ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን እንደ ወያኔ ዘመን የተዋረዱበት የተናቁበትና የተበደሉበት ጊዜ የለም።በአሁኑ ወቅት አገሪቱና ህዝቧ ከፊታቸው የተጋረጠው ችግር የመሰረታዊ የዲሞክራሲና የሰብኣዊ መብቶች አለመከበር ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የሕልውና ጥያቄና ኢትዮጵያ እንደ አገር የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ ሆኖዋል።
የትጥቅ ትግልም በኢትዮጵያ የወቅቱ የፖለቲካ ሁናቴ እንደ አንድ ምናልባትም እንደ ብቸኛ የትግል አማራጭ እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል።
“የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል” የወያኔ ግፍና በደል በአንገፈገፋቸው በሃገር ወዳድና ለህዝብ ተቆርቋሪ በሆኑ ወጣቶች፣ ምሁራንና በተለያዩ ዜጎች የተመሰረተ ድርጅት ነው። የዚህ ኃይል ራዕይ ደግሞ ሕዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን፣የዜጎች መብቶች፣አገራዊ አንድነት፣ደህንነትንና ጥቅም እንዲከበሩና ጠንካራ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትገነባ መስዋዕትነትን በመክፈል አስተዋጾ ማድረግ ነው።
“የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል” ወያኔን በኃይል ለማስወገድ ፣ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር በአገሪቱ እንዲኖር ማስቻል እና ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ያልወገኑ ነፃ ጠንካራና ብቃት ያላቸው ህገ-መንግስታዊ የመከላከያ፣ የፖሊስ፣የደህንነት ተቋማት እንዲኖሩ አስተዋጽዎ ማድረግን እንደ አንድ ግብ ይዞ የተነሳ ኃይል ነው።
“በግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል” ውስጥ የተመቻቸ ኑሮአቸውን፣ቤተሰቦቻቸውን እና የሚወዱትን አገርና የሰለጠኑበትን ሙያ እርግፍ አድርገው በመተው ትእግስትን የሚፈታተን መከራና እንግልት የሚበዛበትን የትጥቅ ትግል የተቀላቀሉ በርካታ ምሁራን ይገኙበታል። ይህም ከዚህ በፊት በስፋት የሚታወቀውን “ያልተማረውን ዜጋ ወደ ጦር ግንባር” የመላክና የመስክ ላይ ትግሉም በትምህርት ላይ የተመሰረተ አመራር የማጣት ችግርን የቀረፈ እና ታጋዩ ህብረተሰብ በዕውቀት ላይ በመመርኮዝ “ለምንና ለማን ነው የምታገለውና የምሰዋው” ጥያቄን በሚገባና በጥልቀት የተገነዘበ ኃይል ነው።
ይህንን ለኢትዮጵያና ሕዝቧ መልካም ራዕይ አንግቦ የተነሳ ሠራዊት በተቻለ ሁሉ መደገፍና ደጀንነታችንን ማረጋገጥ የውዴታ ግዴታችን መሆኑን የተገነዘብን በኖርዌይ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን አንድ ግዜያዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ግብረኃይል በማቋቋም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ጀምረናል።
በግብረኃይሉ መርሃግብር መሰረት መስከረም 28 ቀን 2013 (እ.ኤ.አ) “የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል” አመራር ተወካዮች በሚገኙበት ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በኦስሎ ከተማ ተዘጋጅቷል።
በፕሮግራሙ ላይ ውይይት፣ የገቢ ማሰባሰቢያና የመዝናኛ መርሃግብሮች ተካተዋል። በመሆኑም ነፃነት ለኢትዮጵያ ሃገራችንና ለሕዝቧ ከዚያም በላይ ለእኔ ስብዕና ያስፈልገኛል ብለን የምናምን ሁሉ በዝግጅቱ ላይ በመገኘት ደጀንነታችንን “ለግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል” እንድናሳይ ጥሪያችንን በትህትና እናቀርባለን።
ነፃነት፣ ፍትህ፣እኩልነትና ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ተከብራ ትኖራለች !!!
በኖርዌይ “የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል” ድጋፍ አሰባሳቢ ግዜያዊ ኮሚቴ
ኦገስት 14፣ 2013 ኖርዌይ፣ ኦስሎ
የፌስ ቡክ ኢቬንቱን እንዲጎበኙ ተጋብዘዋል
No comments:
Post a Comment