Saturday, July 13, 2013

“አገራችንን እና ህዝቧን ከአሸባሪዎች፣ ከጽንፈኞችና ከጅሎች በመስዋዕትነትም ቢሆን እናድናታለን፡፡”

ይህ መፈክር አይደለም:: አደራችሁን የእኔ እንጉርጉሮም አይደለም፤ የአገሩን ፕሬዝዳንት ከስልጣን ሊያስወግዳቸው ሰዓታት ሲቀሩ የግብጽ የጦር ሃይል ከሰጠው መግለጫ የቀነጨብኩት ዋነኛ መልእክት እንጂ:: መቼም ጽንፈኛና አሸባሪ የተባሉትን በጽሁፌ ለማስተዋወቅ ወይም ለመተንተን እንዳልተነሳው ትገምታላችሁ:: ስለነሱ እኛን ምን አገባን:: የኔ ትኩረት በእንግሊዘኛው “ፉልስ” የተባሉት ጅሎቹ ላይ ነው:: ጅል ከአሸባሪ እኩል ሲፈረጅ ትኩረት አይስብም? ጅሉ ማነው?
ለአንባቢዎቼ ስለ ጅሉ ማንነት መደምደሚያዬን ከመሰንዘሬ በፊት የሰሞኑን የግብጽ ክራሞት በጣም በአጭሩ እጠቃቅሳለሁ፤ ጅሉ ፈጥጦ እንዲወጣ፡፡ እንሆ ተከተሉኝ፦
የቀድሞው ጉልበተኛ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ በህዝብ ጡጫ መመታትን ተከትሎ በምርጫ ወደ መሪነት መንበር የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲው መሃመድ ሙርሲ መጡ::
ሙርሲ ለዚ ከታደሉም ድፍን አንድ ዓመታቸው:: በዚህ ያንድ ዓመት የስልጣን ዘመናቸው ኢኮኖሚው ቁልቁል ወረደ፣የኑሮ ውድነት የሚያማርር ሆነ፣ ህገ መንግስት ከማርቀቅ ጀምሮ የነበረው ሂደትና አደረጃጀቶች ለአንድ ወገን ያደሉ ሆኑ፣ የእስልምና ሃይማኖትም የአገሪቱ ህጎች የበላይ የሆነው ሕገ መንግስት ብቸኛ መሰረት ሆነ ወዘተ በሚል ህዝብ ብሶቱንና ስጋቱን ያሰማ ጀመር:: ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም መረር ብለው መሞገት ጀመሩ፡፡ እባክዎን ሙርሲ ብዙሃንነትን አይዘንጉ፣ከፓርቲዎ በላይ ለአገርዎ ያስቡ፣ እኛም የግብጽ ልጆች ነን እንወያይ የሚሉ በዙ:: ይሁን እንጂ ሙርሲ ሁሉንም ሳይሰሙ ጠቅላይ ሚኒስትርና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሾሙና የሽሽግግር ወቅት እስኪያልፍ ብለውም ለራሳቸው ፍጹማዊ ስልጣን አለበሱ:: የሕግ አውጪውም ሆነ አስፈጻሚው ልጓምን ተቆጣጥረውም አዲሱ ፈላጭ ቆራጭ መሆን የሚያስችላቸውን መንገድ መጥረግ ተያያዙት:: ወደስልጣን ያመጣቸው የህዝብ ማዕበልና አብዮትን የረሱም መሰሉ::
ነገሩ ከገደቡ ሲያልፍ ተቃዋሚዎች በህብረት ሆነው ከፕሬዝዳንቱ አንደኛ ዓመት የስልጣን ዘመን ጋር አያይዘው ጁን 30፣2013 በመላው ሃገሪቱ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያደርጉ ከወራት ቀድመው አስታወቁ:: ከሰልፉ በፊት በነበሩ ጊዜያትም ለአገሪቱ ችግሮች የጋራ መፍትሄ እናፈላልግ፣ ብሔራዊ መግባባትን እንፍጠር፣ ወዘተ የሚሉ ጥያቄና ልመና ለሙርሲ በተደጋጋሚ ቀረበላቸው:: ሙርሲ ግን ያለው ዲሞክራሲ እኔን ወደስልጣን አምጥቷል፤ ትላላጣላችሁ እንጂ ምንም አታመጡም አሉ:: ፓርቲያቸውም 80 ዓመታት ጠብቄ ያገኘሁት ስልጣን ሊነጥቁኝ ነው ብሎ ተቃዋሚዎችን ፈረጀ እንጂ ህዝብን አላዳምጥ አለ::
ወራቱ ወደ ሣምንታት፣ ሣምንታት ወደ ቀናት አጥረው የተቃውሞ ሰልፉ አይቀሬነት ሲታወቅና ሙርሲን አንፈልግም ባይ ከ20 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ፊርማውን ሲሰጥ ፕሬዝዳንት ሙርሲ ግለቱ ተሰማቸው:: ይሁን እንጂ ሁነኛ መላ አልፈጠሩም፤ ይልቁንም ተቃዋሚዎችን የቀድሞ ስርዓት ርዝራዦች ብለው ፈረጁና የህዝቡን ጥያቄ የፓርቲዎቹ ብቻ እንደሆነ ገልጸው የኔም ደጋፊዎች ሰልፍ ይወጡልኛል አሉ::
የሁኔታው መጦዝ ያስተዋለውና ለወትሮም ከሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ጋር ታሪካዊ ጠላትነት ያለው የአገሪቱ ጦር ኃይል ከወር በፊት አስቀድሞ መፍትሄ እንዲፈለግ ሲያስጠነቅቅና አቋሙን ሲያስታውቅ ቆየ:: በተቃዋሚዎችና በደጋፊዎች መሃል የሚፈጠር ግጭት አገሪቷን አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነም ጣልቃ እገባለው አለ:: ይህም ለተቃዋሚዎቹ “አይዞአችሁ ሞቅ አድርጉት እንጂ” የሚል መልእክት የሰጠ ይመስል ሰልፋችንና ጩኧታችን የሚጠናቀቀው በሙርሲ ከስልጣን መወገድ ብቻ ነው ወደሚል መደምደሚያ ደረሱ::
ነገሮች በዚህ መልክ ጦዘው ሚሊዮኖች ከቤታቸው ውጪ በመላው አገሪቱ ከተሞች ባሉ አደባባዮች ላይ ተሰባሰቡ:: የተቃውሞ ሰልፉም በአንድ አሜሪካዊ ወጣት ሞት ተጀምሮ በደጋፊና በተቃዋሚዎች ግጭት መነሻነት የበርካታ ግብጻውያንን ሕይወት ይወስድ ጀመር:: በሁለት ቀናት ውስጥ የፈርኦኖች አገር ግብጽ እጅግ አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ገባች::
በዚህን ጊዜም ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ የሆነው የጦር ኃይል ለተቃዋሚዎችም ለፕሬዝዳንቱም ለልዩነታቸው መፍትሄ አስቀምጠው አገሪቷን እንዲታደጉዋት የ48 ሰዓታት የጊዜ ገደብ ሰጠ:: ግን ማን ተቀራርቦ ይነጋገር? መፍትሄው ቀርቶ ጡዘቱ ከረረ:: በጊዜ ገደቡ የመጨረሻ ሰዓታት ላይም ሙርሲ ሆዬ ጦሩ ምን አገባውና ጊዜ ገደብ ይሰጣል፤ ተመራጭ ፕሬዝዳንቱ እኔ ነኝና በራሴ ጊዜ የራሴን መፍትሄ እሰጣለው አሉ:: ውስጥ ውስጡንም እንዴት ብናቅ ሳይሉ አልቀሩም:: ሆኖም መፍትሄውን ሊያመጡ ሳይችሉ የሁለቱ ጎራ ፍጥጫና ግጭት ለግብጽ አዲስ መራር ታሪክ ሊያጽፍ ከጫፍ ላይ ደረሰ:: የጊዜ ገደቡ መጠናቀቅን ተከትሎም ጦሩ 1፣2፣3 ብሎ መፍትሄው ይህውና ብሎ ለፕሬዝዳንቱ የመጨረሻ ዕድል ሰጠ::
ሙርሲ የፖለቲካ መፍትሄ ሊሰጡ የሚችሉበት አቅም አልነበራቸውምና በ80 ዓመታት ያገኘሁትን ስልጣን ምን ሲባል ይነካብኛል በሚለው ፓርቲያቸውና በጦሩ መሃል ተወጠሩ:: ቀናቸው እየጨለመች መሆኗን ያልተረዱት ሙርሲ ታሪካዊ ስህተት ሰሩ:: በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ስልጣኔን ማነው የሚነጥቀኝ ፤ በምርጫ ያገኘሁት ስለሆነ እስከደም ጠብታ ድረስ ከፍዬ ስልጣኔን አስጠብቃለው አሉ:: ተቃዋሚዎችንም ያለፈ ስርዓት ናፋቂዎች አሏቸው:: የጦር ኃይሉንም በቃላት ጎሸም አደረጉና ደጋፊዎቻቸውን አይዟችሁ በተጠንቀቅ ሁኑ አሉ፤ ከሞላ ጎደል የክተት ጥሪ በሚመስል መልኩ:: ከሃያ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሕዝብ እርሶ ስልጣን አስረክበው ዞር ካላሉ ቤቴ አልገባም እያለና በተለይ በካይሮ የታደመው ሰልፈኛ ሃይሉን ሊጠቀም ወደ ቤተ መንግስት ሊተምም አኮብኩቦ እያለ ሙርሲ ስልጣናቸው አሳዘናቸው:: ይሄኔ ታዲያ በበኩሌ መሃመድ ሙርሲ በቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ ወቅት አልተወለዱም ይሆን ብዬ ራሴ ላይ እንዳፌዝ ገፋፉኝ፤ ቢያንስ የተቆጣ ህዝብ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ከወቅቱ የሩማኒያ ፕሬዝዳንትና ቤተሰባቸው ፍጻሜ መማር ነበረባቸውና::
ወደ ርዕሰ ጉዳያችን ልመልሳችሁና የፕሬዝዳንቱ የመጨረሻ ንግግር ነርቩን ያሞቀው የጦር ኃይልም ከላይ በርዕሴ የሰፈረውን ሃሳብ የሚያጎላ ቆፍጠን ያለ መግለጫ አወጣ፤ ፊቴ የሚቆመውንም አያለው ዓይነት ዛቻ ጨምሮበት ከጅሎችም ነጻ እንወጣለን አለ:: በዚያው የሙርሲ የስልጣን ዘመን ተደመደ::
ከላይ ባለፉት ሂደቶች እንደታዘብኩት ከአሸባሪና ከጽንፈኛ ጋር ተፈርጆ እኩል የጦሩ ኢላማ ውስጥ የገባው ጅል ተለይቶልኛል:: የመረጠው ህዝብን ጩኧትና ለቅሶ ሰምቶ ያልሰማ፣ ወደ ቤተ መንግስቱ የሚመጣውን መዓት እያየ ቆሞ የሚጠብቅና የተቀመጠበት ወንበር ከስሩ እየነደደ ብድግ ብሎ ራሱን የማያድንና እሳቱን የማያጠፋ ሙርሲ ጅል ያልተባለ ማን ሊባል:: በመጨረሻዎቹ ሰዓታትስ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ” ዞር በልልን” እያለው እስከደም ጠብታ ለመፋለም የሚጋበዝ መሪ ምን ስም አለው?
ግብጽ በፖለቲካ ቁማር ጨዋታ የተካነ፣ ከወከለው ፓርቲ አልፎ አገሩንና ህዝቡን ለማየት የታደለና የመሪነት ስብዕና ያለው መሪ አጥታ ጅሉ ሙርሲ ላይ አንድ ዓመት ከርማ እነሆ ፍቺ ፈጸመች:: ሙርሲም የአገራቸው ደደቢት ወይም አሲምባ ወይም ደግሞ በረሃ አልመሸጉም፤ ከጆሮ ግንዳቸው ስር ሆኖ ወላፈን ትንፋሹን ይልክባቸው የነበረው ጦር ባሻው ቦታ ላይ ቆልፎባቸው ተቀምጠዋል:: አይዞህ ባይ የሽብር አበጋዞቻቸውም ካሉበት ተለቅመው ዘብጥያ ወርደዋል:: ያለፈውን የዘነጉ፣ የአሁኑን ያላዩና መጪውን መገመት ያልቻሉ የራሳቸው ዓለም ጅሎች ሆነው ቀሩ:: አገራቸውንም ቢያንስ በሶስት ዓይለኛ ተቃራኒዎች የተከፋፈለችና ይህ ጽሁፍ እስከተዘጋጀበት ቀን ድረስ ዜጎቿ እርስ በርስ የሚገዳደሉባት አገር አደረጓት ፤ይህም መቼና እንዴት እንደሚቆም እንኳን እኔ የሙርሲ አባራሪ ጦር ሀይልና ህዝቡም አያውቅ፡፡ አቦ እኛንም ከጅሎች ይጠብቀን! ቢያንስ አሜን በሉ እንጂ ምርቃትም አይደል!
እሸቱ ነኝ ከመካከለኛው ምስራቅ

No comments:

Post a Comment