Wednesday, September 25, 2013

እኔን እሠሩኝ”


ነጋሶ ጊዳዳ
ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በአንድ የታሪክ አጋጣሚ የዚህች አገር ርዕሰ-ብሔር የነበሩ ሰው ናቸው።ቢዘገይም፤ እየተጓዙበት ያለው ያረጀ ባቡር ለእርሳቸው ተስማሚ እንዳልሆነ በመገንዘብ የፖለቲካ አሰላለፋቸውን ቀየሩ። የአቋም ልዩነት በማሳየታቸው ሳቢያም፤ እርሳቸውን በችጋር ለመቅጣትና ለማንበርከክ ታስቦ በወጣ የመቅጫ ህግ ሊያገኟቸው የሚገቡትን እና ሲያገኟቸው የነበሩትን ጥቅማ ጥቅሞችና መብቶቻቸውን ተነፈጉ።(መቼም ኢህአዴግ አንድን ግለሰብ ለመቅጣት ሳይቀር ህግ ሚያወጣ ጎረምሳ መንግስት መሆኑን እናውቃለን)

ዶክተር ነጋሶን በዚያ ደረጃ ማንከራተት የኢትዮጵያን ህዝብ ከመናቅ የመነጨ ድርጊት ለመሆኑ ምንም የሚያጠራጥር ባይሆንም፤ኢትዮጵያን በምታህል ታላቅ አገር ላይ ፕሬዚዳንት የነበሩ ሰው መኖሪያ ቤትና መጓጓዣ መኪና አጥተው ሲንከራተቱ በመታየታቸው የተዋረዱት ገዥዎቹ ራሳቸው እንጂ ዶክተር ነጋሶ እንዳልሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነበር።
ለዚህም ነው ሁሌም ከተጠቃ ጎን መቆምን የሚያውቀውና በህሊና ዳኝነቱ የተመሰገነው የኢትዮጵያ ህዝብ ለዶክተር ነጋሶ ድጋፉን የገለጸላቸው። ዶክተር ነጋሶም የዋዛ አልነበሩምበና ለለመዱት ሊሞዚን ፊት ሳያሳዩት ከምዕመኑ ጋር ታክሲ ለመያዝ መጋፋቱን ለመዱ። የፈርዖን ወይንና ጮማ እንደታሰበው ሳያስገብራቸው እነሆ ላለፉት ዓመታት በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ውስጥ ታቅፈው እየታገሉ ይገኛሉ።
ብዙዎች፤በአንድ ቢሮ ውስጥ ከነበራቸው ውስን ሃላፊነት ሢሰናበቱ፤በሌላ ቦታ በሚያገኙት ከዚያ ዝቅ በሚል ቦታ ለመቀጠርና ዝቅ ብሎ ለመሥራት አቀበት ሲሆንባቸው ተመልክተናል። ከዚህ አንፃር እንደ ኢትዮጵያ ባለች አገር ፕሬዚዳንት ለነበረ ሰው ብዙም ባልጠናከሩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ታቅፎ ለውጥ ለማምጣት ለመታገል መወሰን፤ የሚደንቅ ነው።ዶክተር ነጋሶ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው በህይወታቸው የወሰኗቸውን እነዚህን ውሳኔዎች ሳጤን መጀመሪያ ወደ አእምሮዬ የሚመጣብኝ ጥያቄ ፦”እኚህ ሰው ወትሮውኑም እንዴት የኢህአዴግ አባል ሊሆኑ ቻሉ?” የሚል ነው። እነ አቶ ስዬ አንደነገሩንም ሆነ እኛም አንደምናውቀው ብዙዎቹ የኢህአዴግ አባላት(የዶክተር ነገሶን የኦህዴድ ጓዶች ጨምሮ) ድርጅቱን የተቀላቀሉት ፦” ለእህል ውሃ “ ነው። በዚህና በመሣሰሉት የሙስና ቅሌቶች ካልተበከሉ በጣም ጥቂት ሰዎች አንዱ ነጋሶ ናቸው። ነጋሶ፤ከድርጅታቸው ለመልቀቅ ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ሆነው ለመታገል ድፍረትና በራስ መተማመን ያገኙትም፤ ኢህአዴግ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሊመዝባቸው የሚችል የክስ ካርድ እንደሌለው በማወቃቸውም ነው።
በተለየ መልኩ ፦“ኢህአዴግ ህገ-መንግስቱን ያክብር!” በሚል የተቃውሞ ድምፃቸው የሚታወቁት የቀድሞው ፕሬዚዳንት እና የአሁኑ የ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ዶክተር ነጋሶ እነሆ ዛሬ ፓርቲያቸው ከጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ጋር በተያያዘ የታሰሩባቸውን አባላት ለማስፈታት ወደ ጣቢያ ሄደው ራሳቸው በፖሊስ መታሰራቸውን ሰማን።
ከሳምንታት በፊት አንድነት ፓርቲ ለሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ ሲያሳውቅ -ወቅቱ ከአዲስ ዓመት ጋር ተያይዞ በዓላትና ግርግር የሚበዛበት ስለሆነ ሰልፉን ለመስከረም 19 እንዲያደርግ ፓርቲው ተጠየቀ። አንድነትም የመንግስት ጥያቄ ምክንያታዊ ነው በማለት ተቀብሎ ሰልፉን ለመስከረም 19 ለማድረግ ወሰነ። የፓርቲው አባላት የታሰሩት ለዚህ መንግስትና-አንድነት ፓርቲ ለተስማሙበት ሰልፍ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነው። ዶክተር ነጋሶም አባላቱ ወደታሰሩበት ወደ ሽሮ ሜዳ ፖሊስ ማዘዣ በማምራት ልጆቹ ህጋዊ በመሆናቸው እንዲፈቱ ቢጠይቁም ተቀባይነት ሳያገኙ ይቀራሉ። በመጨረሻም ፦”እነሱ ህገ-ወጥ ናቸው ከተባሉ እንዲቀሰቅሱ የላካቸው እኔ ስለሆንኩ እኔንም እሠሩኝ” አሏቸው። ፖሊሶቹም አሠሯቸው።
ለዶክተር ነጋሶ እና ለታሰሩት ወገኖች ድጋፋችንን የምንሰጠው በማዘን አይደለም። የታሰሩለትን ዓላማ ጠንክረን በማራመድ እንጂ።ከሩቅም ፣ከቅርብም ያለን ነፃነትን የተራብን ኢትዮጵያውያን ሁሉ የዶክተር ነጋሶ ፓርቲ መስከረም 19 ቀን በጠራው ሰልፍ በመሳተፍ፣ መሳተፍ ያልቻልን በሙያችንና በምንችለው መንገድ ከያለንበት ድጋፍ በመስጠት አጋርነታችንን እንግለጽ! “ጉድ ጉድ” ከማለት ባለፈ ጠንክረንና እጅ ለእጅ ተያይዘን ለተግባር እስካልተነሳን ድረስ ሁላችንም በየተራ መታሰራችን ይቀጥላል።

No comments:

Post a Comment