Friday, August 2, 2013

የቃሊቲ እንግልት

የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ
ጎበዝ እንግዲህ እዚህ ሀገራችን ኢትዮጵያ ጉድ ሳይሰማ አይታደርም አይደል፡፡ ዛሬ ከአቤል አለማየሁ ጋር አንዱዓለም አራጌን እና ርዕዮት ዓለሙን እንጠይቅ ተባብለን ወደ ቃሊት ወረድን፡፡ ለዛሬው የነበረን ዕቅድ ሁለቱን ብቻ የማየት ነበር፡፡ ለዚህም እንዲሆን በቂ የሚባል ሰዓት ይዘን ልክ ከቀኑ አምሰት ሰዓት ላይ ቃሊት በር ደረሰን፡፡ በቅርቡ ቃሊት የሚገኙትን ወዳጆቻችን ለመጠየቅ የተለሳለስ ሁኔታ መኖሩን በአገኘሁት አጋጣሚ የገለፅኩ ሲሆን ይህንኑ ሃሳብ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ለአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ሪፖርት ሲያቀርቡ ገልፀውት ነበር፡፡ ምሰጋናችን አንድ ሳምንት ሳይሞላው እብድ ይሻለዋል እንጂ አይደንም እንደሚባለው ሆኖ አገኘነው፡፡ 
ዛሬ (ሐሙስ ሐምሌ 25) ቃሊት በሩ ላይ ስንደርስ አንድ አንድ ነገር እንግዛ በሚል ቆም ባልንበት አጠገባችን ያሉት ዘቦች እኔን እየተመለከቱ ሲጠቃቀሱ ተመለከትኩ፣ ውይይቱን ያስነሳው በበሩ ላይ የቆመው ባለ አንድ ኮከብ ማዕረግ ባደረገ በአሁኑ አጠራር ረዳት ኢንስፔክተር (በቀድሞ ምክትል የመቶ አለቃ) ነው፡፡ ባደረገው ማዕረግ ልክ ግን ያልሆነ ሰው ነው፡፡ በሚያደርገው ነገር እምነት እንደሌለው የሚያሳብቀው ንግግሩ ብቻም አይደለም ሰሙን ለመናገር ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ማነኛውም የመንግሰት ሰራተኛ አገልግሎት ሰጪ ሙሉ ስሙን በግልፅ መፃፍ እንደሚጠበቅበት ግልፅ ነው፡፡ ይህ ባለ ማዕረግ ግን ይህንን አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን ሲጠየቅ ስሙን ለመናገር ድፍረት የለውም፡፡ እንግዲህ ለዚህ ነው ኮኮብ ማዕረግ በትከሻው ላይ የተደረገለት እና ለዚህም በሚል ደሞዝ የሚቆረጥለት፡፡ በነገራችን ላይ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ ከዚህ ከፍ ያለ ማዕረግ ያለው እሼ ግደይ (በቅፅል ስሙ ሻቢያ) የሚባል ሰሙን አልናገርም ብሎ ህዝብ በተሰበሰበበት ተሳድቦ፣ ይህ ስድብ እኔን ሳይሆን የምክር ቤቱን ክብር የነካ ነው ብዬ ከስሼው ነበር፡፡ በኋላ ላይ የምክር ቤት አባል መሆናቸውን አልተናገሩም እንዳውም ተሳድበዋል የሚል ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል በሚያስብል መልኩ መከላከል ጀምሮ ነበር፡፡ የዛሬው ረዳት ኢንስፔክተር አልተሳደቡም ሰደበኝም አላሉም በዚህ አደንቃቸዋለሁ፡፡
ወደ ዝርዝር ድራማው ከመግባቴ በፊት ግን አንድ ነገር ማለት ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ የተገልጋዩን መታወቂያ እያገላበጡ የሚያዩ አገልጋይ ነን እያሉ የሚመፃደቁ ሁሉ በህግ አምላክ ስማችሁን ቢቻል ከነፎቶ የሚገልፅ ነገር በደረታችሁ ላይ አድርጉልን፡፡ ይህን የሚመለከተው አካል ይህን ጉዳይ በአሰቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን ያድርግልን እላለሁ፡፡ እዛው በምዝገባ ላይ ከነበረች ረዳት ሳጅን (ሰሜ አስቴር ነው ብላኛለች) እንደሰማሁት ባጁ አለ የሚል ነው፡፡ ከፍተኛ የመንግሰት ሀብት ወጥቶበት ከተዘጋጀ በኋላ ለምን እንደማይደረግ ግን መልስ እንፈልጋለን፡፡ በነገራችሁ ላይ በደርግ ጊዜ ፖሊሱ ሁሉ የመለያ ቁጥር በደረቱ ላይ ያደርግ ነበር፡፡
ከላይ እንደገለፅኩላችሁ ሲጠቃቀሱ የነበሩት ዘቦች ጠጋ ብዬ በቀልድ ዓይነት ልክ ናችሁ በቴሌቪዥን የምታዩኝ ግርማ ነኝ ብዬ ተቀላቀልኳቸው፡፡ መዋሸት ጀመሩ እኛ ሰለአንተ አልተነጋገርንም ብለው በአድማ ዋሹ፤ ችግር የለም ብዬ መንጃ ፍቃድ ሰጠዋቸው ስሜን ተመልክተው እርግጠኛ ከሆኑ በኋላ የቀበሌ መታወቂያ አምጣ አሉኝ፤ ለምን? አልኳቸው፣ በዚህ አናስገባም፡፡ ሌላ ጊዜ በዚህ ነው የምገባው ብል የሚሰማኝ አጣው፡፡ ደግነቱ መኪናዬ ውስጥ የቀበሌም የምክር ቤትም መታወቂያ ስለያዝኩኝ ሄጄ አምጥቼ ይህው የቀበሌ መታወቂያ ብዬ ሳሳይ አማረልኝ ያለች አንዷ ገብቶሃል ቁጭ በል የሚል ትዕዛዝ ሰጠችኝ፣ አልገባኝም፣ ስላት በሚገባህ ቋንቋ ይነገርሃል ብላ ተናግራ ልታናግረኝ ዘለግ ካለም ልታስፈራራኝ ስትፈልግ፣ የምችለው ቋንቋ አማርኛ ነው ከዚህ ሌላ ካለሽ አምጭ አልኳት፡፡ አታካሮው በዚህ አበቃ ይህች ሴት በዛው ሄዳ ቀረች፡፡ ከጀርባ ሄዳ እሼ ግደይ (ሻቢያ) እንዳደረገው ልትከሰኝ ማለት ነው፡፡ ይህ አካሄድ ተቋማዊ እንደሆነ የገባኝ በኋላ ነው፡፡
እኔም በረዳት ኢንስፔክተሩ ትዕዛዝ መሰረት ሰልክ ተደውሎ እስኪፈቀድ ቆይ ተባልኩ፣ እሺ ብዬ ቁጭ ብዬ ስጠብቅ 45 ደቂቃ ቆየው፡፡ በዚህ ቆይታዬ አጠገቢ ካለው ኢንስፔክተር ጋር ለምን ሰሙን እንደማይነግረኝ፣ ይህ ደግሞ ተገቢ እንዳልሆነ፣ እየነገርኩት እርሱም ባይለጠፍ ችግር እንደሌለው ሲያስረዳኝ ቆይቶም ሲሰለቸው እንደሚያጣራ ሄዶ ሲጠፋ ጊዜውን ገደልነው፡፡ በመሃሉ ሌሎች ተሰተናጋጆች መጥተው ሲገቡ ሲወጡ እያየሁ አንድ ጥያቄ ጠየኩት ለምንድነው መንጃ ፍቃድ አይሆንም ያልከኝ? እዚህ ቁጭ ብዬ በመንጃ ፍቃድ ሌሎች እየገቡ አይቻለሁ አልኩት፡፡ እዚህ ድረስ መጥተው ሰዎች እንዳይጉላሉ ነው ብሎኝ አረፈው፡፡ የምክር ቤት አባል አጉላሉ ተብላችኋል ወይ? ብዬ ያልጠበቀውን ጥያቄ ዱብ ሳደርግ አጠገቤ የነበረችው መዝጋቢ ሳጅን አይደለም እኔ አላውቅህም እነርሱ ግን ስላወቁ የሚያጠሩት ነገር እስኪያጣሩ ብሎ ነው ተወው ብላኝ ቅድም ስለ አንተ አልተነጋገርንም ብለው የዋሹትን አጋለጠች፡፡ እኔም በዚሁ አበቃው፡፡ ድንገት ሌላ ሴት መጥታ በዋናው በር ይሂዱ! አይናደዱ ብላኝ ወደ ዋናው በር አመራሁ፡፡ በሩ ስደርስ፤
ወዴት ነው? የሚል ጥያቄ በአንድ ታዛ ስር ያለች ሴት ፖሊስ አቀረበችልኝ፡፡
እስረኛ ልጠይቅ፡፡
በዚህ ነው የሚጠየቀው? ብላ ስትጠይቀኝ
በመጠየቂያው በኩል በዚህ ሂድ ተብዬ ነው ብዬ መለስኩ፡፡
ለምን?
ለምን እንደሆነ የሚያውቁት ወደዚህ እንድሄድ የላኩኝ ናቸው፡፡ በዛ በኩል ተከለከልኩ በዚህ እንድሄድ ታዘዝኩ፡፡
አትናደድ ከተናደድክም እዚሁ ጨርስና ትገባለህ ብላኝ እንደገና ታናድደኝ ገባች፡፡
አሁን እንግዲህ ሌላ እላፊ ቃል እንዳትናገር በሚል የምክር ቤት አባል መሆኔን የሚያሳይ መታወቂያ ሰጠኋት መታወቂያዬን ይዛ ወደ ውስጥ ገባችና ተመልሳ መጥታ ይግቡ አለችኝ፡፡ ውስጥ ስገባ ወደዚህ ወደዚህ ብለው አንድ ዘብ መድበው ከአንዱዓለም ጋር አገናኙኝ፡፡ እውነት እላችሁ አለው ከአንዱዓም ጋር ብዙ መጫወት አልቻልንም፡፡ ርዕዮትንም መጠየቅ ሰዓት ረፈደ፡፡ እንደዚህ አድርገው አዋክበው ስልችቶን እንድንቀር፣ ጠያቂ አጣው ብሎ አንዱዓለምን ተስፋ እንዲቆርጥ ነው እቅዱ፡፡ ከአንዱዓለም ጋር የምናወራውን የሚያደምጠው ዘብ መውጣት ስለምፈልግ ከመውጣቴ በፊት ግን የተቋሙን ኃላፊ ማግኘት እፈልጋለሁ፣ ዝም ብዬ ከዚህ ግቢ አልወጣም ስለው ደውሎ ሐጎስ የሚባል ስው ጠራላኝ፡፡
እኔ ቢሮ ውስጥ ሆኜ በስርዓቱ ነበር መነጋገር የፈለኩት፡፡ አንዱዓለም እንዲገባ ተደርጎ እዛው በቆምኩበት ለምን እንደዚህ እንደሚደረግ ቢቻል በክብር ካልተቻለ እንደ ዜጋ ለምንድነው የማልስተናገደው የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ በር ላይ ያሉት አሰተናጋጆች የምክር ቤት አባላት እንዴት እንደሚስተናገዱ ስለማያውቁ ነው፡፡ እኛ በስነ ስርዓት ለማስተናገድ ብለን የበላይ አካል ጠይቀን ነው የምናስገባው (ልብ ቡሉ የበላይ አካል ጠይቀን የሚለውን) አቶ ግርማ እርሶ ያውቃሉ ለምን እንደታሰረ፣ እርሶም ትንሽ ትዕግሰት ቢያደርጉ ጥሩ ነው በር ላይ ካሉ ሰዎች ጋር ለምን ይጨቃጨቃሉ፡፡ ይቅር ብለን ነው እንጂ ስብዕናዬን ነክቶኛል ብለው አቤት ብለዋል ብሎ አረዳኝ፡፡ እሼ (ሻቢያ ትዝ አለኝ) ሰዎቹ ይጠሩ አልኩና ተጠርተው መጡ (በር ላይ በሚገባህ ቋንቋ ብላ የተሰወረችው ዘብና መግቢያ ላይ እትናደድ እያለች የማላቀውን ጥያቄ ስትጠይቀኝ እና ስታናድደኝ የነበረች ብዙዬ የምትባል ሴት መጡ) ምን እንዳደረኩ ሲጠየቁ ሲናገሩ ይቆጣሉ ወደሚል ዝቅ ብሎ እነርሱን አሰናበታቸውና ከዛሬ ጀምሮ እስረኛ ለመጠየቅ ሰመጣ ሐጎስ ብዬ በዋናው በር ብቻ እንድመጣ በዚሁ መሰረት እንደ ምክር ቤት አባል ወንበር ተዘጋጅቶልኝ እንደምስተናገድ መመሪያ ተሰጠኝ፡፡
የዛኑ ዕለት ሪፖርት ጋዜጣ ላይ ክቡር ሚኒስትር በሚል ርዕስ ስር ያነበብኩት ትዝ አለኝ፡፡ ተጠሪ ወደ አልሆኑበት ተቋም እየደወሉ የስራ መመሪያ የሚቀበሉ፣ በማያገባቸው ገብተው መመሪያ የሚሰጡ እንዳሉ በፌዝ አድርጎ ይነግረን ነበር፡፡ የቃሊቲ የበላይ አካል ማን ነው? ይህ ስው ከቃሊት ተደውሎለት የተከበሩ አቶ ግርማ ሠይፉ መጥተዋል እናስገባቸው? ወይስ አናስገባቸው? ተብሎ የሚጠየቀው ከውጤቱ እንደተረዳሁት ይህ ሰው የሰጠው መልስ አስገቧቸው ግን አጠገባቸው ሰው መድቡና ምን እንደሚያወሩ አድምጡ ነው የሚለው፡፡ ይህ ምን ያህል ውርደት እንደሆነ ለሚያዘውም ለሚታዘዘውም ግልፅ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ሐጎስ ያለኝ በምን እንደታሰረ ታውቃለህ ነው ያለኝ፡፡ አዎ አውቃለሁ አንዱዓለም ሲሰርቅ፣ ቦንብ ሲያፈነዳ አልተያዘም ባለው የፖለቲካ አቋም እንደታሰረ እና የፖለቲካ እስረኛ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ለዚህም ነው ከአምስት እስረኛ በተለየ ሁኔታ አንዱዓለምን ልንጠይቅ የምንታገደው፡፡ ሐጎስ ግን አንዱዓለም ይህን ጥያቄ ሲጠይቀኝ ምን አስቦ ይሆን፡፡ አንዱዓለም አሽባሪ ነው ብሎ አያምንም፡፡ ለነገሩ የማረሚያ (ለእነ አንዱዓለም እስር ቤት) ስራው የመጣለትን እስረኛ መጠበቅ ብቻ ነው መሆን ያለበት እንጂ ለምን እንደመጡ ማወቅ ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ እረ በህግ፣ መታሰራችን አንሶ መጠየቅ ስንከለከል፣ ወይም መጎላላት ሲደርስብን ወዴት ነው ልትገፉን የምትፈልጉት? ብለን ለመጠየቅ ግድ ይለናል፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግሰት አንቀፅ 21 በጥበቃ ስር ስላሉ ዜጎች ግልፅ ድንጋጌ አለው፡፡ ከዚህ በተፃራሪ የተፃፈ ህግ፣ መመሪያ ደንብ፣ ወዘተ ህገ መንግሰቱን እንደመናድ ይቆጠራል፡፡ ከሳሾቻችን ህገ መንግሰቱን ስለ ማክበርና ማስከበር በህገ መንግሰቱ አንቀፅ 9 ማንበብና ተግባራዊ ማድረግ ግድ ይላችኋል፡፡
Top of Form

No comments:

Post a Comment