በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ አስቀድሞ ደራሲ በዓሉ ግርማ በኋላም ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ግጥሞቻቸውን ጽፈው ነበር፡፡ ሌላም የጻፈ ይኖራል፡፡ ነገር ግን እነኝህ የሥነ-ጽሑፍ ሰዎች ግጥሞቻቸውን ሲጽፉ የተቆነጸለ ወይም የተሳሳተ ትርጉም ሊያሰጥ በማያስችል ሁኔታ ግጥሞቻቸውን ባለመጻፋቸው እንደምገምተው እነሱም ሊሉ ባልፈለጉት መንገድ ተተርጉሞ የቅጥረኞች መጠቀሚያ እስከመሆን ድረስ በቃና ሕዝብን ለማደናገሪያ አገለገለ፡፡ ከሕዝቡ ጥቂት የማይባል ወገንም በመወናበድ ይሄንን የተሳሳተ ትርጉም ይዞ ማንጸባረቅ ያዘ፡፡ ይህም መሆኑ ሀገር በሕዝብ ልብ ውስጥ የነበራት ቦታና ትርጉም ከመዛባቱም ባሻገር በወደፊት የሀገር ህልውና ላይ ከባድ አደጋ የጋረጠ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ እናም እንደዜጋ አሳሰበኝና ይሄንን የተሳሳተ ትርጉም ለማረም የሀገርን ትርጉም ሳይቆነጸል ሳይጎነጠል ለማስፈር ተገደድኩና ይህችን ግጥም ጻፍኩ፡፡ ግጥሙ እንዳልኩት የሀገርን ምንነትና ሙሉ ትርጉም ለማስቀመጥ ሲባልና ሁሉም ሰው ሊገባው ሊረዳው በሚችል አገላለጽ ሲገለጽ ትንሽ ሊረዝም ችሏል፡፡ ለዚህ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ በግጥሙ ላይ የተገለጹትን ተግሳጾችንና ስድቦችን ሁሉንም በግጥሙ ላይ ከተወከለው ገጸ ባሕርይ ተውሻለሁ ለራሱ ለባለቤቱ መመለስ ይኖሩባቸዋልና፡፡
ሀገር ማለት:-
አየ የኛ ተርጓሚ ፤ በቃላት ፍች ተራቃቂ
ወግ አሳማሪ ቀማሚ ፤የነገር ብልት ዐዋቂ
ከቃላት ሁሉ የከበደን ፤በሰዋስው ቃል እርባታ
ከምሥጢራት እረቂቁን ፤ሲተረጉሙት ባአንድምታ
ጠሊቅ ሰፊ ጥጥሩን፤ ሲተረተር ሲፈታ
በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀቱ ፤ያለሀፍረት ያለይሉኝታ
ተርጓሚ ነኝ አለና ፤ሞከረና ሊያምታታ
ሀገር ማለት ወንዝ አይደለም ፤ጋራ ሸንተረር ድንበር
ሀገር ማለት ሰዉ ነው ፤ብሎ ነገረን መምህር
ግድ የለኝም አይገባኝም ፤ለወንዙ ጋራው ሸንተረር
እያለ ተረጎመልን ፤አምልጦት ከከንፈር
አንጀትም የበላ መስሎት ፤ልባችንን ሊሰረሥር
አቤት አቤት ማስመሰል ፤አቤት አቤት አለማፈር
ለሕዝብ ሰብአዊ መብቶች፤ እንደሚያስብ በመቆርቆር
እንደሚመኝ እንደሚሰጥ ፤ለዜግነታቸው ክብር
ለማያውቁሽ ታጠኝ አያ ፤ ስንት እያለ የሚያይ አሣር
ያለ ሥራው ባልዋለበት ፤ መብቴን ስላለ ለመኖር
ዜጋነቱን እስኪረግም ፤እስኪጠላም መፈጠር
ለሕዝብ ጥሩ በተመኘ ፤መልካም በሠራ ለሀገር
ከሕዝቡ ዓይኑን የገለጠው ፤ለሀገር ይጠቅም የነበር
ታዲያ እሱ ግድ ከሌለው ፤ይቆራረስ የካሳ ሀገር
ለዚህ ኖሯላ ቀድሞውን ፤ስንት ዋጋ ስንት አሣር
ስንትና ስንት መስዋዕትነት ፤ የተከፈለበትን ምድር
እየገመደልክ ያደልከው ፤ ማንነኝ እኔ ሳትል ሳታፍር
የቃሉ ትርጉም ነው ብለህ ፤ ሊቅ ዐዋቂ መስለህ መምህር
ለማምታታት ማወናበድ፤ተመኝተህ እንድንደነቁር
ቃል በቃላት ሲተረጎም ፤እንዲህ ነው ተብሎ ሲነገር
እራሱን ቃሉን ነው እንጂ ፤በውስጡም ያለውን ምሥጢር
ምኞትን ማውራት አይደለም ፤ከቶም የማይመስል ነገር
ስሕተትህን ልክ ለማድረግ ፤ላለመዋረድ ላለማፈር
በሚገባ ስላወከው ፤ተሳስተህ እንደነበር
በእቃ እቃ ፍልስፍናህ ፤ የትም በሌለ ባልሠለጠነ
እየገመደልክ ማደልህ ፤ መፍትሔያችን እንዳልሆነ
ጊዜ ገልጦ ካስረዳህ ፤እንደመመለስ ወደ ምክር
ስሕተትህን ላለማረም፤ ከስሕተትህ ላለመማር
ሀገር ማለት ወንዝ አይደለም ፤ ጋራ ሸንተረር ድንበር
ብለህ ዐረፍከው አኞ ግትር ፤ የእኛ ዐዋቂ የኛ ምሁር
ምንነበረበት አሁን ፤ ይቅር በሉኝ ማለት ብትደፍር
ይሄው አይደል ድንቁርና ፤ ለራስ የማይበጅ ለሀገር
የከአፈርኩ አይመልሰኝ ፤የደናቁርት ፈሊጥ ቁማር
አንተ የእነሱው ፈላስፋ ፤የእኛው ደንቆሮ ልበ እውር
እንዲያው በሞቴ እባክህ ፤ሙታ ጉዳይህ ካላልከኝ
አንድ ነገር ልጠይቅህ ፤ሳትሸሽ ሳትዋሽ መልስልኝ
ሀገር ማለት ለኔ ሰው ነው ፤ያልክለትን ሰው ህልውና
ያለ መሬቱ እስኪ አሳየኝ፤ እንዲህ እንዲህ ነዋ በልና
አቃፊው ደጋፊው ቀርቶ ፤ማረፊያ መጋቢው ሳይያዝ
በልእኮ እንደምን ሆኖ ነው ፤ሀገር የምንለው አንት ውጉዝ
በላ ተናገር አይጭነቅህ ፤ አይደለም ወይ አፍህ ደኅና
መሠረት አልባ ነው እንዴ ፤ልጆችህ ያሉት ፍልስፍና
ባዶ ቅዠት ነው እንዴ፤የማይጨበጥ ደመና
አየህ የአንተን ዐለማወቅ ፤ድቅድቅ ድውይ ድንቁርና
መልስ አሳጣህ አስፈጠጠህ ፤ይሄ ብቻ ገና ገና
የማይነጣጠሉትን ከቶም፤የነፍስ የሥጋን ዝምድና
ለመነጣጠል ስትሞክር ፤በድን ለማድረግ ሙት መና
ቀን ሲያጋልጥህ አዋረደህ ፤መቼምም አትልም ቀና
የሚገርመው የሚደንቀው ፤ አንተ ባታውቅ ባትረዳ
ለራስህ ምንም አልነበር ፤ለእኛም መትረፉ እንጅ የጎዳ
የአንድ ሀገር የሀገሩም ሕዝብ ፤እጣ ፋንታው ሁሉ እንዳለ
የነበረውም ዋጋ ያለው ፤ሀገርን ከሌላው ያለዐለ
በአንተ እንጭጭ አስተሳሰብ ፤በማይዋጠው ተወዶ
የማማረጥ ዕድል ሳትሰጥ ፤እንዲወድቅ ማድረግህ ተቀዶ
ከሥር ነቅሎ አንጓለለን ፤ሁሉን ነገር አርጎ ባዶ
ገናገና መች ዓየነው ፤አለብን ገና ብዙ ዕዳ
የቀበርክብን ቦምብ በዕያይነት ፤ጊዜ ጠብቆ ሲፈነዳ
ከሸር ክፋት ተንኮልህ ፤መራሩና የበሰና
እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ፤በአህያ ሰብእና
ከህልውናህ ማጣመርህ ፤የሀገርን ህልውና
እንዳንተ አይሆንም እንጅ ፤አምላከ አበው አለና
ጠባብ ዘረኛ ከሆነ ፤ከዚህ ሌላ የጠበቀ
እሱ የዋሕ ነው ተላላ ፤ሥነ ልቡናን ያላወቀ
ሀገር ማለትስ ወገኔ ፤ሳትሸራረፍ ተቆራርጣ
ከጥንቱ ከመሠረቱ ፤ከሊቃውንቱ የመጣ
የሰው ልጅ ብቻ አይደልም፤ ነውም እንጂ ሳይቀር ሣሩ
እንስሳት አራዊት አዕዋፍ ፤ያለው ነገር ሁሉ በምድሩ
ከዳሸን እስከ ዐባይ አዋሽ፤ከዋልያ እስከ ግራሩ
ከዋዕይ ቃጠሎው ዳሎል ፤እስከ ደጋው ብርድ ቁሩ
ያለው ነገር ሁሉ ነው ፤አጥረህ የያዝከው በድንበሩ
ከቶውንም ጆሮ እንዳትሰጥ ፤እንዳትደነቁር በምክሩ
መቆሚያም እንኳን ታጣለህ ፤እንኳን መኖሪያ በኩራት
ሀገር ማለት መሬት አይደል፤እያልክ ቆራርሰህ በመስጠት
ከሀገር ትርጉም ዐቢዩ ፤ባይሆን ኖሮ ምድር መሬት
ሰው ብቻ ቢሆን ኖሮ፤ዘመድ ወዳጁ ያለበት
ተፋቅሮ የሚተሳሰብ ፤ተግባብቶ ያለው በኅብረት
ተነቅለህ ሄደህ ባለህበት ፤ እየተዋከብክ በውርደት
ስደተኛ መጻተኛ ፤እያሉ ስምክን ባልጠሩት
በሀፍረት ባልተሸማቀክ ፤ባላስደፋህ ባይተዋርነት
ልብ አድርግ ወገኔ ስማኝ ፤ሲዘረዘር ሀገር ማለት
ሀገር ማለት ሰንደቅ ናት ፤የቃልኪዳኑ ምልክት
ሀገር ማለት ሃይማኖት ናት ፤በቃሉ የነገረላት
ሀገር ማለት ጥበብ ናት ፤ተራቀው የማይጨርሷት
ሀገር ማለት ዕውቀት ናት ፤ብርሃን የሞላት ፍኖት
ሀገር ማለት ታሪክ ናት፤ማንነትህ የሚታይበት
ሀገር ማለት ቅርስ ናት፤ አሻራህ ቀርጾ ያወጣት
ሀገር ማለት ውርስ ናት፤ጸጋ ሀብት የምታፍስባት
ሀገር ማለት አደራ ናት ፤በእንክብካቤ የምትጠብቃት
ሀገር ማለት እናት ናት፤እጅጉን የምትወዳት
ሀገር ማለት አባት ናት ፤በጣሙን የምትኮራበት
ሀገር ማለት ሚስት ናት ፤ በፍቅሯ የምትሞትላት
ሀገር ማለት ልጅህ ናት ፤ በኃያሉ የምትሳሳላት
ሀገር ማለት ልጅህ ናት ፤ ደጀንነቱ የሆነህ ትምክሕት
ሀገር ማለት ወገን ናት ፤ መጠጊያ የምትሸሽበት
ሀገር ማለት ሕዝብ ናት ፤ብዙውን በአንድ ያዋሐደች ቋት
ሀገር ማለት ወግ ባሕል ናት ፤ ስትኖረው የምትደምቅበት
ሀገር ማለት ዙፋን ናት ፤ሉዓላዊ የሥልጣን ሹመት
ሀገር ማለት ዘውድ ናት ፤ግርማ ሞገስን የምትደፋባት
ሀገር ማለት ማዕረግ ናት ፤ልብ የምትሞላ በሐሴት
ሀገር ማለት ጌጥህ ናት ፤የሚሳሱላት የክት
ሀገር ማለት ክብር ናት ፤ በምንም የማይለውጧት
ሀገር ማለት ኩራት ናት ፤ ደረትህን የምትነፋባት
ሀገር ማለት ጽናት ናት ፤ የማይሠበር የማይወድቅ ቁመት
ሀገር ማለት ጀብድ ናት ፤የሠራት የጀግና ድፍረት
ሀገር ማለት አንድነት ናት ፤መነጣጠሉ የሚያፈራርሳት
ሀገር ማለት ፍቅር ናት ፤መሥዋዕትነት የማይፈሩላት
ሀገር ማለት እፎይታ ናት ፤ ምቾት የሞላት ዕረፍት
ሀገር ማለት ሥጋት ናት ፤የምትነሳ እንቅልፍ ቀን ከሌት
ሀገር ማለት ማተብ ናት ፤የማትፈታ ከአንገት
ሀገር ማለት ሕመም ናት፤ ስቃይዋ ዜማ ማኅሌት
ሀገር ማለት ጤና ናት፤የሕይወት መድኅን መድኃኒት
ሀገር ማለት ምሥጢር ናት፤ገመናን የምትከትባት
ሀገር ማለት ፊደል ናት ፤የሚገለጥባት የውስጥ ስሜት
ሀገር ማለት ሀቅ ናት ፤የልብ የኅሊና ሀብት
ሀገር ማለት ምግብ ናት ፤ሰውነት የምትራባት
ሀገር ማለት ጥማት ናት፤ ሲጠጧት የምትሰጥ ሕይወት
ሀገር ማለት ሥራ ናት ፤የህልውናህ መሠረት
ሀገር ማለት ዋስትና ናት፤ለሁሉም የምትቆምለት
ሀገር ማለት ደስታ ናት፤ የልብ ሰላም ሥምረት
ሀገር ማለት ሐዘን ናት፤የግድ ምንሠዋላት
ሀገር ማለት እርስትህ ናት፤ማርና ወተት የምታልብባት
ሀገር ማለት ጉልትህ ናት፤ሁሉንም የምትሆንባት
ሀገር ማለት ሁሉንም ናት፤የምናውቅ የማናውቀው
ሀብት አዎ ኢትዮጵያ ማለት መሠረት ናት ፤የምድርን ካስማ የተከለባት
ኢትዮጵያ ማለት የትም የሚያዩዋት ጉልላት ናት ፤የዓለም ጣራ ጠፈራት
ኢትዮጵያ ማለት የገባርት እርሻ ናት ፤የምትመግብ ዘለለት
ኢትዮጵያ ማለት የካህናቱ ጸሎት ናት ፤ከአምላክ የምታወርድ ምሕረት
ኢትዮጵያ ማለት የወታደሩ ትጥቅ ናት ፤የጠላት መቅሰፍት ወመዓት
ኢትዮጵያ ማለት የከያኔያን ጥበብ ናት ፤ዘወትር የሚቀኛት በስሜት
ኢትዮጵያ ማለት የመምህራን ሀሁ ናት፤ቁልፍ ምሥጢሩ ለዕውቀት
ኢትዮጵያ ማለት የነጋዴያን ንብረት ናት ፤እያደር የምትበረክት
ኢትዮጵያ ማለት የጋዜጠኞች እውነት ናት ፤ለክፉው የምትመር ሀሞት
ኢትዮጵያ ማለት የመሐንዲሶች ትልም ናት ፤የምትጠቅስ ሰማየ ሰማያት
ኢትዮጵያ ማለት የአብራሪዎች ዓለም ናት ፤የማትለየው በየሄደበት
ኢትዮጵያ ማለት የዳኞች ፍትሕ ናት ፤ሚዛኑ የሚፈርድበት
ኢትዮጵያ ማለት የሐኪሞቹ መድኃኒት ናት ፤ፈውሳ የምትሰጥ ሕይወት
ኢትዮጵያ ማለት የስፖርተኞቹ ጥረት ናት ፤ድል የምታቀዳጅ ጽናት
ኢትዮጵያ ማለት የሾፌሮቹ መንገድ ናት ፤ቢጓዝ የማይጨርሳት
ኢትዮጵያ ማለት የአናጢዎቹ መለኪያ ናት ፤የምትመጥን እንደ ፍላጎት
ኢትዮጵያ ማለት የግንበኞቹ ውኃልክ ናት ፤የምታስቀምጥ ያለመዛባት
ኢትዮጵያ ማለት የቀጥቃጮቹ እሳት ናት ፤አቅልጣ የምትቀርጽ ብረት
ኢትዮጵያ ማለት የወዛደሮቹ ጋዕር ናት ፤ነጭ ላቡ የምትወርድ በአንገት
ኢትዮጵያ ማለት የኮረዶቹ ሽልም ሞሰብ ናት ፤ነገዶች የተሠፉባት በአንድነት
ኢትዮጵያ ማለት የቆራጥ መሪ ዓላማ ናት ፤ተሳክቶ ሊያያት የሚሻት
ኢትዮጵያ ማለት የመሀይማን ዕውቀት ናት ፤ከምሁራኑም የሚልቁባት
ኢትዮጵያ ማለት ንግሥት ናት ፤ ተፈጥሮ የገበረላት
ኢትዮጵያ ማለት ጥበብ ናት ፤ ሥነ-ኪን ያረገደላት
ኢትዮጵያ ማለት መቅደስ ናት ፤ አማልክት የሚቀናኑባት
ኢትዮጵያ ማለት የሁሉም ሁለ ነገር ናት ፤ለሁሉም የሆነች ሕይወት
አይ አይ ተሳሳትኩ መሰለኝ ፤የለም አይደለም ከእነዚህ ፤ከእነዚህም ሁሉ በላይ ናት
በመሆኗም ነው ልጆቿ ፤ እነዚህን ሁሉ ጣል አርገው ፤ትተው ቁጭ አርገው የሞቱላት
በል እንዳትሞኝ ወገኔ፤ በቅጥረኛ ባንዳ ሰበካ
ነቅተህ ጠብቅ ድንበርህን፤እንኳን መስጠት አታስነካ
እንደአባት እናትህ ሳሳላት፤ዘራፍ በልላት ጦር እንካ
የነሱን አጥር አስከብር፤አደራቸውን እንዳትበላ
ደም አጥንታቸው እዚያ አለ ፤ዋ ይወቅስሃል በኋላ
ለዚህ አማላጅ የለውም ፤አለበት ጽኑ መሐላ
ለህልውናዋ ሙትላት፤ ለነፍስህ አላት ከለላ
እስካሁን እንደነበረች ፤ለዘለዓለምም ያለ ዲካ
አንተ ሞተህ ሕያው አርጋት፤እንዳትነጠቅ ተማርካ
ለመኖር ለባዕድ ሰጥተሀት፤ ያንተም ሳትሆን ከምትቀር
ሞተህ ለልጅህ አድርጋት ፤በሞት ወርሰሃት ተከበር
በልጅ በዘመድ ትኖራለህ፤ለዘለዓለም ቀርጸህ ዱካ
ተጠብቃ ትኖራለች፤ያለችግር ያለ ሳንካ
ደም አጥንትህ ያስከብራት፤ትውልድም ባንተ ይመካ
ያንተነቷ እንዲጸና ፤ምኞት ሕልምህ እንዲሳካ
ደም አጥንትህ ያስከብራት ፤ ትውልድም በአንተ ይመካ
የአንተነቷ እንዲጸና ፤ ምኞት ሕልምህ እንዲሳካ!
amsalugkidan@gmail.com
No comments:
Post a Comment