የተጋጋለ የቃላት ጦርነት ውስጥ መግባት ያስፈራል፤ አለመግባት ደግሞ ቢያንስ አዎንታዊ ሚና ለመጫወት የመሞከር ኃላፊነትን መሸሽ ይሆናል፡፡ … ስለዚህ ለራሴ የሚመረጠው በሰከነ አዕምሮ የሚሰማህን ዘርዘር አድርጎ መጻፍ ነው፡፡ ሰዎች ትኩረታቸውን በምታሰፍረው ሐሳብ ላይ አድርገው ጽሑፍህን በጥሞና ካነበቡት እሰየው ነው፡፡ ያ ካልሆነ ግን ከግራም ከቀኝም የሚተኮሱ የኃይለ-ቃላትና የስድብ ጥይቶችን የሚመክት የብረት ጥሩር ታጥቀህ ቆፍጠን ብለህ መጠበቅ ነው … አልሁትና ይህንን ፃፍሁ፡፡ …
የሰሞኑ የድር አምባው ማኅበረሰብ መነጋገሪያ በሆነው የጀዋር መሐመድ ንግግር መነሻነት ለተሰጡ አሉታዊ አስተያየቶች ምላሽ እንዲሆን በዑባህ አብዱሰላም የተሰጠውን አፀፋ አስተያየት አነበብሁ፡፡ በዑባህ የአፀፋ አስተያየት ላይ የአባ ሳሙኤል አንድ መጽሐፍ እና “ተዓምረ ማርያም” ተጠቅሰው አንብቤአለሁ፡፡ በጀዋር ንግግር ላይ የተሰጡ አሉታዊ አስተያየቶችን በሙሉ አንብቤአለሁ ለማለት አልችልም፡፡ የውዝግቡን ሂደት ሳየው ግን በንግግሩ መነሻነት የሚካሄዱት እሰጥ አገባዎች በጣም ፈር እየለቀቁ፣ በስሜታዊነት፣ በወገንተኝነት እና ከግራም ከቀኝም በጭፍንነት እየተናጡ ያሉ ይመስለኛል፡፡ … ይህን በመሰለ የተጋጋለ የቃላት ጦርነት ውስጥ መግባት ያስፈራል፤ አለመግባት ደግሞ ቢያንስ አዎንታዊ ሚና ለመጫወት የመሞከር ኃላፊነትን መሸሽ ይሆናል፡፡ … ስለዚህ ለራሴ የሚመረጠው በሰከነ አዕምሮ የሚሰማህን ዘርዘር አድርጎ መጻፍ ነው፡፡ ሰዎች ትኩረታቸውን በምታሰፍረው ሐሳብ ላይ አድርገው ጽሑፍህን በጥሞና ካነበቡት እሰየው ነው፡፡ ያ ካልሆነ ግን ከግራም ከቀኝም የሚተኮሱ የኃይለ-ቃላትና የስድብ ጥይቶችን የሚመክት የብረት ጥሩር ታጥቀህ ቆፍጠን ብለህ መጠበቅ ነው … አልሁትና ይህንን ፃፍሁ፡፡ …
የጀዋርን ንግግር በከፊል ነው የሰማሁት፡፡ ከዩ ቲዩብ ላይ በሰማሁት የሰባት ደቂቃ ንግግር ጀዋር “እኔ ስለ እስልምና መናገር የጀመርሁት ከጎንደር ከመጣ ሙስሊም ጋር ከተገናኘሁ በኋላ ነው” ሲል ይጀምራል፤ በዚህ ዓረፍተ ነገር ተንደርድሮ ሲቀጥልም “እኔ ባለሁበት 99 በመቶ ሙስሊም ነው፡፡ ስለዚህ ማንም ደፍሮ ቀና አይልም፡፡ በሜንጫ አንገቱን ነው የምንለው” ይላል፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ እና ተንታኙ ጀዋር መሐመድ እንዲህ ሲል መስማት ያስደነግጣል፤ በጣምም ያሳዝናል፡፡ የሁከት አልባ የፖለቲካ ትግል (Non-violent political activism) አቀንቃኝና ተንታኝ ነኝ እያለ አፉን ሞልቶ ሲናገር ከኖረው ጀዋር አንደበት እንዲህ ያለ ከሁከትም የከፋ አረመኔያዊ ድርጊትን የሚያፀድቅ ንግግር ስሰማ በግሌ ያለምንም ማጋነን በጣም ደንግጫለሁ፡፡ አንድ በህዝብ ተደማጭና ተጽዕኖ ፈጣሪ ወደ መሆን ከፍ እያለ የሚገኝ ሰው እንዲህ ያለ ኃላፊነት የጎደለው ንግግር በህዝብ ፊት ሊናገር ይቅርና ለብቻው ሊያስብም የሚገባው አይመስለኝም፡፡ … በዚህ የጀዋር አነጋገር ላይ ያለኝ አስተያየት ሙሉ ንግግሩን ከመስማትና ካለመስማት ጋር ምንም ተያያዥነት የለውም፡፡ የእኔ ጽሑፍ መነሻ የሆነው ሐሳብ ይኸው የጠቀስሁት የጀዋር ንግግር ክፍል ነው፡፡
እኔ ብዙውን ጊዜ ነገሮችን የማየው የነገሩን ባለቤት (subject) በማለዋወጥ፣ በሰዎች ቦታ ላይ ራሴን በማስቀመጥ ነው፡፡ በዚህም መንፈስ ሙስሊም ወንድም እና እህቶቼ ለጀዋር ንግግር ከመሟገታችሁ በፊት ይህንን ዓረፍተ ነገር ከአንድ የክርስትና እምነት ተከታይ አንደበት ብትሰሙት ምን ሊሰማችሁ እንደሚችል እንድታስቡት እጠይቃችኋለሁ፡፡ አንድ ክርስቲያን በርካታ የክርስትና እምነት ተከታዮች በተሰበሰቡበት አዳራሽ፣ “እኔ ባለሁበት አካባቢ ህዝቡ 99 በመቶ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ አንድም ሙስሊም ደፍሮ ቀና አይልም፡፡ በሜንጫ አንገቱን ነው የምንለው” ሲል ብትሰሙ ምን ይሰማችኋል? ምላሻችሁስ ምን ይሆን ነበር? ……….. ከዚህ ዕይታ ሳየው እኔ በግሌ ጀዋር መሐመድ በተናገረው ነገር ከልቤ አዝኛለሁ፡፡ ንግግሩ በጣም አስደንጋጭም፣ በጣም ስህተትም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህንን መካድ ለማንም አይጠቅምም፡፡
ተዓምረ ማርያምን እዚህ ምን አመጣው? …
ይህንን የጀዋር ንግግር defend ለማድረግ በቀረበው የዑባህ ጽሑፍ ላይ፣ “ተዓምረ ማርያም እንዲህ እና እንዲህ ይላል” የሚል አንብቤአለሁ፡፡ ትክክል ነው፡፡ በጣም አሳዛኝ እና ፀያፍ ንግግሮችን ያካተተ የ“ተዓምረ ማርያም” ቅጂ ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላም ለአሥር ዓመታት ገደማ ገበያ ላይ ነበረ፡፡ የድሮዎቹ ቅጂዎች ዛሬም ገበያ ላይ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በአዳዲስ የ“ተዓምረ ማርያም” ቅጂዎች ላይ እርማት የተደረገው በዑባህ እንደተጠቀሰው በደርግ ዘመን ሳይሆን፣ በ1990ዎቹ የመጀመርያ አጋማሽ ነው፡፡ ይህ የሆነው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሐጅ አብዱራህማን (ረሂመሁሏህ) ሊቀ መንበርነት እና በአቶ አብዱልረዛቅ ዋና ፀሐፊነት፣ የአዲስ አበባው መጅሊስ ደግሞ በሐጅ ኑሩ (ረሂመሁሏህ) ይመራ በነበረበት ዘመን ከቤተ ክህነት ጋር በተደረገ ግልፅ ውይይት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ የምክር ቤቱ አመራሮች በ“ተዓምረ ማርያም” ውስጥ የነበሩ ፀያፍ ትረካዎችን ነቅሰው በማውጣት “እነዚህ ትረካዎች የሁለቱን ሃይማኖቶች ተከታዮች በመልካም የመኗኗር እሴት ከመሸርሸር በቀር ምን ጠቀሜታ አላቸው?” በሚለው ሐሳብ ላይ ከቤተ ክህነት መሪዎች ጋር ውይይት አድርገው ቤተ ክህነት ትረካዎቹ መንፈሳዊ ፋይዳ የሌላቸው ከመሆናቸውም ባሻገር የኋለኛውን ዘመን የተዛባ አስተሳሰብ የሚያንፀባርቁ መሆናቸውን በማመኗ ትረካዎቹ ከመጽሐፉ ውስጥ እንዲወጡ ተደረገ፡፡ በእኔ እምነት ይህ እርምጃ “ከታሪካችን የወረስነውን ጠባሳ” እያከሙ ወደፊት የመጓዝ ትክክለኛ ሂደት አንድ መገለጫ ነው፡፡ ትናንት በሌሎች ወገኖች የተሠራና፣ ስህተት መሆኑ ታምኖበት የታረመን ጉዳይ ለሰሞነኛው የጀዋር አስደንጋጭ አነጋገር መከላከያ አድርጎ ማቅረብ ግን ትክክል አይመስለኝም፡፡ … ታሪክ የሚጠናው ከትናንት ሁነቶች ውስጥ በጎውን ለመውረስና ይበልጥ ለማጎልበት፣ ስህተቱን ደግሞ ለማረምና ከዚያ በመማር ነገን የተሻለ ለማድረግ ነው፡፡ ጀዋር በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተናገረውን ንግግር በራሱ መዳኘት፣ “አነጋገሩ ስህተት አይደለም” የሚል ካለም ይህንኑ በራሱ ማስረዳት እንጂ፣ ወደ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተመልሶ “እናንተም እኮ እንዲህ እና እንዲህ ብላችሁን ነበር” እያሉ መሞገት ተገቢም ትክክልም አይመስለኝም፡፡ የኋላ ዘመን ታሪክ ወደኋላ የሚጎትተን ከሆነ የትም አንደርስም፡፡ የዛሬ ስህተትና ነውርን በሌሎች የትናንት ስህተትና ነውር ተገቢ ለማድረግ የምንሞክር ከሆነ ወደፊት አንራመድም፡፡ ከስህተት ቀለበትም አንወጣም፡፡ ስለዚህ ጀዋር ተሳስቷል ለማለት ድፍረት ልናጣ አይገባም፡፡ “99 በመቶ ክርስቲያን በሚኖርበት አካባቢ ያለ ሙስሊም ቀና ለማለት የደፈረ እንደሁ በሜንጫ አንገቱን ይመታል” የሚል አነጋገር ስንሰማ የምንደነግጥ፣ የምንቆጣ ከሆንን፣ የክርስቲያኖቹም ስሜት እንደዚያው ሊሰማን ይገባል፡፡ …
የአባ ሳሙኤል ስህተትም ለጀዋር “ሜንጫ” ማስተባበያ አይሆንም …
በሚያዝያ ወር 2000 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጳጳስ በሆኑት አባ ሳሙኤል የተጻፈ “በኢትዮጵያ የሃይማኖት መቻቻል አለን?” የተሰኘ መጽሐፍ ገበያ ላይ ዋለ፡፡ በመጽሐፉ ላይ አባ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከ1,400 ዓመታት በፊት ከመካ በስደት ከመጡት የነቢዩ ሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ.) ባልደረቦች ጋር በማዛመድ፣ እኛ ሙስሊሞች የዚህች አገር እንግዳ እንደሆንን ሊነግሩን ሞከሩ፤ ማለትም ነገሩን፡፡ …
አባ ሳሙኤል በዚያ መጽሐፋቸው ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ያላቸው ዕይታ ጤናማ እንዳልሆነ በግልፅ አሳይተዋል፡፡ ጤናማ ያልሆነ ዕይታቸውን በምን ያህል ክርስቲያን ወገኖቻችን አዕምሮ ውስጥ እንዳሰረፁት በእርግጠኝነት ለማወቅ አይቻልም፡፡ ደግነቱ “ገለል በልና ገለል አድርጋቸው / ወደመጡበት ወደ አገራቸው” ለማለት ባለመድፈራቸው ይኸው እንደ እርሳቸው ምኞትና ፍላጎት “በእንግድነት”፣ እንደ እውነቱ ደግሞ ወደ መካ ሳንባረር ማንም ሊሰጥም ሆነ ሊነሳን ከማይችለው ዜግነታችን አለን፡፡ …
ይህ በሆነ በአምስተኛው ዓመት …
የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ይመስለኛል አንዲት ስዊድን ውስጥ የምትኖር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያዊት የሙስሊሞችን የሃይማኖት መብት ጥያቄ በመደገፍ ስቶክሆልም ውስጥ በተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተሳትፋ ነበር፡፡ ይህች እህታችን ከአራት ዓመት በፊት የአባ ሳሙኤልን መጽሐፍ አንብባ ስለ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አሉታዊ ስሜት አድሮባት እንደነበረ ለቢ.ቢ.ኤን ራዲዮ ጋዜጠኛ ነግራዋለች፡፡ ነገር ግን እህታችን ቀስ እያለች ወደ አቅሏ በመመለስ መሬት ላይ ያለውን ሐቅ አሰላሰለች፡፡ ለበርካታ ዓመታት ከሙስሊሞች ጋር ተጎራብታ ያለ አንዳች ችግር መኖሯን አስታወሰች፡፡ የአባ ሳሙኤል መጽሐፍ ታላቅ እህቷ የእስልምና እምነት ተከታይ መሆኗን እንኳ አስረስቷት ነበር፡፡ የአባ ሳሙኤል መጽሐፍ ለጥቂት ዓመታት በአዕምሮዋ ውስጥ ያሰረፀው የሙስሊም ጥላቻ በክፋት የተረጨባት መጥፎ መርዝ መሆኑን የኋላኋላ ተረዳች፡፡ እናም ዓይኗን ገለጠች፡፡ አባ ሳሙኤል ሊያጠለሹ የሞከሩት የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ገፅታ የተሳሳተ መሆኑን ከማመን አልፋ፣ ስለ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖት ነፃነትና መብት መከበር አደባባይ ወጥታ ከሙስሊሞች ጋር ድምጿን አሰማች፡፡ ከዓመታት በፊት አባ ሳሙኤል የረጩባትን የጥላቻ መርዝ አሸንፋ ነገሮችን በሰከነ አዕምሮ ለማየት ስለመቻሏና የሙስሊሞች የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ የእሷም ጥያቄ መሆኑን በስካይፕ አማካይነት ለቢ.ቢ.ኤን ተናገረች፡፡ … ይብላኝ ለአባ ሳሙኤል እንጂ፣ ጤናማ አዕምሮ ያላቸው ሰዎች ለጊዜው ወደተሳሳተ መንገድ ቢገፉ እንኳ ሰዎች ናቸውና ወደ አቅላቸው መመለሳቸው አይቀርም፡፡ … የህዝቦችን በሰላም አብሮ የመኖር እሴትን የሚጎዳ ንግግር መናገር ግን ራስን ትዕዝብት ላይ ይጥላል አባ ሳሙኤልን እንደጣላቸው፡፡ … የህዝቦች በሰላም ተከባብሮ የመኖር እሴትንም ይሸረሽራል፡፡ … አሁን ያች በስዊድን ነዋሪ የሆነች እህታችን የጀዋርን ንግግር ብትሰማ ደስ የሚላት ይመስላችኋልን? …
የ“ትናንት ጠባሳ”ን እያከምን ወደፊት እንራመድ …
የትናንቱን ጠባሳማ ኢህአዴግም “የነፍጠኛው ሥርዓት ትናንት እንዲህና እንዲያ ሲያደርግ ነበር” እያለ በሰፊው እየተረከ ተደላድሎበታል፡፡ ግና ኢትዮጵያችን ዛሬም ከነፍጠኛ ሥርዓት አልተላቀቀችም፡፡ ኢህአዴግ በሚባል ሌላ ነፍጠኛ ሥርዓት (regime) እየተገዛች ነው፡፡ የዛሬውን የነፍጠኛ ሥርዓት ከቀደምቶቹ ለየት የሚያደርገው አስገራሚው የአገዛዝ ጥበቡ ነው፡፡ አቤ ቶክቻው ከትናንት በስቲያ ባስነበበው ጽሑፉ በትክክል እንደገለፀው፣ ኢሕአዴግ ኦሮሞውን በኦሮሞ (ባንዳ)፣ ሶማሊውን በሶማሊ (ባንዳ)፣ አማራውን በአማራ (ባንዳ)፣ ሙስሊሙን በሙስሊም (ባንዳ)፣ ክርስቲያኑን በክርስቲያን (ባንዳ)፣ ትግሬውን በትግሬ (ባንዳ)፣ መምህራንን በባንዳ መምህራን፣ ጋዜጠኞችን በባንዳ ጋዜጠኞች፣ እውነተኛ የብሔር ንቅናቄዎችን በባንዳ (ተለጣፊ) የብሄር ንቅናቄ በማስመታት ነው ላለፉት ሃያሁለት ዓመታት እየገዛ ያለው፡፡ …
ከእነዚህ ሁሉ ጀርባ ነፍጥ አለ፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ጀርባ ለሕዝቦች ሳይሆን ለገዢው ፓርቲ ታማኝ የሆነ የፍትኅ( አልቦ) ሥርዓት አለ፡፡ በፍትኅ አልቦው ሥርዓት ውስጥ በህዝባቸው ላይ ባንዳ የሆኑ የሕግ ባለሙያ ተብዬዎች አሉ፡፡ ፖሊስ የህዝብ ሳይሆን የኢህአዴግ አገልጋይ ነው፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የህዝብ ሳይሆኑ የገዢው ፓርቲ የፕሮፖጋንዳ መሣርያ ናቸው፡፡ ራሳቸውን “የሕገ መንግሥቱ ዘብ” እያሉ የሚያንቆለጳጵሱት የፌደራል ፖሊሶች (Paramilitary police) በትክክል የሕገ መንግሥቱ ሳይሆን የኢሕአዴግ ዘቦች ናቸው፡፡ ከተራ ወታደሮች ስብጥር አኳያ ከብሄር፣ ብሄረሰቦች የተውጣጣ ነው የሚባለው የአገር መከላከያ ሠራዊት እንኳ፣ በመኮንኖችና በከፍተኛ ባለ ማዕረግ አዛዦች ደረጃ የገዢው ፓርቲ፣ ብሎም የህወሓት የክፉ ቀን አለኝታ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ የሕዝቦች መብቶች እና ነፃነቶችን ገዢው ፓርቲ እንዳሻው ሲደፈጥጣቸው ለዚህ ሕዝብ የሚደርስለት አቅም ያለው አንድም ነፃ አካል የለም፡፡ …
ኢትዮጵያውያን በሙሉ በመርዘኛ አምባገነናዊ ሥርዓት መዳፍ ሥር ወድቀዋል፡፡ ይህንን ሥርዓት መርዘኛ የሚያሰኘው ለእርሱ ሰጥ ለጥ ብለው እስካላደሩ ድረስ አይደለም የተለያዩ ብሄር፣ ብሄረሰቦችንና የተለያዩ ሃይማኖቶችን፣ የአንድ ብሄር ህዝቦችንም ሆነ የአንድ ሃይማኖት ተከታዮችን ከእነርሱው መካከል በወጡ የብሄር አልያም የሃይማኖት ወንድሞቻቸው የማስረገጥ፣ አስፈላጊ ሲኾን እርስ በእርስ የመከፋፈልና የማናጨት ስልትን በትጋት የሚጠቀም መሆኑ ነው፡፡ ለክፋቱ ደግሞ ከየብሄር ብሄረሰቡ፣ ብሎም ከየሃይማኖቱ ይህን መርዘኛ ስልቱን የማስፈፀም በጎ ፈቃደኝነት ያላቸው ትጉሃን ባንዳዎች ሞልተውለታል፡፡
የጋራ ርዕይ
ከዚህ በተጓዳኝ ለነፍጠኛው የኢህአዴግ ሥርዓት ዕድሜ መራዘም አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ነጥቦች ዋነኞቹ በተጨቋኞቹ እና ነፃነት በተጠሙት የኢትዮጵያ ህዝቦች ውስጥ፣ ወይም “ለኢትዮጵያ ህዝቦች ወይም ለዚህኛው ብሄር ወይም ብሄረሰብ ከኢህአዴግ አምባገነናዊ የአገዛዝ ቀንበር መላቀቅ እንታገላለን” በሚሉት በጥቅል አነጋገር “የተቃዋሚ ጎራ” ተሰላፊዎች ውስጥ ያሉ ዛሬም ድረስ በውል ሊጠገኑ ወይም ሊታረሙ ያልቻሉ ደካማ ጎኖች ወይም መሠረታዊ ህፀፆች ናቸው፡፡ ኢህአዴግን መጥላትና ኢህአዴግ እንዲወገድ መሻት የብዙዎቹ ተቃዋሚዎች የጋራ ህልምና አጀንዳ ቢሆንም፣ ኢህአዴግ ተወግዶ በኢትዮጵያ ምድር ዕውን እንዲሆን በሚፈለገው ቀጣይ ሥርዓት ላይ “የተቃዋሚው ጎራ” ተሰላፊዎች ነን በሚሉት ልዩ ልዩ አካላት መካከል ዛሬም የጋራ ርዕይ ወይም ስምምነት (Consensus) የለም፡፡ … “የአማራን ገዢ መደብ አስወግጄ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ነፃነት አረጋግጫለሁ” የሚለው ኢህአዴግ “የብሄር ጭቆና እየፈፀመብን ነው” የሚሉ የተለያዩ ብሄር፣ ብሄረሰብ ልሂቃን በየብሄር፣ ብሄረሰባቸው ተደራጅተው ኢህአዴግን ለማስወገድ ሲታገሉ ወይም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ ብሄር ተኮር አደረጃጀት ያላቸው ድርጅቶች ህብረ ብሄራዊ ቅርጽ ካላቸው የፖለቲካ ቡድኖች ጋር የሚጋሩት ፀረ ኢህአዴግነትን ብቻ ይመስላል፡፡ በእኔ እምነት “ፀረ ኢህአዴግነት” ብቻውን “የነገይቱ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት?” ለሚለው ቁልፍ ጥያቄ ሁነኛ ምላሽ የሚሰጥ ርዕይ አይደለም፡፡
በእኔ እምነት መላ ኢትዮጵያውያንን ወደጋራ ርዕይ እና ስምምነት የሚያመጣው ገዢ ሐሳብ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ዛሬም ድረስ ያልተጎናፀፏቸውን መሠረታዊ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች፣ እንዲሁም ፍትኅ እና እኩልነትን ማዕከል ያደረገ የጋራ አስተሳሰብ ነው፡፡ ወደ ሰማንያ አምስት ገደማ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በኢህአዴግ አገዛዝ አላገኙትም የምለው እውነተኛ መሠረታዊ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነትን፣ እኩልነትን፣ ፍትኅን ወዘተ. ነው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች/ነፃነቶች ለኦሮሞውም፣ ለአማራውም፣ ለትግሬውም፣ ለአፋሩም፣ ለጉራጌውም፣ ለጋምቤላውም፣ ለክርስቲያኑም፣ ለሙስሊሙም፣ ለነባር ባህላዊ እምነት ተከታዩም በምልዓት አልተከበሩለትም፡፡ እነዚህ ታላላቅ እሴቶች የሚከበሩባት ኢትዮጵያን የጋራ ርዕይ በማድረግ መላ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ርዕይ ዕውንነት በጋራ መታገል እስካልቻሉ ድረስ ከብሄርና ከሃይማኖት አጥር ባልወጣ የተናጠል የትግል ጉዞ የት ሊደርሱ እንደሚችሉ ለእኔ ግልፅ አይደለም፡፡ …
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሃይማኖታዊ ነፃነትና መብትን የማስከበር ሰላማዊ ትግል በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ በርካታ አዳዲስ እመርታዎችን ለማድረግ ያስቻለ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል የሚል እምነት ይዤ ቆይቻለሁ፡፡ ከእነዚህም አንዱ የተለያዩ እምነት ተከታዮች፣ እንዲሁም የተለያዩ ብሄር፣ ብሄረሰብ አባላት የሆኑ ኢትዮጵያውያን የብሄር እና የእምነት አጥር ሳይገድባቸው የሃይማኖት ነፃነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋራ መብትና የነፃነት ጥያቄዎቻቸውን በጋራ ማስተጋባት መጀመራቸው ነው፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት በአገር ውስጥና ይበልጡንም በባህር ማዶ ደምቆና ተጋግሎ በታየው በዚህ የህዝቦች የአንድነት መንፈስ ላይ የጀዋር ስሜታዊ ዲስኩር ጥላ አጥልቶበታል፡፡ የእርሱ ሳያንስ አቶ ነጂብ መሐመድም የጀዋርን ንግግር አጽድቆ ግልብ ንግግር ማድረጉ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖት ነፃነትና መብትን የማስከበር ሰላማዊ ትግል ላይ ስቅታ ፈጥሯል፡፡ ስህተትን ላለመቀበል ገታራ (Defensive) መሆን ምንም አይጠቅምም፡፡ “አልሳሳትም፤ ልሳሳትም አልችልም” ብሎ ማሰብ ጤናማ አይደለም፡፡ ይባስ ብሎ ለተሳሳተ ሰው ጥብቅና በመቆም ከቅንነት በራቀ መንፈስ ውዝግቡን ማክረርና መለጠጥ ትክክልም፣ ተገቢም ነው ብዬ አላምንም፡፡ … ወሏሁአዕለም፡፡ አላህ (ሱ.ወ.) ቅኑን መንገድ ይምራን፡፡
No comments:
Post a Comment