Monday, August 5, 2013

ያልተዘመረለት ጀግና – አብዲሳ አጋ

Meseret Bitsu

Posted by መቲ

አብዲሳ አጋ ጣልያን በአድዋ የደረሰበትን ሽንፈት
ለመበቀል ባደረገው 1928. ወረራ ወቅት
በምርኮኝነት ጣልያን ተወስዶ ከታሰረ በኋላ የተሰጠውን
ብርድልብስ ቀዳዶ በመቀጣጠል በመስኮት በኩል
ማምለጡ ጎልቶ የሚወሳለት አርበኛ ነበር። ተሳክቶለት
ቢያመልጥ እንግዳ የሆነ አገር እንደሚቀላቀል እና
ለሃገሩም እሩቅ መሆኑን እያወቀ እንኳን ነጻነቱን አሳልፎ
ላለመስጠት በሚል ብልጠት በታከለበት ሁኔታ ያመለጠው
አብዲሳ አጋ አስገራሚ ጀግንነቱን ያሳየው ከእስር ቤቱ
ካመለጠ በኋላ ነበር።

በኦሮሚያ ወለጋ የተወለደው አብዲሳ የኢትዮጲያን ጦር
የተቀላቀለው 14 አመቱ ሲሆን ጣልያን ኢትዮጲያን
ስትወር አገሩን ለመከላከል በውጊያ ላይ በአስደናቂ ወኔ
ይዋጋ ነበር። በውጊያ ከተማረከ በኋላ ጣልያኖች
አገራቸው ወስደው በሲሲሊ ደሴት ላይ ባሰሩት ግዜ ነበር
አብሮት የታሰረውን የዩጎዝላቪያ ምርኮኛ ሁሊዮ
የተወዳጀው። በጋራ እቅድ ካወጡ በኋላ ከእስር ቤት
ያመለጡት እነ አብዲሳ በሲሲሊ ደሴት ላይ ተደብቀው
አልተቀመጡም። ካመለጡ ከጥቂት ቀናት በኋላ
በአብዲሳ መሪነት እና እቅድ አውጪነት በሌሊት ታስረው
ወደነበረበት እስር ቤት በመሄድ እና ጥቃት በመፈጸም
የታሰሩትን እስረኞች ነጻ በማውጣት የኢትዮጲያውያንን
ጀግንነት በአድዋ ብቻ ሳይሆን በጣልያን ምድርም
ያስመሰከረ ድንቅ ተዋጊ ነበር።
የአብዲሳ ጀግንነት በዚህ አላበቃም ከእስር ቤት
ያስመለጧቸውን ሰዎች በማሰባሰብ የራሱን ጦር ካደራጀ
በኋላ ጣልያኖችን በገዛ አገራቸው ያንቆራጥጣቸው ገባ።
ከአድዋ ጀምሮ የኢትዮጲያውያንን ወኔ የተረዱት
ጣልያኖች የአብዲሳን ጦር በፍርሃት ያዩ የነበረ ሲሆን
በተለያዩ ቦታዎች ከጣልያን ጦር ጋር በመዋጋት ብዙ
ድሎችን እያስመዘገበ ነበር። ቆራጥነቱን የተረዱት
ጣልያኖች የሚያረጉት ግራ ቢገባቸው ከበርካታ ስጦታዎች
ጋር ጦሩን ይዞ የጣልያንን ሰራዊት እንዲቀላቀል
መማጸን ጀምረው ነበር። ለፋሺስት ጦር መዋጋት አገር
መክዳት እንደሆነ አስረግጦ የተናገረው አብዲሳ ትግሉን
አፋፍሞ በቀጠለበት ወቅት የሁለተኛው የአለም ጦርነት
ተቀሰቀሰ።
የተባበሩት የአሜሪካ እና እንግሊዝ መንግስታት ከጀርመን
ጋር ያበረችውን ጣልያንን እየተዋጉ በነበረ ሰዓት ስለ
አብዲሳ ዝና ከሰሙ በኋላ ለጦሩ የሚገባውን ድጋፍ
በማድረግ ፋሺስት ስራቱን ለማዳከም እንደ ዋንኛ መንገድ
ሆኗቸው ነበር። በድጋፉ በመጠናከርም የጣልያንን
ሰራዊት ድባቅ በመምታት ጦሩን እየመራ ሮም ከተማ
ከአሜሪካኖቹ ሁላ ቀድሞ የኢትዮጲያን ባንዲራ
እያውለበለበ የገባው ጀግናው አብዲሳ አጋ ነበር። በኋላ
ሮም የደረሰው የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ እና የአሜሪካ ጦር
አብዲሳን በማሞካሸት ከተጨማሪ ወታደሮች ጋር
በአለም አቀፉ ህብረት ስር የሚመራ ጦር መሪ አድርገው
ሾመውት ነበር።
በኋላም ጀርመንን ለማሸነፍ በሚደረገው የመጨረሻ
ውጊያ ወቅት የአብዲሳ አመራር መኖር ያመኑበት
እንግሊዞች ወደ ጀርመን ልከውት ግዳጁን በሚገባ
በመወጣት የኢትዮጲያን ባንዲራ ከእጁ ሳይለይ በርካታ
የጀርመን ከተሞችን ነጻ ማውጣት ችሎ ነበር። ከጦርነቱ
መገባደድ በኋላም የእንግሊዝ፣ የካናዳ እና የአሜሪካ
መንግስታት ጦራቸውን ተቀላቅሎ እንዲቀጥል በርካታ
ጥቅማ ጥቅሞችን አቅርበውለት ነበር። እብዲሳ ግን
ኢትዮጲያ ምንም ያህል ድሃ ብትሆንም ህዝቡን እና
መንግስቱን ጥሎ እንደማይሄድ አስረግጦ በመናገር
ጥያቄውን ውድቅ አደረገ። በዚህ የተናደዱ
ምዕራብውያንም በፈጠራ ወንጀል ከሰው ወደ እስር ቤት
አስገብተውት ነበር። በኋላም እስሩ ወደ ገንዘብ ቅጣት
ተቀይሮ ከተከፈለ በኋላ በክብር ወደ ሃገሩ ሊመለስ
ችሏል።
ወደ ኢትዮጲያ ከተመለሰ በኋላ ሰራዊቱን በቅንነት
ያገለገለው አብዲሳ በኮረኔልነት ማዕረግ የአጼ ሃይለስላሴ
ልዩ ጠባቂ ጦር እየመራ ቆይቶ ንጉሱ ከስልጣን ከወረዱ
ከጥቂት አመታት በኋላ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።
የአብዲሳ አጋን ሙሉ የህይወት ታሪክ በደንብ ማወቅ
ከፈለጉበኢጣሊያ በረሃዎች (ሻምበል አብዲሳ አጋ
በአርበኝነት ጀብዱ የሰራ ኢትዮጵያዊ ታሪክ) “ የተሰኘ
የህይወት ታሪክ መጽኃፉን ማንበብ ይችላሉ።

No comments:

Post a Comment