Tuesday, September 24, 2013

አዜብ እና "የሌጋሲው" እምቧይ ካብ

ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ፣ በተለይም ሙሰኝነትን እንዋጋ የሚለውን ዘመቻ (ከልብ ሙሰኝነትን ለመዋጋትም ይሁን በሰበብ ቤት ለማጽዳት) የህወሃት መንግስት ከጀመረበት ሰዓት አንስቶ በተለያየ ማህበራዊ ድህረ ገጾች የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር ባለቤት / አዜብ የሙስና ማጽዳቱ ዘመቻ ሰለባ ከመሆን እንደማያመልጡ ብዙወች ተንብየዋል፡ ታዓማኒ ይሁኑም አይሁኑ መረጃወችን ለማቅረብም ሞክረዋል። 
እኔ እንደሚመስለኝ ግን፡ አሁን በስልጣም ሽሚያ ተፋጥጠው ካሉት ሁለት ወይም ከዛ በላይ የህወሃት አንጃወች የትኛውም ቢሆን /ሮዋን ለመንካት የሚደፍር አይመስለኝም። ማናልባት ከነሱ መሃከል ከፖለቲካ መድረክ ገለል ማለቷን ብዙወቹ እንደሚፈልጉት ግልጽ ቢሆንም፡ የትኛውም አንጃ ግን እሷን ከሙስና ጋር በተገናኘ ውንጀላ ለማሰር ወይም ለመክሰስ ይፈልጋል ብዬ አልገምትም። ለዚህ ድምዳሜዬም ያደረሰኝ ብቸኛ ምክንያት አንድ እና አንድ ብቻ ነው።

ህወሃት ባሁኑ ወቅት እርዮተ አለም የሚባል ጠፍቶበት፣ ምናልባት "አባይን ግድብ" ያለፈ የህብን ቀልብ የሚስብበት ካርታ ያጣበት ወቅት ነው። በአንጀ ተከፋፍለው የሚቦጫጨቁት የህወሃት ክፍሎች የትኛውም ቢሆኑ ተመረኩዘው የቆሙበት "የፖለቲካ" እሴት፡ "የመለስ ሌጋሲ" "የመለስ እራዕይ" እያሉ በሙት መንፈስ ህዝብን ተማጽኖ መንገታገት ነው። እንዲህ ያለው sympathy politics (የህዝብን ሆድ የመብላት እና ሃዘኔታን የመለመን) ፖለቲካ የትድረስ እንደሚያደርስ ፈጣሪ ይወቀው። 
ያም ሆነ ይህ ግን እንዲህ ባለው ወቅት / አዜብን በሙስና መክሰስ ህወሃቶች እንዲህ ተንከባክበው እያለሙት ባለው የመለስ ዜናዊ "ሌጋሲ እና እራዕይ" በሚሉት ተረት ተረት ላይ እጣቢ ከመድፋት አልፎ እስከመጨረሻው ገርስሶ እንደመጣል ይቆጠራል። አዜብ በሙስና ስትወነጀል ህዝቡ "እንዴት ነው እኒያ ባለ እራዕይ ለሃገር ሃሳቢ በሳል መሪ፣ ለሊቱ አልጋቸውን እድሜ ልካቸውን ኑሮዋቸውን የምትጋራቸው ሚስታቸው በዚህ ሁሉ ሙስና ስትዋኝ እንዴት ዝም ብለው ተመለከቱ? የት ነበሩ? መቼም አያውቁም አይሰሙም ማለት አይቻልም። የመከላከያ ሚኒስቴራቸው ስየ አብርሃን በንቅዘት እና ጠቅላይ ሚኒስቴራቸውን ታምራት ላይኔን ስኳር መላስ ወንጅለው ያባረሩ ምነው የእሷን ከመሬት እስከ አየር የተንሰራፋ ሙስና አላስተዋሉ?" ብሎ መጠየቁ አይቀርም።
ህዝብ ይሄን ባደባይ እንዲጠይቅ የሚያበረታታ ውንጀላ በወ/ አዜብ ላይ ቀርቦ ፍርድ ቤት ቆመች ማለት እራሱ መለስ ዜናዊን ከመቃብር ቀስቅሶ በሙስና ወንጅሎ ለፍርድ ከማቅረብ የሚለይ አይመስለኝም። መለስ ተከሰሰ. . . እራዩ የሚለው የእምቧይ ካብ ፈረሰ. . . ህወሃቶች እራቁታቸውን በስልጣን ለመቆየት እየረግተረተሩ በህዝብ ፊት ቆሙ ማለት ይሆናል። ስለሆነም ህወሃቶች አዜብን የፈለገው ያክል ቢጠሉ እና ባይፈልጓት እንኳን "የመለስ እራዕይ" የሚለውን የእምቧይ በጀርባዋ ስለተሸከመች ግፋ ቢል ደገፍ እና አቀፍ አድርጎ ወደ ጓዳ የሚያስገባ እንጂ እሷን ለመገፍተር የሚደፍር እጅ ይኖራቸዋል ብዬ አላስብም።
ሳምሶን ደቻሳ

No comments:

Post a Comment