የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ስድስት ሚኒስትሮች ሥልጣን ለቀዋል
እ.ኤ.አ. በ2011 የተቀጣጠለው የግብፅ ሕዝባዊ አብዮት ግቡን አልመታም በሚል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ግብፃውያን ታህሪር አደባባይ ለተቃውሞ መውጣታቸውን ተከትሎ፣ የግብፅ ጦር ኃይል ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲና ዋነኛ ተቃዋሚዎች ችግሮቻቸውን ካልፈቱ ጣልቃ እንደሚገባ የ48 ሰዓት ጊዜ በመስጠት ለመፈንቅለ መንግሥት መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡
ባለፈው ሰኞ ጦር ኃይሉ ያወጣው መግለጫ የፕሬዚዳንቱን ደጋፊዎች ሲያበሳጭ፣ ተቃዋሚዎቻቸውን ደግሞ አስደስቷል፡፡
ማክሰኞ ዕለት በቀይ ባህር ዳርቻ ከምትገኘው የስዊዝ ከተማ ወታደሮች ወደ ካይሮ መንቀሳቀሳቸው የተሰማ ሲሆን፣ ጦር ኃይሉ ሊከሰት የሚችለውን የእርስ በርስ ግጭት በማስወገድ በቀጥታ ወታደራዊ ግልበጣ ለማካሄድ መዘጋጀቱ ተሰምቷል፡፡
የጦር ኃይሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባት በግብፅ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ላይ የራሱን ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሎ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ሥጋት የፈጠረ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት (ተመድ) ፕሬዚዳንት ሙርሲ ጦር ኃይሉ ዕርምጃውን ከመውሰዱ በፊት ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ይሰጡ ዘንድ አበክሮ ጠይቋል፡፡
ጦር ኃይሉ የግብፅ ፕሬዚዳንትና ተቃዋሚዎቻቸው የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ ይገባቸዋል የሚል መግለጫ ቢያወጣም፣ ከ22 ሚሊዮን በላይ ግብፃውያንን ከጀርባቸው ያሠለፉት ዋነኛ ተቃዋሚዎች ፕሬዚዳንቱ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን እንዲያስረክቡ፣ ካልሆነ ደግሞ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት መወገዳቸውን የሚፈልጉ መስለዋል፡፡ማክሰኞ ዕለት በቀይ ባህር ዳርቻ ከምትገኘው የስዊዝ ከተማ ወታደሮች ወደ ካይሮ መንቀሳቀሳቸው የተሰማ ሲሆን፣ ጦር ኃይሉ ሊከሰት የሚችለውን የእርስ በርስ ግጭት በማስወገድ በቀጥታ ወታደራዊ ግልበጣ ለማካሄድ መዘጋጀቱ ተሰምቷል፡፡
የጦር ኃይሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባት በግብፅ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ላይ የራሱን ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሎ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ሥጋት የፈጠረ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት (ተመድ) ፕሬዚዳንት ሙርሲ ጦር ኃይሉ ዕርምጃውን ከመውሰዱ በፊት ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ይሰጡ ዘንድ አበክሮ ጠይቋል፡፡
ምንም እንኳ ጦር ኃይሉ በቃል አቀባዩ በኩል ለመፈንቅለ መንግሥት እንዳልተዘጋጀ ቢገልጽም፣ ፕሬዚዳንቱና የሙስሊም ወንድማማቾች የሚባለው ድርጅታቸው ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ካልሰጡ ከ48 ሰዓታት በኋላ በኃይል እንደሚያስወግዳቸው የብዙዎች እምነት ሆኗል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች የጦር ኃይሉን መግለጫ በመቃወም ለተቃውሞ ሠልፍ ወጥተዋል፡፡
ተመድ ፕሬዚዳንቱ ብሔራዊ ውይይት ጠርተው ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ካልሰጡ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ አይቀሬ ነው ሲል ደምድሟል፡፡ የተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ናቪ ፒላይ ቃል አቀባይ ሩፐርት ኮልቪል እንዳሉት፣ ፕሬዚዳንቱ ለሕዝባዊው ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጡ መፈንቅለ መንግሥቱ አይቀሬ ነው፡፡ ‹‹በመሆኑም ፕሬዚዳንቱ ባለፉት ቀናት በግብፅ ሕዝብ ለተነሱት ቁልፍ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ይሰጡ ዘንድ ጥሪ እናቀርባለን፤›› ብለዋል፡፡
በግብፅ መከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ሲሲ የሚመራው ጦር ኃይሉ፣ ፕሬዚዳንቱ ለሕዝቡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ የትዕዛዝ ያህል መግለጫ ሲያወጣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችም መግባባት እንዲፈጥሩ ቢልም፣ ከ48 ሰዓታት በኋላ የሚወስደው ዕርምጃ ፕሬዚዳንቱንና ካቢኔያቸውን ሊያሰናብት ይችላል ተብሏል፡፡
ከፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ማክሰኞ ማለዳ የወጣው መግለጫ እንደሚያስረዳው፣ ፕሬዚዳንቱ ብሔራዊ ዕርቅ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ይህም ቢሆን ግን ግብፅ ከዚህ በፊት አይተው በማታውቀው ዲሞክራሲያዊ ሒደት ላይ በመሆኗ የጦር ኃይሉን ጣልቃ ገብነት አላስፈላጊ ነው፡፡ ማክሰኞ ምሽት ላይ ፕሬዚዳንቱ ፈጽሞ የጦር ኃይሉን ጥሪ እንደማይቀበሉ ገልጸው፣ ጥሪውን መቀበል ማለት ግብፅን ወደኋላ መመለስ ስለሆነ አይታሰብም ብለዋል፡፡ ግብፅ በአብዮቱ አማካይነት ዲሞክራቲክ የሲቪል መንግሥት ስለመሠረተች ወደኋላ አትመለስም በማለት የጦር ኃይሉን ማስጠንቀቂያ ቸል ብለዋል፡፡ ምንም እንኳ በግብፅ ውስጥ የታየው ጥልቅ ክፍፍል ተቃዋሚዎችንና ደጋፊዎችን በተለያዩ ጎራዎች ማሠለፉ ቢታይም፣ ፕሬዚዳንቱ ግብፅ ውስጥ ዲሞክራሲ ሰፍኗል ማለታቸው አስገራሚ ነው ተብሏል፡፡
በግብፅ ውስጥ በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሥራ አቁመው በተለያዩ ጎራዎች ሠልፍ የወጡ ሲሆን፣ በተለይ ከተቃዋሚዎች ጋር የተሠለፉት ግብፃውያን ቁጥር በብዙ ሚሊዮኖች ተገምቷል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች ቁጥር ደግሞ በመቶ ሺዎች ውስጥ ነው ተብሏል፡፡ ከታህሪር አደባባይ እስከ ፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት ድረስ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሰብዓዊ ሠንሠለት የፈጠሩት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ግብፃውያን፣ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣናቸው ካልወረዱ ወደቤታቸው እንደማይመለሱ አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል አገሪቱን ወደ እስላማዊ ሪፐብሊክነት እየለወጡ ነው የሚሏቸውን ፕሬዚዳንት ሙርሲ ጦር ኃይሉ እንዲያስወግዳቸው የሚፈልጉት፡፡
እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2011 ተቀስቅሶ የቀድሞውን የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን ያባረረው አብዮት ዳቦ፣ ነፃነትና ማኅበራዊ ፍትሕ በሚሉ ሚሊዮኖች ነበር የተጀመረው፡፡ ፕሬዚዳንት ሙርሲ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠው ሥልጣን ላይ በቆዩበት አንድ ዓመት እነዚህን የአብዮቱን ጥያቄዎች ካለመመለሳቸውም በላይ፣ የአብዮቱን ዓላማዎች በመጥለፍ ወዳልሆነ አቅጣጫ ግብፅን በመምራታቸው ይወገዱ በማለት ካለፈው እሑድ ጀምሮ ታህሪር አደባባይ ወጥተዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል በግብፅ ውስጥ መግባባት ካልተፈጠረ ጦር ኃይሉ የራሱን ‹‹ፍኖተ ካርታ›› ይዞ ወደ ፖለቲካው መንደር ዘው ብሎ ለመግባት የተዘጋጀው፡፡ በታህሪር አደባባይ አናት ላይ ሔሊኮፕተሮች የግብፅን ሰንደቅ ዓላማ አንግበው መብረራቸው ጦር ኃይሉ የሕዝቡን ድጋፍ ለማግኘት አስመስሎበታል፡፡ ፖለቲከኞችን መፍትሔ አፈላልጉ ከማለት በዘለለ ሥልጣኑን መንጭቆ ሊወስድ ያሰበም መስሏል፡፡
‹‹ሬበል ካምፔይን›› በመባል የሚጠራው የተቃዋሚዎች ስብስብ ግብረ ኃይል ቃል አቀባይ መሐሙድ ባድር፣ ፕሬዚዳንት ሙርሲ ተወግደው አስቸኳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መደረግ አለበት ብለው፣ ‹‹የጦር ኃይሉ ፍላጎትም ይኼንን ስለሚያንፀባርቅ ለመግለጫው ድጋፋችንን እንገልጻለን፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹የጦር ኃይሉ ታሪካዊ ሚናም ከሕዝቡ ጎን መሰለፍ ነው፤›› በማለት ለጦር ኃይሉ እንቅስቃሴ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅት ግን የጦር ኃይሉን ጣልቃ ገብነት አውግዟል፡፡ ጦር ኃይሉ በዲሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጠ ፕሬዚዳንት ላይ እንዲህ ዓይነት መግለጫ ማውጣት የለበትም በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ የግብፅ ሰለፊስት ኑር ፓርቲ ከፕሬዚዳንቱ ጎራ በመኮብለል ተቃዋሚዎች ያቀረቡትን ጥያቄ በመደገፍ አስቸኳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
የፕሬዚዳንት ሙርሲ ካቢኔም ከወዲሁ የመልቀቂያ ጥያቄ ባቀረቡ ሰዎች ተደናግጧል፡፡ እስከ ማክሰኞ ድረስ ሰባት ሚኒስትሮች መልቀቂያ ያቀረቡ ሲሆን፣ የተቃዋሚዎቻቸው ሕዝባዊ ድጋፍ እየተጠናከረ ነው፡፡ የልብ ልብ የተሰማቸው ተቃዋሚዎች ከሙርሲ የሚቀርብላቸውን የድርድር ጥያቄ ወደጎን በመግፋት ‹‹ውረዱ›› ማለቱን ቀጥለዋል፡፡ የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎድሮስ ዳግማዊ ለሕዝባዊው አብዮት ድጋፋቸውን ገልጸው፣ ሙርሲ በአስቸኳይ ሥልጣን እንዲለቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ግብፃውያን የተሰረቀባቸውን አብዮት ማስመለስ ግዴታቸው ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የጦር ኃይሉ ወደ ፖለቲካው መምጣት ያሳሰባቸው ግብፃውያን አሉ፡፡ በገማል አብዱልናስር፣ በአንዋር ሳዳትና በሆስኒ ሙባረክ መዳፍ ውስጥ በአምባገንነት የተገዛችው ግብፅ ጦር ኃይሉ ሥልጣን ላይ ከወጣ አብዮቷ ይኮላሻል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ ጦር ኃይሉ ሥልጣን ላይ ወጣ ማለት ዲሞክራሲ ተመልሶ ይዳፈናል ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ ጦር ኃይሉ የ48 ሰዓታት ማስጠንቀቂያው ከመፈንቅለ መንግሥት ጋር የተያያዘ አይደለም ቢልም፣ ማስጠንቀቂያውን ምን አመጣው የሚሉ አሉ፡፡ ጦር ኃይሉ የፖለቲካ መፍትሔ መፈለግ የሚለው የፕሬዚዳንቱን መወገድ ነው ብለው፣ ፕሬዚዳንቱ ደግሞ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጥኩ ስለሆነ ንቅንቅ የለም ስለሚሉ ግብፅ አይታው የማታውቀው ትርምስ ውስጥ ትገባለች በማለት ይሰጋሉ፡፡
ከተመድ በተጨማሪ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ፕሬዚዳንቱ ለሕዝባዊ ተቃውሞው ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀው፣ ይህ ካልሆነ ግን ግብፅ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እንደሚገጥማት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዲሞክራሲ ማለት ከምርጫም በላይ ነው፤›› ያሉት ኦባማ ፕሬዚዳንቱ ለፖለቲካ መፍትሔ ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዚህም አማካይነት ብጥብጥ እንዳይነሳና ደም መፋሰስ እንዳይከተል አሳስበዋል፡፡ ንቅንቅ አልልም ያሉት ሙርሲ ግን በአቋማቸው ፀንተዋል፡፡
ሙርሲ በዚህ አቋማቸው ቢፀኑም፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ለመደራደር በቅርቡ አዲስ አበባ መጥተው የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ ካሚል አምርን ጨምሮ ሰባት ሚኒስትሮች ራሳቸውን ከካቢኔው አሰናብተዋል፡፡ የሚኒስትሮቹ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣን መልቀቅ ለሙርሲ የፍፃሜው ጅማሬ ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው፡፡ የግብፅ ብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ላይ ወድቋል የሚለው የጦር ኃይል አጋጣሚውን በመጠቀም ግልበጣ ለማድረግ ወደኋላ አይልም የሚለው ስሜትም አይሏል፡፡
በሕዝቡ ጥቅም ስም ጣልቃ የሚገባው ጦር ኃይል እንደተለመደው አምባገነንነትን ይዞ ይምጣ፣ ወይም የሕዝቡን ጥቅም ያስከብር ባለየበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት ግብፅ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መግባቷ ብዙዎችን ያስማማል፡፡ አሁን በግብፅ ውስጥ የተፈጠረው ውጥረት ፕሬዚዳንቱን ሕጋዊና ሕገወጥ ከማድረግ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ በግብፃውያን መካከል ደም መፋሰስ ሊከሰት ይችላል የሚለው አስጊ ሆኗል፡፡
አብዮታቸው በሙስሊም ወንድማማቾችና በፕሬዚዳንቱ እንደተጨናገፈባቸው የሚያስቡት ግብፃውያንና የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎዎች ተፋጠዋል፡፡ ባለፈው ሰኞ በሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅት ጽሕፈት ቤት ሕንፃ ላይ በደረሰው ቃጠሎና ዝርፊያ ደም መፋሰስ የተከሰተ ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱ ግጭት አድማሱ ከሰፋ ለግብፅ አደጋ ይሆናል፡፡ ጦር ኃይሉ ብጥብጥ እንዳይነሳና ብሔራዊ ደኅንነት ችግር ውስጥ እንዳይገባ በማለት ጣልቃ ለመግባት ሰዓታት ብቻ ቀርተውታል፡፡ ወታደራዊው መፍትሔ ከአሳሳቢ በላይ የሆነባቸው ግብፃውያን ፍራቻ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ የግብፅ ትርምስ ውስጥ መግባት ለራሷም ሆነ ለጎረቤቶቿ ጭምር ጠንቅ ሊሆን እንደሚችል በስፋት እየተነገረ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment