Thursday, September 26, 2013

”አልሻባብነት” በተዋህዶ !

widemodern_westgate08_130923620x413
ሰሞኑን በ አሜሪካዉ የዜና ማሰራጫ በCNN ዜና የተከታተልነዉ በኪኪዮዎቹ ሀገር በኬንያ ምድር የተፈጸመዉ አሰቃቂና ዘግናኝ የሰነፎች ተግባር የሆነዉን አሸባሪነት ነዉ። ”አልሻባብ” የተባለዉ የሶማሊያ አሸባሪ ቡድን ሀላፊነቱን ወስዷል። ከላይ የምትመለከቱት ሥዕል ጥቃት የደረሰበትን የገበያ ማዕከል ያሳያል። ”አልሻባብ” የንፁሀንን ደም በየሜዳዉ ሲያፈሰዉ ፤ የሀገር ና የሕዝብ ንብረት ሲያወድም፤ እንደ ጽድቅ መስፈርት መቁጠሩ እጅጉን ያሳዝናል።ልብ ብሎ ላስተዋለዉ በኛም በቅድስት ቤተክርስትያን ዉስጥ ”አልሻባባብነት” አለ። በተዋህዶ ዉስጥ ያለዉ ”አልሻባባብነት” ከዋናዎቹ አልሻባቦች የባሰ ቢሆን እንጂ ከቶ በምንም አያንስም። ልዩነቱ በተዋህዶ ዉስጥ ያለዉ አልሻባብነት በስዉር የሚከናወን ሲሆን የዓለሙ አልሻባብነት ደግሞ በግልፅ  የሚከናወን መሆኑ ነዉ።
የተዋህዶዉ አልሻባብነት ደጋግ መዘምራንን፣ሰባክያንን፣የክህነት አገልጋዮችን፣መልካም ና ጸሎተኛ አባቶችን ለማዋረድ ና ስም ለማጥፋት፣ምንም የማያዉቁ ምዕመናን እንዲታወኩ፣ የነፍሳቸዉን የጽድቅ ዋጋ እንዳያገኙ፣ ጽድቅንና ደህንነትን የሚያገኙበት መንገድ እንዲጠፋ፣ ቤተክርስትያንንም ዘወትር በትርምስና በዉዝግብ ዉጥንቅጡ በወጣ ሥርዐት ዉስጥ እንድትዋኝ ለማድረግ፤ ”የተዋህዶዉ አልሻባብ” ”በተዋህዶ አልሻባቦቹ” ዘወትር በቤተክርስትያን ቅፅር ዉስጥ ሲዶልት ይዉላል።
”ኢትዮጲያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር” የሚለዉ ቅዱሱ ቃል በተዋህዶ አልሻባቦች ዘንድ ቦታ የለዉም። በቅድስት ሐገር ኢትዮጲያ የሚገኙ ከ፩ሺ በላይ ቅዱሳን ገዳማት በዉስጣቸዉ የሚፀልይባቸዉ መነኮሳት ጠፍተዉ እየተፈቱ ና እየተዘጉ ነዉ። ዛሬ በቅድስት ተዋህዶ ቤተክርስትያን የቅዱሳን አባቶች ትዉፊት ተረስቶ፤ አንዳንድ ጺማቸዉን ስላሳደጉና መስቀል ስለጨበጡ ብቻ ቅዱስ የሆኑና በራሳቸዉ የቆሙ በሚመስላቸዉ፣ በየካፌዉ ና ሬስቶራንቱ አይናቸዉ እንደተራበ አንበሳ በሚንከራተት፣ በምዕመናን የስራ ቦታ ና በየንግድ ስፍራዉ ሳይቀር ስራዬ ብለዉ ምዕመናን እየተከታተሉ ያልታወቀባቸዉ መስሎአቸዉ የያዙትን የሀሰት ወሬ የሚያናፍሱ፣ የበግ ለምድ በለበሱ አስመሳይ ”አልሻባብ” የቀበሮ መነኮሳትና አገልጋዮች ተሞልታለች።

”የተዋህዶ አልሻባቦች” በዕዉቀት ፣ በቅንንነት፣ በስነምግባር የሚበልጣቸዉ ሁሉ ጠላታቸዉ ነዉ። በጸሎት የሚተጋ፣ ጉልበቱን በእግዚአብሔር ፊት የሚያጥፍ ሁሉ ደመኛቸዉ ነዉ። ”የተዋህዶ አልሻባቦች” በተጠናወታቸዉ የዘረኝነት መንፈስ እንደነሱ ከምባታ፣ጎንደሬ፣ጎጃሜ፣ጉራጌ፣ሸዌ፣ወሎዬ፣ትግሬ፣ኦሮሞ፣ሲዳማ እና የመሳሰሉትን ያልሆነ ሁሉ ጠላታቸዉ ነዉ። ቅዱሱ መጽሓፍ ”ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠዉ” (ራዕ ዮሐ ፩፫፥፯) ብሎ እንደሚናገር ሁሉ ”የተዋህዶ አልሻባቦች” በተሰጣቸዉ በዚህ የስድብ ”ፀጋ” ተጠቅመዉ ሕዝበ ክርስትያኑን ያሸብራሉ፣አባቶችን ያዋርዳሉ፣ ቤተክርስትያንን ሰላም ለመንሳት ይጥራሉ።
ነገር ግን በጣም አስደናቂዉ ነገር ሁለቱም የአልሻባብ ዓይነቶች ፤ በአለም ዉስጥ ያሉት እራሳቸዉን አልሻባብ ብለዉ የሚጠሩትም ሆነ የኛዎቹ ”የተዋህዶ አልሻባቦች” አንድ የሚያደርጋቸዉ ነገር አለ። ይኸዉም፦ሁለቱም የአልሻባብ ዓይነቶች መጨረሻቸዉ እንደማያምር ና ከምድረ ገጽ እንደሚጠፉ አለመገንዘባቸዉ ነዉ።
እግዚአብሔር አምላክ ቅድስት ቤተክርስትያንን ይጠብቅ!
ቸር ይግጠመን !
hamerebirhan.com

No comments:

Post a Comment