Sunday, September 1, 2013

ከውሃ የቀጠነ ደም

ዓባይን በጭልፋ ቀድተው አይጨርሱም
የፈሰሰ ውሃም ደግሞ አይታፈስም
ይባል ነበር ዱሮ በቀደሙ አበው
እንደምንሰማው ከተረታቸው::
ለካስ ይወፍራል ውሃም ይታፈሳል
ግዜውን ጠብቆ ተረትም ይሻራል
ዓባይም ወፍሮ ይኸው ሊታፈስ ነው
በመረጋገጡ ትርፍና ኪሳራው::
ያባይን መታፈስ ማንም አይቃወም
ከሚጠላ በቀር የኢትዮጵያን ጥቅም
ግን የቱ ይብሳል የትኛውስ ይቅደም
የዓባይ ውሃ ነው ወይስ የሕዝብ ደም?
በግብጽ በሱዳን ደግሞም በሰሃራ
ወገን ሲንከራተት ለአንዲት እንጀራ
እንደወጣ ሲቀር በማያውቀው ስፍራ
መገደብ ያለት ይሄ ነው ኪሳራ::

ምንድነው ጥፋቱ በደሉስ ምንድነው
በጨካኝ ዐረቦች የሚቀጠቀጠው
ደሙን እያዘራ አንገቱን የደፋው
የወገን አለኝታ የአገር ተስፋ እኮ ነው::
ያባይን ወንዝ ያህል ትኩረት ያልተሰጠው
በወያኔ መንግስት ችላ የተባለው
ኢትዮጵያዊነት ከጉም የቀለለው
በባዕድ ሀገር ላይ በከንቱ የሚፈሰው
በዓለም ሚድያ መሳቂያ የሆነው
የወገናችን ደም ከውሃ ቀጥኖ ነው?
ዜግነት ተንቆ ክብር ተነፍጎት
ካሸዋ ሲለወስ በጨካኝ ጠላት
ሕይወት ቀን መሽቶበት ሞት ሲያጠላበት
መገደብ ያለበት ከዓባይ በፊት
ይህ ነበር ኪሳራ ትልቁ ጉዳት::
ጊዜውን ጠብቆ ውሃ ከወፈረ
ለመታፈስ በቅቶ ኪሳራው ከቀረ
ምነው ያበሻ ደም ከውሃ ቀጠነ
በባዕድ ሀገርስ ስለምን ባከነ?
ቢመረምሩማ ታሪካቸውን
ወይም ቢጠይቁ ነብያቸውን
ይነግራቸው ነበር መልካም መልካሙን
እንዳትነኩ ብሎ ውድ አበሾቼን::
በገዛ ሀገራቸው ቀን መሽቶባቸው
ተሻግረው ሲመጡ ከጦር አምልጠው
በፍቅር ነው እንጂ የተቀበልናቸው
ጸጉረ ልውጥ ብለን መቼ መለስናቸው?
እግራቸውን አጥበን ምግብ አብልተን
መኝታውን ሰጥተን የሚመቸውን 
አስተናግደን ነበር ያለ አድሎና ማግለል 
እንደመሰከሩት በታላቁ መድበል::
ታዲያ ውለታችን ይሄ ሆኖ ሳለ
ልባቸው በክፋት ለምን ተቃጠለ
መኝታ ነፈጉን ምግባቸውም ጠፋ
አለንጋ አመጡልን አንገት የሚያስደፋ::
ጀርባችን እስኪላጥ እግራችን እስኪቆስል
ገረፋን በተራ ክንዳቸው እስኪዝል
ዳዊት በመዝሙሩ እንደጠቀሰልን
ስለ መልካም ፋንታ ክፉን መለሱልን::ያለ ዋጋ ሲፈስ ክቡሩ ደማችን
ለዜጋው አስቦ ተቆርቁሮ የሚያዝን
መብት አስከባሪ መንግስት ቢኖረን
መቼም መቼም ቢሆን ደም ከውሃ አይቀጥን::
እረኝንት አይችል ወይ ኪሳራ አይገባው
መንጋውን በትኖ ተኩላ የሚያሰማራው
ምን ዓይነት እረኛ ምን ዓይነት መሪ ነው?
ታዲያ እንደዚህ ዓይነቱን በምን እንመስለው
ለባዕድ አበባ ለወገን ሳማ ነው
ለዚህ ሁሉ ችግር መፍትሄው ምንድን ነው
አቤት ያንተ ያለህ እያሉ ዝም ነው?
ወይስ ኡ ኡ ማለት ድምጽ ማሰማት ነው?
ሰዎች ኡ ኡ እንበል ከፍ ይበል ድምጻችን
ምድር እንድታደምጥ ሰማይ እንዲሰማን
ምን ቸገረን ብለን ዝም ካልንማ
ሲፈጸም ይኖራል የጨቛኙ ዓላማ::
ድምጽ መሳሪያ ነው ከጦር ይበረታል
ጠላትን አሳዶ ርስትን ያወርሳል
እያሱን አስቡ እስራኤልን ጭምር
የጠላታቸው ልብ በድምጽ ሲሸበር
መዶሻም አልያዙ ድጀኖም አላነሱ
በድምጽ ብቻ ነው ምሽግ ያፈረሱ::
ስለዚህ ወገኖች በተለይ ወጣቶች
ተኝታችሁ ሳይሆን ነቅታችሁ አልሙ
መለከትን ንፋ ነጋሪት ጎስሙ
ጠላት ሲንበረከክ እናንተ እንድትቆሙ
ርስታችሁንም እንድትሸለሙ::
እባካችሁ ሰዎች እንዳትታዘቡኝ
አባ ምን ነካቸው ምን ሆኑም አትበሉኝ
እኔስ አላበድኩም ወይም አልሰከርኩኝ
የበዓድ ሃገር ሞት ወገኔን ሲቀማኝ
እያየሁ በዓይኔ ልቤን እያደማኝ
ኢትዮጵያዊነቴ እየቆረቆረኝ
አላስኬድ አላስቆም አላስቀምጥ ያለኝ
አበሻነቴ ነው ደጋግሞ ደጋግሞ ደጋግሞ የነካኝ
በጽሞና መንፈስ ስለሰማችሁኝ
አመሰግናለሁ እግዚአብሔር ይስጥልኝ::
አባ ኃ/ጊዮርጊስ ድንቅነህ

No comments:

Post a Comment