Tuesday, July 2, 2013

ለፓርላማው፤ የይሁኔ በላይን “እልል በይ አገሬ--” መርጬለታለሁ!

ከ ኤሊያስ
እናንተዬ --- ሰሞኑን በኢቴቪ የቀረበውን በአሰላ ከተማ ላይ የሚያጠነጥን ጉደኛ “ፊልም” አይታችሁልኛል - ርዕሱ “የመልካም አስተዳደር ችግሮች” የሚል ነው፡፡ እኔማ እንደ አሪፍ ልብ አንጠልጣይ ፊልም ነው የኮመኮምኩት - አንዴ ሳይሆን ሁለቴ፡፡ ኢቴቪ አይደግመውም እንጂ አሁንም ደግሜ ባየው አልጠግበውም፡፡ (ኢቴቪ በህዝብ ጥያቄ መድገም ተወ እንዴ?) እውነቴን ነው --- ከአንዳንድ የአገራችን ቀሽም ፊልሞች አስር እጅ ያስንቃል እኮ! በእርግጥ ይኼኛውም የአሰራር ቴክኒኩ እንጂ ጭብጡ ቀሽም የመንግስት ሹማምንት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በጉጉት የሚታይ ምርጥ የመርማሪ ጋዜጠኝነት ሥራ ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ የኢቴቪ መርማሪ ጋዜጠኞችን ላደንቃቸው እፈልጋለሁ (አንዳንዴ መርማሪ ፖሊስ የሆኑ ቢመስላቸውም!) እውነቴን እኮ ነው --- የአሰላ ከተማ አስተዳደርና የከንቲባ ቢሮውን ገበና አፍረጠረጡት እኮ፡፡ እኔ የምለው--- ኢንተርኔት ከመጣ ወዲህ የሰው ገመና የሚባል ነገር ቀረ አይደለ? የ“ቢግ ብራዘር አፍሪካዋ” ቤቲ ገመናዋ የወጣው እኮ በኢንተርኔት ነው (እሷ የአገር ገፅ ግንባታ ብትለውም!) ኢንተርኔት የአምባገነን መሪዎችንም ገመና አልማረም (እኔን ያላመነ እነ ሆስኒ ሙባረክን ይጠይቅ!) እንግዲህ በኢቴቪ ዘገባ መሰረት፣ የአሰላ ከተማ ከንቲባ ቢሮና ማዘጋጃ ቤት ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉባቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡
ወዳጆቼ --- የፈፀሙት ጥፋት ቀላል እንዳይመስላችሁ --የመጪውን አመራር ጥፋት ሳይቀር የፈፀሙ ነው የሚመስሏችሁ፡፡ እኔማ ዘገባውን እየተከታተልኩ ሳለሁ ከአሁን አሁን እንደ እግር ኳስ ፌዴሬሽን “ይቅርታ” ሊጠይቁ ነው ብዬ በጉጉት ስጠባበቅ ነበር፡፡
ይቅርታ መጠየቃቸው እንዳማረኝ ቢቀርም ለአሪፍ ድራማ የሚሆን አሪፍ መነሻ ሃሳብ በነፃ ስላገኘሁ አልቆጨኝም፡፡ ይኸውላችሁ --- ሥራ አጥ ወጣቶች ተደራጅተው ሊሰጧቸው ይገቡ ከነበሩ ሱቆች መካከል የሚበዙት ታሽገዋል፡፡ (ለማን ይሆን የታሸጉት?) ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ባለሃብቶች ደግሞ አራትና አምስት ሱቆች ይዘው እንደሚያከራዩ ኢቴቪ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በምሬት ተናግረዋል (ጦቢያችን ምሬት ብቻ ሆነች እኮ!) ኑሮና የመንግስት ሹማምንቶች መከራዋን ያበሏት የአሰላ ነዋሪ፣ ዓይኖቿ በእንባ እርሰውና በርበሬ መስለው “ባዕድ አገር ብንሰደድ ምን ይጠቀማሉ?” ስትል በምሬት ጠይቃለች - በአገራችን እንዳንሰራ አድልዎ ፈፅመውብናል ያለቻቸውን አመራሮች፡፡ የከተማዋ ሌላ ችግር ደግሞ ምን መሰላችሁ? ባለሃብቶች ለኢንቨስትመንት ብለው የተረከቡትን መሬት እስከ አስር ዓመት ድረስ አጥረው ቢያስቀምጡም ቀጪም ተቆጪም አጥተዋል ተብሏል (ምናልባት በ“እጅ” እየሄዱም ሊሆን ይችላል!) በአዲስ አበባ የሚገኝ አንድ የሃይማኖት ተቋም የፃፈው አስገራሚ ደብዳቤ ምን ይላል መሰላችሁ? “የማዘጋጃ ቤትና የወረዳ ቢሮክራሲውን በቀላሉ ማለፍና ጉዳያችንን ማስጨረስ እንድንችል በእግር ብቻ ሳይሆን በእጅም መሄድ ስለሚያስፈልግ ለዚሁ ተግባር የሚውል 50ሺ ብር ያለ ደረሰኝ ከባንክ እንዲወጣ ---” ሲል ማዘዙን ሰምተናል፡፡
(ሃይማኖትና ሙስና እጅና ጓንት እንዳይሆኑ ሰጋሁ) እቺ አገር እኮ ግርም ትላለች፡፡ ከአምስት ደርዘን በላይ የሙስና ተጠርጣሪዎች ተይዘው በከፍተኛ ምርመራ ላይ ባሉበትና ጠ/ሚኒስትሩ ጉዳዩን በግሌም ጭምር እከታተለዋለሁ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት፣አንድ አቃቤ ህግና ፖሊስ “የክስ መዝገብ እናዘጋለን” በሚል አስር ሺ ብር ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ሰሞኑን በኢቴቪ ዜና ሰምተናል (ከዚህ በላይ “ፋታሊስት” መሆን አለ እንዴ?) የአሰላን ነገር አልጨረስኩም እኮ! የኢቴቪው ጋዜጠኛ እንዳልኳችሁ የከተማዋን አስተዳደርና የከንቲባውን ቢሮ ቀውጦት ነው የሰነበተው - ዘገባው መቼ እንደተሰራ ባላውቅም፡፡ መቼም ለአመራሮቹ --- ጋዜጠኛ ሳይሆን “የባለቤቱ ልጅ” ሳይመስላቸው አልቀረም ብዬ ጠርጥሬአለሁ፡፡ እኔ የኢቴቪን ጋዜጠኛ ብሆን ግን ምን እንደማደርግ ታውቃላችሁ? የአስተዳደሩ አመራሮችና ከንቲባው ጭምር እንደ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር ህዝቡን ይቅርታ እንዲጠይቁ አደርጋቸው ነበር - ሥልጣን ማስለቀቁ ቢቀር እንኳን (የግምገማ ጊዜ ለመቆጠብ እኮ ነው) ለምን መሰላችሁ? በጋዜጠኛው ከቀረቡላቸው ጥፋቶች ውስጥ አንዱንም በስህተት እንኳን አላስተባበሉም እኮ! ሁሉንም አምነዋል፡፡
በዚያ ላይ ተበዳዮችም ግጥም አድርገው መስክረውባቸዋል። ስለዚህ በነካ እጄ ይቅርታ ጠይቁ ብላቸው ህግን መጣስ ይሆናል እንዴ? (የፌዴሬሽኑ አመራርም እኮ ይቅርታ የጠየቀው በስፖርት ጋዜጠኞች ፊት ነው!) ከሁሉም ደግሞ አዝናኝና አስገራሚ ምላሽ የሰጡት ከንቲባው ናቸው! በእርግጥ መጀመሪያ ላይ ኮራ፣ ጀነን ለማለት ዳድቷቸው ነበር - ሃላፊነቱን በቅጡ እንደተወጣ ሃላፊ፡፡ እናም --- ለአንዳንድ ጥያቄዎች-- “ማለት?” “ሲባል?” ፣ “አልገባኝም!” የሚሉ በትዕቢት የታጀቡ የሚመስሉ ምላሾችን ሲሰጡ ታይተዋል፡፡ ደግነቱ ብዙም አልዘለቁበትም። ጋዜጠኛው መረጃዎችን እየዘከዘከ ሲያፋጥጣቸው የዋዛ እንዳልሆነ ገባቸው፡፡ (የአራዳ ልጅ ናቸዋ!) እናም ከመቅፅበት የአጨዋወት ስልታቸውን ቀየሩ፡፡ ከመጀነንና ከመኩራራት ወደ መለሳለስና ማግባባት ገቡ፡፡ በነገራችሁ ላይ አብዛኞቹ የመንግስት ሹማምንት ጋዜጠኛ ኢንተርቪው በሚያደርጋቸው ወቅት የአደጋ ቀጠና ውስጥ የገቡ ከመሰላቸው፣ ሸውደው የሚያልፉባት የተለመደች የአነጋገር ስታይል አለቻቸው - ከሸማቾች የህብረት ሥራ ማህበር በራሽን የተከፋፈለች የምትመስል፡፡
ከመደጋገሟ የተነሳ የማያውቃት ያለ አይመስለኝም። ለምሳሌ ጋዜጠኛው “ለምንድነው ታዲያ ችግሩ እስካሁን ያልተፈታው?” ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ከንቲባው ሲመልሱ “እየሄድንበት ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው” ብለው ቁጭ ይላሉ (ግራ ለማጋባት እኮ ነው!) ቆይ ግን-- “እየሄድንበት ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው” ሲባል ምን ማለት ነው? ችግሩን እየፈታን ነው ማለታቸው ነው? ወይስ ገና ሊፈቱ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ? ወይስ ምንም ማለታቸው አይደለም? የሚገርመው ደግሞ ጋዜጠኛውም ማብራርያ አለመጠየቁ ነው፡፡ ለሌላ ተመሳሳይ ጥያቄ ደግሞ “እኔ እንደተኬደበት ነው የማውቀው” ብለዋል - ከንቲባው (የማወሳሰብ ጥበብ ይሏል ይሄ ነው) ሌላው በጣም ያስገረመኝ ---- ከንቲባው ብዙዎቹን የከተማዋን ችግሮች ከጋዜጠኛው የሰሙ መምሰላቸው ነው፡፡ (የአራዳ ልጅ ናቸው ብያችሁ የለ!) እናም ጋዜጠኛው ስለአንድ ጉዳይ ሲጠይቃቸው “እንዲህ ያለ ነገር ተፈፅሞ ከሆነ በጣም አሳፋሪና ህገወጥ ተግባር ነው! አጣርተን --” የሚል ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ እንዲህ የሚሉት ደግሞ አንዴ እኮ አይደለም - በተደጋጋሚ ነው፡፡ “ግን እኮ 10 ዓመቱ ነው--- አልዘገየም?” ሲል ጋዜጠኛው መልሶ ይጠይቃቸዋል፡፡ ከንቲባውም ልስልስ ባለ አንደበት “አዎ አዎ እሱ ልክ ነህ ---- በጣም ዘግይቷል!” ይሉላችኋል፡፡ (ነገሩን ለማረጋጋት እኮ ነው!) ካፌና ሱፐርማርኬት እንገነባለን በሚል መሬት የወሰዱ ባለሀብቶች 10 ዓመት ሙሉ ምንም ሳይሰሩ አጥረው መቀመጣቸውን ሲያነሳባቸው ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “እንዲህ የሚያደርጉትንማ እያየን እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለብን!” (እኮ መቼ?) ይቅርታ አድርጉልኝና ---አንዳንድ የመንግስት ሹማምንት ተደብቀው ወደ አዳዲሶቹ አገራት (ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ) ጐራ እያሉ የትርፍ ሰዓት ሥራ ሰርተው የሚመለሱ እየመሰለኝ ነው (ዶላር ሊያምራቸው ይችላላ!) እኔ የምላችሁ ---- በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የክልሉ መንግስት ባለስልጣናት ስድስት ወር ቤተመንግስት ሲያስተዳድሩ ቆይተው፣ ስድስት ወር ደግሞ መሳሪያ ታጥቀው ከኦብነግ ጋር የኢትዮጵያን መንግስት ሲወጉ እንደከረሙ ሰምታችኋል?(ጦቢያ እኮ ያልተሸከመችው ጉድ የለም!) ምን ይሄ ብቻ---ብሔራዊ መዝሙራቸውም ታላቋን ሶማሊያ የሚያወድስና ጦቢያን የሚራገም እንደነበር የክልሉ ፕሬዚዳንት መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ (በአንድ ልብ ሁለት ዜግነት ማለት እኮ ነው!) በነገራችሁ ላይ በቅርቡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልንና ሌሎች ምስራቃዊ የአገሪቱን ክፍሎች ጐብኝተው የመጡ አንዳንድ አርቲስቶች “የክልሉ ፕሬዚዳንት ሃይለኛ ኮሜዲያን ናቸው!” በማለት ሲያደንቋቸው ሰምቻለሁ፡፡ እሱስ ባልከፋ ነበር። ስለአመራራቸው ምንም አለማለታቸው ግን ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡
አርቲስቶች ዋዛ ፈዛዛ ብቻ ነው እንዴ የሚያውቁት ያስብላል እኮ፡፡ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም በጉብኝቱ ወቅት “አርቲስቶች” እና “አትሊስቶች” የሚል ሁለት ጐራ የተፈጠረው፡፡ (የግል ግምቴ ነው!) ሌላው በትልቁ የታሙበት ጉዳይ ምን መሰላችሁ? ከባለስልጣን ጋር የመሞዳሞድ ምኞትና ጉጉት ታይቶባቸዋል ይላሉ - የሙያ ባልደረቦቻቸው፡፡ በየክልሉ መሬት ይሰጠን የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውም ለሃሜት ዳርጓቸዋል (እንኳን ሊሰጣቸው ቃል ባይገባላቸውም) እኔ ግን የመሬቱ ጥያቄ ለሃሜት የሚያበቃ አይደለም ባይ ነኝ (አንዳንዴ እንደ ዳያስፖራ ቢያደርጋቸውስ?) አሁን ደግሞ “የብርሃናችንን ጌታ” በደንብ እንቦጭቀው - የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ኮርፖሬሽንን ማለቴ ነው፡፡ ባለፈው ረቡዕ ቀላል ተጫወተብን መሰላችሁ? ተማረን ከአገር እንድንሰደድ ከሆነ እርሙን ቢያወጣ ይሻለዋል --- ህዳሴ ግድብ ሳያልቅ ከጦቢያ ንቅንቅ አንልም፡፡ እንዴ --- በአንድ ተሲያት በኋላ ብቻ እኮ ስምንት ጊዜ መብራት ጠፍቷል (በታሪኩ አዲስ ሪከርድ መሆን አለበት) በነገራችሁ ላይ በተመሳሳይ ሰዓት ኢትዮ ቴሌኮምም ኔትዎርክ አልነበረውም - እናም እርስ በርስ እየተደዋወልን ንዴታችንን መወጣት እንኳ አልቻልንም፡፡
አሁን አሁን ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሳስብ ስጋት የሚፈጥርብኝ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? የግብፅ ጉዳይ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል! ግብፅማ አመነች እኮ - እጅ ሰጠች፡፡ አሁን ችግሩ ያለው እዚሁ ነው - አፍንጫችን ሥር! ይኸውላችሁ --- የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ አገልግሎት ሲጀምር ማነው የሚያስተዳድረው የሚለው በጣም ነው ያሳሰበኝ፡፡ መንግስት ኮርፖሬሽኑ ያስተዳድረዋል ብሎ ካሰበ እድሜ ልኩን “ይቅርታ” ሲጠይቅ መኖር አምሮታል ማለት ነው፡፡ ሃይል እንሸጥላቸዋለን የምንላቸው አገሮች እኮ እንደኛ ዝም የሚሉ አይደሉም (እኛ እኮ ችሎ ነዋሪ ስለሆንን ነው!) እኔ የምላችሁ --- የዝነኛውን ፓርላማችንን አብዮት እያስተዋላችሁልኝ ነው? (ታላቅ የታሪክ ክስተት እንዳያመልጣችሁ!) ይሄው እንግዲህ ፓርላማችን የድሮ ታሪኩን አውልቆ ጥሎ ሚኒስትሮቹን ማፋጠጥ፣ መጠየቅ፣ መፈተሽ ወዘተ-- ገፍቶበታል። (የሰይጣን ጆሮ አይስማብን!) እኔማ ባለፉት 20 ዓመታት ያሁኑን ግማሽ ያህል እንኳ ቢንቀሳቀስ ኖሮ ስንት ሥራ በተሰራ እያልኩ መቆጨቱ ሊገለኝ ነው። (የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም!) የመንግስትና የግል ሌቦች መጫወቻም አንሆንም ነበር እኮ፡፡
በነገራችሁ ላይ ሰሞኑን ጠ/ሚኒስትሩ ከባለሃብቶች ጋር ባደረጉት ውይይት “ለራሳችንም ሆነ ለግል ሌቦች አንራራም” ማለታቸውን ማጤን ተገቢ ነው፡፡ (የድሮዋ ጦቢያ መስላኝ ነው ብሎ መፀፀት አያዋጣም) ወደ ፓርላማው ስንመለስ -- ባለፈው ሳምንት ለምክር ቤት አባላት ሪፖርት ያቀረቡት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊው “በሰብዓዊ መብት ትንሽ ወደ ኋላ የተጓተትንበት ሁኔታ ያለ ይመስለኛል። የውጭዎቹ ሜዳውን የራሳቸው አድርገው የተጫወቱበት ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ ተናግረዋል። በዚህ ከቀጠልን እኮ እነ“ሂዩማን ራይትስ ዎች” ሰብዓዊ መብት ተጥሷል ምናምን እያሉ አይወቅሱንም - እኛው ራሳችን ቀድመን መጣሱን እናምንላቸዋለና። እኔ የምላችሁ ግን --- ኢህአዴግ አሁንም ምስጢረኛነቱን አልተወም ማለት ነው፡፡ ቢተውማ ኖሮ--- በፓርላማችንና በኢቴቪ አሰራር እየታየ ያለው መነቃቃት ከምን የመጣ እንደሆነ በግልፅ ይነግረን ነበር፡፡ ራሳቸው የፓርላማ አባላቱም እኮ “ፓርላማው ጥርስ እያወጣ ነው?” ለሚለው ጥያቄ መች በአግባቡ መልስ ሰጡን - “እኛ ድሮም ሥራችንን በአግባቡ ነው የምንወጣው” ከማለት በቀር! በዚህ አጋጣሚ ኢቴቪም የህዝብ ንብረትነቱን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን መፍጨርጨር ልናደንቅለት ይገባል።
(ቡዳ እንዳይበላው መፀለያችንን ሳንረሳ!) በነገራችሁ ላይ ፓርላማው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለፈጠረው ታላቅ አብዮት ለመናገር ብንሞክርም --- ሁሉም በመሸምጠጡ እኛ ያየነውን አይቻለሁ የሚል ሁነኛ ሰው ከየት እናገኝ ይሆን እያልኩ ሳስብ ነበር፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ግን ከ “ሰንደቅ” ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት አንጋፋው የህወሃት መስራች አቦይ ስብሃት ምስጋና ይግባቸውና ሃቃችንን አረጋገጡልን፡፡ አቦይ “የፌደራል ዋና ኦዲት ሪፖርት ለእርስዎ የሚሰጥዎት ትርጉም ምንድነው?” በሚል ተጠይቀው ሲመልሱ “በዚህ አገር በዚህ ስርዓት በአሁኑ ጊዜ ትልቁና የማያጠራጥር ተስፋ ሰጪ ሁኔታ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ መጀመሩና ከሁሉም በላይ ደግሞ የፌደራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህዝብ ተወካይነቱን ማረጋገጥ መጀመሩ ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ የስልጣን አካል ሥራ መጀመሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ የምስራች ነው” ብለዋል፡፡ እኔ ደግሞ በዚህ የምስራች ለፓርላማው አባላት በሙሉ የወጣቱን ድምፃዊ የይሁኔ በላይን “እልል በይ አገሬ---” የሚል ዜማ ጋብዤአቸዋለሁ። በዚህ አጋጣሚ አንድ ሃሳብ አለኝ፡፡ ፓርላማው ነፃነቱንና የህዝብ ተወካይነቱን የተቀዳጀበት ወር ለምን በየዓመቱ አይከበርም? (ሌላ ግንቦት 20 ማለት እኮ ነው!)

No comments:

Post a Comment