Monday, September 23, 2013

የኤርትራው ፕሬዝደንት «ኢሳያስ አፈወርቂ » ‹‹ወደቦች አሉን ብለን መናገር አንችልም" አሉ

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ፊታቸውን ለምን ወደ አሰብ ወደብ አዞሩ? 

አንድ ወር አልሞላውም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የሚመሩት ቡድን ነበር ለብዙ ጊዜ በጠላትነት ሲተያዩ የቆዩ ሁለት የሶማሊያ ወገኖች (የፌዴራሉ መንግሥትና የጁባላንድ ግዛት አስተዳደር) የተሳካ እርቅ እንዲፈጥሩ ያደረገው፡፡

ይኼ በአብዛኛው ለአልሸባብ ድጋፍ ይሰጣል ተብሎ የሚታማውና ኪስማዩና ሌሎች እጅግ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሥፍራዎችን የሚያጠቃልለው ግዛት አንድም ቀን የፌዴራሉ መንግሥት አካል ሆኖ አያውቅም፡፡ አንዱ ለሌላው ዕውቅና አይሰጡም ነበር፡፡ አሁን ግን በፌዴሬሽን ቅርፅ በጋራ ለመሥራት አንዱ ለሌላው ዕውቅና እንዲሰጥ ተስማምተዋል፡፡ 
ይህ ዕርቅ ዕውን በሆነበት ዕለት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተርን ጨምሮ ሁለት ጋዜጠኞች አነጋግረዋቸው ነበር፡፡ ለሶማሊያ ሕዝብ ብቻም ሳይሆን ለአካባቢው ሰላም ስምምነቱ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ሲያስረዱ፣ ‹‹ወንድማማች ሕዝቦች ናቸው፡፡ ዕርቅ መፍጠር ብቻ ነው የሚጠቅማቸው፡፡ ከጦርነትና ከጥላቻ አንድም ወገን አይጠቀምም፤›› አሉ፡፡ ታዲያ ጋዜጠኞቹ፣ ‹‹በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል መቼ ነው ሰላም የሚወርደው?›› የሚል ጥያቄ ጣል አደረጉላቸው፡፡ ውይይቱ ቀጥሏል፡፡ በነገራችን ላይ ከሌሎች የኢሕአዴግ መንግሥት ባለሥልጣናት ለየት ባለ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ በሒልተን ሆቴል በአንድ ጥግ ሆነው ሲወያዩ፣ ጋዜጠኞቹ እንደ ጋዜጠኛ እሳቸውም እንደ ባለሥልጣን ሆነው አልነበረም፡፡ ሁለቱንም እጆቻቸውን በጋዜጠኞቹ ትከሻ ላይ ጣል አድርገው በጨዋታ መልክ እንጂ እንደ ባለሥልጣን በፕሮቶኮል ተጨናንቀው አልነበረም፡፡ አጃቢዎቻቸውም ፀባያቸውን በደንብ ያወቁላቸው ይመስላል ከሩቅ ሆነው ከመጠባበቅ ውጪ ምንም የሚያደርጉት ነገር አልነበረም፡፡ ‹‹በሉ በርቱ፣ ደህና ሁኑ›› ብለው ከመለየታቸው በፊት ግን፣ ስለተነሳው የኤርትራ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹አንድ ቀን የማይቀር ነው፡፡ አንድ ሕዝብ አይደለንም? አንድ ነበርን አንድ መሆናችን ሩቅ አይደለም፡፡ የሚጠቅመንም እሱ ብቻ ነው፡፡ የእኔ ተስፋ እሱ ነው፤›› በማለት አብራሩ፡፡ ‹‹ሩቅ ሊሆን ይችላል እንጂ አንድ ቀን ይፈታል፡፡ አይቀርም፡፡ ማን ያውቃል ‘ኢስት አፍሪካ’ የሚባል አገርም እኮ ሊፈጠር ይችላል፡፡ አብሮ ማደግ ነው የሚጠቅመን፡፡ የኢኮኖሚ ትብብሩ ብቻም ሳይሆን የፖለቲካ ‘ኢንተግሬሽኑ’ ሊፈጠር ይችላል፤›› ብለው ፈገግ ካሉ በኋላ ‘አይደለም?’ ካሉ በኋላ መልሰው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ 

‹‹ወደቦች አሉን ብለን መናገር አንችልም››

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኤርትራ ሕዝብ የሚከበረውን የቅዱስ ዮሐንስ በዓል ምክንያት አድርገው በሰጡት ሰፊው ቃለ ምልልሳቸው (ባለፈው ሳምንት ባቀረብነው ዘገባ) ያልነኩት ጉዳይና ያላወሩት ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ በማጠቃለያቸው ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠቀናቀቅ በኋላ የተፈጠረች አገር እንደሆነችና ኤርትራንም በቀጥታ ገዝታ የማታውቅ መሆኗን ባወሩበት አንደበታቸው፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ካልተባበረች የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ጨለማ እንደሆነ የሚያሳይ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ኤርትራ ውስጥ ውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ወደብ፣ አውሮፕላን ማረፊያ ምንም እየፈየደ እንዳልሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ አምነዋል፡፡ ኢትዮጵያን በተመለከተ ደመነፍስ በሚመስል ስሜት ከሰጡት አስተያየት በተጨማሪ፣ ኤርትራ ውስጥ ባሉ እዚህ ግባ የማይባሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና በተለይ ወደቡን በተመለከተ የሰጡት አስተያየት ‹‹ነገሩ ወዴት ነው?›› የሚያስብል ነው፡፡ ከአራቱ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ በአንፃራዊ በራስ መተማመን ጥያቄዎችን ሲያቀርብ የነበረው፣ ‹‹ኤርፖርቶቹና ወደቦቹ በአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ያላቸው ግንባር ቀደም ሚና አይዘነጋም፡፡ እናም በዚህ መሠረት እነዚህን መሠረተ ልማቶች ለማስፋፋት የተሠራ ሥራ አለ ወይ? እንዲሁም በእነዚህ መሠረተ ልማቶች የአካባቢውን ዓለም አቀፋዊ ተፈላጊነት ከፍ ለማድረግ የተያዘ ዕቅድስ አለ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ሌላውም ጋዜጠኛ፣ ‹‹ተጠቃልሎ እንዲመለስልን›› ያለውን ተጨማሪ ጥያቄ ያቀርብና ፕሬዚዳንቱ ምላሻቸውን ይቀጥላሉ፡፡ 

‹‹ወደቦች አሉን ብለን መናገር አንችልም፡፡ እንደዚያም ስለሆነ ከነፃነት ቀን ጀምሮ ያሉን ወደቦች ባፅዕና [ምፅዋ] አሰብ ተሠርተው ስለቆዩን ወይም መጠቀም ስለምንፈልግ ብቻ ሳይሆን፣ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጣቸውና ጠቀሜታቸው ምክንያት ሌላ መፍጠር ስለማይቻል ነው፡፡ እነዚህ የባህር ወደቦች ለመውጪያና ለመግቢያ ብቻ የምንጠቀምባቸው ከሆነ ዋጋ የለውም፡፡ አስፍተንም ካወራን ምናልባት ከአቅማችን በላይ ጉራ እንዳይመስል እንጂ፣ እነዚህ ሁለት የባህር ወደቦች ሳያድጉ የሚሰጡት (አገራዊው አገልግሎትን እርሳው) ይኼንን ጠባብ አድማስና ጥቅም ነው፡፡ የእነዚህ ወደቦችን አስፈላጊነት ከአካባቢያዊ [Regional] ጠቀሜታቸው ነው ማየት ያለብን፡፡ ወደድንም ጠላንም የምርጫ ጉዳይም አይደለም፡፡ የግድ መልማት አለባቸው፤›› አሉ፡፡ 

ፕሬዚዳንቱ በተለይ አሰብ ወደብን በተመለከተ ንግግራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ‹‹ስለ አሰብ ብዙ ነው የሚወራው፡፡ እኔ ይኼንን ፖለቲካዊ ነው የምለው፡፡ አሰብ መልማት ያለባት ወደብ ነች፡፡ ለምን እዚህ ላይ ብዙም መከራከር አልፈልግም፡፡ አሰብ ማደግ አለባት፤›› ሲሉ አነጋገራቸው ቀለል ያለ ይመስል ነበር፡፡ ድንገት ፊታቸውን ቋጥረውና ኮስተር ብለው አንድ አዲስ መልዕክት ማስተላለፍ የፈለጉ ይመስል እጆቻቸውን ግን ዘና አድርገው ወደ ግራና ቀኝ እያወራጩ፣ ‹‹ምናልባት ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ዝምድና፣ የድንበር ግጭት ጦርነት … አሰብ ከለማች የምትሰጠው አገልግሎት ለኢትዮጵያ አይደለም፡፡ የእውነት ወደብ ከሆነች ዓለም አቀፋዊና አካባቢያዊ ጠቀሜታ አላት፡፡ ያንን አገልግሎት ለመስጠት መልማት የምትችለውን ያህል መልማት አለባት፡፡ አንዳንድ የፖለቲካና የፀጥታ ግምቶች አሉ፡፡ እንዲህ ሆነ እንዲህ ነው ተብሎ አጓጉል የምንይዝበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት ነው፡፡ እንዴት ነው የሚተገበረው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ አሁን ያለውን አሰብ ግን ወደብ ብለህ የምታወራለት አይደለም፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የነበረ ወደብ ለአሁኑ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን አይጠቅምም፡፡ ወደብ የለም፡፡ እናም እንኳን ለዓለም አቀፍ ለአገራዊ አገልግሎትም አሁን ወደብ አለን ብለህ የምታወራበት ደረጃ ላይ አይደለም፤›› አሉ፡፡

ፕሬዚዳንቱ አሁን ያለው ወደብ ምንም ዓይነት ጠቀሜታ የለውም ብለው ዝም አላሉም፡፡ መንግሥታቸው የያዘው አዲስ ዕቅድ አለ፡፡ ‹‹ብንችለውም ባንችለውም፣ ጊዜ ብናገኝም ባናገኝም አንድ የተጠና ዕቅድ ሊኖረን ይገባል፡፡ አሁን መናገር እንችላለን፡፡ አንድ የውል ስምምነት አለን ብለን ማውራት እንችላለን፡፡ መቼ ነው የምንተገብረው? አብሮ የሚነሳ የውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት አለ፡፡ በእነሱ ልክ ትልቅ ኤርፖርት ያስፈልጋል፡፡ ወደብ ስለሆነ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ አስመራ ውስጥ ከምንሠራው እዚህ ላይ የምንሠራው ነገር አለ፤›› ብለዋል፡፡ 

በነገራችን ላይ ስለ አውሮፕላን ማረፊያ ቀደም ብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ የአስመራው አውሮፕላን ማረፊያ ምንም ጥቅም የለውም የሚል ምላሽ ሰጥተው፣ በምፅዋ ያለውን ማጠናከር እነደሚያስፈልግ ተናግረው ነበር፡፡ አሁንም በዚህ ላይ በወረቀት ላይ ያለውን ዕቅድ አስመልክተው ሲናገሩ፣ እነዚህን ወደቦች የመሠረተ ልማትና የመርከቦች ማመላለሻ ብቻ ሳይሆን፣ የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ እነዚህን ወደቦች ለመሥራት ያለብንን ውሱንነት እዚህ ላይ አላወራም፡፡ ነገር ግን በዕቅድ ደረጃ ቢያንስ በመካከለኛው ምሥራቅና በምሥራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ መቻል አለብን፡፡ በአገልግሎት ደረጃ ሜዳው ይኼው ፈረሱ ይኼው ብለን ነው የምንሠራው፤›› ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ወደቦቹ አሁን ያሉበትን ሁኔታና እየቀረበ ስላለው ቅሬታም ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሰብ መብራት የለውም፡፡ ብዙ ቅሬታ ነው የሚቀርበው፡፡ ስለዚህ በአጭር ጊዜ መሠራት አለበት ብለን አቅደናል፤›› ብለው የመንገድና የዓሣ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎችና ትላልቅ ኤርፖርቶችን የመሥራት የመንግሥታቸውን ዕቅድም ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሰብና ባፅዕ [ምፅዋ] በዚሁ መንገድ መልማት አለባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ ልትጠቀምበት ትችላለች፡፡ ጂቡቲ ልትጠቀምበት ትችላለች፡፡ ሜዳ ላይ መወዳደር እንችላለን፡፡ እነዚህ ፕሮግራሞች ግን ይዋል ይደር የሚባሉ አይደሉም፤›› ብለው ጉዳዩን በተመለከተ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

አሰብ የግመሎች መዋያ ሆኖ ይሆን?

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአንድ ወቅት የባህር በርን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹የአሰብ ወደብ ኢትዮጵያ ካልተጠቀመችበት የግመሎች መዋያ ከመሆን አያልፍም፤›› ብለው ነበር፡፡ ይህ ከብዙዎች ኢትዮጵያውያን የማይጠፋ ትዝታ ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ንግግር የወደብ አገልግሎት አማራጭ የማየት የገበያ ጉዳይ እንደሆነ ቀላል አድርገውት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት ከገባች ባሉት አሥራዎቹ ዓመታት የጂቡቲን ወደብ እየተጠቀመች ቢሆንም፣ ይኼኛው ወደብ እንደታሰበው አልጋ በአልጋ አልሆነም፡፡ ከአገልግሎቱ ጥራት ማነስ ጀምሮ በየቀኑ እየጨመረ የመጣው የአገልግሎት ክፍያ ለአገሪቱ ዓመታዊ ገቢ ከባድ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ቃለ ምልልስ መረዳት እንደሚቻለው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን አባባል ቃል በቃል መድገም ቢቀራቸው እንጂ፣ በተግባር ግን የአሰብም የምፅዋም ወደብ ምንም ጠቀሜታ እየሰጡ አይደሉም፡፡ ህልውናቸውም አደጋ ላይ ነው፡፡ 

ችግሩ ተጠቃሚ ማጣታቸውም ብቻም አይደለም፡፡ ኢሳያስ እንዳሉት፣ ወደብ ብሎ ለመጥራት የሚያስችል ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት አልተገነባላቸውም፡፡ በነገራችን ላይ እሳቸው በዚሁ ንግግራቸው አስመራን ዝቅ እያደረጉ ፊታቸውን ወደ አሰብ ያዞሩ ሲሆን፣ አገሪቱ የተለመቻቸውን መሠረተ ልማቶችና ፋብሪካዎች በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ምክንያት ከሥራ ውጪ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እናም በመፍትሔነት የጠቆሙት ታዳሽ የንፋስ ኃይል መጠቀምና ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛትን ጭምር ነው፡፡ 

ባለፈው ዓመት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሆኑ ጥቂት ወራት በኋላ ከአልጄዚራ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ከኤርትራ ጋር አስመራ ድረስ በመሄድ መነጋገር እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር፡፡ ይኼው በወቅቱ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ የተብጠለጠለው ንግግራቸው ግን ከአንድ ዓመት በኋላ ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ‹‹ኤርትራ በኢትዮጵያ ተገዝታ አታውቅም›› የሚለው አዲስ ፈሊጥ ከመናገራቸው ውጪ፣ እንደበፊቱ በኢትዮጵያ ላይ ያሰሙት ክስና ውርጅብኝ ቀንሷል፡፡ የለም ማለትም ይቻላል፡፡ በዚሁ ምትክ ቃል በቃል ዕርቅ እፈልጋለሁ ባይሉም፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብር የሚሰኝ ጥሪ እያደረጉ ነው፡፡ ኤርትራ ወደቦችዋን በማልማት ተወዳዳሪ አድርጋ ለኢትዮጵያ በገበያነት ለማቅረብ ዕቅድ ያላት ሲሆን፣ በምላሹ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት ትፈልጋለች፡፡ ይኼው የኢኮኖሚ ትብብር ከእርቅ በፊት ቀድሞ ይመጣል ማለት ዘበት ነው፡፡ ስለዚህ የኢሳያስ የአሁኑ ንግግር ‹‹አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ ዕርቅ መፍጠር እፈልጋለሁ›› ከማለት የሚተናነስ አይደለም፡፡ 

አሰብና ኢትዮጵያዊያን

ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ 22 ዓመቱ ሲሆን፣ የኤርትራም ዕድሜ እኩል ነው፡፡ በሕዝብ ላይ የተሠራ ጥናት ባይኖርም፣ በተለያዩ መንገዶች ሐሳባቸውን የመግለጽ ዕድል ያገኙ ኢትዮጵያውያን ልሂቃን ግን በዚሁ የኤርትራ ፍቺ ላይ ያላቸው ቅሬታ ወሰን የለውም፡፡ በራሳቸው አገላለጽ ከኢትዮጵያ ‹‹ቅኝ ግዛት›› ነፃ ለመውጣት ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ትግል ያካሄዱት ኤርትራውያን ከሕወሓት (በኋላም ከኢሕአዴግ) ጋር በመሆን ወታደራዊውን የደርግ መንግሥት ከሥልጣን ካባረሩ በኋላ ነፃነታቸውን ለማወጅ ብዙም ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ኢሕአዴግ የአራት ኪሎውን ቤተ መንግሥት ከመቆጣጠሩ ጥቂት ቀናት ቀደም ብለው ነበር የአስመራውን ቤተ መንግሥት በቁጥጥራቸው ሥር የዋለው፡፡ አዲሱ የኢሕአዴግ መንግሥት ያደረገው ነገር ቢኖር ያንን በተግባር (ዲፋክቶ) በሕዝባዊ ግንባር ኤርትራ (ሻዕቢያ) የወደቀው ግዛት ይፋዊ (ዲጁረ) ዕውቅና መስጠት ብቻ ነበር፡፡ 

የኤርትራ አዲሱ መንግሥት ለሰላሳ ዓመታት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ መስዋዕትነት ከፍሎ ኤርትራ የምትባል ነፃ ግዛት መፍጠር መቻሉ ብዙም አጠያያቂ አልነበረም፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እስካሁን ለተለያዩ የማንነት ጥያቄዎችና ጥርጣሬ የሚያስነሱ ውሳኔዎች ተደርገው ነበር የተወሰዱት፡፡ በአገር ውስጥም፣ በውጭም በኤርትራ መገንጠል የታመሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ 

ከኤርትራ መገንጠል በላይ ግን ብዙዎቹ ያነሱት ጥያቄ የፍቺውን ሕገወጥነት ነበር፡፡ ይህ አብዛኛዎቹን የ60ዎቹ የደርግ ተቃዋሚዎች ከሻዕቢያ የነጠለ አቋም በኤርትራ ላይ የነበረው ስስ አቋም ሲሆን፣ የአሰብን ወደብ በተመለከተ ደግሞ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን የሚጋሩት የኢትዮጵያ ንብረት ነው የሚል ነው፡፡ የኤርትራን መገንጠል የሚቀበሉ ሳይቀሩ አሰብ ባለቤትነቱ የኤርትራ ነው የሚለውን የማይቀበሉ አሉ፡፡ አሰብ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚም፣ የፖለቲካም እንዲሁም የደኅንነት ጉዳይ ስለሆነም አይደለም፡፡ አሁን ኤርትራ የሚባለው ግዛት አሰብን አያጠቃልልም ነበር የሚል ማከራከሪያ በማቅረብም ጭምር ነው፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት (ጆቤ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመመረቂያ ጽሑፋቸው በዚህ ላይ ሲሆን፣ ይህንን የሕግ መከራከሪያ የሚያቀርብ ሙግት አለው፡፡ በብዙዎችም ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የቅርቡን መድረክ ጨምሮ በኢትዮጵያ ብቅ የሚሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች በሙሉ ጉዳዩን የምርጫ አጀንዳ ማድረጋቸውም ከዚሁ ‹‹ሎጂክ›› የመነጨ ነው፡፡

በኢትዮ ኤርትራ መለያየት በውል እልባት ሳያገኙ በቂ ንግግርም ሳይደረግባቸው በይደር የቆዩ አራት አንኳር ጉዳዮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የዜግነት ጥያቄ፣ በኤርትራ ግዛትና በባህር ስለነበረው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ የሆነው ሀብት፣ የድንበርና የአሰብ ባለቤትነት ጥያቄ ናቸው፡፡ የድንበር ጉዳይ በሁለቱም አገሮች መካከል የነበረው በተግባር ‹‹ኮንፌዴሬሽን›› ሊሰኝ የሚችል ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ውጥንቅጡን ቢያወጣውም፣ በዚያው የ70 ሺሕ ሕይወት የበላ ጦርነት ይነሳል ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡ በዚህም የወደብ ጉዳይ ለሁለተኛ ጊዜ ዝም የተባለ ጥያቄ ነበር፡፡ በእርግጥም ከጦርነቱ በፊት ብቅ ጥልቅ ብሎ ከጦርነቱ በኋላ ሕወሓትን ለመሰንጠቅ ያበቃው ትልቁ አጀንዳ የኤርትራ ጉዳይ እንደነበር ይነገራል፡፡ በኤርትራ ላይ ጠንካራ አቋም ነበረን የሚሉ የሕወሓት ሰዎች ከፖለቲካ ውጪ መሆናቸውን ተከትሎ፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ሲያሟግት የነበረው ከኤርትራ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ጥቅም ድርሻ በሌሎች አጀንዳዎች እንዲዳፈን ተደርጓል፡፡ የሁለቱም አገሮች ግንኙነት በድንበሩ ጦርነትና ውዝግቡ ምክንያት ቢጨልምም፣ የኢትዮጵያውያን የአሰብ የባለቤትነት ጥያቄ ግን ጦርነቱ አጠቃላይ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ‹‹አጠቃላይ ጦርነት ሳይካሄድ አጠቃላይ መፍትሔ አይመጣም›› የሚል አቋም ያላቸው የፖለቲካ ተንታኞች፣ በሁለቱም አገሮች ድንበሩን መሠረት ያደረገው ውዝግብ ለመፍትሔው ይኼው የባህር ወደብ ካልታከለበት ‹‹አጠቃላይ መፍትሔ›› አይሆንም የሚል አቋም አላቸው፡፡

በቅርቡ ካታር ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማስታረቅ ስትንቀሳቀስ የነበረች ሲሆን፣ የአገሪቱ መሪ ወደ አስመራ በመሄድና ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከሁለቱም መሪዎች ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል፡፡ ይህ የዕርቅ ጥረት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ግን በቂ መረጃ አልተገኘም፡፡ 


source reporter by Yemane Nagish.

No comments:

Post a Comment