ሀገራቸን ኢትዮጵያን ለቀው ለስደት የተዘጋጁት ዜጎችን ቁጥር መገመት አስቸጋሪ ቢሆንም በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት መውጣት የቻሉት ግን ላለመመለስ ብዙ ምክንያቶች አሉዋቸው፡፡ ይህን የዜጎች (በተለይ የተማሩና ወጣቶች) ስደት ሀገራችንን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት እንደሆነ እና ወደፊትም ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ለማወቅ ሊቅ መሆን የሚያስፈልግ አይመሰለኝም፡፡ አሜሪካኖች በዲቪ እንኳን ሊወስዱት የሚፈልጉት ፊደል ቆጥሮ አንድ ነገር ሊያደርግላቸው የሚችለውን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ለዜጎች ስደት ምክንያቱ መንግሰት እንደሚለው ህገወጥ ደላሎች አይደሉም ይልቁንም የመንግሰት የተለያየ ፖሊሲ ውጤቶች ናቸው ብዬ ማሳየት ፈለኩኝ እና ይህን ፅሁፍ ጀመርኩ፡፡
የስራ ዋስትና በሀገራችን የተረጋገጠ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል የመንግሰት ስራ ያልተመቸው ኢትዮጵያዊ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ገብቶ በሞያው ማገልገል አንድ የሚታይ ጠባብ አማራጭ ነበር፡፡ ይህ ጠባብ አማራጭ እንደሚታወቀው ከ1997 ምርጫ በኋላ ይህ “የኪራይ ሰብሳቢዎች ምሽግ እንዲፈርስ” በሚል በወጣ አዋጅ ጠባብ አማራጭነቱ ቀርቶዋል፡፡
የዚህ አማራጭ የተዘጋው ህጋዊ በሚመስል እና ለድሆች በማሰብ በሚል ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 621/2001 የበጎ አድራጎትና ማህበራት ምዝገባ አዋጅ እና ተከትለው የወጡትን መመሪያዎች ማየት በቂ ነው፡፡ ውጤቱ ግን ኢህአዴግ እንደሚያስበው የመንግሰት ተቀጣሪነት የሰለቻቸው ሰዎች ፀጥ ለጥ ብለው እንዲገዙ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋሞች ውስጥም አንፃራዊ ነፃነት አግኝተው ይሰሩበት ከነበረበት ወደ መንገስት ተቋም በመምጣት የመንግሰትን ተቋምን አላሳደጉም፡፡ በተቃራኒው የተገኘው ውጤት አቅም ያለው ሁሉ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሀገሩን ጥሎ ነፃነት ወደአለበት ምድር ሁሉ እየተሰደዱ ነው፡፡የስራ ዋስትና በሀገራችን የተረጋገጠ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል የመንግሰት ስራ ያልተመቸው ኢትዮጵያዊ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ገብቶ በሞያው ማገልገል አንድ የሚታይ ጠባብ አማራጭ ነበር፡፡ ይህ ጠባብ አማራጭ እንደሚታወቀው ከ1997 ምርጫ በኋላ ይህ “የኪራይ ሰብሳቢዎች ምሽግ እንዲፈርስ” በሚል በወጣ አዋጅ ጠባብ አማራጭነቱ ቀርቶዋል፡፡
የኪራይ ሰብሳቢ ምሽግ ለመናድ የተዘረጋው ወጥመድ በሀገራችን የሚገኙትን የመንግሰትም ሆነ መንግሰታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በሰለጠነ የሰው ሀይል ከማሳጣት የዘለለ ፋይዳ አላመጣም፡፡ ያመጣው ጥቅም ግን ሳይጠቀስ መታለፍ የለበትም፡፡ መንግሰታዊ ባልሆኑ ተቋሞች የሚሰሩ ዜጎችም አንድ ቀን ውጭ የሚሄዱበት ዕድል እሰኪያገኙ ልኑርበት በሚል ባሉበት ዝም ብለዋል፡፡ አንድ በቅርቡ ያገኘኋት በቅርብ የማውቃት ልጅ ለምን ወደ ሀገር እንደማትመለስ ስጠይቃት አሁን የምትስራበት መሰሪያ ቤት አልተመቻትም፣ ከዚያ ወጥታ ሌላ ተመሳሳይ ቦታ ለመግባት ደግሞ አሁን ባለው ፖሊስ ሰራተኛ መቀነስ እንጂ መጨመር የብዙ መንግሰታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፕሮግራም አካል አይደለም፡፡ ሰለዚህ አሁን ከምትኖርበት የባሰ ኑሮ ለመኖር ፈቃደኛ ስላልሆነች፤ “የሀገር ፍቅር የትም አይሄድም ነፃነት እና የስራ ዕድል ባለበት ብቆይ ይሻላል” ነው ያለችኝ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪ በያዘችበት ሙያ ስራ ባታገኝም፤ አሁን የምትሰራው ስራ እንደተመቻት አጫውታኛለች፡፡ ይህ እንግዲህ አወጅ ቁጥር 621/2001 ያስገኘው ድል ነው፡፡ ይህችን ልጅ በፍፁም ህገወጥ ደላላ አላሳሳታትም፡፡ እርሷን እና መስሎቿን ያሳሳትው የመነግሰት የተሳሳተ የፖሊሲ አቅጣጫ ነው፡፡ የስራ ዋስትናን ማረጋገጥ የማይችል መንግስት ትክክለኛ የህዝብ ድምፅ የሚቆጠርበት የፖለቲካ ምዕዳር ቢኖር እንኳን ለተከታታይ አራት አይደለም አንድ ተጨማሪ ዙር ምርጫ ማሸነፍ የሚችልበት ዕድል አይሰጠውም፡፡ አሁንም መንግሰት ከጊዚያዊ የስልጣን ጥቅምና ፍላጎት ይልቅ ለዘላቂ ሀገራዊ ጥቅም ሲባል በዚህ ምክንያት ሀገር ጥለው የሚሰደዱትን ዜጎች ለመታደግ ይህን አዋጅ ሊያሻሽለው ይገባል፡፡ መንግሰታዊ ያልሆኑ ተቋማትም እሺ እያሉ ነፃነትን ሸጦ ከመኖር በቃን ብለው ድርጅት በመዝጋት ጭምር ተቃውሞ ሊያሰሙ ይገባል፡፡ ካላጎነበሳችሁ አትጫኑም ነው ያለው ማርቲን ሉተር ኪንግ፡፡
በሀገራችን የባለሞያ ስደት ልላው ምክንያት በቂ ክፍያ አለማግኘት እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዚህ ምክንያት ከሚሰደዱት ዜጎች አብዛኞቹ የህክምና ባለሞያዎች እንደሆኑ ቢታወቅም በሌሎች መስኮቸም ይህ ችግር ጎልቶ ይታያል፡፡ እነዚህንም ዜጎች መንግሰት እንደሚለው ህገወጥ ደላሎች ያሳሳታቸው ሳይሆኑ መንግስት በሚከተለው ፖሊሲ ምክንያት በሞያቸው የድካማቸውን ያህል ስለማያገኙ፣ እንዲሁም በያዙት ሙያ በሌላ ቦታ የተሻለ ዕድል ስለሚያገኙ ጭምር ነው፡፡ ዘወትር የእኛ ሀገር የባለስልጣናት ደሞዝ ትንሽ ሰለሆነ እውነት የሚመስለው ብዙ ሰው አለ፡፡ ባለስልጣኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የሚያገኙት ደሞዝ (እዚህ አካባቢ ወ/ሮ አዜብ ትዝ እንደምትላችሁ ገመትኩ) በእርግጥ ትንሽ ነው፡፡ ደሞዝ የሚባለው ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በተለያየ መንገድ የሚያገኙት ምንዳ ግን በጣም ብዙ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምሳሌ በቦርድ ሰብሳቢነት እና በውጭ ጉዞ የሚያገኙትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በውጭ ሄዶ መታከም፣ ነዳጅ፣ የመኖሪያ ቤት እና ሌሎች ብዙ ጥቅማ ጥቅሞችንም ማንሳት ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር አንድ ባለሞያ ይህ ዕድል ሳይኖረው በወር ደሞዝ እንዲኖር ሲጠየቅ ጥያቄው የሀገር ፍቅር ሳይሆን የምንኩስና ይሆን እና ስደት አንድ አማራጭ ይሆናል፡፡ ከፍተኛ ሀብት ፈሶባቸው የሰለጠኑ ባለሞያዎች የተወሰነ የማጣሪያ ፈተና በማለፍ ብቻ ሌሎች ሀገሮችን ማገልገል አማራጭ እየሆነ ነው፡፡ አንድ በጥቁር አንበሳ የሚሰራ ሀኪም የነገረኝ ከካርድ ብቻ የሚሰበሰበው ገንዘብ ለሀኪሞች ደሞዝ ቢመደብ ሀኪሞች በደሞዝ ማነስ ምክንያት ከመልቀቅ ይድናሉ ነው የሚለው፡፡ በእውነት ለመናገር በየጤና ተቋሙ የሚመደቡ ካድሬዎች የሚፈጥሩት ጫና በዝቅተኛ ደሞዝ መቋቋም ግዴታ አይደለም፡፡
በነፃነት ለመስራት ያለመቻል በሀገራችን በመንግሰት መስሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን በግል ተቋምም ቢሆን ዜጎች በነፃነት የሚሰሩበት የስራ ድባብ ባለመኖሩ አማራጭ ያለው ሁሉ ከሀገር ተሰዶ መኖርን አማራጭ ካደረገ ውሎ ሰንብቶዋል፡፡ ለኢህአዴግ ዳኝነት ቢሆን ህክምና ወይም ምሕንድስና አብዮታዊ ዲሞክራሲ አመለካከት ካልገባው ትርጉም ያለው ዕውቀት አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ለኢህአዴግ አድረናል ብለው የነበሩ በአጋጣሚ ሁሉ የውጭ ሀገር ዕድል ሲያገኙ እየተንጠባጠቡ የሚቀሩት፡፡ በነገራችን ላይ በተደጋጋሚ ውጭ የሚመላለሱ እና ስልጣን ላይ ያሉ የገዢው ፓርቲ አባላት በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር አንድም ልጅ በቤታቸው የለም፡፡ ልጆቻቸው በሙሉ ውጭ ሀገር ላይመለሱ ሄደዋል፡፡ ይህ የባለስልጣኑ የነፃነት እጦት መገለጫ ነው፡፡ አንድ ቀን ምን እንደሚመጣ ያለማወቅ፡፡ ሁሌ በሀገራችን ይመጣል እያሉ የሚያሰቡት ሟርት ከመጣ ልጆቻቸውን እንዳይነካ በማሰብ የተደረገ ነው፡፡ አሁን በልማት ልናስመነድገው ነው የሚሉት ሀገር ለእነርሱ ልጆች ሳይሆን ለድሆች ልጆች ነው፡፡ ይህ በእውነት ደግነት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ድካም ለሰው ልጅ ብሎ ስለሆነ፡፡ እኔ የምር የምላችሁ እነዚህ ባለስልጣናት በህይወት እያሉ ልጆቻቸው እንደሚያዝኑባቸው ጥርጥር የለኝም፡፡ የመንግሰቱ ኃይለማሪያም ልጆች ከሀገር ተሰደው በመኖራቸው ደስተኞች ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ አላስብም፡፡ የማንም ባለስልጣን ልጅ ሀገሩን የሚናፍቅ እንዲሆን እኔ ፍላጎት የለኝም፡፡ ባለሀገር ልጆች እንዲኖሩን ሁላችንም ልጆቻችንን ለስደት ሳይሆን በሀገራችን በሚፈጠር ሀገራዊ ዕርቅ በነፃነት ሀገራቸው እንዲኖሩ ማበረታታ ያለብን ይመስለኛል፡፡ እባካችሁ ለንግግር እና ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ጊዜ እንመድብ፤ ግንብና ግንባታ ይደረስበታል፡፡ “የሰላም እጆች ይዘርጉ የአዲስ ዓመት መልዕክቴ ነው”፡፡ የሶሪያ ዲሞክራሲና ሠላም ዕጦት ግንቡን ሁሉ ነው የበላው፣ እየበላውም ያለው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ሀገር ለቆ ለመውጣት ብቻ ሳይሆን ለመግባት ፍላጎት ያለቸው እጅግ ብዙ ዜጎች አሉዋት፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል አሁን ያለው መንግስት እነዚህ በአንድ ወይም በሌላ መልክ ከሀገር ወጥተው የነበሩ ዜጎች (ዜግነትም ቀይረውም ቢሆን) አሁን እንዲመጡ የሚፈልገው ኪሳቸውን በዶላር ሞልተው ነፃነት ሲፈልጉ ደግሞ እዛው በለመዱበት ብቻ የሚል አቋም ይዞ ነው፡፡ ነፃነት በለመዱበት ሀገር ሆነውም ቢሆን ግን ገዢውን ፓርቲ በነፃነት መተቸት አይቻልም ከእነርሱ የሚጠበቀው የሚጠይቀውን ገንዘብ ሲጠየቁ መስጠት ብቻ ነው፡፡ የማያምኑበት ፖሊሲ እንዲፈፀም የእነርሱ ገንዘብ ማዋጣት ግድ ብቻ ሳይሆን ካላዋጡ ፀረ ልማት እና ለሀገር ጠላቶች የሚል ቅፅል ስም ሀቃቸው ይመስላል፡፡
በሰለጠኑበት ሙያ ለማገልገል የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ያለመኖር አንዱ ነው፡፡ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሰለጠኑበት ሞያ አገልግሎት መስጠት ቢፈልጉ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም በቀጥታ የሚጠየቅ ሳይሆን የፈለጉ ሳይንቲስት ቢሆን መንግስትን መቃወም አይቻልም፡፡ ሞያቸውን ለሀገር ካለው ፋይዳ አንፃር ሳይሆን የሚመዘነው ለገዢው ፓርቲ ካለው የፕሮፓጋንዳ ጠቀሜታ አንፃር ነው፡፡ አንድ አንድ ባለሞያዎች ከዚህ አንፃር ትንሽ ቀደዳ ሳይኖር አይቀርም ብለው ወደ ሀገር ሲመጡ የመጀመሪያ ሰለባ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ወይም ኢቢኤስ ለሚባል የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው (ይህ ጣቢያ በኢትዮጵያ የብሮድካስት ህግ መሰረት ህገ ወጥ ነው)፡፡ እነዚህ ዜጎች መስጠት የሚፈልጉትን ከመሰጠታቸው በተጨማሪ ገና እንደገቡ በሚከቧቸው አጫፋሪዎች ታጅበው ስለ ሀገሪቱ ዕድገት፣ ሰለ አለው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ወዘተ ዲስኩር እንዲሰጡ በማድረግ ቅርቃር ውስጥ ይከቷቸዋል፡፡ ለዚህ ሁነኛ ምሳሌ የሚሆነው ኤርሚያስ አመልጋ ይመስለኛል፡፡ ሌሎችም ብዙ አሉ፡፡
አሁን በሀገራችን ያለውን ሁኔታ በተግባር ለመፈተን ብለው የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የኤኮኖሚ ምዕዳሩም ጠባብ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን በፍፁም እንደማያንቀሳቅስ ተረድተው ከጫወታ የወጡትን ዜጎች ቤቱ ይቁጠራቸው በማለት የሚታለፍ አይደለም፡፡ እነዚህ ዜጎች በውጭ ደክመው ያገኙት ገንዘብ እንደዋዛ ከስረው ከጫወታ ሲወጡ ሌሎች መምጣት ለሚፈልጉት ምን መልዕክት እንዳለው መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ይህን ፅሁፍ ስፅፍ ኤርሚያስ አመልጋ ወደ ሀገር የመኖሪያ ፈቃድ መልሶ ሲመጣ እና ዛሬ ምን እንደሚሰማው ጥያቄ ማቅረብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያሉ ዜጎች በደረሰባቸው ጉዳት የኤርሚያስን ስም መስማት የሚያስጠላቸው ቢሆንም ይህ ለምን ሆነ ብለው ከስሜት በወጣ እርጋታ ሊያስቡት እንደሚገባ ይሰማኛል፡፡ የኦላንድ ካር ባለቤት የነበረው ኢንጂነር ታደሰም ቢሆን ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ እሲኪ ድምፃችሁን አሰሙና መንግሰት ምን ደገፋችሁ ምንስ አደረጋችሁ፡፡ እንግዲ የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም ይባል የለ፡፡
ደቡቡ ሱዳን የምትባል አዲስ ጎረቤታችን ብዙ ኢትዮጵያዊያ ለስራ እንደሚሄዱ አውቃለሁ፡፡ አዲሷ ሀገር እንኳን አሁን ኢትዮጵያዊያ ወደ ሀገሯ ሲገቡ እንደማይቀሩ ለማረጋገጥ የባንክ አካውንት መጠየቅ ጀምራለች፡፡ እንደ አጋጣሚ እኔም ሄጄ ይህችን ጎስቋላ ሀገር አይቻታለሁ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያዊያ እዚህች ሀገር ለምን ተሰደው ይሄዳሉ? ለሚለው ጥያቄ ሁሌ የምሰጠው መልስ ምንም ነገር ስለሌለ ሁሉ ነገር ስራ ነው በማለት ነው፡፡ ብዙ ትርፍ በአጭር ጊዜ ለማግኘት የፈለገ ከነስጋቱ ሄዶ በአጭር ጊዜ ሊከብር ይችላል፡፡ ይህ በኢህአዴግ ሰፈር “ኪራይ ሰብሰቢ” ያሰብላልና ማንም ብቅ አይልም፡፡
ሌሎች ሀገሮችን በተለይ አሜሪካን እና አውሮፓን ሳይ ቅናት ያድርብኛል ብዙ ስራ እንደሚቀረን ይስማኛል፡፡ በተነፃፃሪም ያለው ነፃነትና ዕድል ብዙ ሰው ሊያማልል እንደሚችል ይገባኛል፡፡ በተለይ ብራዚሊያ የምትባል ከተማ እና ብራዚል የሚባል ሀገር ካየሁ በኋላ ኢህአዴግ 22 ዓመት እንዳባከነ እና የብራዚሊያን ያህል 5 በመቶ እንዳልሰራ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ብራዚሊያ የምትባለው የብራዚል ዋና ከተማ ከተመሰረተች ከ50 ዓመት ብዙ አትዘልም፡፡ ኢህአዴግ ባለፉት 22 ዓመት ግማሹን መስራት ይኖርበት ነበር፡፡ ለዚህም በውጭ የሚኖረ ኢትዮጵያዊያን እውቀትና ገንዘብ ብዙ ሚና ሊኖረው ይችል ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ ማስተባበር የሚችል የፖለቲካ ሰርዓት መዘርጋት ቢቻል፡፡ በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዝዳን ባራክ ኦባማ ብራዚልን እንዲህ ብለው ገልፀዋታል “ከአንባገነን ስርዓት፣ በሰላም ወደ ዲሞክራቲክ ስርዓት የተሸጋገረች” እውነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግሰት በተወሰነ ማሻሻያ የብራዚል ዓይነት ዲሞክራሲ ሊያመጣ እንደሚችል እኔም ይሰማኛል፡፡ የብራዚል ህገ መንግሰት እንደ እኛው ህገ መንግሰት ፓርላሜንተሪ ነበር፡፡ መሪያቸውን በቀጥታ አይመርጡም ነበር፡፡ ህገ መንግስቱን አሻሽለው ብራዚላዊያን ዛሬ ማን እንደሚመራቸው በቀጥታ ይመርጣሉ፡፡ እኛም ሲናፍቀን ይኖራል ማለት አይደለም፡፡ አንድ ቀን ዘሩ/ጎሳው ማን ነው? ሳንል ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ባለው ራዕይ መሪያችንን እንመርጣለን፡፡ ተሰፋ አለኝ፡፡
የተነሳሁበት ሀገር ለቆ የመሰደድ ምንጭ የሚያማልል ነፃነትና ዕድል ያለባቸው የአሜሪካና አውሮፓ ከተሞች ብቻ ሳይሆኑ ጎሰቋላዋ ደቡብ ሱዳን ጭምር ነች እያልኩ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በዚህም በዚያም ሀገራቸው ስትገፋቸው ለምቾት ብቻ ሳይሆን ችግርም ለመጋፈጥ በመወሰኝ በረሃና ውቅያኖስ አቋርጠው ይሰደዳሉ፡፡ መንግሰት ግን የችግሩ ምንጭ ህገ ወጥ ደላሎች ናቸው እያለ ትክክለኛ መፍተሔ ለመሻት ዝግጁ የሆነ አይመስልም፡፡ አሁንም ችግሩን ከስሩ ማየት ተገቢ ነው የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው ጊዜ ወስደን ሃሳባችንን የምናካፍለው፡፡
አንድ እናት ለፆም መፈሰጊያ ምግብ እያዘገጁ ሳለ መፈሰጊያ ሠዓት ሳይደርስ ጨው ለመቅመስ ብለው ቀመሱ፣ ፆም ሲያዝም እንዲሁ የተረፈው እንዳይደፋ ብለው ፆም ገደፉ፡፡ ደግነቱ ይህን ለንስሀ አባታቸው በሀቅ ሲናገሩ አንቺ ሴት ፆሙን እንዳይገባ እንዳይወጣ ከለከልሽው አሏቸው ይባላል፡፡ የእኛም መንግሰት ዜጎች በሀገር እንዳይቆዮ እና ወደ ሀገር እንዳይመለሱ ተግቶ እየሰራ ነው፡፡ ችግሩ ይህን ግልፅ አድርጎ የሚነግረው የንሰሃ አባት ያጣ ይመስለኛል፡፡ በእኔ እምነት የዚህ ድርጊት ጥቅም ጊዚያዊ የስልጣን ፍላጎት ብሎም ለግል ደህንንት ካለ ሰጋት ብቻ የሚመነጭ ነው፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር (እርሳቸው ከልባቸው ከሆነ የአሁኖቹም ሌጋሲ ማሰቀጠል ከፈለጉ) ይሉ እንደ ነበረው ሀገር ማለት ሰዉ እንጂ ጋራና ሽንተረር ብቻ አይደለም፡፡ ባለሀገር ሊሆን የሚገባውን ትውልድ እያባረሩ (የእራሳቸውን ልጆች ጨምሮ)፣ ሌሎች ያባረሯቸውም እንዳይገቡ በሩን ጥርቅም አርገው ዘግተው ሀገር ማለት ሰው ነው የሚለው አይገባኝም፡፡ በቅርቡ እንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ በመብራት ሀይል አዳራሽ በጠራው የህዝብዊ ስብሰባ ላይ ሀብታሙ አያሌው የሚባል ወጣት “ሀገር ማለት ልጄ” የሚል የአንድ እውቅ ገጣሚ ግጥም በሰሜት አንብቦ አስለቅሶናል፡፡ ሀገር ማለት ልጄ ለልጆች የሚተላለፍ ታሪክ ያለው ሲሆን ነው ልጄ፡፡
በሀገራችን በነፃነት ለመስራት ያለመቻል ያቀረበልን አማራጭ ከገዢው ፓርቲ ጋር ተናንቆ ለውጥ እንዲያመጣ መግፋት ወይም ሀገር ለቆ የመስራት ነፃነት እና ዕድል ወደአለበት መሰደድ ነው፡፡ ምርጫው የግል ቢሆንም መንግሰት ግን ዜጎች በዚህን ያህል ደረጃ ለስደት ሲዘጋጁ አሳዳጅ ሆኖ መገኘቱ ሊያሳስበው እና መፍትሔ ሊፈልግለት ይገባል፡፡ ይህ በምንም መመዘኛ “የኒዎሊብራል”፣ የኪራይ ሰብሰቢ፣ ወይም የህገ ወጥ ደላሎች ስራ አይደለም፡፡ መንግሰት የሚከተለው የልማት አቅጣጫ ዜጎችን የሚያገል እና የፓርቲ ደጋፊዎችና ጥቂት የሚባሉ ለገዢው ፓርቲ ለማጎብደድ የቆረጦ ዜጎች ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሰለሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ የሚሰራባት ሀገር ነች፡፡ እንደ ደቡብ ሱዳን ባንሆንም ምንም ከሚባለው ብዙ ከፍ የማንል ሁሉ ነገር ሰራ ሊሆን የሚችልባት ሀገር ነች፡፡ ይህችን ሀገር በጋራ ለማልማት መነሳት ይኖርብናል፡፡ ይህ የፖለቲካ ሹመት ጥያቄ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች ሳይሸማቀቁ መሪዎቻቸውን የሚመርጡበት የፖለቲካ ምዕዳር መፍጠር ብቻ ነው፡፡ ለዚህም መተማመን እና ሀገራዊ መግባባት ማሰፈን ይቅር ባይነት በሁሉም በኩል የግድ ይላል፡፡
ይህ ካልሆነ ግን ወደፊት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በውጭ የሚኖሩ የነበሩ በእደሜያቸው የመጨረሻ ዘመንም ቢሆን በሀገራቸው ለመኖረ የቆረጡ እንዲሁም የትም መሄጃ አጥተው በሀገር የቀሩ የሰድተኛ ወጣቶች ወላጆች ሁሉም የሚያመርቱ ሳይሆን ጡረተኞች ሀገር እንዳትሆን ሰጋት አለኝ፡፡ ይህ ከስጋትም ያለፈ እውነት ነው፡፡ አንድ ዘመዴ ያለችኝ እዚህ ጋ መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ “ምርታማ ዕድሜን ውጭ አሰለፉ ለጡረታ ሀገር ከመሄድ የከፋ በደል የለም ነው” ያለችው በበዳይነት ሰሜት፡፡
ቸር ይግጠመን አዲስ ዓመት የመነጋገሪያ የመግባቢያ ዘመን እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችንን መወጣት ይኖርብናል፡፡ ነፃነታችን በእጃችን ይዘን የሌሎችን ነፃነት እናክብር፡፡ ፈጣሪ ይርዳን፡፡ አሜን!!!!
Zehabesha
No comments:
Post a Comment