በክፍሉ ሁሴን
የአቶ አማረ አረጋዊ ጋዜጣ ብቻ እንዲዘግበው በተፈቀደው መሰረት በቀደም ሶማሊያ ላይ ተከስክሶ የሰዎች ሕይወት የጠፋበት አንቶኖቭ 12 የተባለው ሩሲያ ሰራሽ አውሮፕላን አደጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁለተኛው አደጋ መሆኑን እ.ኤ አ በኦገስት 11,2013 ባሰፈረው ዘገባው ይነግረናል።ሌሎች ይህን ቢዘግቡት ምስጢር በማባከን የ”ብሔራዊ ደህንነትን”ሆነ ብሎ አደጋ ላይ በመጣል ወይም በዚያ በፈረደበት የሽብርተኛ ፍርደ ገምድል ሕግ ዘብጢያ ይወርዱ ነበር።ያም ሆነ ይህ ሪፖርተር በአንቶኖቩ ላይ ይህ አደጋ ከመከሰቱ ጥቂት ቀናት በፊት ሌላ ኤል 100 የተባለ የ”አየር ሃይሉ”አውሮፕላን እዚያው ሶማሊያ ተከስክሶ መሰባበሩንና አብራሪዎቹም የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው በሕክምና ላይ እንደሆኑ፤የዚያ አውሮፕላን ዳፋም ስብርባሪውን ሊያመጣ ለሄደው ለዚህኛው አንቶኖቭ እንደተረፈው ዘግቧል።በነፃ ጋዜጣ ስም የቁርጥ ቀን የወያኔ አፈ ቀላጤነቱን የማይዘነጋው ሪፖርተር የ”አየር ሃይሉ”አውሮፕላኖች እንደደርግ ጊዜ ሳይተኮስባቸውና ቦምብ ሳይቀበርባቸው ባገር ጤና በየሳምንቱ በየሄዱበት ባፍጢማቸው ለምን እንደሚደፉ አጠያይቆ ሊዘግብ አልሞከረም።እሱ ባይዘግብ እኛ እንጠያይቅና የመጠይቃችንን ውጤት እንመልከተዋ!
በቅድሚያ ሪፖርተር ከአንቶኖቩ አደጋ ጥቂት ቀናት በፊት አደጋ ደርሶበት ነበር ባለው ኤል 100 በተባለው አውሮፕላን እንጀምር።ይህ አሜሪካን ሰራሽ አውሮፕላን የፋብሪካ ስሙ ሄርኩለስ ሲሆን በዚሁ መጠሪያ ስም ቀደም ብሎ የተፈበረከና በወታደራዊ የመጓጓዣና የጭነት አገልግሎት አሰጣጡ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው ሲ 130 ተብሎ የሚጠራው ተከታይና ዘመናዊ አውሮፕላን ነው።የማሞ ውድነህን “ዘጠና ደቂቃ በኢንቴቤ”ትርጉም ደህና አድርጐ ያነበበ የዚህን ወታደራዊ የአየር አጋሰስ ጥቅም ይገነዘባል።ለማንኛውም ኢትዮጲያ ብዛታቸው ሁለት የሆኑ ሄርኩለስ ኤል 100 የተባለውን አውሮፕላን የገዛችው በደርግ ጊዜ በ1980 ዓ.ም ነበር።የመንግስቱ ኃ/ማርያም ደርግ ይከተል በነበረው ፖለቲካ ከሶቭዬት ሕብረት ጋር እፍ ያለ ፍቅር ላይ ስለነበር ከአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን መግዛት በዚያን ጊዜ የማይታሰብ ነበር።አንደኛ “አባት አገር” ሶቪዬት ቢሰማ መቀየም ብቻ ሳይሆን ክፉኛ ተቀይሞ ሊያደርግ የሚችለው አይታወቅም ነበር።ሁለተኛ አሜሪካም ኮሚኒስት ነው ብላ ለምታወግዘው መንግስቱ ኃ/ማሪያም የአቋም ለውጥ በማሳየት ወደሷ ካምፕ ሳይገባ አውሮፕላኑን ለወታደራዊ አገልግሎት መሸጥ አይመቻትም ነበር።እናም ሄርኩለስ ኤል 100 የተፈለገው በሻዕቢያ እጅ እየወደቀ ባለው ኤርትራ ክፍለሃገር ላለው የጦር ኃይል በዋነኛነት እንዲሁም ለሲቪሉም ሕዝብ ጭምር ስንቅና ድርጅት ሩሲያ ሰራሹ አንቶኖቭ ሊወጣው ያልቻለውን በምሽትም ጭምር ድምፅ ሳያሰማ የተቀላጠፈ ምልልስ (shuttle ) እያደረገ ድጋፍ እንዲሰጥ ቢሆንም በኢትዮጲያ አየር መንገድ ስም ለንግድ ጭነት አገልግሎት (cargo service ) በሚል ሽፋን ተገዛ።
የመጀመሪያዎቹ የኤል 100 ፓይለቶች በቀድሞው የኢትዮጲያ አየር ሃይል ከድምፅ የፈጠኑ ተዋጊ አውሮፕላኖችንም (super-sonic fighter jets ) ጨምሮ በርካታ ልዩ ልዩ አውሮፕላኖችንና ሄሊኮፕተሮችን የበረሩ፤በበረራ አስተማሪነትና አዛዥነት ወዘተ ከፍተኛ ስልጠናና ልምድ ያካበቱ ሲሆኑ ወደአየር መንገድ እንዲዛወሩ ተደርጎ በአየር መንገዱ ስም ቀድሞ በንጉሱ ጊዜ በወጣትነታቸው ስልጠና ወደወሰዱባት አሜሪካ ከብዙ አመታት በኋላ በድጋሚ ተላኩ።እናም ከአንድ ወር ስልጠና በኋላ ተመልሰው በደርግ ዝርክርክነት ከቀን ወደቀን በሻዕቢያ እጅ በወደቀችው ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ዮሐንስ አራተኛ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሻዕቢያ ከያዘው ከፍተኛ ነጥብ ተኩስ እያዘነበባቸውም ጦሩንና ሲቪሉን ያላንዳች የአውሮፕላን አደጋና የሰው ሕይወት መጥፋት እጅግ ብዙ ምልልስ እያደረጉ ሲቀልቡና ሲደግፉ ከረሙ።”ጩኸን ጩኸን እንዳልጮኸነ ሆነ”እንዳለው መፅሃፉ በመለዮ ለባሽነትም ሆነ በሲቪል ፓይለት የደንብ ልብስ አገራቸውን ከልብ እንዳላገለገሉ አብዛኞቹ ኤል 100ን ለመጀመሪያ ጊዜ ይበሩ የነበሩት እነዚህ ፓይለቶች በበቀለኛው ወያኔ እስር ቤት ተወረወሩ።አውሮፕላኖቹንም ለተወሰነ ጊዜ አየር መንገዱ እንደተባበሩት መንግስታት የምግብ ድርጅት ያለ ተቋም ሲያከራይ ቆይቶ በሽያጭ ይሁን በዝውውር መልክ ከአየርመንገዱ አገልግሎት ወጡ (phased out) ተባለ።በምንም መልክ ይሁን በወያኔ “አየር ሃይል”ቁጥጥር ስር እያለ ሪፖርተር ከአንቶኖቩ በፊት ሶማሊያ ላይ ተፈጥፍጦ ተሰባበረ የሚለን ኤል 100 አውሮፕላን በዚህ መልክ የተገኘ የአገሪቱ አንጡራ ሃብት ነበር።
በአቪዬሽን አደጋ አለ፤በወያኔ “አየር ሃይል“ግን ለምን በረታ?
ኢትዮጲያ በአቪዬሽን መስክ ራሷን ለመቻል ጥረት የጀመረችው ከጣሊያን ወረራ በፊት መሆኑንና ይህም የማይጨው ጦርነት ተብሎ በሚታወቀው ሁለተኛው የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ምክንያት ገና በእንጭጩ እንዳለ መቀጨቱን ታሪክ ይነግረናል።በአድዋ ጦርነት አይዋረዱ መዋረድ የተዋረደው ፋሺስት ኢጣሊያ ቁጭቱን ለመወጣት ኢትዮጲያ በዚያን ጊዜ ባልነበራት የአየር የበላይነት ተጠቅሞ በርካታ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች አሰማርቶ ከአለም አቀፍ ሕግ ውጭ ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ መርዝ በማዝነብ ለጊዜው ውጊያውን አሸነፈ።
ውጊያውን ቢያሸንፍም በአርበኞቻችን አማካይነት የእምቢ ባይነት ጦርነቱ ሲቀጥል፤
“ተአበሻ ጠሎት ጣሊያኖች በለጡ
ባርባ ዘመናቸው ክንፍ አውጥተው መጡ።”ከሚል ቁጭት ጋር ኢትዮጲያ ዳግም ነጻነቷን ስትቀዳጅ ከምንም በፊት ጠንካራ የአየር መከላከያ እንደሚያስፈልጋት ንግግር ሳያስፈልገው የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር።በዚህ መንፈስም የኢትዮጲያ ንጉሰ ነገሥት መንግስት አየር ሃይል (Imperial Ethiopian Air Force ) ተቋቋመ።ንጉሱ የሚወቀሱበት ሌላ የፈለገ ምክንያት ቢኖር በዚህ ረገድ የሰሩት ስራ እጅግ በጣም የሚያስመሰግናቸው እንደሆነ ዛሬ ላይ ሆነን በቁጭት እናነሳዋለን።
ንጉሱን በመስከረም 1967 ከዙፋናቸው ያወረደው ለውጥ ሲመጣ በአሜሪካ አመራር ላይ የነበረው የጂሚ ካርተር አስተዳደር ኢትዮጲያ የከፈለችበትን የጦር መሳሪያ ጭምር ሳይቀር በችኮላ ውሳኔ ሲከለክል ከሶማሊያ ወረራ ጋር የተፋጠጠው ደርግ መሳሪያ ለማግኘት ወደሶቪዬት ሕብረት ፊቱን እንዲያዞር ተገደደ።የንጉሱ መንግስት ከአሜሪካ ጋር የነበረው ግንኙነት ሁሉ አልጋ ባልጋ ነበር ለማለት ባይቻልም አሜሪካኖቹም ሆኑ ከነሱ በፊት አየር ሃይሉን በዘመናዊ መልክ እንዲቋቋም በመጀመሪያ የረዱን ስዊዲኖች ለኢትዮጲያውያን አየር ሃይል ባልደረቦቻችን ያላቸውን የቴክኒክ እውቀት ሳይደብቁ ያለምንም ተንኮል አካፍለዋል።ከዘረኛነት ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎም ተንኮል ሲያጋጥም የኢትዮጲያ አየር ሃይል ባልደረቦችም ሆኑ በኋላ በሲቪልነት ተዛውረው አየርመንገዱን ያቋቋሙት ባልደረቦች ትህትናን ተላብሰው እውቀትን በመሸመትና ቴክኒካዊ ክህሎትን በማዳበር በኢትዮጲያ በማቆጥቆጥ ላይ ያለውን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ባስቸኳይ ከፈረንጆቹ እጅ አውጥተው በኢትዮጲያውኖች እጅ እንዲያስገቡትና እንዲያጎለብቱት ይበረታቱ ነበር።በመሆኑም ለረጅም ጊዜ የበረራ ማስተማሪያ ሆነው ያገለገሉትን ስዊድን ሰራሽ ሳብ ሳፊር አውሮፕላኖች ከስዊድን ድረስ እያበረሩ በማምጣት በኢትዮጲያውያን የበረራ አስተማሪዎችና አዛዦች ከኢትዮጲያ አልፈው የሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገሮች አየር ሃይል ፓይለቶችን ያሰለጠኑ ስመጥር ኢትዮጲያውያን ፓይለቶችን ማፍራት ተችሎ ነበር።የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ እያደገ በሄደ መጠንና ከዚሁ አዲሱ ቴክኖሎጂ ጋር መተዋወቅ ሲያስፈልግ በንጉሱ ጊዜ የነበሩት ፓይለቶችም ሆኑ ሌሎች የአየር ሃይሉ ባልደረቦች በየጊዜው ወደአሜሪካ እየተላኩ በልብሙሉነት መንፈስ ትህትናን ተላብሰው ከአሜሪካ አቻዎቻቸው የሚሰጣቸውን ስልጠና ባጥጋቢ ውጤት እያጠናቀቁ በመመለስ ይህንኑ እውቀታቸውን ለበታቾቸውና ለአዲስ ምልምል ቅጥሮች ያላንዳች ችግር ያካፍሉ ነበር።
ይህ ጸሃፊ ከአየር ሃይል ወደኢትዮጲያ ምድር ጦር አየር ክፍል (Army Aviation ) ተዛውሮ በዚህ መልክ ከአንድም ሁለቴ ሄዶ በመሰልጠን ከአሜሪካኖቹ እጅ የበረራ አስተማሪነት ብቃት የምስክር ወረቀት ያገኘና የዩናይትድ ስቴትስ ምድር ጦር አየር ክፍል አብራሪን ክንፍ (United States Army Aviator Wing ) ከኢትዮጲያ ንጉሰ ነገሥት መንግስት አየር ሃይል ክንፍ ጋር በደረቱ ላይ መሳ ለመሳ እንዲያደርግ የተፈቀደለትን አንድ የቀድሞ መኮንን በቅርብ ያውቅ ስለነበር ከሟቹ መኮንን ጋር በነበረው ቅርበትና ባገር ልጅነቱም እጅግ ይኮራል።አየር ሃይላችን ( የቀድሞውን ማለቴ ነው) እንደሟቹ መኮንን የመሳሰሉና ከሱም የበላለጡ በርካታ መኮንኖችን የአካልና የሕይወት መስዋዕትነትን በጠየቀ ሁኔታም ጭምር አፍርቶ ነበር።
ምንም እንኳ በንጉሱ ጊዜ የነበረው አየር ሃይል አመሰራረቱም ሆነ አስተዳደሩ ሙያዊ (professional ) በሆነ መንገድ ቢሆንም ገና ጀማሪ ከመሆን በሚመጣ ልምድ ማነስ እንዲሁም በጊዜው ከነበረው ቴክኖሎጂ ኋላቀርነት የተነሳ፤ከሁሉም በላይ ደግሞ አቪዬሽን ምንም ግቡ ፍጹም በተረጋገጠ ደህንነት (absolute safety ) አገልግሎት መስጠት ቢሆንም በባህሪው በስሌት ከታሰበበት አደጋ (calculated risk ) ጋር (በተለይ በውትድርና አቪዬሽን) መተሻሸት ስላለበት ስሌቱ ባንዳች ምክንያት በተዛባ ጊዜ በሚያጋጥመው አደጋ በሰው አካልና ሕይወት እንዲሁም በንብረት ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ይደርስ ነበር።በዚሁ መሰረት የቀድሞው የኢትዮጲያ አየር ሃይልም በተለይ በጀማሪነቱ ጊዜ ለተለያዩ አደጋዎች እየተዳረገ የአደጋዎቹን መንሰኤ በሚገባ እየመረመረና እየተነተነ የሚደርሱትን አደጋዎች እጅግ በመቀነስ አስተማማኝና እጅግ የሚያኮራ የአየር ላይ ሃይል ገንብቶ ነበር።
የየካቲት ስድሳ ስድስቱ ለውጥ መዘዝ ኢትዮጲያን ወደሶቪዬት ኅብረት መዳፍ ሲያስገባት አየር ሃይሉ በተለይ ልዩ ፈተና ገጠመው።አንደኛ ለረጅም ጊዜ መሰረታዊ የበረራ ማስልጠኛ የሚሰጥባቸው ስዊድን ሰራሾቹ ሳብ ሳፊር አውሮፕላኖች በአዲስ ሊተኩ የሚገባበት ጊዜ ቢሆንም በነበረው የተካለበ ሁኔታ የሚሆን አልነበረም።ሁለተኛ ከሶማሊያ አሳዳሪነት ወደኢትዮጲያ ፊቱን ያዞረው ሶቪዬት ኅብረት በዚህ ረገድ የአየር ሃይል ከፍተኛ ባለሙያዎቻችንን የሚያረካ የማስልጠኛ አውሮፕላን ያልነበረው ከመሆኑም በላይ በኢትዮጲያ አየር ሃይል ያለው የበረራ ማሰልጠኛ ተጠናክሮ ከሚቀጥል ይልቅ አየር ሃይሉም ሆነ አገሪቷ የሱ ጥገኛ ሆና እንድትቀጥል ባለው ፍላጎት መሰረት በዚህ ረገድ ትብብር የማድረግ ፍላጎት አልነበረውም።ስለዚህ አዳዲስ ምልምል ፓይለቶችን ወደሶቪዬት ኅብረት ልኮ ማሰልጠን የግድ ሆነ።የዚያን ጊዜዋ ሶቪዬት ኅብረት ምንም እንኳ በሁለተኛው የአለም ጦርነት የናዚ ጀርመንን የአየር ሃይል አውሮፕላኖችን (Luftwaffe ) ያረገፉ በርካታ ስመጥር ፓይለቶችን እንዲሁም ሻላቃ ዩሪ ጋጋሪንን ከመሰለ ሶቪዬት ኅብረትን ከአሜሪካኖቹ ቀድማ ወደጠፈር እንድትመጥቅ በማድረግ ከፓይለትነት ወደጠፈርተኝነት (from aviator to astronaut ) የተሸጋገረ ባለሙያን ያፈራች አገር ብትሆንም የሰውን ልጅ ውስጣዊ ነፃነት በመንፈግ ቆፈን ውስጥ በሚያስገባው አገዛዟ ምክንያት በራሳቸው የሚተማመኑ ልብሙሉና የተካኑ ባለሙያዎችን ከማፍራት ይልቅ በአሸር ባሸር ለብ ለብ ተደርገው የሚወጡ የእስከዚህም (mediocre ) ባለሙያዎች አገር ለመሆን በቃች።አለም አቀፍ ዜና ለሚከታተል በተለይም ለአቪዬሽን ዜና ጆሮውን የሚያውስ በአቪዬሽን አደጋዎች አብዛኛውን ድርሻ የሚይዙት ሶቭዬት (ሩሲያ) ሰራሽ አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች እንዲሁም በእነሱ እጅ የሰለጠኑ ባለሙያዎች በሚያንቀሳቅሷቸው ጊዜ መሆኑን ይገነዘባል።
ጥቂት ምሳሌ ለመወርወር ያህል፤በማንኛውም የአቪዬሽን ስራ ፍፁም ደህንነትን ማረጋገጥ ሁሌም የሚጠበቅ ቢሆንም በተለይ ከፍተኛ ባለስልጣናት በሚበሩበት ጊዜ ይበልጥ የደህንነት መስፈርቱ ይጨምራል።ይሁንና በሶቪዬት ሰራሽ አውሮፕላንና በሶቪዬት ፓይለቶች ሲበር የሞዛምቢኩ ፕሬዝደንት ሳሞራ ማሼል መሞቱን ያጤኗል (ምንም እንኳ በሚመለከታቸው ባለሙያዎች ተቀባይነትን ያላገኘ አፓርታይድ ከሲአይኤ ጋር ሆኖ ገደለው የሚል ሌላ ተቃራኒ ዘገባ ቢኖርም)።በቅርቡ ደግሞ የፖላንድ ፕሬዝደንት ከነካቢኔ ሚኒስትሮቹ ይበርበት የነበረው ሩሲያ ሰራሽ አውሮፕላን እዚያው ሩሲያ ክልል ውስጥ ተከስክሶ ጉድ ማሰኘቱ ይታወሳል።አልጄዚራ የተባለው የዜና አውታር “የሊቢያ ሎከርቢ” በሚል ርዕስ ሰሞኑን ያቀረበውን የሚያስደምም አጋላጭ ዘገባ ለተመለከተ በሩሲያ የሰለጠኑ ፓይለቶች ያለባቸውን ግድፈት የሲቪል መንገደኞች የሆነውን አውሮፕላን በከፍተኛ ቸልተኝነት ገጭተው በሰው ሕይወት ላይ አደጋ ካደረሱት የሚግ 23 ተዋጊ ፓይለቶች ይገነዘባል።ከዚህ ጉዳይ ጋር ይበልጥ የሚቀራረብ ምሳሌ የዩጋንዳ ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች ሶማሊያ ለሚገኘው የሰላም አስጠባቂ ጦራቸው የአየር ሽፋን ለመስጠት መንገድ ጀምረው ገና ውጊያ ቀጠና ውስጥ ሳይገቡ ባገር ሰላም ሶስት ተዋጊ ሄሊኮፕተሮቻቸው በኬንያ ተራራዎች ላይ ሆጨጭ ያሉበት ሁኔታም ይታወሳል።ምሳሌዎችን በዚህ መልክ መደርደር ቢቻልም ጊዜና ቦታ ስለማይበቃ እንገታውና አየር ሃይላችን (የቀድሞውን ማለቴ ነው) ከሶቪዬት ኅብረት ጋር ስላሳለፈው ፍጥጫ እንመለሳለን።
በ1969 ዓ.ም የሶማሊያ ወረራ ጊዜ አየር ሃይላችን እንደ ኤፍ 5 በመሳሰሉ አሜሪካ ሰራሽ ተዋጊ አውሮፕላኖችና አሜሪካን አገር በሰለጠኑ ፓይለቶቻችን አማካይነት ሶቪዬት ሰራሽ በሆኑ አውሮፕላኖች የተሞላውንና ፓይለቶቹም የሶቪዬት ምርት የሆኑትን የሶማሊያ አየር ሃይልን ከሰማዩ ላይ ጨዋታ ካሰወገደ በኋላ እየተመናመኑ ያሉትን የራሱን አውሮፕላኖች ለመተካት ከአዲሱ “ወዳጅና አባት”አገር ዘንዳ አዳዲሶቹን ሶቪዬት ሰራሽ ሚግ ተዋጊ አውሮፕላኖችና እንዲሁም ሚ 8 ወዘተ (MI )በሚል መጠሪያ የሚታወቀቱን ሄሊኮፕተሮችና ትላልቆቹን የመጓጓዣ አንቶኖቭ አውሮፕላኖችን እንዲማሩ ፓይለቶቻችን ተላኩ።ፓይለቶቻችን ቀደም ሲል በሙያው የተካኑና ልምድም ያዳበሩ ስለነበሩ ሶቪዬቶቹ በልዩ ልዩ ምክንያት የሚያሳዩትን መሰሪነትንም ተቋቁመው፤እንዲሁም የአቪዬሽን አውራ ቋንቋ እንግሊዝኛ ቢሆንም ሶቪዬቶቹ በዙሪያ ጥምጥም በአስተርጓሚ የሚሰጡትን ስልጠና በሚገባ አጠናቀው አዳዲሶቹን ሶቪዬት ሰራሽ አውሮፕላኖች ሙሉ ለሙሉ በእጃቸው አድርገው ተረከቡ።ችግር የመጣው ተተኪ ማፍራቱ ላይ ነው።
አንደኛ ደርግ በሚከተለው ፖሊሲ ምክንያት ቀድሞ ወታደር መሆን ያኮራ የነበረውን ያህል ተፈላጊነቱን እያጣ መጣ።በተለይ ከፍተኛ መስህብ የነበራቸው አየር ሃይልና ባህር ሃይል እንኳ በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያላቸው ወጣቶች ቀድሞ ይሻሙባቸው እንዳልነበር አይንህን ላፈር ይሏቸው ገቡ።ስለዚህ አየር ሃይሉ በተንጠለጠለ ውጤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁና ሌላ መግቢያ ያጡ የባጣ ቆየኝ መናኸሪያ መሆን ጀመረ።ይባስ ብሎ ለስልጠና የሚላኩት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቀውን ውስብስብ ቴክኖሎጂ ባሸር ባሸር ለብ ለብ ስልጠና ለማስመረቅ ወደማይመለሰውና የስልጠና ቋንቋውም በአቪዬሽን እውቅና ባላገኘውና ባልዳበረው የሩሲያ ቋንቋ ወደሆነበት የሶቪዬት ኅብረት ሆነ።በመሆኑም አየር ሃይሉ ባንድ በኩል ከሻዕቢያና ከወያኔ ጋር ፍልሚያ፤ በሌላ በኩል ሰልጥነዋል የተባሉትን እነዚህን የሩሲያ ምርት ፓይለቶችን የክለሳ ስልጠና በመስጠት ስራ ብቻ ሳይወሰን ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሚነሱ ፍትጊያዎች ተጠመደ።ይህ ፍትጊያ ያንዳንድ የነባር አየር ሃይል ባልደረቦችን ሞራል የነካና በደርጉ እስከማሳሰርም ጭምር የደረሰበት ሁኔታ ነበር።
ይሁንና ለአገራቸው ባላቸው ፍቅር የተነሳ ከአቪዬሽን ሙያቸው በተጨማሪ የአመራር ጥበባቸውን በማከል መንግስቱ ኃ/ማሪያምን ጊዜ ጠብቀው በማሳመን አየር ሃይሉ የራሱን የበረራ ማስልጠኛ ት/ቤት እንደገና እስኪያደራጅ ድረስ ምልምል ፓይለቶችና እጩ መኮንኖች የመጀመሪያ ደረጃ ስልጠና በኢትዮጲያ አየርመንገድ የበረራ ማስልጠኛ ት/ቤት እንዲያገኙ በማድረግ በተለይ ለምድር ጦር አየር ክፍል (Army aviation ) የሚሰለጥኑ ፓይለቶች በአየርመንገዱ ሰልጥነዋል።በኋላም አየር ሃይሉ የራሱን አካዳሚ ኮሌጅ እንዲያቋቁምና የበረራ ት/ቤቱንም በአዲስ መልክ እንዲያደራጅ ባሳመኑት መሰረት ጣሊያን ሰራሽ የሆኑ ለኤሮባቲክስ በረራ ማሰልጠኛ ምቹ የሆኑ ሲያ ማርኬቲ የተባሉ ወደአስር የሚጠጉ አውሮፕላኖችን በማስመጣት የአየር ሃይሉን ት/ቤት ቀድሞ ወደነበረበት ዝና ለመመለስ ጥረት ጀመሩ።በአካዳሚክ ብቃታቸው የተሻሉ ወጣቶችን ለአየር ሃይሉ ለመመልመልም የአሜሪካን ሆሊውድ እንደሰራው ቶፕ ጋን (Top Gun ) የተሰኘ ፊልም አይነት ለመስራት የሚያስችል ነፃነት በአገሪቱ ባይኖርም እንደአቅሚቲ በደርግ ጊዜ በነበረው የቴሌቪዥን የወጣቶች ፕሮግራምና ሌሎች ፈጠራ በታከለባቸው ማስታወቂያዎች የሚቻለውን ሁሉ አደረጉ።ሶቪዬት ኅብረት ሰልጥነው ከመጡት ውስጥም የተሻለ ብቃት ያዩባቸውን ክለሳ በመስጠትና ልምድ በማካፈል ብቃት እንዲኖራቸው አደረጉ።
ለማሳጠር በዚህ መልክ አደጋ ያንዣበበትን አየር ሃይል ለመታደግ ብርቱ ጥረት ቢያደርጉም በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው ስዕል ትውልድን አስቦ በረጅሙ ላለመ ለእንደዚህ አይነቱ ውጥን አመቺ ስላልነበር በመጀመሪያ የግንቦት 8 አስራ ዘጠኝ ሰማንያ አንዱ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ የአየር ሃይሉን በሳል አመራርና የተካኑ ባለሙያዎች አጨደበት።ቀድሞም የአየር ሃይል መኮንኖችን በተለይም ፓይለቶቹን በቅናትና በጥርጣሬ የሚመለከተው መንግስቱ ኃ/ማሪያም የአየር ሃይል አዛዥ ከፍተኛ ማዕረግ የደረሰ፤ ብዙ የበረራ ሰዓት ያስመዘገበና በተቻለ መጠን በአየር ሃይሉ ስር ያሉ አውሮፕላኖችን ሁሉ ማብረር የሚችል ወይም የበረረ መሆን እንዳለበት የሚያዘውን አለም አቀፍ መርሆ በመጣስ ምንም እንኳ በተሰማሩበት መስክ እውቅና ያተረፉ ስመጥር መኮንን ቢሆኑም ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አየር ሃይሉ ፓይለት ያልሆኑ ከፍተኛ መኮንን ከመከላከያ ኮንስትራክሽን ዘርፍ ተጠርተው ተሾሙበት።ሻዕቢያና ወያኔም በዚህ ሁኔታ በማትረፍ የአገሪቱን በርካታ ቦታዎች ከመቆጣጠራቸውም በላይ ብዙ ወጣት ፓይለቶች አውሮፕላንና ሄሊኮፕተር ይዘው እንዲኮበልሉ ለማድረግ ቻሉ።ብዙም ሳይቆይ ወያኔም ሻዕቢያም አገሪቷን ተቆጣጠሩ፤የጦር ሃይሉንም የ”ደርግ ኢሠፓ ጨፍጫፊ ጦር”ሲሉ በተኑ።ወያኔ ከድል ስካሩ ትንሽ መለስ ሲልለት በድንግዝግዝም ቢሆን “አየር ሃይል” እንደሚያስፈልገው ሲገባው እንደልቤ ልዘውራቸው እችላለሁ ብሎ ያመነባቸውን በልምድና ብቃት ያልጎለበቱትን በደርግ ጊዜ ከተቀጠሩት የአየር ሃይል ባልደረቦች ጥቂቶቹን በመውሰድ፤ በጎሳ መስፈርት ደግሞ ከአድዋ የሚወለደውን በኤሌክትሪካል ምህንድስና በቀድሞ አየር ሃይል ጊዜ ከፍተኛ ትምህርት እንዲያገኝ ተደርጎ የመጀመሪያ ዲግሪ ባለቤት የሆነውንና ፓይለት ያልነበረውን ብርጌዲዬር ጄኔራል ሰለሞን በየነን የወያኔ የመጀመሪያ “አየር ሃይል”አዛዥ አድርጎ በአገሪቱ ሃብትና በአገሪቱ ውድ ልጆች ሕይወት ከጄኔራል ሰለሞንም በኋላ ጫካ የነበሩ ስለአቪዬሽን አንዳችም ነገር የማያውቁ አጋሚዶዎችን እና ከደርግ ላይ በምርኮ ያስገባውን በታንከኛነት ሩሲያ የሰለጠነ ሰው በ”አዛዥነት” እያፈራረቀ ያላግጥበት ገባ።
ምንም እንኳ ከስራ አጥነት ተመልሰው በአዲሱ የወያኔ “አየር ሃይል”ሲቀጠሩ የስራ ዋስትናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ወያኔ የጫነባቸውን ነገር ሁሉ መቀበል ቢኖርባቸውም አሰራሩ ከአቪዬሽን ስርዓት ተፃራሪ እንደሆነ የተገነዘቡት ቀድሞ በደርግ ጊዜ ከሰለጠኑት ንቁ ፓይለቶች ውስጥ ጥያቄ በማንሳታቸውና በማንገራገራቸው ለእስርና ለከፍተኛ ሰቆቃ እንዲሁም ለሞት የተዳረጉ እንደሻምበል ተሾመ ተንኮሉ እና ሻለቃ ዳንኤል የመሳሰሉትም እዚህ ላይ ይታወሳሉ።ስሙን የዘነጋሁት በደርግ ጊዜ ሶቭዬት ኅብረት ሰልጥኖ የተመለሰ ፓይለትና ገና የመቶ አለቃ እንዳለና ከበላዮቹ ልምድ ቀስሞ በሙያው ሳይጎለብት ወያኔ መጥቶ ወደመሰረተው “አየር ሃይል”ከመለሳቸው በኋላ ቀድሞ በነበረው የባለሙያ አሰራር ሊታሰብ በማይችል ሁኔታ በጉልበት የበረራ አስተማሪ እንዳደረጋቸውና ያም መሃል ከተማ ላይና የገበሬ ቀዬዎች ላይ በተደጋጋሚ ለአሰቃቂ አደጋ እንዴት እንደዳረጋቸው “ኢትኦጵ”በተባለ ጋዜጣ ላይ የገለጸበት ሁኔታም ትዝ ይለኛል።
መደምደሚያ
በሶማሊያ በቅርቡ ተከስክሶ የሰው ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ የጠፋበት የአንቶኖቭ 12 አደጋ መንስኤ ሰው ሰራሽ ስሕተት ይሁን ወይም ሌላ ለጊዜው የምናውቅበት መንገድ የለም፤ወያኔ በሚከተለው የአፈና ፖሊሲ ምክንያትም ወደፊት ባጭር ጊዜ ውስጥ መንስኤውን የአገራችን ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ልናውቅ ሲገባ የምናውቅበት ተስፋ ያለ አይመስልም።”ምንትስ ያለበት ዝላይ አይችልም”እንዲል ግን ሪፖርተር ጋዜጣ ተሽቀዳድሞ የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ (pilot-in-command ) ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ልምድ ያለው ፓይለት እንደነበረ ነግሮናል።ወያኔ በደርግ ጊዜ ከነበሩት ፓይለቶች ምን አይነቶችን እንደመለሰና በምን ስሌት እንደመለሰ ይህም ውሎ አድሮ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳየሁ ስለመሰለኝ ዳግመኛ አልመለስበትም።
ሪፖርተር ግን በወያኔ ጊዜ በጎሳ መስፈርታቸው ብቻ ተመልምለው የተቀጠሩት የወያኔ “አየር ሃይል ዲሞክራት ፓይለቶች”ያስነሱትን ከፍተኛ ትችትና ነቀፌታ ስለሚያቃት የአንቶኖቩ ፓይለት የ”እኛ”ሳይሆን የ”ናንተው”የራሳችሁ ነው ለማለት “ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ፓይለት”ሲል ከመሞጣሞጣችን በፊት በዘዴ ኩም ሊያደርገን ሞክሯል።ሪፖርተር አሳንሶ ይየን ወይም በሌላ ምክንያት እግረመንገዱንም ከአንቶኖቩ አደጋ ጥቂት ቀናት በፊት ከላይ የጠቀስኩትን አሜሪካ ሰራሽ አውሮፕላን በወያኔ “አየር ሃይል”እጅ መሰባበርን መዘገቡ ከፍተኛ ጥያቄ ሊያጭርብን እንደሚችል መገንዘብ ነበረበት።ከጥያቄዎቻችን መካከል አውሮፕላኖቹ “ልምድ” ባላቸው ፓይለቶች ቢበሩም ምን ያህል ሙያቸው ተከብሮላቸው የደህንነት ዋስትና በሚሰጥ ድባብ ይሰሩ ነበር?የወታደራዊ አቪዬሽንን ሕግ ተፃራሪ በሆነና ለአደጋ በሚዳርግ ተፅዕኖ ስር ይሰሩ እንዳልነበር ምን ዋስትና አለ?አንዳች አገራዊ ፍቅር በሌለበት ሁኔታ ጠባብ አጄንዳውን ለማራመድ ሲል ወያኔ በአየር ሃይል ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሙያዎች ላይ ያደረገውን አይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት በሚገባ የምናውቀው ስለሆነ ማብራራት አያሻውም።የአሜሪካን አየር ወለድ ወታደሮችን ጭኖ ለወታደራዊ ልምምድ ሰማይ ላይ ከወጣ በኋላ ጥቂት ወታደሮች ከአውሮፕላኑ መዝለል እንደጀመሩ ሌሎቹ አውሮፕላኑ ውስጥ እንዳሉ አውሮፕላኑ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ በመከስከሳቸው ያለቁበትን የአውሮፕላን አደጋ መንስኤ ከመረመረ በኋላ አደጋው የተከሰተው ከፓይለቱ ጀምሮ የሚመለከታቸው ሌሎችም በፈጠሩት የአጫጫን ቀመር ስህተትና ሜካኒካዊ ችግር መሆኑን በሳይንሳዊ መንገድ ከተነተነ በኋላ ሲደመድም “ሰማዩ ሲሾፍበት አይወድም (The sky doesn’t like to be mocked. )”ብሎ የደመደመ አንድ ፅሁፍ ከሁለት አስርተ አመታት በፊት በአቪዬሽን መፅሄት ላይ ማንበቤን አስታውሳለሁ።
በሁሉም ዘርፍና ሙያዎች ያሾፈውና ያላገጠው ወያኔ በሌሎች ዘርፍ የሚደርሰውን መዘዝ ለረጅም ጊዜ አለባብሶ ሊያልፈው ይችላል።በአቪዬሽን የሚመጣው መዘዝ ግን እንዲህ በገሃድ የሚታይ አሳዛኝ ትዕይንት (spectacular tragedy) ስለሚተው አንድ ቀን በእጅጉ ያስጠይቃል።
Email;kiflukam@yahoo.com
Twitter@Hussainkiflu
No comments:
Post a Comment