Tuesday, September 24, 2013

የምንለዉና የምናደርገዉ ባይጣረስ ! – ከትዝብቱ

21 ሰፕተምበር 2013 የግንቦት 7 ሳምንታዊ ርእሰ አንቀጽ በሚል ነሐሴ 25 እና 26 ቀን 2005 በኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር ወያኔበሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ የፈጸመዉን የመብት ጥሰት አስመልክቶ የወጣዉን ጽሑፍና አቶ ተክሌ በጽሁፉ ላይ ያቀረበዉን ትችት አንብቤአለሁ:: ወደ መሰረታዊ ጉዳዩ ከመግባቴ በፊት ግንቦት ሰባትም ሆነ ሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ከትግል ስልት ልዩነት በቀር ለአንድ አላማና ግብ ለሚታገሉ ለሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከበሬታ ሰጥቶ ወቅታዊ የሞራል ድጋፍ መስጠት ተገቢና የሰለጠነ አካሄድ ነዉ የሚል እምነት አለኝ:: ነገር ግን ርእሰ አንቀጹ ከአርእስት አመራረጡ ጀምሮ ሳየዉ ቅንነት የጎደለዉና ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ወይንም የአዛኝ ቅቤ አንጓች አይነት ነገር ሆነብኝ::

አንባቢ ይረዳዉ ዘንድ ርእሱን እንዳለ እነሆ “በሰማያዊ ፓርቲ አባላት በደረሰዉ ወያኔያዊ ጥቃት ተቆጭተናል!!! ወጣቶች መንገዳችሁን እንድትመረምሩ እንመክራለን!!!„
በእኔ እይታ ችግሩ የሚጀምረዉ ከዚሁ ነዉ::
ምክንያቱም፦
አንድ የፖለቲካ ድርጅት አቻ ለሆነ ለአንድ አላማና ግብ ለሚታገል የፈለገዉን የትግል ስልት ይምረጥ ከበሬታ ሊሰጠዉና የትግል ስልት ምርጫዉ የድርጅቶች የዉስጥ ጉዳይ መሆኑን ግንቦት ሰባት የዘነጋው መሰለኝ:: አልዘነጋንም አዉቀን ነዉ ካሉ ደግሞ ድፍረትም ነዉርም ነዉ የሚሆነዉ::
አንድ የፖለቲካ ድርጅት የትግል ስልቱን ሲመርጥ የሀገሪቷን፣ የካባቢዉንና የአለም አቀፍ ነባራዊና ሂልናዊ ሁኔታዎችን አጥንቶና አገናዝቦ የራሱንም አቅም ገምቶ ወደፊት እመሰርታለሁ ለሚለዉ ፍትሀዊ ሰርአት የማያደግም አስተማማኝ አማራጭ መሆኑን አምኖ እንጂ በሌላ የፖለቲካ ድርጅት ምክር ወይንም ጣልቃ ገብነት አይመስለኝም:: በመሆኑም ግንቦት ሰባት በማያገባዉ የገባ ይመስለኛል::
አሁንም ከአርእስቱ ሳልወጣ “ወጣቶች መንገዳችሁን እንድትመረምሩ እንመክራለን!!!„ ይላል በዚህ አገላለጽ G7 ምን መልእክት ለማስተላለፍ እንደፈለገ መቶ በመቶ አዉቃለሁ ባልልም ካጠቃላይ ጽሁፉ ጋር ሳገናዝበዉ ወጣቶች የሚለዉ አገላለጽ ገና ልምድ አላካበታችሁም ወይንም አልበሰላችሁም በመሆኑም ወያኔን የሚመጥን የትግል ስልት ባለመምረጣችሁ ለጥቃት ተጋልጣችኋልና ያንን ትታችሁ እኛን ተቀላቀሉ የሚል ነዉ:: ይሂም ቢሆን ንቀት የተሞላበት ትልቅ ስህተትና እራስን አግዝፎ የማየት ችግር ይመስለኛል:: G7ን በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ዉስጥ የወያኔ ገፍ አንገፍግፎት የወንድ ያለህ እያለ የሚጮህ ስንት ወጣት እያለ ሰማያዊ ፓርቲ በራሱ ጥረት ያሰባሰባቸዉን ወጣቶች ለመጥለፍ ወጥመድ ፍለጋ መኳተኑ አልገባኝም:: እንዲያዉም ከወሬ በዘለለ ወደተግባር ገብተዉ ጠሽ ጠሽ ቢጀምሩ እድሜ ለወያኔ የከፋዉ በጣም ብዙ በመሆኑ አባላትም ሆነ ሰራዊት ለመልመል መኳተን የሚያስፈልጋቸዉ አይመስለኝም::
በጽሁፉ ውስጥ “ያለን ምርጫ ሰላማዊ ትግል ብቻ ነዉ ብሎ የደነገገልን ማነዉ?„ የሚል ጥያቄ ለማን እንደቀረበ ባይታወቅም ተጠይቋል:: እኔ እንደማዉቀዉ አገር ቤት ሰላማዊ የትግል ስልት የመረጡ የፖለቲካ ድርጅቶች በመረጡት ስልት ከመታገል ባሻገር ብቸኛ አማራጭ ነዉ ብለዉ የትጥቅ ትግልን በወያኔ ግፊት እንኳን ለማዉገዝ አልፈለጉም:: እንዲያዉም ጠብመንጃ ያነሱት ባንተ ግፊት እንጂ ጦሪነት ናፋቂ ወይንም ቴረሪስት ሆነዉ አይደሉም ብለዉ ሽንጣቸዉን ገትረዉ ወያኔን ስሞግቱ ነዉ የምንሰማዉ::
በማጠቃለያዉ “ሰላማዊ ትግል ብቻዉን ዉጤት ለማምጣቱ ማረጋገጫ የለም„ ፡ “ ሰላማዊ ትግልና የአመጽ ትግል ዉሀና ዘይት ወይንም እሳትና ጭድ አይደሉም አንዱ ያለ ሌላኛዉ ዋጋ የለዉም„ የሚሉ አገላለጾች ይገኛሉ:: በዚህኛዉ አገላለጽ ሁለቱ የትግል ስልቶች ተጻራሪ ሳይሆኑ ተደጋጋፊ እንደሆኑ ነዉ:: ያ ከሆነ እሰዬሁ ነዉ ምክኒያቱም ዕንቁላላችን ባንድ ቅርጫት አልተከተተምና ነዉ:: ስለሆነም ግንቦት ሰባትን የሚያሰገዉ ነገር የለም ሌላዉ በመረጠዉ ስልት ሲታገል እርሱም በመረጠዉ ታግሎ ዕንቁላል አስቀምጠን ጫጩቶች እናገኛለን ማለት ነዉ::
የሰማያዊ ፓርቲም ሆነ ሌሎች ሰላማዊ ትግል የመረጡት ሁሉም አልጋ በአልጋ ይሆናል ብለዉ አይመስለኝም በተቃራኒው ከትጥቅ ትግል ለየት የሚያደርጋቸዉም የትጥቅ ትግል ጥሎ በመዉደቅ ለዉጥን ለማምጣት ሲታግል ሰላማዊ ታጋዮች ሳይገሉ በመሞት ለዉጥን ለማምጣት መቁረጣቸዉ ነዉ:: ይህንን እዉኔታ የG7 አመራሮች አያዉቁትም የሚል ግንዛቤ የለኝም:: ሆኖም ግን በጽሑፋቸዉ ማጠቃለያ ከደረሰባችሁ ጥቃት ትምህርት በመዉሰድ የስትራቴጂ ለዉጥ ለማድረግ የወሰናችሁ ተቀላቀሉን ማለታቸዉ በጣም አስገርሞኛል::
ሀሳቤን ከማጠቃለሌ በፊት በሕዝባችን መሀል ሆነዉ መከራዉን እየተጋሩ ሳይገድሉ ሞተዉ፤ ሳያቆስሉ ቆስለዉ፤ ሳያደሙ እየደሙ ትግሉን በማካሄድ ላይ ለሚገኙ የሰማያዊና የአንድነት ፓርቲ ያለኝን አድናቆትና አክብሮት እየገለጽኩኝ ለሀገርና ለወገን ጥሩ ራዕ አለን የምትሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ፈጣሪ አምላክ ከግልም ሆነ ከድርጅት ጀብደኝነት አላቋችሁ የምትሉትና የምታደርጉት መጣረሱን አስቁሞ ለድል እንዲያበቃን ምኞቴ ነዉ::
በትግሉ ቀጥተኛ ተሳታፊ ያልሆን ደግሞ ሁሉም ታጋይ መሆን አይችልምና በትግሉ ከተሰማሩት ድርጅቶ ለመረጥነዉ ድጋፋችንን እየቸርን ላልመረጥነዉና ድጋፋችንን ለማንሰጠዉ እንቅፋት ከመሆን ብንታቀብ በራሱ እንደ መደገፍ ነዉና ብናስብበት መልካም ይመስለኛል::
ፈጣሪ አምላክ አገራችንና ሕዝባችንን ይጠብቅልን
ለኛም ልቦና ይስጠን
ትዝብቱ

No comments:

Post a Comment