Wednesday, September 25, 2013

የአልሸባብ የናይሮቢ ጥቃት እየተወገዘ ነው

3
ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2006 ዓ.ም. በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኘው ዝነኛው ዌስትጌት የገበያ ማዕከልን በመውረር፣ 62 ሰዎችን ገድሎ ከ200 በላይ በሚሆኑት ላይ የአካል ጉዳት ያደረሰው አሸባሪው አልሸባብ በዓለም ዙሪያ እየተወገዘ ነው፡፡
የአልሸባብ አረመኔያዊ ድርጊት ሰለባ ለሆኑት ሰዎች ቤተሰቦችና ለኬንያ መንግሥት የሐዘን መግለጫዎች እየጎረፉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አማካይነት የአልሸባብን ጥቃት አውግዟል፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ አልሸባብ በንፁኃን ሰዎች ላይ በፈጸመው አደጋ ማዘናቸውን ገልጸው፣ የጥቃቱን ፈጻሚዎች በቁጥጥር ሥር ለማዋልና ለሕግ ለማቅረብ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር በመሆኗ በፀረ ሽብር ትግሉ ሌሎች የአፍሪካ አገሮችን በማስተባበር ግንባር ቀደም ሚና ለመጫወት ቁርጠኛ መሆኗን አስረድተዋል፡፡ የአልሸባብን የሽብር እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ለማኮላሸት እንዲቻል የሶማሊያን መንግሥት የፀጥታና የደኅንነት መዋቅሮችን ለማጠናከር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፉን በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
የሽብር ጥቃቱ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ከሽብርተኝነት ራሳቸውን ለመከላከል በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥት (ኢጋድ) ግንባር ቀደም መሪነት በተቀናጀ ሁኔታ መምራት እንዳለባቸው አመላካች መሆኑን ዶ/ር ቴድሮስ አስታውቀዋል፡፡
ኢጋድ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ በዌስትጌት የገበያ ማዕከል በሽብርተኞች በደረሰው ጥቃት ማዘኑን ገልጾ፣ ለኬንያ መንግሥት፣ ሕዝብና የአደጋው ሰለባ ለሆኑ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝቷል፡፡ ድርጊቱንም አውግዟል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን በበኩላቸው፣ በናይሮቢ የተፈጸመው የሽብር ጥቃት እጅግ አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡ ድርጊቱ አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ ሊወገዝ የሚገባው ነው ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በናይሮቢ በተፈጸመው የአሸባሪዎች ጥቃት ለሞቱትና ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች፣ መንግሥትና ሕዝብ መፅናናትን ተመኝተው፣ መንግሥታቸው አሸባሪዎችን ለሕግ ለማቅረብ ከኬንያ መንግሥት ጎን እንደሚሰለፍ አስታውቀዋል፡፡ በኬንያና በአሜሪካ መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት በማስታወስ ሽብርተኞችን ለማንበርከክ አሜሪካ ድጋፏን ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊሊያም ሔግ መንግሥታቸው በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኘውን አሸባሪ ድርጅት አልሸባብን ከኬንያ ጎን ሆኖ ይፋለማል ብለዋል፡፡ ድርጊቱንም አረመኔያዊ በማለት ገልጸውታል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የአልሸባብን ድርጊት አውግዞ ከኬንያ ሕዝብና መንግሥት ጎን እንደሚቆም አረጋግጧል፡፡ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትናያሁ እንዲሁ ሐዘናቸውን ገልጸው፣ መንግሥታቸው ከኬንያ ጋር በፀረ ሽብር ትግሉ እንደሚተባበር ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካና የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው አሸባሪዎች በተሳተፉበት በዚህ ጥቃት የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችና ፈንጂዎች ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን፣ ሦስት የኬንያ ወታደሮችን ጨምሮ 62 ሰዎች መገደላቸውን ዘግይተው የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ የ18 ወይም የ19 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶቹ አሜሪካዊያን የሶማሊያ ወይም የዓረብ ዝርያ ያላቸው ሲሆኑ፣ እንግሊዛዊቷ ግን ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሽብር ተግባሮች የተሳተፈች መሆኗን የኬንያ ባለሥልጣናት መናገራቸው ተሰምቷል፡፡ ሳማንታ ሊውትዌይት እንደምትባል የተነገረላት እንግሊዛዊት ከዚህ ቀደም የተገደለው ጀርሜይን ሊንድሴይ የተባለ አሸባሪ ሚስት እንደሆነች ተዘግቧል፡፡ ይህች ሴት ከአሜሪካዊያኑ ጋር መገደሏ ተነግሯል፡፡ የእዚህች ሴት ባል እ.ኤ.አ. በ2005 በለንደን የቦምብ ጥቃት ሲያካሂድ የተገደለ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ የአሜሪካና የእንግሊዝ ባለሥልጣናት ስለተጠቀሱት አሸባሪዎች ጉዳይ ምርመራ መጀመራቸው ታውቋል፡፡
ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ የኬንያ ፀጥታ ኃይሎች የዌስትጌት ገበያ ማዕከልን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠራቸውንና በአሸባሪዎቹ የተጠመዱትን ፈንጂዎች ማንሳታቸው በተለያዩ ዘገባዎች ተገልጿል፡፡ ምንም እንኳ የገበያ ማዕከሉን እየተቆጣጠሩ በነበረበት ወቅት ተኩስና ፍንዳታዎች ቢሰሙም፣ ከአራት ቀናት ትንቅንቅ በኋላ ዘመቻው ትናንት ማምሻውን ወደ መጨረሻው እየተቃረበ ነበር ተብሏል፡፡
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚና መሐመድ በአሸባሪዎቹ የታገቱት በሙሉ ነፃ መውጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡ አንድ የኬንያ ፖሊስ ባለሥልጣን ደግሞ በአሸባሪዎች ላይ የተጀመረው ዘመቻ እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል የት እንደደረሱ ያልታወቁ 63 ሰዎች እንደነበሩ ቢገለጽም ዕጣ ፈንታቸው አልታወቀም፡፡ አልሸባብ በትዊተር ድረ ገጹ ታጋቾች በእጁ እንደሚገኙ አስታውቆ፣ በርካታ አስከሬኖች በየቦታው መውደቃቸውን ገልጿል፡፡ የኬንያ ፀጥታ ኃይሎች ግን አንድ ወይም ሁለት አሸባሪዎች በሕይወት ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ዘመቻው እየተጠናቀቀ መሆኑን እየገለጹ ነበር፡፡ ታጋቾችም ሙሉ በሙሉ ነፃ መውጣታቸውንም አስታውቀዋል፡፡ አልሸባብ ማክሰኞ ማምሻውን በትዊተር እንደገለጸው፣ ታጣቂዎቹ ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱንና በተጠናከረ ሁኔታ የገበያ ማዕከሉን ተቆጣጥሯል፡፡
በሌላ በኩል የናይሮቢ የሆስፒታል ምንጮች መሞታቸው ከተረጋገጠው 62 ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች 60 አስከሬኖችን ለመቀበል እየተጠባበቁ እንደነበር ተሰምቷል፡፡ ምናልባትም የደረሱበት ያልታወቁ የተባሉ ሰዎችን አልሸባብ ፈጅቷቸዋል የሚል ግምት አሳድሯል፡፡ መሞታቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ውስጥ ብዙዎቹ ኬንያውያን ሲሆኑ 18 ያህሉ ደግሞ የእንግሊዝ፣ የሆላንድ፣ የፈረንሳይ፣ የአውስትራሊያ፣ የፔሩ፣ የህንድ፣ የስዊዘርላንድ፣ የቻይና፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የኒውዚላንድና የካናዳ ዜጎች ሲገኙበት፣ ታዋቂው የጋና ገጣሚ ፕሮፌሰር ኮፊ አዎኒ መገደላቸው ታውቋል፡፡ አምስት አሜሪካውያን ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል ይገኛሉ፡፡
የኬንያው ጭፍጨፋ በአልሸባብ ቢፈጸምም ከጀርባው ግን ዓለም አቀፍ አሸባሪው አልቃይዳ እንዳለበት መረጋገጡን የኬንያ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡ የአልሸባብና የተባባሪው አልቃይዳ ዓላማ ኬንያ በሶማሊያ ሰላም ለመፍጠር በሚደረገው ትግል አልሸባብን በመደምሰስ ተሳታፊ በመሆኗ ለመቅጣት ነው፡፡ እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ በገበያ ማዕከሉ የተወሰነ ሥፍራ ውስጥ የመሸጉ አሸባሪዎች በእጃቸው ላይ ታጋቾች መኖራቸውን በመግለጻቸው የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል ተብሏል፡፡ የኬንያ ባለሥልጣናት ግን ዘመቻው ወደ መጠናቀቂያው መቃረቡን ገልጸዋል፡፡ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ በገበያ ማዕከሉ ውስጥ የኬንያ የፀጥታ ኃይሎችና አሸባሪዎቹ የተኩስ ልውውጥ እያደረጉ እንደነበር ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
አልሸባብ በናይሮቢ ውስጥ በፈጸመው የጭካኔ ተግባር ምክንያት የኢጋድ አባል አገሮችና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተጠናከረና በተደራጀ ሁኔታ እንዲዘምቱበት እየተነገረ ሲሆን፣ በተለይ ለሰላማቸውና ለደኅንነታቸው በእጅጉ የሚጨነቁት ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ኡጋንዳ ኃይላቸውን አስተባብረው ወሳኝ ዕርምጃ ሊወስዱበት እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡ በአልሸባብ ላይ የሚደረገው ዘመቻም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚቸረውም ይጠበቃል፡፡
Source/www.reporter.com

No comments:

Post a Comment