Thursday, July 18, 2013

ወዴት እያመራን ነው?

ከአንድ ወዳጄ ጋር ካፍቴሪያ ተቀምጠን ሻይ ቡና፣ወተት ማኪያቶ፣ ካፑቹኖና እስኘሪስ እያልን ነው፡፡ ከበላያችን ከተሠቀለው ስፒከር ቁልቁል ወደኛ ዋና ዋና ዜናዎች በሻወር መልክ ይጎርፋሉ…..
በሕገ ወጥ መንገድ ሃያ አምስት ሚሊየን ብር ከባንክ የተደረገው ግለሰብ እየተፈለገ ነው፡፡ ያለ በቂ መስፈርት በጥቅም ተሳስሮ ብድሩን የፈቀደው የባንክ ኃላፊ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
ይቀጥላል ዜናው…….
ከብሔራዊ ባንክ በማስያዥ አርባ አምስት ሚሊየን ብር የተበደረውና ማስያዣዎቹን ሸጦ ከሀገር የተሠወረው ግለሰብ በፌዴራል ፖሊስና በኢንተርፖል እንዲሁም በየመን መንግስት ትብብር ሰንዐ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡


እነዚህን የከባድ ሚዛን የዝርፊያ ጋጋታዎች ከባለፈው የጉምሩክ እና የባለሀብቶች ጣምራ የህዝብ ሀብት ቅርምት ጋር ደምሬ በማሰብ “ወዴት እያመራን ነው?” ስል ከፊት ለፊት የተቀመጠውን ወዳጄን ጠየቅሁት፡፡
ገብስማ ፂሙን በእጆቹ እያተራመሠ “የእኛ እንደዚህ በፍጥነት ማቆልቆል ይደንቀኛል በንጉሱ ዘመን ብትመለከት ማሰብ ሲጀመር “እኔ” ተብሎ ሣይሆን “ሀገሬ” ተብሎ ነው፡፡ ለዚያ ነው ያ ሁሉ ወጣት አሜሪካና አውሮፖ ተምሮ ወደ ሀገሩ በመመለስ በስንት ደጅ ጥናት በሀገር ውስጥ መስሪያ ቤቶች የሚቀጠረው፡፡
በደርግም ስትመለከት ከአመራሩ እስከ ወታደሩ ባመኑበት ያደረጉት ሁሉ ለእናት ሀገር በማሠብ እንጂ ለግል ጥቅምና ምቾት አልነበረም ዛሬ ……”
ወያኔ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላማ ሀገር፣ ባንዲራ ትውልድ በጠቅላላው ኢትዮጵያዊነት እንዲከስም በሙሉ አቅሙ እየለፋ ነው፡፡ እየተሣካለትም ነው፡፡ እናማ የኢትዮጵያዊነት ኅልዮትም በጥቂቶች ልብ ውስጥ ጭል-ጭል የሚል የተምኔት ሃሳብ እየሆነ ነው፡፡
ዛሬ ትውልድ ተንሸዋሯል፡፡ ዜጎች እይታቸው ተጥበርብሮ ከራሣቸው /ከጎሣቸው አልያም ከጥቅማቸው/ አሻግረው ማየት አቅቷቸዋል፡፡ ተስፋ እየቆረጥኩ ነው እንዴ?

No comments:

Post a Comment