Thursday, August 1, 2013

ሀገሬ ገመናሽ

ከበድሉ ዋቅጅራ
(ክፍል አራት) (ፋክት መጽሔት)


እኔ የምልሽ ሀገሬ፣ ምነው ፋብሪካ እንጂ ዩኒቨርሲቲ አልዋጣልሽ አለ!?

እንደምን አለሽ ሀገሬ? እኔ ምን እሆናለሁ ብለሽ ነው! ከሁለመናሽ . . . ከጭለማሽም ቢሆን እንኳ ተስፋን እቧጥጣለሁ፡፡ ዋናው መኖር አይደል፤ ህይወት ካለ መች ተስፋ ይገዳል፡፡ ያንቺና የእኛ ነገ ከዛሬያችን የተሻለ መሆኑን ብመኝ፣ ይኸው ዛሬም ጉድፉን ትነቅሽለት ዘንድ ገመናሽን ጠንቁዬ እሞግትሽ መጣሁ፡፡

መቼም ሀገሬ እንዳንቺ የማለዳ ጉዞውን አለምን ባስደነቀ የስልጣኔ መንገድ ዳዴ ብሎ የጀመረ ሀገር የትምህርትና የእውቀት ጥቅም እንቅልፍ ቢነሳው፣ በዚህም የተነሳ ከዘመናት እንቅልፉ ነቅቶ ትምህርት ትን ቢያሰፋ ምኑ ይደንቃል፡፡ እናም ተራራውን አሻቅቦ፣ ሜዳውን የሚያቋርጥ ጎዳና ዘረጋሽ፤ በየዥረቱም ላይ ድልድዮችን አቆምሽ፤ ከየዥረቱ ማዶም ትምህርት ቤቶችን ከፈትሽ፤ ዩኒቨርሲቲዎችንም ጭምር፡፡ አበጀሽ ሀገሬ! ዜጋውን ከድንቁርና የማይታደግ ሀገር እንደ ክፉ የእንጀራ እናት ነው፡፡ እኔ ግን ሀገሬ ፊትሽ መገተሬ አበጀሽ ልልሽ አይደለም፡፡ ይልቁን ለየዩኒቨርሲቲዎችሽ ገመና የገደል ማሚቱ ሆኜ፣ እንደ ብራቅ አግንኜ፤ ጆሮሽን ላደነቁረው ነው፤ መላ ትፈልጊለት ዘንድ፡፡ 
እኔ ሁለተኛ ደረጃ እያለሁ በአርሲ ክፍል ሀገር ውስጥ ያሉሽ የሁለተኛ ደረጃ /ቤቶች ሶስት ብቻ ነበሩ፡፡ ዳሩ ላንቺ ምኑ ይነገራል፤ ታውቂዋለሽ፡፡ በሶስት ፈረቃ ተምረን ነው ዩኒቨርሲቲ የገባነው፡፡ ያኔ በየአመቱ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት ተማሪዎችም ከአምስት ሺህ አይበልጡም ነበር፡፡ እርግጥ ነው ሀገሬ እዚያ ትምህርት ቤትና እነዚያ ሶስት ዩኒቨርሲቲዎች መግባት፣ እንደዛሬው ዩኒቨርሲቲ ያለመግባት ከባድ ነበር፡፡ ግን ገብተው የተማሩትን፣ ከየዩኒቨርሲቲው ያስመረቅሻቸውን ምን እንደሰሩልሽ ወይም እንደሰሩብሽ፣ የት እንዳሉም ታውቂያለሽ፡፡ ከሀገራቸው ውጭም ‹‹ስለጠንን›› ያለውን አለም ጉድ ያሸኙ አልነበሩም? 

አንቺ ግን ጥቂቶች የሚቋደስዋት ማዕድ መሆንን ጠላሽና ለዜጎችሽ በየማዕዘናቱ ዩኒቨርሲቲዎችን አቆምሽ፡፡ እንዳሰብሽው ግን አልሆነም፡፡ እንዴት? እንዴት እንደሆነማ መች አጣሽው፡፡ ለማንኛውም የዩኒቨርሲቲዎችሽን ነገር ሳስብ አያቴን ትመስይኛለሽ፡፡ ነፍስዎን ይማረውና የእናቴ እናት እኔና ወንድሞቼ እስዋ ለማደር የሄድን እንደሆነ፣ ከመተኛታችን በፊት ገላችንን የግድ መታጠብ አለብን፡፡ እና በዚያ የተጨራመተ የውሃ መወዘቻ ብረት ድስት ያንተከተከችውን ውሃ ታወርድና ‹‹አይዟችሁ! አይቀዘቅዝም፡፡ እኔ አያታችሁ ቤት መጥቶ በቀዝቃዛ መታጠብ የለም፡፡›› ትለኛለች፡፡ ከዚያው የተፍለቀለቀውን ውሃ በሳፋ ትገለብጥና በቁጥራችን ልክ አምስት ወይ ስድስት በዚያው ብረት ድስት ቀዝቃዛ ትጨምርበታለች፤ትበርዘዋለች ሳይሆን ታቀዘቅዘዋለች፡፡ ሁላችንም የሞቀ ውሃ እየጎመዠን በቀዝቃዛ ውሃ ታጥበን እንተኛለን፡፡ እውነቴን እኮ ነው! አንዳንዴ ሳስበው እነዚህ ወደ ሰላሳ የሚደርሱ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችሽ የቀደሙትንም ጭምር በርዘው ያቀዘቀዝዋቸው ይመስለኛል፡፡ እውነቴን እኮ ነው! በእርግጥ አያቴ አንድ ወይም ሁለታችን ብቻ በሞቀ ውሃ እንድንታጠብ እንደማትሻ፣ አንቺም የተወሰኑ ብቻ በጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች ተምረው ቢወጡ አለመሻትሽ የእናትነት ነው፡፡ ግን አየሻቸው ከዩኒቨርሲቲው የምታመስመርቂያቸው ልጆቻችንን! 

ቆይ እኔ የምልሽ ምነው ፋብሪካ እንጂ ዩኒቨርሲቲ አልዋጣልሽ አለ!? እውነቴን እኮ ነው! ልጅ ሆኜ የነበረው የድሬዳዋ ሲሚንቶ ፋብሪካ ጥሩ ሲሚንቶ ያመርት ነበር፡፡ ዛሬም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች የተገነባው የድሬዳዋ ሲሚንቶ ፋብሪካ (በርግጥ ስሙን ቀይሯል) ልክ እንደመጀመሪያው ድንጋይ ፈጭቶ፣ ቀምሞ ሲሚንቶ ያወጣል፡፡ የፖስታ ፋብሪካሽም ቢሆን ስንዴ ወስዶ ፓስታ ያመርታል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችሽ ግን ሀገሬ እንደድሮው ያልተማረ አስገብተው የተማረ ማውጣት ትተዋል፡፡ ያልተማረ አስገብተው እድሜው በአራት አመት የጨመረ ያልተማረ ያወጣሉ፡፡ ድሮ ድሮ ከዩኒቨርሲቲ ከሚመረቁት መካከልየብስል መሀል ጥሬውበሰለጠነበት ሙያ ብቁ ያልሆነው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሀገሬ . . . ! 

ሀገሬ አንቺም በመንግስትሽ ወጥተሸ ስህተትሽን ቶሎ ማረም አትወጂም፡፡ በምጣኔ ሀብት፣ በአስተዳደር በሒሳብ አያያዝ . . . ያስመረቅሻቸውን በኮብል ድንጋይ ስራ፣ በዶሮ እርባታ ወዘተ. . . እያሰማራሽ ‹‹ስራ ፈጠራ›› እያልሽ ጉራሽን ስትነዢ ትንሽ አፍሽን አይዝሽም! በአካውንቲንግ የተመረቀው በሂሳብ ስራ ቢሰማራ፣ በግብርና የተመረቀው ዶሮ ወይ አሳማ አርቢ ቢሆን ስራ መፍጠሩ ባትነግሪንም የገባንል፡፡ እንደኔ እንደኔ ሀገሬ አራት አመት ታሪክ ተምሮ የተመረቀ ድንጋይ የሚጠርብ ከሆነ፣ ዩኒቨርሲቲሽ ከህይወቱ ላይ አራት አመት ሰርቆታልና በህግ ያስጠይቅሻል፡፡ እና ይህንስራ ፈጠረ›› ምናምን የምትይውን በአግባቡ አድርጊው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችሽን ፈትሺ! እውነቴን እኮ ነው! ምን ያስቃል? እኔ አንቺን ብሆን ሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎችሽን ለአንድ አመት ከርችሜ፣ ከመምህሩም ከተማሪውም ጋር ጉባኤ እቀመጥ ነበር፡፡ ከዚያ መቼም ዜጋሽ መናገር ትቷል፤ ከተናገረ ገመናሽን አፍረጠረጠው ከነገሩሽ መፍትሔ ትፈልጊ ነበር፡፡ 

እውን አሁን ሀገሬ በምድርሽ ላይ ያለውን ብቸኛ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ያለ ተማሪ አስቀርተሸ ተኝተሽ አደርሽ? ጉደኛ እኮ ነሽ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲሽ በያዝነው አመት የፍልስፍናና የታሪክ ትምህርት ክፍሎችን ጦም አሳደርሻቸው፡፡ ግሪኮች የዩኒቨርሲቲ መሰረቱ ፍልስፍና ነው የሚሉትን ረሳሽው? በርግጥ ልጆቻችንሲመረቁስራ የሚያገኙበትን መስክ መርጠው እንዲማሩ መፍቀድሽ መልካም ነው፡፡ ግን እኮ ስራ አገኘም አላገኘም አንቺ ታሪክሽን የሚያጠና ትፈልጊያለሽ፤ አሳቢ (thinker) ትፈልጊያለሽ፡፡ ሀገር እኮ በእህል ውሀ ብቻ አይቆምም፡፡ እንደነዚህ አይነት የእውቀት መስኮች የእለት እንጀራቸው ስስ ቢሆንም፣ አንቺና ዜጎችሽ እንድንቀጥል የነፍስ ዋጋ ናቸው፡፡ እንዴ እንዴት አንቺም እንደ ሰው የእለት እንጀራ ቃራሚ ትሆኛለሽ! እና የውልሽ አንዱ የዩኒቨርሲቲዎችሽ ገመና ይህ ነውእውቀትን ሳይሆን የእለት እንጀራን የቋመጠ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ መላክሽ፡፡ 

ሀገሬ ዩኒቨርሲቲ እኮ የሚያስፈልገው የዛሬ ችግርሽን ብቻ እንዲፈታልሽ፤ ድንጋይ ጠርቦ መንገድ እንዲሰራልሽ፣ ህንፃ እንዲያቆምልሽ አይደለም፡፡ ዩኒቨርሲቲ እኮ የትላንት ማንነታችን ማቆያና የነገ ውጥናችን መዳረሻ መንገድ ነው፡፡ የትላንት ታሪክሽ ቢጠፋ፣ የነገ ግብሽ ቢሰናከል ተጠያቂው ከዩኒቨርሲቲዎችሽ ሌላ ማን ነው? እንዴ ሀገሬ! ዩኒቨርሲቲ እኮ የሴሚስተር ውጤት ጉዳይ ወይም የአመቱ ተመራቂ ቁጥር ጉዳይ አይደለም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ለሙሉ ህይወት ዘመን የሚያገልግል፤ ከራስ አልፎ ለወገን፣ ለአንቺም ጭምር የሚተርፍ እውቀት የሚገበይበት ተቋም ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ እኮ የሀገርና ዜጎች የኋላ ቅርስ የሚጠበቅበትና የወደፊቱ አለም ቅርፅ የሚነደፍበት ተቋም ነው፡፡ያንቺስ ዩኒቨርሲቲዎችሽ ሀገሬ!

በጣም የሚገርመው ደግሞ በየዩኒቨርሲቲዎቹ ያስቀመጥሻቸው ሀላፊዎችና አብዛኞቹ ምሁራንም ገመናሽን አጋልጠንመላ በይውከማለት ይልቅ፣ ለገመናሽ ገመና መሆናችን ነው፡፡ ትዝ ይልሻል ለሁለተኛ ዲግሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ ዜጎችሽን ስትልኪ በመጀመሪያ ዲግሪ 2.5 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያለውን መርጠሽ ነበር፡፡ በዚያ ላይ የመግቢያ ፈተና ነበረው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ሁሉ ለሁለተኛ ዲግሪ መማር ይችላል ያልሽ ጊዜ፣ የየትኛውም ሀገር ደንብ ነውና የዩኒቨርሲቲዎች ሃላፊዎችም ምሁራኑም ይሁን አልን፡፡ አንቺ ግን ሀገሬ መች በዚህ ብቻ በቃኝ አልሽ፡፡ መንግስትሽ እንዲማሩለት የሚልካቸው ዜጎች መግቢያ ፈተናውን ማለፍ ባቃታቸው ጊዜፈተና ይቅርአልሽ፡፡ የየዩኒቨርሲቲው ሃላፊዎችምእሺአሉሽ፡፡ የዛሬ ገመናሽ መቆለል የጀመረው ያኔ ነው፡፡

እንኳን ደስ ያለሽ ሀገሬ! አንድ ዜና ልንገርሽ፡፡ አንቺና መንግስትሽ እንዲማሩ የምትልኳቸው የመግቢያ ፈተናውን ማለፍ ቢያቅታቸው፣ ምሁራኖችሽ አንቺና መንግስትሽን ለማስደሰት የሁለተኛ ዲግሪ መግቢያ ፈተናን በሁለተኛ ክፍል ፈተና መጥነው አዘጋጁልሽ! የአማርኛ ፊደል መፃፍ በቋንቋ የሁለተኛ ዲግሪ ለማግኘት የመግቢያ ፈተና ሆነ! እንኳን ደስ ያለሽ! እንኳን ለዚህ አበቃሽ፡፡ መንግስትሽ ጀመረው እኛ ምሁራኖችሽ ጨረስንልሽ፡፡ እኔ የምልሽ ለአንድ ሀገር የትምህርት ጥራት መውደቅ ከዚህ በላይ አስረጅ አለ! ንገሪኝ እስቲ የምን ማቀርቀር ነው!

እንዲህ ነው እንግዲህ ሀገሬ! አንቺና መንግስትሽ በየጊዜው ‹‹ይህ የትምህርት አሰጣጥ ጥሩ ነው፣ ይሞከር›› እያላችሁ፣ ገንዘብ የሰጣችሁን ፈረንጅ ሀገር ትምህርት አሰጣጥ ታመጣላችሁ፡፡ አንዳንድ ለህሊናቸው ታማኝ የሆኑ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን፣ ጉዳዩን አጢነው ‹‹ይህ ለእኛ አይሆንም›› ሲሉ፣ ልባቸውን በአንቺና በመንግስትሽ ፍቅር ያነደዱቱ ወይም ጉዳዩ ከእውቀታቸው አልጠጋ ያላቸው ሃላፊዎችና ምሁራን ይረግሟቸዋል፤ ላንቺና ለመንግስት ያሳቅሏቸዋል፡፡ አንቺና መንግስት ደግሞ እርግማኑ ይደርስ ዘንድ ትተጋላችሁ፡፡ መቼም ስንቱን ምሁር ቀስፈሽ፣ ምን ያህል ስለት እንደገባልሽ ከእኔ በላይ አንቺ ታውቂያለሽ፡፡

ለምን? እንዴ ሀገሬ! አሁን ማን ይሙት ሀላፊዎችሽ ይህን ለምን እንደሚያደርጉ አታውቂም? አላውቅም ካልሺኝ አላምንሽም! እስቲ እኔ ልጠይቅሽ! እነዚህን ሃላፊዎች እንዴት ነው የመረጥሻቸው? አይዞሽ አትፍሪ እውነት እንነጋገር! የትምህርት ክፍል ሃላፊዎችን፣ ዲኖችንና ፕሬዝዳንቶችን እንዴት ነው የመረጥሻቸው? መልሺልኛ! ስለራሱ የማይናገር፣ ጭምት (introvert) ዜጎች መኖሪያ ሆነሽ፣ ለምስራቃዊ ጭምት ባህል ምሳሌ ነኝ እያልሽ፣ምረጡኝብሎ ያመለከተን አይደል እንዴ የሾምሽው! እሱ ማነው? ምን ተምሯል? ምን ሰርቷል? ሌላውን አስተባብሮ እውቀትን ያሳልጣል ወይ? ብለሽ መርምረሻል? እረ ቆይ መመርመር ይቅር ጠይቀሻል? አንቺ ግን ሀገሬ ማፈሪያ አይደለሽ፣ እኔን ባይወደኝም መንግስትን ይወዳል ወይ? ከአካዳሚያው የበለጠ ለመንግስት ታማኝ ነው ወይ? ብለሽ ጠየቅሽ፡፡ ከዚያም ሾምሻቸው፡፡ እና ይኸው እንደጠበቅሽው የመንግስትሽን ሞራ እያነበቡ፣ እቅድና ፕላኑን እያጠኑ አስደሳች ሪፖርት ወደ ቤተመንግስት ይልካሉ፤ በዩኒቨርሲቲዎችሽ ውስጥ ግን የትምህርት ጥራትን መውደቅ ያፀድቃሉ፤ ለጎሳና ለወንዝ ልጅነት አድባር ይሰግዳሉ፣ በማይፈልጉት ላይ በር ይዘጋሉ፤ ለሚፈልጉት በር ይከፍታሉ! የሚፈልጉትን ይቀጥራሉ፣ የማይፈልጉትን ያባርራሉ፡፡ መስከረም የተቀበሉትን፣ ሰኔ ላይ ያስመረቁት ተማሪ ቁጥር ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችን ከበው ስለተደረደሩ (በጥቃቅንና አነስተኛ ይደራጁ አይደራጁ አላውቅም) የመመረቂያ ጽሁፍ አሰናጂዎች (በነገራችን ላይ አብዛኛው የዘመኑ የመመረቂያ ጽሁፍ ይሰናዳል እንጂ አይጠናም) ቢያውቁም አያውቁም፡፡ በሚቀጥለው አመት የሚከፍቷቸው ፕሮግራሞች ስያሜ እንጂ የመምህራንና የመፃህፍት አለመኖር አያስጨንቃቸውም፤ ስንቱ ይዘረዘራል ሀገሬ! 

በገንዘብ ተገዝቶ የመጣ የመመረቂያ ጥናት ያስመርቃል፤ ከአመታት በፊት የተሰራ ወረቀት ተገልብጦ ዲግሪ ያስገኛል፡፡እኛ ምሁራኑ፣ የሰየምሻቸው ሀላፊዎችም ሁሉ ይህን ያውቃሉ፡፡ እኛ ቡና ሻይ ላይ እናወራለን፡፡ እነሱ ሪፖርታቸው ውስጥ አያካትቱትም፡፡አንዳንዴ ሲቆጨኝእንዲያው ሪፖርቱን ሁሉ እውነት የሚያደርግ ተአምር ቢፈጠር ብዬ የጅል ምኞት እመኛለሁ፡፡ እውነቴን እኮ ነው ሀገሬ! ቢሆን በአለም ላይ እንዳንቺ ያደገ ሀገር የት ይገኛል! 

እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቅሽ ሀገሬ! ከፖለቲካና ከእውቀት የቱ ይልቃል? ላደለውማ ፖለቲካም ሳይንስ ነው፡፡ ላንቺና ለአፍሪካ ጓደኞችሽ ግን ሀገሬ ፖለቲካ ለቂም መወጫ፣ ለአድሏዊነት፣ ሌሎችን ለማፈን የሚውል ከጠመንጃ የሚገኝ ሀይል ነው፡፡ ለነገሩ ለአንቺ ይህ አይነገርም፡፡ ፖለቲከኞችሽ (ባለጠመንጃዎቹ) ከምሁራኖችሽ የበለጠ ጉልበት አላቸው፡፡ ፖለቲከኞችሽ የአስተዳደርሽን ፍልስፍና፣ የህገ መንግስትሽን አይነት ብቻ አይደለም የሚወስኑት፡፡ የትምህርት ፖሊሲ ይነድፋሉ፤ ለዩኒቨርሲቲ ስርአተ ትምህርት ይነድፋሉ፤ ለዩኒቨርሲቲ ምሁራን የማስተማር ዘዴን ሳይቀር ይመርጣሉ፡፡ እና ሀገሬ በየት በኩል ዩኒቨርሲቲዎችሽ ዩኒቨርሲቲ ይሁኑ፡፡ ፖለቲከኞችሽ በየዩኒቨርሲቲዎችሽ ምረቃ ላይ የሚያደርጉት ንግግር እንደ ተመራቂዎቹ ካባ የጠቆረ ነው፤ ስለዩኒቨርሲቲ መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳብ (essence) የሚያውቁት ነገር የለም፣ ወይም አያገባቸውም፡፡ ስለድንጋይ ጠረባና ስለዶሮ እርባታ ያወራሉ፤ ስለአንቺ ሀገራችንና ስለእኛ ዜጎችሽ ትልቅነትና ራእይ ሳይሆን፣ ስለአንድ ፓርቲ ገድልና ራእይ ይነግሩናል፡፡ ከፊታቸው የተደረደረውን ተመራቂ የሚለኩት አስቦና ተመራምሮ ለሀገሩ ሊበረክት ከሰነቀው አዲስ እውቀት አንጻር ሳይሆን፣ የእነሱ ለእውቀትና ለክርክር የማይቀርብ ራእይ ለማስፈጸም ካለው ቅርጠኝነት አንጻር ነው፡፡ . . . ተይ ሀገሬ የፖለቲከኞችሽ መዳፍ ይጥበብ!

በፖለቲካሽ የተነሳ ዛሬ በዩኒቨርሲቲው እውቀት የማይዳስሳቸው ቁምነገሮች እየበረከቱ ነው፡፡ ዛሬ የአንድን ብሔረሰብ ያለፈ ታሪክ አጥንቶ እንዲህ ነበር ማለትእውቀት ሳይሆን ፖለቲካ ነውለዩኒቨርሲቲዎችሽም አይነኬ (taboo) የእውቀት መስክ እየፈጠረሽ ነው፡፡ የሚገርመው ሀገሬ ተማሪዎችሽም ይህን አውቀው የሚጨነቁት ከዩኒቨርሲቲ ከመውጣታቸው በፊት እውቀት ቀስሞ ሙሉ ሰው ለመሆን ሳይሆን፣ የገዢው ፓርቲ አባልታማኝዜጋ ለመሆን ነው፡፡ አየሽ ሀገሬ፣ ልጆቻችን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚያውቁት ለወደፊት ህይወታቸው ወሳኙ እውቀት ሳይሆን፣ ፖለቲካዊ ታማኝነት እንደሆነ ነው፡፡ እውነቴን እኮ ነው! ዲግሪ ብቻውን ስራ ለማግኘት ዋስትና አይደለማ! የገዢው ፓርቲ የአባልነት መታወቂያ በአባሪነት ያስፈልጋል፡፡. . . ስንቱ! 
ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራልአሉ! ለነገሩ እድሜ ለአይሸፈን ገመናሽ ብዛት ሁሉን ተናግረን፣ ሆዳችን ባዶ ሆነልን ብለና እፎፎይ . . . ሳንል ወዲያው ይሞላል፡፡ ለማንኛውም ሀገሬ፣ ለአንቺና ለዜጎችሽ ዲሞክራት አስተዳዳሪ ያፈራል ያልሽው ዩኒቨርሲቲ፣ በመልካም አስተዳደር እጦት ይታመሳል፡፡ ከሀያኛው ክፍለ ዘመን ስልጣኔ ጋር አቀራርቦ አብሮ የሚያራምድ ፖሊሲ ነዳፊዎችን ያወጣልኛል ያልሽው ዩኒቨርሲቲ፣ እራሱን የሚመራበት ወጥ ፖሊሲ የለውም፤ ከየፈረንጅ ሀገሩ የተቃረሙ ፕሮግራሞች መፈተሻ ቤተሙከራ ሆኖልሻል፡፡ ስንቱ!. . . . . ለማንኛውም ምን ያህል ገመናሽ እንዳገጠጠ ታዪው ዘንድ የታደለው ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ከሁለት አመታት በፊት ለዩኒቨርሲቲው ምሁራን ጉባኤ ላይ ስለዩኒቨርሲቲ ምንነት ከተናገሩት ቀንጭቤ ልንገርሽና ልሰናበትሽ፡፡ 
‹‹The essence of a university is that it is uniquely accountable to the past and to the future – not simply or even primarily to the present. A university is not about results in the next quarter; it is not even about who a student has become by graduation. It is about learning that molds a lifetime, learning that transmits the heritage of millennia; learning that shapes the future.›› 
በጎውን ያምጣልሽ፡፡

No comments:

Post a Comment