Thursday, July 4, 2013

ከግብጦቹ መማር ከቻልን ፤ ይቻላል!!!

አበው "ነገር በምሳሌ ..." እንዳሉት፤ በቅርቡየአረብ ስፕሪንግተብሎ የሚጠራው በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪካ የተካሄደውን የህዝብ አመፅ እንደ አብነት ማንሳቱ ጠቃሚ ይመስለናል:: ቱኒዚያ የአረብ ስፕሪንግ ጀማሪዋ ሃገር መሆኗ ይታወቃል:: የህዝብ አመፁ በቱኒዚያ በተሳካ ሁኔታ ከተጠናቀቀና ቤንአሊም ከተባረረ በኋላ ይህ የህዝብ አመፅ ወደ ግብፅ ሊሄድ ይችላል ይሆን? በሚለው ጥያቄአዊ ሃሳብ ላይ የፖለቲካ ጠበብቶች ብዙ ብለው ነበር:: በተለይ ቱኒዚያ ግብፅ አይደለችም ስለዚህ የህዝብ አመፁ እንደ ቱኒዚያ ሁሉ በግብፅ ሊከሰት አይችልም የሚለውን አስተሳሰብ ደግፈው ምክንያታቸውን ሲደረድሩ የነበሩ ብዙ ናቸው:: 
ቱኒዚያ ግብፅ አይደለችም የሚል ሃሳባቸውን ለማስረዳት ሲጠቅሷቸው ከነበሩት ምክንያቶች መካከል በቱኒዚያ ህዝብ መካከል ያለው የሙስሊሙና የክርስትናው ሃይማኖቶች ውጥረት ግብፅ ካለው እጅግ በጣም ያነሰ ስለሆነ በግብፅ ህዝብ አንድ ሆኖ ሊታገል አይችልም፣ ቤንአሊ እንደ ሙባራክ ጨካኝ አይደለም፣ ሙባራክ ጠንካራ የጦር ሰራዊት አለው ስለዚህ በቀላሉ ከህዝብ መካከል ጥቂቶችን ገድሎ ሊቀጨው ይችላል፣ ቱኒዚያዎች ከግብፆች የበለጠ የተማሩ ናቸው፣ የፌስቡክና ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያዎችንም ቱኒዚያዎች በስፋት ተጠቃሚዎች ስለሆኑ ግብፅ ውስጥ እንደ ቱኒዚያ ያለ አመፅ ሊከሰት አይችልም፣ ሌላም ሌላምእያሉ ትንታኔዎችን ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወቃል::
ይታዩአቸው የነበሩት ምክንያቶች ግብፆች በሙባረክ አምባገነናዊ አገዛዝ ለአመታት ብዙ ተረግጠዋል፣ ተጎድተዋል፣ ተበዝብዘዋል፣ እነርሱ በድህነት እየማቅቁ ሳሉ ጥቂት ግለሰቦች በሃብት ሲትረፈረፉ ምንም አላደረጉም የሚሉት ብቻ ነበሩ:: ነገር ግን ፍፃሜው ላይ የታየው እውነታ፤ ግብፆች እጅግ ማራኪ የሆነ የህዝብ ትብብርና ሰላማዊ ተጋድሎን በአደባባይ ለአለም ህዝብ በሚገባ ማሳየታቸውና፤ አስፈሪና ጨካኝ እየተባለ ሲነገርለት የነበረውን የሙባረክ ስርዓት ከትከሻቸው ላይ አሽቀንጥረው መጣል መቻላቸው ነው:: በዚህ ዙሪያ ምሁሮቹና ፖለቲከኞቹ ያለማስተዋል ችላ ብለውት የነበረው ዋናው ቁምነገር የህዝብ እምቅ ሃይል በአምባገነኖች አስፈሪነት ሊሟሽሽ ፈፅሞ እንደማይችል ነበር:: 

የወያኔ/ኢህአዴግ ቡድን ስልጣን ከተቆናጠጠበት ሰአት ጀምሮ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እጅግ ስር የሰደዱ ችግሮችንና በደሎችን ሲፈፅም ኖሯል:: የኢትዮጵያ ህዝብ የተጫነበት ህመም ከግብፅና ከቱኒዚያ እጅግ የከፋ ነው:: በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ 11ኛው ሰአት ላይ እንደሚገኝ ለሁላችንም ግልፅ ነው:: ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ልክ እንደ ግብፆቹ ሁሉ፤ የወያኔ/ኢህአዴግ ጦር ሰራዊት መብዛት፣ ፍቅር እያለው በዘር በሃይማኖት ሳይወድ መከፋፈሉ፣ ጥቂቶች ሲበለፅጉ እርሱ ግን በድህነት መማቀቁ፣ በተቃውሞ ሰልፍ ብሶቱን ለማሰማት በወጣ ቁጥር በአጋዚው የወያኔ ሃይል በተደጋጋሚ በግፍ መጨፍጨፉ፣ መታሰሩና፣ ስቃይን መቀበሉ የህዝብን እምቅ ሃይል በበለጠ ያጎለብትለት እንጂ ሊያዳክመው ፈፅሞ አይቻለውም:: 
ነገር ግን በግብፅ የተደረገው የተሳካ አመፅ ዝም ብሎ በመላ የመጣ አይደለም:: የአመፁ አስተባባሪዎችና አንቀሳቃሾች እጅግ በጣም በሳል ስራዎችን ስለሰሩ፣ የህዝቡን የልብ ትርታ እጅግ አድርገው በመረዳታቸው፣ ቁስሉ ስለተሰማቸው የሙባረክ ስርዓት ህዝብን እንደሚያጠፋ ስለተረዱት እውነታውን ለህዝብ ስላመላከቱት ብሎም ህዝብ ወዶና በቃኝ ብሎ ትግሉን እንዲቀላቀል ስላስቻሉት ነው:: የኛም ፖለቲከኞችና የድርጅት መሪዎች ፍፁም የሆነ የአመለካከትና የአካሄድ መሰረታዊ ለውጥ በማድረግ፤ የህዝብ ቁስል ሊያማቸው፣ እውነታውንም ሊነግሩትና፣ አደራጅተው ከዚህ ስቃይና መከራ ሊታደጉት ይገባል:: ስለሆነም እጅግ ብዙ ስራዎች እንደሚጠብቃቸው መረዳት ያለባቸው ይመስለናል:: ከግብፆቹ ተምረው እራሳቸውን ካስተካከሉ የምንመኛትን፣ ለሁሉም እኩል የሆነችና፣ የህዝብ የበላይነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን በቅርቡ እንደምናያት ጥርጥር የለንም::
 ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!


ስምንቶቹ
Email: nleethiopia@gmail.com


No comments:

Post a Comment