Tuesday, July 2, 2013

የህወሓት/ ኢሕአዴግ ሰወች ለምን ለጃዋር ጥብቅና ቆሙ ?

ከማሰተዋል

የሰሞኑን የአልጀዚራን ፕሮግራም ተከትሎ ስለፕሮግራሙ እና ስለጃዋር የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ሰንብተዋል:: ከነዚህ አስተያየት ሰጭወች መካከል በአፍቃሪ ህወሓት/ኢሕአዴግ የሚታወቁ ሰወች የሰጧቸአው አስተያየቶች ትንሽ ግራ የሚያጋቡ ናቸው :: እነዚህ ሰወች በመጀመሪያ ራሱን የአልጀዚራን ፕሮግራም የሰላ ትችት ሲሰነዝሩበት የሰነበቱ ሲሆን ከመሀከላቸው በፕሮግራሙ ላይ መንግስትን ወክለው ለመሳተፍ አልጀዚራን ጠይቀው ከአልጀዚራ ፍቃድ ሲከለከሉ ሃሳባቸዉን በኢሜል ለአልጀዚራ እንደላኩ በሁአላም አልጀዚራ መልዕክቴን አዛብቶ አቀረበብኝ እያሉ በማማረር በፌስ ቡክ ገፃቸው ሲያስነበቡን የሰነበቱ ይገኙበታል :: በተጨማሪም የፕሮግራሙን ተሳታፊወች በተለይም ጃዋርን የተሳሳተ መረጃ በማቅረብ ሲወነጅሉ ከሰነበቱ በሁአላ ሰሞኑን እንደገና ጃዋር ትክክል ነው እያሉ የጃዋር ጠበቃ መስለው ለመታየት ሙከራ እያደረጉ ነው :: እነዚህ ሰወች ለምን እንደዚህ ያደርጋሉ?


በፖለቲካ ምንግዜም የሃሳብ ልዩነት እና ትችት አይጠፉም፤ ለምሳሌ ኢትዮጵያን እንዴት ሁላችንም በእኩልነት የምንኖርባት የተሻለች አገር እናድርጋት በሚለው ላይ በአንድ ኦሮሞ እና የሌላ ብሔር ሰው መካከል የሃሳብ ልዩነት ሊኖር ይችላል ሌላዉ ቀርቶ የኦሮሞን መብት እንዴት እናስከብር በሚለው አጀንዳ ላይ እንኩአን የተለያዩ ኦሮሞወች የተለያዩ አቁአም ሊያራምዱ ይችላሉ:: ስለዚህ ጃዋር የሰጣቸዉን አስተያየቶች ላይም ሌሎች ሰወች ከስም ማጥፋት በፀዳ መልኩ ሃሳቡን ብቻ ነጥለው ትችት ቢያቀርቡ ጤናማ ነው:: ነገር ግን ጃዋር የሰጣቸው አንዳንድ አስተያየቶች በአንዳንድ መንግስትን በሚቃወሙ ሰወች የተነሳበትን ትችት ተከትሎ የህወሓት/ ኢህአዴግ ሰወች ተቃዋሚወችን እርስ በእርስ ለማጋጨት ቀዳዳ እንዳገኙ ተረዱ ስለዚህ የጃዋር ጠበቃ መስለው አስተያየት በመስጠት ጃዋርን የሚደግፉ ኦሮሞወችን ከተቀረው ተቃዋሚ ጋር ለመነጠል ዘመቻ ከፈቱ:: 

ከዚህ በፊት እንደፃፍኩት ህወሓት/ ኢህአዴግ ስልጣኑን ለማራዘም የሚጠቀምበት አንድ ስልት አለው ይኽዉም በሀገር አንድነት በሚያምኑት እና መገንጠል በሚፈልጉት ኢትዮጵያዉያን መካከል የኃይል ሚዛን እንዲኖር ማድረግ እና ሁልጊዜም ቅራኔ እንዲኖር ሌት ተቅን ተግቶ መስራት:: በሀገር አንድነት የሚያምኑት ጠንከር ብለው ለስልጣኑ አስጊ ሲሆኑ መገንጠል የሚፈልጉትን ለቀቅ በማድረግ ለራሱ የሚመቸዉን እርምጃ ይወስዳል:: ለምሳሌ በጥር 1997 የኦሮሚያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ መሆን አለበት ያሉ 300 በላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ተማሪወችን ካባረረ በሁአላ በሰኔ ከምርጫ 97 ማግስት ኢህአዴግ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ዋና ከተማ በማድረግ የወሰደዉን እርምጃ ልብ ይሏል:: መገንጠል የሚፈልገው ሲጠናከር እና ለህወሓት/ ኢህአዴግ ስልጣን አደጋ ሲጋርጥም በአንድነት የሚያምኑትን ጠንከር እንዲሉና ሚዛኑን እንዲጠብቁ በማድረግ ለራሱ ፖለቲካዊ ትርፍ ይጠቀምባቸዋል :: ስለዚህ የህወሓት እድሜን ከሚወስኑት ወሳኝ ነገሮች አንዱ እና ዋነኛዉ የነዚህ ሁለት ኃይሎች የመተባበር እና የመተማመን ሁኔታ ነው:: በመሆኑም ኦሮሞወች ጭቆናዉ በዝቶባቸው ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቻቸው ጋር የመተባበር አዝማሚያ ሲያሳዩ የህወሓት/ ኢህአዴግ ሰወች ታሪክ እየጠቀሱ ዛሬ በህወሓት/ ኢሕአዴግ የሚደርስባቸዉን ግፍና መከራ ረስተው በትናንቱ ቁስላቸዉን ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር እንዲጋጩ ያደርጋሉ:: 

በተጨማሪ አሁን የጃዋር ጠበቃ ለመታየት የፈለጉት የህወሓት/ ኢሕአዴግ ሰወች በአሁኑ ወቅት ያለዉ የኢትዮጵያ ሁኔታ በእኩልነት ላይ የተመሰረተና ፍትሃዊ ነው ብለው የሚያምኑ ሲሆን በኦሮሞወችና በሌሎች ኢትዮጵያዉያን ላይ ግፍ አይፈፀምባቸዉም ብለው የሚከራከሩ ናቸው:: ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በርካታ ኦሮሞወች በኦነግነት ተፈርጀው በስር ቤት እንደሚሰቃዩ ጃዋር ሲከራከር የህወሓት/ ኢህአዴግ ሰወች ደግሞ በጠቅላላዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለው የፖለቲካ እስረኛ 400 ብቻ ነው ይላሉ:: እንዲሁም እነምናሴአባ ዱላብለው እየሰየሙ ኦሮሞን እንደሚያስተዳድሩ እያወቁ ኦሮሞ እራሱን እያስተዳደረ ነው፤ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ዘርፎችም እኩል ተጠቃሚ ነው ብለው ያፌዛሉ:: ብዙ ማለት ይቻላል::

ማጠቃለያ 

ዛሬም እንደትናንቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ የብሔር እኩልነት አልተረጋገጠም፤ ይህ እኩልነት ሊረጋገጥ የሚችለዉ እና ሁሉም በማንነቱ ሳይሸማቀቅ እና ሳይጨቆን መኖር የሚችለው ግን ኦሮሞወች ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቻቸው ጋር በመተባበር መታገል ሲችሉ እንጅ በጨቁአኞቻቸው ወጥመድ ዉስጥ እየገቡ ባለፈ ታሪክ እርስ በእርስ ሲጋጩ አይደለም:: ከትናንት ጥፋት ከታሪክ እየተማሩ የዛሬን ችግር ለመፍታት መታገል ብልህነት ሲሆን የትናንትን መጥፎ እያነሱ የዛሬን ችግር ማባባስ ወይም የችግሩን እድሜ ማራዘም ግን ሞኝነት እና አላዋቂነት ነው::

No comments:

Post a Comment