Monday, August 19, 2013

ግልጽ ደብዳቤ ለኮሎኔል መንግሥቱ ሃይለማሪያም:

ከሁሉም በማስቀደም የጸሃይ አሳታሚ አርታኢ ለሆኑት ለአቶ ኤልያስ ወንድሙ በኮሎኔሉና ሌሎች ደራሲያንና ታራኪ ጸኃፊዎች የሚጻፉትን በመጽሃፍ አዘጋጅተው ለአንባቢያን ለማቅረብ አቅደው በመናሳትዎት የዘገየም ቢሆን ምስጋናዬን እያስቀደምኩ ትእግስቱን ብርታቱንና ጽናቱን እመኝልዎታለሁ።
ይህንን የግልጽ ደብዳቤ እንድጽፍ ያስገደደኝ ኮሎኔሉ ትግላችን /ቅጽ አንድ/ በሚለው መጽሐፍዎት ምዕራፍ አስራ አንድ “ደርግና ዓፄ ኅይለሥላሴ” በሚለው ዐርስተ ጉዳይ ገጽ 259 አምስተኛ እና ስድስተኛ ፓራግራፎች ያሰፈሯቸው ሀሳቦች አሳሳቢ ሁነው ስለአገኘኋቸው ነው።

በአምስተኛው ፓራግራፍ
“አንደኛ ወይም የመጀመሪያ የተሳሳተ ወርቅማ ዕድል ይባል የነበረው በአገራችን ሠፍኖ በኖረው ጉልታዊ ሥርዓትና የሥርዓቱም ነጸብራቅ በሆነው የአመራር ጉድለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዓያሌ ምዕተ ዓመታት የነበረበት አሣፋሪ ድሕነትና የሰቆቃ ሕይወት ያነሰ ይመስል በ 1928 ዓም በፋሽስት ኢጣሊያ መወረሩን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ክብሩንና ነፃነቱን ተገፎ ቅኝ ከመሆኑ ጋር የሚስተካል ውርደትና አሳዛኝ ነገር የለም” ይላሉ።
በስድስተኛው ፖራግራፍ ደግሞ
“የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ካደረሰው እልቂትና ውርደት ወዘተ ጋር ታክለው በታሪክ ከሚታሰቡ አሳዛኝ ጉዳዮች አንዱ ደግሞ የቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴ መሰደድ ነው” ይላሉ።
ታሪክን ዋቢ ጠርተን ለመናገር ኢትዮጵያ የጣሊያን ቅኝ እንደነበረች ሳይጠራጠር ማስረጂያ ሳያቀርብና በልበ ሙሉነት ደፍሮ ለመጻፍ ከሙሲሊኒ አፈቀላጤዎች ሌላ እርስዎ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የሆኑ ይመሥሉኛል።
የፋሽስት ሙሱሉኒ መንግሥት የ League of Nations Covenantsን እና እአአ በ 1928 ዓም በኢትዮጵያ መንግሥትና በኢጣሊያን መንግሥት የተፈረመውን የወዳጅነት ስምምነት በመጣስ የወረራ ጦርነቱን እአአ ኦክቶበር 3/1935 ሲጀምር ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአዝማችና አዋጊ-ተዋጊ መሪዎቹ ፤ ራስ አበበ አረጋይ፡ ራስ ዕምሩ ኅይለሥላሤ፡ ራስ ስዩም መንገሻ፡ ቢትወድድ ወልደጻዲቅ ጐሹ፡ ቢትወድድ ያረጋል ረታ፡ ደጃዝማች ጸሀይ ዕንቁሥላሤ፡ ደጃዝማች ወርቁ ዕንቁሥላሤ፡ ራስ ካሳ ስዩም፡ ራሥ መሥፍን ስለሺ፡ ራስ መንገሻ ሥዩም፡ ፊታውራሪ በላይ ዘለቀ፡ ሻለቃ አብዲሣ አጋ፡ ፊታውራሪ አሊ ፈሪሣ፡ ቢትወድድ አዳነ መኰንን፡ ደጃዝማች አዕምሮ ሥላሤ አበበ፡ ደጃዝማች ክፍሌ ዳዲ፡ ጀነራል አማን አንዶም፡ ጀነራል ሙሉጌታ ቡሊ፡ አቶ አብርሐም ደቦጭ፡ አቶ ሞገሥ አስገዶም፡ ደጃዝማች ከበደ ብዙነሽ፡ ቀኝ አዝማች ሽዋፈራ ፈንታ፡ ደጃዝማች ደረጀ መኰንን እና ሌሎቹም እየተመራ አገሩን ከወራሪው ኅይል ለማዳን እና እንደ የአፍሪካ አህጉር እህት አገሮች የቅኝ ግዥ ሰለባ ላለመሆን መሳሪያ ያለው በመሣሪያው አለዚያም በጦሩ እና በጎራዴው ሲያመች ፊት ለፊት በመግጠም ሳያመችም በሽምቅ በመታገል በመጣልና በመውደቅ የአገሩን አንድነት ዳር ድንበር ነጻነትና ሕልውና ለማስከበር ያደረገውን ትግል ታሪክ ለዘላለም የሚያስታውሰውና የኢጣሊያን መንግሥትና ሠራዊትም የማይረሳው ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብና ሠራዊት እአአ ጃንዋሪ 1941 በእንግሊዝ ወታደሮች በመታገዝ ድል እስከ ተቀዳጀበት ድረስ አምስቱን የጦርነት ዓመታት ታሪክ ዘጋቢዎችም ሆኑ የ League of Nations የወረራ ጊዜ/Occupation በማለት ይገልጹታል። ለዚህ ገላጭ-ምሣሌ የሚሆነው የጀርመን ናዚ ጦር ኅይል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የፈረንሣይን ጦር በማሸነፍ እአአ ከሜይ 1940 እስከ ዲሴምበር 1944 ድረስ ወታደራዊ አስተዳር በማቋቋም ያስተዳደረበትን ጊዜ እንደዚሁ የወረራ ጊዜ/Occupation በማለት ይገልፁታል። እዚህ ላይ ሳላነሳ ማለፍ የማልፈልገው በፈረንሣይና በኢትዮጵያ መካከል የነበረውን የወረራ/Occupation ይዘት ልዩነት ይሆናል። ይኸውም በአሸናፊው የጀርመን ጦር እና በተሸናፊው የፈረንሣይ ጦር መካከል ጊዜያዊ ጦርነት የማቆም ስምምነት/armistice ተፈርሞ የነበረ ሲሆን በሰደት በነበረው በንጉስ ኅይለሥላሴ መንግስትም ሆነ ንጉሡን ተክተው ኢትዮጵያን በማሥተዳደርና ጦርነቱን በማቀነባበር ይመሩ በነበሩት በቢትወደድ ወልደጻድቅ ጎሹ እና በፋሽስት መንግስት ወይንም የጦር ኅይል ተመሳሳይ ስምምነት አልነበረም።
ከዚህ በተጨማሪ በ Rutgers State University of New Jersey የምርምር ጥናት የሚያደርጉት Mr. Anthony W. Orr እአአ April 26, 2011 The Italian Occupation of Ethiopia 1936-1941: A Seminal Event in the Formation of Modern Nation
2
በሚል ዐርዕስት በፃፉት ጽሑፋቸው ኢትዮጵያዊው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሠር ባሕሩ ዘውዴ ከጻፉት History of Modern Ethiopia በመጥቀስ የጣሊያን ወታደሮች ይዘውት የነበረው ከኢትዮጵያ ጠቅላላ የመሬት ስፋት ከአርባ በመቶ የማይበልጥ/ 40 %/ ነበር ይላሉ።
እንግዲህ ነባራዊው ሁኔታ/objective reality/ እንዲህ ሆኖ ሳለ እርስዎ ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቅኝ ሆነች የሚለውን አባባልዎትን ማስረጅያ በማቅረብ እንዲያስረዱ ዓለያም ተሣስተው ከሆነ ያስቀየሙትን ያሣዘኑትን በተለይም ለሐገራቸው ሕልውና ነጻነትና አንድነት በመስዋትነት ያለፉትን ጥቂትም ቢሆኑ ከመካከላቸው ደርግ ከገደላቸው ስድሳ የዓጼ ኀይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት ስለ አሉበት የዘገየም ቢሆን ኢትዮጵያዊ የሆነ ይቅርታ መጠየቅ የሚኖርብዎት ይመስለኛል።
በፓራግራፍ ስድስት በቀዳማዊ ኅይለሥላሤ መሰደድ የንዴት-ሐዘንዎትን ገልፅው ተከታታይ በሆኑት ፓራግራፎች….ንጉሡ ከእንግሊዝ አገር አምስት ዓመታት ቆይታ ሲመለሡ…. አገሪቷ ወደነበረችበት አስከፊ ሑኔታ ከመመለስ ይልቅ…. በእንግሊዝ ዘውዳዊ መንግሥት የዴሞክራሲ ዘይቤ ይመሯታል ተብሎ ሲጠበቅ…. የባንዳን የስደተኛ ግምባር ከመፍጠር ሌላ የፈረሠውን የመሣፍንት መደብ መልሰው በማቋቋም ኢጣሊያን ነጻ ያወጣውን አርሶ አደር ገባርና ጢሠኛ አደረጉት በማለት ይከሷቸዋል።
እዚህ ላይ እርስዎ አስከፊ ሁኔታ የሚሉት የፊውዳሉን ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት ብዙዎች አገሮች ያለፉበትና ሌሎችም የሚያልፉበት የኤኮኖሚ የፖለቲካ የባሕልና የሶሻል ወይንም ማሕበራዊ ዕድገታቸው የሚገለፅበት ደረጃ/ Stages of development/ ከመሆኑ ሌላ የሚቀጥለው የዕድገት ደረጃ ካፒታሊዝም የሚፅነስበትና ዕድገቱ ያለ አንዳች እንከን ከቀጠለ የሚወለድበት ይሆናል።
የኢጣሊን መንግሥት ጦሩን ወደ ኢትዮጵያ የላከው የኢትዮጵያን ፊውዳል ሥርዐት ለማፍረስና የመሣፍንቱን መደብ ለመለወጥ ሳይሆን ከሌሎች ቅኝ አገሮች ታሪክ መማርና መገንዘብ እንደሚቻለው የሚይዟቸውን አገሮች ዕድገት ለመግታትና የተፈጥሮ ሐብታቸውን በመበዝበዝ የእናት አገራቸውን ኢኮኖሚ ለማዳበር ነው። ዶ/ር ኅይሌ ላሬቦ እአአ 1994 ዓም በ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ታትሞ በወጣው The Building of an Empire : Italian Land Policy and Practice in Ethiopia በሚለው መጽሐቸው ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ላይ ሶስት ዓላማና ዕቅድ እንደነበራቸው ይገልጻሉ። የመጀመሪያው አላማቸው ተሳክቶ ኢትዮጵያን ቢይዙ ኢትዮጵያ ብታምጽና የነጻነት ጦርነት ብትጀምር ጦራቸው በአስቸኳይ የጦር ዕርምጃ ለመውሰድ እንዲያስችለው ስትራቴጂክ የሆነ ቦታ መያዝና በዛ ላይ ማስፈር ሲሆን ሁለተኛው ዓላማ ቁጥሩ ያልታወቀ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ኢጣሊያንያዊያኖችን በአገራቸው ሕዝብ ብዛት ከተጨናነቀበት መሬቶች በማንሳት ለምለም በሆኑት የኢትዮጵያ መሬቶች ማስፈር ሲሆን ዶ/ር ኅይሌ Demographic colonization በማለት ሲገልጹት ሶስተኛው ደግሞ Commercial farming በማቋቋም የኢትዮያን ኢኮኖሚ በማቆርቆዝና ጥገኛ በማድረግ የአገራቸውን ኤኮኖሚ መገንባት ነበር። ሆኖም ይላሉ ዶ/ር ኅይሌ አገር ውስጥ ሠፍኖ የነበረው የመሬት ይዞታ ሥርዐት Indigenous land tenre system ከፍተኛ ዕንቅፋት ስለሆነባቸው ፈልገውትና ዐቅደውት የነበረውን መሬት አለማግኘታቸው ብቻ ሣይሆን በኅይል በወረሱት መሬት ላይ የሠፈሩትም ያጋጠማቸውን ችግር መቋቋም ስላልቻሉ ዕቅዳቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
ከዚህ በተጨማሪ በተለይ በአውሮፓዊያን አቆጣጠር የ 1940 መጀመሪያዎቹ ዓመታት ለዙፋኑ እኔ እቀርባለሁ/እኛ እንቀርባለን ለእኔ ይገባኟል/ለእኛ ይገባናል ከሚሉ የአማራና የትግሬ መሣፍንታዊ ኅይሎች እና እንዲሁም በአርበኞችና በስደተኞች መካከል ተጧጡፎ በመካሄድ ላይ የነበረው ቅራኔ ፋታ የሚሰጥ ያልነበረ ከመሆኑ ሌላ በወቅቱ የተደራጀ የጠነከረ የፖሊስ ኅይል ያልነበረበትና ግብር መሠብሠብ እንኳ ያማይቻልበት ጊዜ እንደ ነበር ታሪክ መዝግቦታል። ከዚህ በተጨማሪ የእንግሊዝ የጦርና ሲቪሊያን አማካሪዎቻቸው ከፖለቲካ ነፃ የሆነ የተማረውንና የሠለጠነውን ያቀፈ ቢዩሮክራሲ በአስቸቋይ መቋቋም አለበት በማለት ያስጨንቁ እንደነበር ታሪክ የሚያስታሰው ሁኖ ሳለ እርስዎ ንጉሡን ጣሊያን ነጻ ያወጣውን አርሶ አደር መልሰው ገባርና ጢሰኛ አደረጉት በማለት ታሪክን ሳያስደግፉ ይከሷቸዋል። የኢትዮጵያ የፓለቲካ የኢኮኖሚ የባሕልና የማሕበረሰብ ወቅታዊ ሁኔታ Objective reality እላይ እንደገለጽኩት ሆኖ ሣለ ንጉሡ አገሪቷን “በእንግሊዝ ዘውዳዊ መንግሥት የዴሞክራሲ ዘይቤ” ለመምራት አለመፈለጋቸው ትዝብትዎትን አትርፈዋል። እርስዎ “ዘውዳዊ መንግስት የዴሞክራሲያዊ ዘይቤ” የሚለው ሐረግ ምን ማለት እንደሆነ ፍችውን ወይንም ትርጉሙን አይሰጡም። Constitutional Monarchy ወይንስ Bourgeois democracy ለማለት አስበው ይሆን? ፊውዳሊዝም በሠፈነበት አገር ቡርዡዋ ዴሞክራሲ መመኘት ወይንም እንዲሠፍን ለማድረግ መሞከር የማሕበረ ሰቦችን ሳይንሳዊ ዕድገት በሚገባ ካለ መገንዘብና ካለ መረዳት የሚመነጭ ሐሳብ ከመሆኑ ሌላ ቢሞከር እንኳን የሚያስከትለው ጥፋትና ችግር ቀላል አይሆንም ነበር።
3.
ሌላው የታሪክ መሠረት የሌለው ወይንም ከሐቁ የራቀ ወይንም አጠቃላይ ስእሉን በማይሰጥ ሁኔታ ዕላይ ጠቀሼ እንዳለፍኩትንጉሡን “በታሪክ ከሚታሰቡ አሳዛኝ ጉዳዮች አንዱ ደግሞ የቀዳማዊ ኅይለ ሥላሤ መሠደድ ነው” በማለት የከሰሷቸው ነው። የክስዎትን ሐሳብ በሚገባ ለመረዳትና አጥጋቢ መልስ ለመስጠት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማንሣትና ተገቢ ገለጻ መስጠት ተገቢ ይሆናል እላለሁ። ስደቱ ለምን አስፈለገ? ከስደቱ በፊት ምን ተደረገ? እርስዎስ ሐሳቡን በሚገባው Context ለማየት ሞክረዋል?
እላይ ያነሷኋቸውን ጥያቄዎች በሚገባ ለመገምገም ክስዎትን ከወቅቱና ከታሪካዊ ኮንቴክስቱ በማየት እጀምራለሁ። መንግስታት የመጀመሪያውን የዓለም ጦርነት ለማቆም ሲስማሙ የዓለምን ሰላም ለማስከበርና በመካከላቸው ሊነሱ የሚችሉትን ግጭቶች በሰላም መፍታት አስፈላጊ መሆኑን በመገንዝብ እአአ በ 1919 42 ነፃና ቅኝ ያልሆኑ አገሮች የ League of Nations ሲያቋቋሙ የኢጣሊያን መንግሥት ከመሥራቾቹ አንዱ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት እአአ ሰፕተምበር 28/1923 አባል ሆነ። የድርጅቱ መተዳደሪያ ሕግ /Covenant/ አንቀጽ 10 አባል አገሮች በመካከላቸው የጦር ወረራ እንዳያደርጉ ያግዳል። ከዚህ ሌላ እአአ ኦገስት 6/1928 የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢጣሊያን መንግሥት በመካከላቸው ለሃያ ዓመታት ፅንቶ የሚቆይ የወዳጅነት ስምምነት ተፈራረሙ። ከእነኝህ ወቅታዊና አስፈላጊ ሥምምነቶች በተጨማሪ እአአ ኦገስት 27/1928 በአገሮች መካከል ጦርነት የሚከለክለውን በ Kellogg-Braind Pact የሚታወቀውን ዓለም አቀፋዊ ስምምነት ሁለቱም አገሮች ፈርመዋል።
እነኝህ ስምምነቶች በመካከላቸው ቢኖሩም የኢጣሊያን መንግሥት እአአ 1934 ዓም በኢትዮጵያ ግዛት በተለይም በወልወል ያደርግ የነበረው ወረራ እየበዛ ከመሄዱ ሌላ በሶማሊያና በኤርትራ የጦር ኅይሉን ማደራጀትና መገንባቱን ይያዘዋል። የጣሊያን መንግሥት በማከታተል ይወስድ የነበረው እርምጃ የኢትዮጵያን ባለሥልጣናትንና ንጉሡን ስላሳሰበ ንጉሡ እአአ ጃንዋሪ 3/1935 እና ማርች 8/1935 በማከታተል ድርጅቱ ጉዳዩን በአንክሮ ተመልክቶ ዳኝነት እንዲሰጥ ቢጠይቁም ዕርዳታ ከመነፈጋቸው ሌላ የእንግሊዝ መንግሥት በሁለቱም አገሮች ላይ የመሣሪያ ዕቀባ አደረገ። የንጉሡ መንግሥት እቀባው እንዲነሣ ቢጠይቅም አዳማጭ በማጣቱ እርዳታ ሳያገኝ ቀርቷል። የኢትዮጵያ መንግሥትም የኢጣሊያን ሰይጣናዊ-ዓላማ ስላሳሰበው ሕዝባዊ ወታደሩን ማስታጠቅና ማዘጋጀት ሲጀመር እንደተፈራውና እንደታሰበው የኢጣሊያን ጦር እአአ ኦክቶበር 3/1935 ኢትዮጵያን ወረረ።
እዚህ ላይ መነሳት ያለበት የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ የድርጅቱ የወቅቱና የጊዜው ኅያላን አገሮች እንገሊዝና ፈረንሣይ ወረራውን ለምን አላቆሙም የሚለው ይሆናል። የጀርመን ናዚ መሪ የነበረው ሂትለ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ለመጀመር ይዘጋጅ ስለነበር ፋሽስት ሙሱሊኒ ከሂትለር ጋር በማበር አውሮፓን እንዳያስጨንቁና በተቀነባበረ ኅይል እንዳይወሩ ለማድረግ የፈረንሣይና የኢንግሊዝ መንግሥታት ስትራቴጂ ማውጣት ግዴታ ሆነባቸው። ጠቃሚ ስትራቴጂ ሁኖ ያገኙት ኢትዮጵያን ለኢጣሊያን መሥዋት ማድረግ ነው። ይህም የኢጣሊያንን መንግሥትና ወታደሮች በኢትዮያ ውስጥ እንዲጠመዱ ከማድረጉ ሌላ፦ ሂትለርን በአውሮፓ ለመርዳት እንዳይችሉ ያግዳል በማለት ላይ የተመሠረተ ዕቅድ እንደነበር የታሬክ ምሑራኖች ጽፈዋል።
ስደቱ አስፈላጊ ለምን ሆነ? የድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት ጄኔቫ ስለነበር እአአ ኤፕሪል 30/1936 ንጉሡና አማካሪዎቻው ባደሩጉት አስቸኳይ ስብሰባ የወቅቱ ችግር አስቸኳይ እንደሆነ ተገንዝበው አቤቱታንና ዕሮሮን ለማሰማት የንጉሡ ወደዚያ መሔድ አማራጭ የሌለው ሐሳብ እንደሆነ ተስማምተው ቢትወደድ ወልደ ጻድቅ ጎሹ አገሪቷን በተጠባባቂነት እንዲያስተዳድሩና ጦርነቱንም በማስተባበር እንዲመሩ መርጧቸው። ንጉሡም የተጣለባቸውን ሐላፊነት ለመወጣት ወደ አውሮፓ በመሄድ ከድርጅቱ ዋና እና መሪ ከነበሩት አባል አገር መሪዎች ጋር በመገናኘት አገራቸው የድርጅቱ አባል በሆነ አገር ጦር ኅይል ስትወረር ድርጅቱ ሊያስቆምና ዕርዳታ ለማድርግ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የእሳቸውን እና የሕዝባቸውን ቅሬታ አሰምተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ምን አልባት እርስዎ ሊያስታውሱት ወይንም ሊያነሱት ያልፈለጉት ነገር እአአ ሰኔ 30/1936 ንጉሡ ጄኔቫ ይገኝ በነበረው የ League of Nations አዳራሽ የድርጅቱ አባል አገራት መሪዎች በተሰበሰቡበት የኢጣሊያን ደጋፊዎችና ሑከተኞች እየጮሁባቸው እየሰደቧቸውና እያፏጩባቸው ታሪክ ሲያስታሰው በሚኖረው ንግግራቸው ድርጅቱ በመተዳደሪያው ስምምነቱ መሰረት Collective security የኢጣሊያን መንግሥት ከወረራ እንዲታገድ አለማድረጉንና የኬሚካልን እና የመርዝ ጋዝ በመጠቀም በኢትዮጵያ ሕዝብና ሠራዊት እንዲሁም በከብቶችና በተፈጥሮ ሐብት የሚያደርሰውን ጥፋት እንዲያቆም አለማድረጉ ታሪክ ሲያሥታውሰው እንደሚኖር አስታውቀው አውሮፓም በኢትዮጵያ በመድረስ ላይ ካለው ዕልቂትና ጥፋት ልታመልጥ እንደማትችል በመተንበይ ተናግረው ድርጅቱ ከአሉት ሁለት አማራጮች Collective Security or International Lawlessness አንዱን መምረጥ እንዳለበት አሳስበው ንግግራቸውን አብቅተዋል። እርስዎ የንጉሡን መሰደድ በወቅቱና ታሪካዊ ኮንቴክስቱ ተመልክተውት ቢሆን ኖሮ ሀዘን ባላተሰማዎት ነበር እላለሁ። ከዚህ ሌላ ታዋቂ የነበረው ጀርመናዊው የጦርነት ቲዎሪስት Carl Von Clausewitz በፖለቲካና በጦርነት መካከል ያለውን አንድነትና ልዩነት ሲገልጽ war is a continuation of politics by other means ይላል። ስለሆነም የንጉሡ ጥረትና ድርጊት ይህንኑ የሚያስገነዝብ ይሆናል።
4.
ስለ ስደት ከተነሳ አይቀር በመጽሐፍዎ ምዕራፍ 9 ገጽ 236 ፓራግራፍ 5 ስለ የዕድሜ ልክ ጓደኛና የፖለቲካ ዕምነትዎ ተጋሪ የነበሩት የሻለቃ ተፈራ ተክለዓብን ማረፍ የሰሙት “በስደት ላይ ሆኜ” ነው በማለት ገልፅዋል። እላይ የንጉሡን ስደት ለመግለጽ የሞከርኩት በወቅቱና ታሪካዊ ኮንቴክስቱ በማየት ስለሆነ የእርስዎንም እንዲዚሁ ለስደት ባስገደድዎት የወቅቱ ታሪካዊ ኮንቴክስት መመልከትና መመዘን ትክክል ይሆናል እላለሁ። ይኽውም የኤርትራው “ሻቢያ” እና የትግሬው “ሕወአት” ክፍላተ ሐገራቸውን ከእናት አገራቸው ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ለ 30 እና 17 ዓመታት ከተዋጉ በኋላ እአአ በ 1991 ዓም ድል ተቀዳጅተው አዲስ አበባን ለመያዝ ሲቃረቡ እርስዎ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ከዚያም አሁን መኖሪያዎ ወደ ሆነችው ዚምባቡዌ መሄድዎ ለሕዝቡ ተገለፀ። እንግዴህ እርስዎ ስደት የሚሉትን በኮንቴክስቱ ካየነውና ከመዘነው የሥራ ጓደኞችዎትን ለእሥር ዳርገው መሄድዎት ኢትዮጵያ ውስጥ ቀርተው ቢሆን ኖሮ የእርስዎም ዕጣ ከእነሱ የሚለይ እንደማይሆን ግልጽ ስለሆነ ሽሽት እንጅ በምንም መንገድ ስደት ሊባል አይችልም። ከአገር ከወጡ በኋላ ንጉሡ በአውሮፓ እንዳደረጉት ወደ ሥልጣንዎ ለመመለስም ሆነ ወይንም የሕዝቡን ብሶት በዓለም አቀፍ ደረጃ ልማሳወቅ ሙከራም ሆነ ጥረት አለማድረግዎት ያለውን ሁኔታ ወደዱም ጠሉም እንደተቀበሉ ይገልጻል።
በጽሁፍዎት ላይ objective የሆነ ትንተናዬን ግንዛቢዬንና ግምገማዬን ከሰጠሁ በኋላ አንድ የኢትዮጵያ መሪ የነበረ ሰው ለአገሩና ለሕዝቡ ቅኝ አገዛዝን colonialism እንዴት ይመኛል የሚለው ጥያቄ ስለአብሰለሰለኝ የሚከትልውን ለማለት ተገድጃለሁ።
ለንጉሡ ያለዎት ምን አልባት ከንቃተ ሕሊናዎ ድብቅ የሆነ መጠን የሌለው ጥላቻ የማሠብ የማመዛዘንና በአንክሮ ነገሮችን የመመልከት ችሎታዎትን ስለነፈገዎት አገሪቱ በነፃነቷ በታሪኳና በባሕሏ ኮርታ ታፍራና ተከብራ ከመኖሯ ይልቅ የኢጣሊያን ቅኝ ሁና ቢሆን ይሻል እንደነበር ግልጽ አድርገው ባይጽፉትም የሚመርጡት ምኞት እንደነበረ ግልጽ ነው። በቅጽ ሁለት መጽሐፍዎት የሚያሰፍሩትን ለማንበብ ቸኩያለሁ።
ፕሮፌሰር ሰለሞን ተርፋ በ st2151@bellsouth.net አድራሻ ይገኛሉ።

No comments:

Post a Comment