Wednesday, August 7, 2013

አንድነት በጠ/ሚ ኃይለማርያም የትውልድ ቦታ ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳላካሂድ ተከለከልኩ አለ

በዘሪሁን ሙሉጌታ

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የትውልድ ቦታ በሆነው ወላይታ ሶዶ ከተማ ሐምሌ 28 ቀን 2005 ዓ.ም በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የተጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳይካሄድ መደረጉ ጥያቄ አስነሳ።
የፓርቲው የደቡብ ቀጠና ኃላፊና የብሔራዊ ም/ቤት አባል አቶ ዳንኤል ሺበሺ በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገሩት ፓርቲው በአርባምንጭ ከተማ በበርካታ ችግሮች ውስጥ ሆኖ የተሳካ ሰላማዊ ሰልፍ ቢያካሂድም በወላይታ ግን ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳያደርግ የተለያዩ መሰናክሎች መፈጠራቸውን ተናግረዋል።
በከተማዋ ፓርቲው ሕዝባዊ ስብሰባውን እንዲያካሂድ የተደረገው ሆን ተብሎ ከፌዴራል በወረደ መመሪያ መሆኑን በመግለፅ የማፍያ ተግባር ተፈፅሞብናል ሲሉ አቶ ዳንኤል አማረዋል። በከተማዋ ሕዝባዊ ስብሰባ የሚካሄድበትን አዳራሽ ከተፈቀደ በኋላ የአዳራሹ የመግቢያ በር ቁልፍ በመሰወር፣ ታርጋ በሌላቸው ሞተር ሳይክሎች በሰፈር ወሮበሎች አማካኝነት ወከባ ተፈፅሞብናል፣ የምንበትነውን የበረራ ወረቀት ተነጥቀናል ብለዋል።
ሕዝባዊ ስብሰባውን ከሚያስተባብሩ መካከል ሦስት ሰዎች መታሰራቸውንና ከሦስቱ ደግሞ አንዷ ሴት መሆኗን ተናግረዋል። በከተማዋ ሕዝቡን እንዳይቀሰቅሱ ጄኔሬተር እንዳያከራዩ መደረጉን፣ የሕዝብ መቀስቀሻ ሞንታርቦ መዘረፋቸውንም አያይዘው ገልፀዋል።
‘‘የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የትውልድ ቦታ ይህንን የመሰለ አሳፋሪ ተግባር መፈፀሙ ያሳዝናል’’ ያሉት አቶ ዳንኤል ፓርቲው በቀጣይ በዞኑ በተለየ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ የሞት ሽረት እንደሚያደርግ አመልክተዋል። ከፍተኛ የፓርቲ አመራሩን ጨምሮ ጋዜጠኞችና ዲፕሎማቶችን ወደ ከተማዋ በመጋበዝ ትግሉ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። 
በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ 735 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው የጅንካ ከተማ ሰላማዊ ሰልፉ መካሄዱን በስፍራው ያመሩት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ ተናግረዋል። እንደ አቶ ዳንኤል ገለፃ ሰላማዊ ሰልፉ ከመካሄዱ በፊት ሕዝቡ በሰልፉ እንዳይሳተፍ ከፍተኛ ቅስቀሳ ቢካሄድም በተደረገው እልህ አስጨራሽ ድርድርና በሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፎ ጭምር ሰልፉ በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ውስጥ ሆኖ መካሄዱን አመልክተዋል። በከተማዋ ከሰሞኑ የሼህ ኑሩ ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪው ገዳይ ከጅንካ ከተማ በመሄድ ግድያውን ፈፅሟል በመባሉ ሽብር ይቀሰቀሳል በሚል ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሮ እንደነበር አመልክተዋል። ያም ሆኖ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከ5ሺ ያላነሰ ሕዝብ መውጣቱ ይህም በከተማዋ የተቃዋሚ ፓርቲ ሰልፍ ሲጠራ የመጀመሪያ ከመሆኑ አንፃር አጥጋቢ እንደነበርም አያይዘው ገልፀዋል።
በተያያዘ ፓርቲው በባህርዳር ከተማ በተመሳሳይ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂዷል። ይሄንን ሰላማዊ ሰልፍ የመሩት አቶ አስራት ጣሴ ሰልፉ ውጤታማ ሊባል የሚችል እንደነበር ገልፀዋል። ከ50ሺህ ያላነሰ ሕዝብ ዝናብ ሳይበግረው ወጥቶ ጥያቄዎቹን በልዩ ልዩ መፈክር ማሰማቱን ገልፀዋል።
በተመሳሳይ ሐምሌ 28 ቀን 2005 ዓ.ም ፓርቲው በመቀሌ ሰላማዊ ሰልፍ ቢጠራም የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ሰልፉን እንዳይካሄድ መደረጉን ፓርቲው አስታውቋል።
ፓርቲው ባወጣው የሦስት ወር ሕዝባዊ ንቅናቄ መሠረት በቀጣይ በኦሮምያ ከተሞች በወሊሶ፣ በናዝሬት (አዳማ) በፍቼና በባሌ ሰላማዊ ሰልፎች የሚካሄዱ ሲሆን በአምቦ፣ በሐዋሳና በደብረማርቆስ የአዳራሽ ውስጥ ስብሰባ ይደረጋል፤ በተመሳሳይ በድሬዳዋ በአሶሳና በጋምቤላ ሰላማዊ ሰልፍ በነሐሴ ወር እንደሚከናወን እና የንቅናቄው ማጠቃለያ መስከረም 5 ቀን 2006 በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑንም ከአቶ ዳንኤል ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።
በወላይታ የተከለከለውን ሕዝባዊ ስብሰባ ምክንያት ለማወቅ የዞኑ ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት የኃላፊዎቹ የግል ስልካቸው ባለመነሳቱ ሊሳካ አልቻለም።

ሰንደቅ ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment