በአሸናፊ ደምሴ
በመርካቶና አካባቢዋ የሚገኙ አንዳንድ የንግድ ሱቅ ባለንብረቶች ለፀሐይና ለዝናብ መከላከያ ያሰራነውን መጠለያ በአስቸኳይ እንድናፈርስ መገደዳችን በስራችን ላይ መስተጓጐል ፈጠረብን ሲሉ ነጋዴዎች ቅሬታ አሰሙ። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች በበኩላቸው ንግድ ፈቃድ ከወጣበት ቤት ውጪ ባለ ስፍራ ላይ የንግድ እንቅስቃሴ መፈፀም አይችሉም በሚለው በአዋጅ ላይ ተመስርተው የደንብ ማስከበር ስራዎችን መሰራታቸውን ይገልፃሉ።
በመርካቶ በሸራ ተራ፣ ሸማ ተራ እና አዳራሽ አካባቢን ጨምሮ ሰሞኑን በመላው አዲስ አበባ እየተሰራ የሚገኘው የበረንዳ ማፍረስ ተግባር በሕግና በአዋጅ የተከለከለ መሆኑን የገለፁት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አህመድ ሺፋ፣ በ2005 ዓ.ም የወጣው አዋጅ የበረንዳ ላይ ንግድ እንደሚከለከል በግልፅ ተቀምጧል ይላሉ። ማንኛውም ነጋዴ ግብር በሚከፍልበት ሱቅ ውስጥ ብቻ መገልገል ሲኖርበት ከበር መዝጊያ መለስ ዘርግቶ መሸጥ አይችልም ያሉት ኃላፊው፤ ይህን አድርጐ ቢገኝ ግን ሕገ-ወጥነቱን ያመለክታል ብለዋል።
ነጋዴዎች ባሰሙት ቅሬታ ግን ለፀሐይና ለዝናብ መከላከያ ብለን ያስቀመጥነውን መጠለያ ያውም ባስቸኳይ እንድናፈርስ መታዘዛችን ተገቢ ያልሆነና በስራችንም ላይ ጫና የፈጠረ ነው ሲሉ ያስረዳሉ። የበረንዳ ንግድ እንዳይካሄድ መከልከሉ ተገቢ ቢሆንም፤ መጠለያውን ግን እንድናፈርስ መደረግ አልነበረበትም ያሉት በመርካቶ አካባቢ ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች፤ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን አጢኖ መፍትሄ ይስጠን ብለዋል። ለዚህ ቅሬታም መልስ የሰጡት የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የደንብ ማስከበር ጸ/ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር አህመድ ሺፋ የበረንዳው ግንባታ ለሕገወጥ አሰራርን አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል ሲሉ ይመልሳሉ። በረንዳ ላይ የሚደረድሯቸውን ዕቃዎች የደንብ ማስከበር ቡድኑ አባላት አንሱ ባሏቸው ጊዜ ሲያነሱ በሌላ ጊዜ ደግመው እያኖሩ መቀጠሉ አግባብ ስላልሆነ፤ ይህን ምቹ ሁኔታ የፈጠረውም መጠለያው በመሆኑ በረንዳው ላይ የተገነባ ማንኛውም አይነት መጠለያ እንዲፈርስ አድርገናል ይላሉ።
በሌላም በኩል የፈረሰባቸውና ያልፈረሰባቸው ነጋዴዎች የመኖራቸውን ያህል፤ የደንብ ማስከበሩ አሰራር ወጥነት የለውም የሚሉ ቅሬታዎች የመኖራቸውን ጉዳይ ለኃላፊው ያነሳንላቸው ሲሆን፤ በረንዳቸውን ለመገንባት የግንባታ ፈቃድ አውጥተው መንቀሳቀስ ይችላሉ ስለመባሉም ኃላፊው መልስ ሰጥተዋል። እንደ ምክትል ኢንስፔክተር አህመድ ከሆነ፤ ከፀሐይና ከዝናብ ለመዳን በሚል ነጋዴዎቹ ያቀረቡት ጥያቄ ተገቢነት ያለው መሆኑን በማመን የአየር ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባት አመቺ አሰራር እንዲፈጠር ለማድረግ እየጣሩ መሆናቸውን በመግለፅ፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ስራው በጅምር ላይ ያለና አንድ ወጥ የሆነ አካሄድ ለመፍጠር በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን በማስረዳት ጉዳዩን ወደፊት በጋራ እንደሚያጤኑት ተናግረዋል። ይህም በመሆኑ በቀጣይነት ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በሁሉም ላይ ተመሳሳይ ስራን እንሰራለን ይላሉ።
አስተዳደሩ በአዋጅ ደረጃ ይህን ሕግ ያወጣው ሕገ-ወጥ የበረንዳ ላይ ንግድን ለመከላከል ከመሆኑም ባሻገር በተለይም ለእግረኛ መተላለፊያ ምቹ ስፍራን መፍጠር ያለመ መሆኑን ይናገራል። ነጋዴዎቹ በበኩላቸው ዕቃችንን እንድናነሳ ተደርገናል፣ ነገር ግን ጥላውን ማጣት አልነበረብንም ባይ ናቸው።
በ2005 ዓ.ም አዋጁ ፀድቆ ቢወጣም ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ ድንገት ደንብ አስከባሪዎች መጥተው አፍርሱ ማለታቸው ተገቢ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን የሚያሰሙት በተለያዩ የንግድ መስኮች የተሰማሩት ነጋዴዎች፤ ጊዜ ሊሰጡን ይገባል ባዮች ናቸው። ይህን አስመልክቶ ሕጉ አዋጅ ሆኖ ከወጣ በኋላ ለንግዱ ማኅበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥታችኋል ወይ ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ኃላፊው ሲመልሱ፤ በደንብ ቁጥጥርና ክትትል ኦፊሰሮች አማካኝነት በመስክ ጉብኝታቸው ወቅት በቃል ለነጋዴዎቹ እንደሚገልፁ እና በበራሪ ወረቀቶችም እንዲደርሳቸው መደረጉን አስረድተዋል። ይህ ሳይሆን ሕግ ሳይከበር ከቀረ ግን እርምጃ መውሰድ ይጀመራል ሲሉ የሰሞኑንም እንቅስቃሴ የዚህ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም የበረንዳ ላይ ንግዱን አካሄድ ለማስቀረት በከተማ አስተዳደሩ ደረጃ እየተሰራ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እስኪሆንም ያዝ-ለቀቅ አይነት ነገር ሊኖር እንደሚችል ኃላፊው ያስረዳሉ። ነገር ግን ጉዳዩን የሚከታተል ቡድን በመኖሩ በቀጣይም አንድ ወጥ የሆነ ጠንካራ አሰራር እየፈጠሩ እንደሚሄዱ ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment