- ‹‹[ቅዱስ] ሲኖዶሱ አሁን ያለችውን ቤተ ክርስቲያን በብቃት የሚመራበት ደረጃ ላይ ነው ወይ? ለውጡ መጀመር ያለበት ከራሱ ከ[ቅዱስ] ሲኖዶሱ ነው፡፡››
- ‹‹ወደፊት የሚመጡ ጳጳሳት ይኖራሉ፡፡ የጳጳሳቱ አመራረጥ የሕዝብን ይኹንታ የሚያገኝ ነው[ን] የሚለው ገና የሚታይ ነው፡፡››
- ‹‹ዕርቀ ሰላሙን እኛ ቀድመን ብናመጣው ጥሩ ነው፡፡››
ሰባኬ ወንጌል እና ጸሐፊ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ከዕንቊ መጽሔት ጋራ ያደረገው የቃለ ምልልስ ቆይታ ሁለተኛ ክፍል ቅዳሜ፣ መስከረም ፲፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ታትሞ በወጣው ቅጽ 6 ቁጥር 102 የመጽሔቱ እትም ለንባብ በቅቷል፡፡ ቃለ ምልልሱ፥ በታሪክ እና ቅርስ ምንነት፣ አጠባበቅና ጠቀሜታ ላይ የሚታዩ የአመለካከትና ተግባር ችግሮች፤ የቤተ ክርስቲያን፣ መንግሥትና ምእመናን ድርሻዎች፤ በቅዱስ ሲኖዶስ አሠራርና በዕርቀ ሰላሙ ቀጣይ ኹኔታዎች ዙሪያ ትኩረት አድርጓል፡፡
ከአወዛጋቢው የ፮ኛው ፓትርያርክ ምርጫ በኋላ በሚታዩት የተቋማዊ አመራርና አሠራር ለውጦች፣ በዕርቀ ሰላሙወቅታዊ አዝማሚያና ቀጣይ ዕድሎች ላይ ያተኮሩትን የቃለ ምልልሱን ክፍል ለይተን አስተናግደነዋል፤ ይከታተሉት፡፡
ዕንቊ፡- በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጊዜ ‹‹በቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙ መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች አሉ›› እያልክ ስታሳስብ መቆየትኽ አይዘነጋም፡፡ በአሁኑ ፓትርያርክ የሥራ ጊዜ የተሻሻሉና ለውጥ ያየኽባቸው ነገሮች አሉ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ለውጦችን በመጠኑ አያለኹ፡፡ አቡነ ጳውሎስ አፈንግጠው ከሄዱበት አለባበስ ጀምሮ መሻሻል ይታያል፤ ወደ መሥመር የመጣ ነገር ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ÷ የተንዛዛ ድግስን የማስቀረት ነገርአስተውዬአለኹ፡፡ ዝም ብሎ ለተርእዮ (ለታይታ፣ እዩኝ እዩኝ ለማለት. . .) ተብሎ የሚደረጉ ነገሮችን ማስቀረት ተጀምሯል፡፡
አቡነ ጳውሎስ እኮ ከሥራው በላይ መታየትን ነበር የሚፈልጉት፡፡ አሁን አቡነ ማትያስን ብዙ ቦታ አናያቸውም፡፡ አቡነ ጳውሎስ የአንድ ምእመን ልጅ የክርስትና ሥርዐትም ቢኾን መገኘት አለብኝ ካሉ አይቀሩም፡፡ ለአንድ ሰው የሚሰጡት ቦታ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሥራ ከሚሰጡት ትኩረት ይበልጥ ነበር፡፡ እርሳቸውን አንድ ካህን[እንኳ] ከማያስፈልግበት ቦታ ተገኝተው ታያቸዋለኽ፡፡ ያ የሚያስፈልግ አልነበረም፡፡ መታየት አለብኝ ማለታቸው ለእርሳቸው ልክ ነበር፡፡ አለመገኘትን እንደ ትልቅ ጉዳት ነበር የሚቆጥሩት፡፡ አሁን ከዚህ ዐይነቱ ድርጊት የመቆጠብ ኹኔታ ይታያል፡፡
በ[ቅዱስ] ሲኖዶስ ደረጃ በሚደረጉ ስብሰባዎች ነው ወይስ አይደለም ብሎ መከራከርና መወሰን ከተጀመረ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ተከራክሮ ምን ይኾናል የሚለውን ሂደት ነው የሚወስነው፡፡ ነገር ግን መከራከር መቻል፣ አንድ ጉዳይን ወስደኽ የምታመለክትበት አካል መኖር መቻሉ በራሱ አንድ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ጥናት ለማጥናት መሞከራቸው፣ ቤተ ክርስቲያንን በሚያስወቅሱ ሙስናን በመሰሉ ጉዳዮች ዙሪያ በዐደባባይ በግልጽ መናገር መቻላቸው ለውጦች ናቸው፡፡
ኾኖም እነዚህ በቂ ለውጦች አይደሉም፤ ግን የለውጥ መንገድ ላይ መኾናቸውን ያሳያል፡፡ ለውጡ መጀመር ያለበት ከራሱ ከሲኖዶሱ ነው፡፡ ሲኖዶሱ አሁን ያለችውን ቤተ ክርስቲያን በብቃት የሚመራበት ደረጃ ላይ ነው ወይ? ከግብጽ፣ ከሶርያ ሲኖዶሶች፣ ከቫቲካን ተነጻጽሮ መታየት አለበት፡፡ አደረጃጀቱ ምን ያህል ብቁ ነው? የመረጃው ፍሰትስ? የውሳኔ አሰጣጡስ? በተለይ ውሳኔዎቹ የሚወሰኑት ጥናት ተደርጎባቸው ነውን? አጥኚ ቡድንስ አለ? ቋሚ ኮሚቴዎችስ አሉ? እነዚህ ውስጥ የሚታዩት ነገሮች ሁሉ ሲዳሰሱ ገና ብዙ ይቀራል፡፡
ለምሳሌ ያህል፣ ወደፊት የሚመጡ ጳጳሳት ይኖራሉ፡፡ የጳጳሳቱ አመራረጥ የሕዝብን ይኹንታ የሚያገኝ ነው? የሚለው ገና የሚታይ ነው፤ምክንያቱም ፍትሐ ነገሥቱ አንድ ጳጳስ ሲመረጥ የሕዝቡንም የቤተ ክርስቲያኒቱንም ይኹንታ እንዲያገኝ ይጠይቃል፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ነውር ነቀፋ የለበትም የሚባለውን ነው እንዲሾም የሚያዝዘው፡፡ ግብጾች[ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን] አንድ ሰው ጳጳስ ከመኾኑ በፊት ከወንጀል ነጻ ስለመኾኑ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከፖሊስ እንዲመጣ ያደርጋሉ፡፡ ለምንድን እኛ ይህን የማናደርገው? አንድ ሰው ጳጳስ ከኾነ በኋላ ክሥ እየመጣ ነው፤ እንዲህ፣ እንዲያ አደረገ እየተባለ ነው፡፡ ይህን ማስቀረት የሚቻለው ከመሾሙ በፊት ንጽሕናውን በማረጋገጥ ነው፡፡
አንዳንዴ ምእመናን ከተለያዩ ቦታዎች ‹‹እኚህ ይነሡልን! አስቸግረውናል›› የሚሏቸው ሰዎች ከነበሩበት ሥፍራ ሲነሡ በጵጵስና የሚሾሙበት ኹኔታ አለ፡፡ ይህን እነዚያ የተቃወሟቸው ምእመናን የሚቀበሉት ነው ወይ? ወደፊት በአውሮፓ የደረሰውና ጳጳስን የመጥላት፣ ጳጳስን አንቀበልም የማለት ነገር በኢትዮጵያ ደረጃ ይከሠታል ብዬ እፈራለኹ፡፡ ስለዚህ አሁን ማስተካከያው ከላይ ወደ ታች መደረግ አለበት፡፡ ካላስተካከልነው ትውልዱ/ጋሪው ይቀድምና ከዚያ በኋላ ጉዞው አይኖርም፡፡
ዕንቊ፡- ሲኖዶሱን ለሁለት ከፍሎታል የሚባለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውዝግብ ይቀጥላል ወይስ በአዲሱ ፓትርያርክ መሾም አክትሟል?
ዲ/ን ዳንኤል፡- አያከትምም! አንድ ቀን ነገሮች ይስተካከላሉ፡፡ ይህ እኮ ወቅት ያመጣው ነገር ነው፡፡ ወደፊት መፍትሔ ይገኝለታል፡፡
ዕንቊ፡- ድርድሩ ጸጥ ረጭ የማለት ነገር አይታይበትም?
ዲ/ን ዳንኤል፡- አንድ ሰው ከቤቱ ጅብ ይገባበትና ያን ጅብ ለማስወጣት ጦሩን ሰብቆ ሲወረውር አፉን ያገኘዋል፡፡ አፉን የተመታው ጅብም አመለጠ፡፡ ቆይቶ ሰውዬው አንድ ወዳጁን ያገኝና ‹‹ያን ጅብ እኮ አፉን ወጋኹት›› ብሎ ነገረው፡፡ ጓደኛውም ምኑ ላይ ወጋኸው ቢለው ‹‹አፉ ላይ›› ብሎ መለሰ፡፡ በዚህን ጊዜ ወዳጁ ተገርሞ፣ ‹‹ታዲያ አፉን አሰፋኸው እንጂ ምን አተረፍክ›› አለው የሚባል ጨዋታ አለ፤ እና አሁንድርድሩ ጭራሽ ነገሩን አሰፋው እንጂ ጉዳዩን ቅልብጭ አድርጎ አልቋጨውም፤ ግን አንድ ቀን ይህ መለያየት የሚያከትምበት ጊዜ ይመጣል፡፡ እኛ ቀድመን ብናመጣው ግን ጥሩ ነበር፡፡
No comments:
Post a Comment