Tuesday, August 13, 2013

ለኢትዮዽያዊው የኦሮሞ ህዝብ የተሰበከው ልቦለዳዊ የሀሰት ታርክ

ማሳሰቢያ፡- አሁን እዚህ ያቀረብኩት የትርጉም ሥራ ከወቅቱ የፖለቲካ ንፋስ አኳያ በጣም ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መሆኑን አውቃለሁ፡፡ በቃላት የምንዛሬ ትርጉም ዜጎች እየተላለቁ በሚገኙባት ሆደባሻ ዓለም ውስጥ ይህን መሰሉን ጉዳይ በቀላሉ መተርጎም እንደማይቻል እረዳለሁና ማንኛውም ዓይነት በዋናው ጽሑፍ ላይ ያልተጠቀሰ ሃሳብ በዚህ ትርጉም ውስጥ በስህተት ቢገኝ ኃላፊነቱ ፕሮፌሰሩ ሣይሆን የኔ የተርጓሚው መሆኑን ለአንባቢያንና ለፕሮፌሰር ፈቃዱ ከታላቅ ይቅርታ ጋር በትህትና እገልጻለሁ፡፡ በተቻለኝ መጠን የዋናው የእንግሊዝኛ ጽሑፍ ወዘና እንዳይጠፋ ጥረት አድርጌያለሁ – የኔ የራሴ ሥነ ልሣናዊ ‹የተፈጥሮ ለዛ›ም እንዳይከፋብኝ ከሚል ቅን አስተሳሰብ በመነሣት የተጠጋጋ ግን ከዋናው እምብዝም የማያፈነግጥ ‹ኮዝሞቲክስ› እጅግ አልፎ አልፎ በጣም በስሱ ፈንጠቅ ለማድረግ ሞክሬያለሁ – ለዚህ ደግሞ ፕሮፌሰርን በድጋሚ ይቅርታ እጠይቃለሁ – እንዲህ የማደርገው እንግሊዝኛው ወዳማርኛ ሲመለስ ድርቅ እንዳይልብኝና መሸጋገሪያ ድልድዩ ቢጠናከር ትርጉሙ ይበልጥ እንደሚያምር ሳምንበት ነው ፤ ለማንኛውም ግን ሰው ነኝና ብሳሳት በቀናነት እዩልኝ እንጂ ልፋቴን በሚያጣጥል የከፋ ደረጃ እንዳታብጠለጥሉኝ አደራ እላለሁ፡፡ ዛሬም መልካም ንባብ፡፡
(ኦሮሞዎችንና የኢትዮጵያን ታሪክ በሚመለከት ዳሰሳ ለሚያደርጉ የውጭ ጋዜጠኞች የመነሻ ግንዛቤ መጨበጫ ይሆናቸው ዘንድ የተዘጋጀ) ኦሮሞና ኢትዮጵያ፤ ምሥጋና ለ: ayyaantuu.com ድረ ገጽ)
(ናዝሬት፣ ኢትዮጵያ) – መሠረቱን ኳታር ያደረገው የአልጀዚራ ቴሌቪዥን የኢትዮጵያ ኦሮሞዎችን በሚመለከት በርካታ ዝግጅቶችን በቅርቡ አየር ላይ ማዋሉ የሚታወስ ነው፡፡ የሕዝባችንን ገጽታ በመሰለው መልክ ለዓለም ማኅበረሰብ በስፋት በማስተዋወቅ ረገድ ይህ የሚዲያ ተቋም የመጀመሪያው በመሆኑና እያደረገ ያለውም አስተዋጽዖ ቀላል ባለመሆኑ ሊወደስ ይገባዋል፡፡
ይህ ዓይነቱ ሕዝብን የማስተዋወቅ ሥራ ከሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች ውስጥ አንደኛው፣ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት በነሱና በተከታዮቻቸው አማካይነት በሕዝቡ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ግፍና በደል እንዲሁም የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች የሚከታተል ገለልተኛ ወገን መኖሩን ተገንዝበው የሚያካሂዷቸውን የሰብኣዊ መብት ረገጣዎች በቀላሉ እንዳይመለከቱ ማስገደዱና በዚያም ሳቢያ እነኚሁ ባለሥልጣናት የሚያስተዳድሩትን ሕዝብ የወቅት ሁኔታ የዓለም ሕዝብ በግልጽ እየተከታተለው መሆኑን እንዲያውቁት ማስቻሉ ነው፡፡ ኦሮሞዎችና ሌሎች ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው ለእኩልነትና ለዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው መከበር ላለፉት በርካታ አሠርት ዓመታትና አሁንም ድረስ ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ ስለኦሮሞ ሕዝብ ጥንተ አመጣጥና ታሪካዊ ዳራ የመዘገቡ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የማይገባ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ይህ ሲደረግ ግን በትክክል መዘገብ እንደሚኖርበት መረዳት ለማንኛውም ወገን ጠቀሜታ አለው፡፡ ትክክለኛ ያልሆነና የተጣመመ መረጃን ወይም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ወደ አንድ ወገን የሚያጋድል ዘገባን ማቅረቡ ለዴሞክራሲ የምናደርገውን ሁለንተናዊ ትግል ይጎዳብናልና ከዚህ መሠረታዊ ነጥብ አንጻር ሁላችንም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡ ይህ የተንሻፈፈ አካሄድ ብሔራዊ መግባባትንና ሰላምን ከመፍጠር ይልቅ ቁጣንና አንዱ ባንዱ ላይ መንገፍገፍን እያስከተለ ቅራኔን ያባብሳል፡፡
በቅርቡ አልጀዚራ ትክክል ያልሆነ ወይም የተሳሳተ ዘገባ እንዲያርቀብ ከተገደደበት ምክንያቶች አንደኛው የመረጃ ምንጩ ግራና ቀኙን ያማከለ ሣይሆን በአንድ አቅጣጫ ብቻ ማለትም በአብዛኛው በዉጭ የሚንቀሳቀሱ ኦነግንና ኦ.ኤፍ.ዲ.ኤምን የመሳሰሉ የኦሮሞ ድርጅቶች መሆናቸው ነው፡፡ በዚህ ግን አልጀዚራ ብዙም ሊወቀስ አይገባውም፤ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የሚገኙ ትክክለኛውን መረጃ የሚያውቁ ሰዎች ወይም ድርጅቶች የሚያውቁትን እውነት ቢናገሩ የሚደርስባቸውን ያውቃሉና ለደኅንነታቸው ይሰጋሉ፡፡ ስለዚህም አልጀዚራን የመሳሰሉ የውጪ የመገናኛ ብዙኃን የተሻለ አማራጭ ሲያጡ በመረጃ ምንጭነት ለመጠቀም የሚገደዱት በውጭ ሀገራት በስደትና በልዩ ልዩ ኢኮኖሚያዊም ይሁን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሠማርተው የሚገኙ ሰዎችን ወይም ቡድኖችን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ የሦስተኛው ዓለም ሀገራትን ሁኔታ መዘገብ ለሚፈልጉ ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ የውጭ የመረጃ ተቋማት ትልቁ የራስ ምታት ነው፡፡ ምክንያቱም ከአንድ ወገን የሚያገኙትን መረጃ ሊያረጋግጡ የሚችሉባቸው የሀገር ውስጥ በሮችና መስኮቶች በሚዲያ አፋኝ አምባገነን መንግሥታት ስለሚዘጉባቸው በአብዛኛው ያልተረጋገጠና የአንድ ወገን መረጃ ለመዘገብ ይገደዳሉና፡፡
ለዛሬው ለመማማር ያህል እንዲጠቅመን ሰሞኑን አልጀዚራ በኦሮሞ ሕዝብ ታሪክና ለዴምከራሲያዊ መብቶቻችን መከበር በምናደርገው ትግል ዙሪያ ያስተላለፋቸውን ዘገባዎች በሚመለከት መታረም የሚገባቸው ዋና ዋና ህፀፆችና እውነትነት ጨርሶውን የሚጎድላቸው አሳሳች ጉዳዮች ስላሉ በነዚያ ላይ አንዳንድ የማስተካከያ ነጥቦችን ከዚህ በታች እንመለከታለን፡፡ የሚከተሉት የማስተካከያ ሃሳቦች ከፖለቲካዊ አስተሳሰብ በጸዱ ሃቀኛ ምሁራን የሚደገፉ ቢሆኑም በፖለቲካ ጠበል የተጠመቁ የማንኛውም ጎራ ‹ምሁራን› ግን ላይደገፏቸው ወይም ተቀባይነት ሊያሳጧቸው ይችላሉ፡፡ ይሁንና እነዚህን ሃቆች ማንም ይገፍትራቸው ወይም ይቀበላቸው ዋናው ጉዳይ እውነታዎቹ ስሜት ወለድ ሳይሆኑ የታሪክ መዛግብትን፣ የአውሮፓ ተመራማሪዎች የደከሙባቸው የታሪክ መጻሕፍትንና በዕውቅ ምሁራን የተዘገቡ የታሪክ ማስታወሻዎችን መሠረትና ዋቢ ያደረጉ በመሆናቸው የትኛውም ወገን ሊጠራጠራቸው አይገባም፡፡
ልቦለድ ቁጥር አንድ:-
“ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1868 እስከ 1900 ከጠቅላላው የኦሮሞ ሕዝብ መካከል ግማሹ የሚሆነውና ወደ አምስት ሚሊዮን አካባቢ የሚገመተው ሕዝብ ሙሉ በሙሉ [በሀበሾች ንጉሥ በአጤ ምኒልክ ጦር]ተገደለ፡፡”
ሃቅ ቁጥር አንድ፡-
ይህ መነሻና መድረሻ የሌለው ተራ አሉቧልታ እንጂ እውነት አይደለም፡፡ ይህንና ሌላም ይህን መሰል መሠረተቢስ ወሬ ተደጋግሞ የሚነገረውና እንደማለፊያ ዜማ ዘወትር የሚቀነቀነው በአብዛኛው የኦሮሞን መገንጠል በሚደግፉና ዓላማውንም በሚያራምዱ ‹ተምረናል› በሚሉ የተወሰኑ የኦሮሞ ማኅበረሰብ አባላትና ውጪ ባሉ አክራሪ የጎሣ ፖለቲካ አቀንቃኞች እንዲሁም ‹gadaa.com›ን በመሳሰሉ የኦነግ ደጋፊ ድረ ገፆች አማካይነት ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን እነዚህ ወገኖች በዚያን ዘመን የተገደለው የኦሮሞ ቁጥር አምስት ሚሊዮን ማለታቸው የቁጥር ዕውቀታቸው ዜሮ መሆኑን ከማመልከቱ ባሻገር የሚያስተላልፈው መልእክት ሚዛን የሚያነሳ እንዳልሆነ ታሪክንና የሕዝብ ብዛት ዕድገትን የሚያውቅ ይረዳዋል፡፡ በዚያን የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ አካባቢ 90 የሚደርሰውን የኢትዮጵያን ዘውጎች ሁሉንም ሥሌት ውስጥ ባካተተ የሕዝብ ቆጠራ ጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከአምስት ሚሊዮንም በጣሙን የሚያንስ እንደነበር በታሪክ መጻሕፍት ሠፍሮ ይገኛል፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ታዲያ ከዘጠናው ዘውግ ውስጥ የኦሮሞው ማኅበረሰብ ብቻ ተነጥሎ “10 ሚሊዮን ይደርስ ነበር፤ ከዚያም ውስጥ አምስቱ ሚሊዮኑ በ‹ጨካኝ ንጉሥ ተጨፍጭፎ› ተገደለ” ማለቱ በራሱ የጤናማነት ጉድለት እንጂ አንድም ተጠየቃዊ አመክንዮ የለውም፡፡ ለመዋሸት ደግሞ ይህን ያህል ረጂም ርቀት መሄድ ለምን እንዳስፈለገ ለማንም ግልጽ አይመስልም፡፡ ስለዚህ አምስት ሚሊዮን ኦሮሞዎች በአፄ ምኒልክ ጦር ተገደሉ የሚለው የተሳሳተ መረጃ የማንንም ቀልብ የማይስብና የትኛውንም ዓላማ ለማራመድ የማያገለግል ተራ የፈጠራ ወሬ ነው፡፡ እውነቱ ግን በዚያን ዘመን በተቀሰቀሱ የገብር አልገብርም የርስ በርስ ግጭቶችና ጦርነቶች ሳቢያ በብዙ ሺዎች የሚገመቱ ኦሮሞዎችና ሌሎች ኢትዮጵያውን – በሁለቱም ጎራዎች – ለሕልፈት መዳረጋቸው ነው፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞች ለራሳቸው ጠባብ አጀንዳ ሲሉ የዚያን ጊዜውን ዕልቂት ‹ጄኖሣይድ› እንደሆነ ቢፈርጁም እውነቱ ግን ሌላ ነው፡፡ እውነቱ ታዲያ የጄኖሣይድ ሣይሆን በዘመኑ በአውሮፓ መሣሪያና በሰለጠነ የሰው ኃይል ተደራጅቶ የነበረው በንጉሠ ነገሥት ምኒልክ የሚታዘዘው የሸዋ ጦር በኋላቀር መሣሪያና ካለበቂ የጦር ልምድና ሥልጠና ለጦርነት ከተሰለፈው የደቡቡ ኃይል ጋር በተፈጠረ የኃይል ሚዛን መበላለጥ ምክንያት በተከሰተው ግጭት በተለይ በደቡቡ በኩል ብዙ ወገን ማለቁ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ባልተመጣጠኑ ኃይሎች መካከል የተከሰተን ጦርነት ወይም ግጭት ያመለክታል እንጂ አንድ የታጠቀ ዘመናዊ ጦር ለልዩ ተልእኮ ወደ አንድ መንደር ወይም ቀየ ገብቶ ባዶ እጃቸውን በቤታቸው የተቀመጡ ንጹሓን ዜጎች እንደፈጀ በማስመሰል የዚያን ጊዜውን የርስር በርስ ውጊያ ወደ‹ጄኖሳይድ›ነት ለውጦ የተለዬ ስዕል መፍጠር ተገቢ አይደለም ብቻ ሣይሆን ጥፋት ነው፡፡ ታሪካዊ እውነቱ የዚያን ዓይነት መልክና ቅርጽ የነበረው አይደለም፡፡ እንዲያውም በነዚያ ያለፉ የመከራ ዓመታት ኦሮሞ ባልሆኑ ሰዎች ከተገደሉ ኦሮሞዎች ይልቅ በኦሮሞዎች የተገደሉ ኦሮሞዎች ቁጥር በጣም ይበልጣል፡፡ ምክንያቱም በኦሮሞ የተለያዩ ነገዶች ውስጥ በሀብትም ይሁን በአስተዳደር የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክርና መቀናቀን ስለነበር ከጎረቤቶቻቸው ኦሮሞዎችና ከሲዳማዎችም የነበራቸውን ሽኩቻ በጠረጴዛ ዙሪያ የቃላት ድርድር ሳይሆን አንዱ አንዱን በኃይል በመጨፍለቅ የበላይነቱን ለማረጋገጥ ሲል በጦር መሣሪያ ይፋለሙ ስለነበር ነው፡፡የዚያ ዓይነቱ ወንድም በወንድሙ ላይ ‹የሚቀዳጀው› ግንጥል ጌጣዊ ድል ደግሞ በአፍሪካ የመጀመሪያው እንዳልሆነና የተፈጥሮ ሀብትንም ይሁን ሌላ ጥቅም የሚያስገኝን ነገር ለመቀራመት ሲባል በሚደረግ ፍልሚያ በሌሎች የኢትዮጵያ ጎሣዎችና ነገዶች መካከልም የከረሩ ግጭቶች ይካሄዱ እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል፤ ስለሆነም በደቡቡ ይበልጡን ኦሮምኛ ተናጋሪ በነበረው ማኅበረሰብና በሸዋው ባመዛኙ አማርኛ ይናገር በነበረው የአንዲት ሀገር ዜጎች መካከል የታዩ ግጭቶችን በሀገሪቱም ሆነ በሌላው ዓለም እንዳልታዩ ልዩ ተዓምሮች በመቁጠር ይህን ያህል ግዘፍ ነስተው መራገባቸው ማንንም ስለማይጠቅም እውነቱን ከእውነተኛ ምንጮች መረዳት አይከፋምና በተለይ በዚህ ቅንነት በሚጎድለውና የተንኮል ሤራ በተሸረበበት የጥፋት ጎዳና የሚራመዱ ወገኖች በአፋጣኝ ወደቀናው መንገድ በጊዜ እንዲመለሱ ይመከራሉ፡፡ ይህን ሃሳብ ጠቅለል ለማድረግ፣ የጂማ ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ጳውሎስ መንግሥቱ የቀኝ ክንፍ የኦሮሞ ነጻነት ጎራን ፍልስፍና በሚመለከት ውብ በሆነ አገላለጽ በጽሑፍ ካስቀመጡት ሀተታ ውስጥ የሚከተለውን ቀንጨብ አድርገን እንመለክት፡-
የኦሮሞን ማኅበረሰብ ታሪክ በሚመለከት ሆን ተብለው ተንሻፍፈው የተጻፉ ወይም የሚነገሩ በርካታ የፈጠራ ድርሰቶችና ልቦለዶች አሉ፡፡ እነዚህ በሬ ወለደ ዓይነት አሉታዊ ጥላ ያነገቡ የውሸት ታሪኮችን በጭፍን ተቀብለውና እውነት እንደሆኑ አምነው በጭፍን የሚጓዙ ወገኖችም ሞልተዋል፡፡ የፖለቲካ ኪሣራ ያጋጠማቸውና ወደጎን የተተው እንደኦነጉ አሰፋ ጃለታን የመሰሉ አስመሳይ ‹የታሪክ ተመራማሪዎች›ና ‹ጸሐፊዎች› በቤተ ሙከራዎቻቸው የፈበረኳቸው እነዚህ የሀሰት ወሬዎች የየዋሃንን ቀልብ በመሳብና በማሳሳት ረገድ የተጫወቱትና እየተጫወቱ ያሉት አሉታዊ ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ይህ በስም የተጠቀሰ ግለሰብ በተለይ፣ አንድን ነገር ሆን ብሎ በማጣመም ለራሱ በሚያመቸው መልክ በመጥቀስና ቃላትን ወይም አባባሎችን ከቆሙለት ዐውዳዊ ፍቺ ሌላ ያልተፈለገ ትርጉም በማሸከም ሰውን የሚያወናብድ አሳሳች ሰው ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ወስደን እንይ፤ አሌክሳንደር ቡላቶቪች የተባለ የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሩሲያዊ ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ ተከሰተ ባለው በሽታና ርሀብ እንዲሁም በኦሮሞ ጎሣዎች መካከል ተካሄደ የተባለን ግጭት ጨምሮ ኦሮሞዎች ከሌሎች የሀገሪቱ ጎሣዎች በተለይም ከአማራው ጋር አካሂደዋል በሚላቸው ጦርነቶች ሳቢያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሽ በግማሽ እንዳለቀ ‹ምሁራዊ ግምቱ›ን ሰጥቶ ነበር፡፡ አጅሬ አሰፋ ጃለታ ይህን ዘገባ ካነበበ በኋላ ከአንድ ጤናማ ሰው በጭራሽ በማይጠበቅ ሁኔታ አጣምሞ በመተርጎም “ግማሹ የኦሮሞ ሕዝብ በ‹ክፉዎቹ› አማራዎች ተጨፍጭፎ ተገደለ፡፡” በማለት በኦሮሞ ታሪክ ውስጥ የግል ፈጠራ ድርሰቱን ሰንቅሯል፡፡ ይህ ተራ ነገር አይደለም፤ የአንዲት ሀገር ዜጎችን ጥርስ ለማናከስ በተንኮል የታቀደ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ማንም አይጠቀምም፡፡ ይህ የልቦለድ ታሪክ በአቶ ጃለታ የተፈለሰፈው ኦሮሞና አማራን በማጣላት ይገኛል ተብሎ የሚገመትን የሥልጣንና የኢኮኖሚ ጥቅም ታሳቢ ያደረገ የጎሣ ፖለቲካ ውጤት ነው፡፡ ከመነሻው ሚስተር ቡላቶቪችም ቢሆን ያን በአኀዛዊ ግምት ያስቀመጠውን የኢትዮጵያውያን ዕልቂት ሊደርስበት የሚያስቸለው አንዳችም የሕግ ድጋፍም ሆነ በግሉ የሚታወቅባቸው አቅምና ችሎታ የነበሩት ሰው አልነበረም፡፡ በሁለተኛም ያ ሰው የኦሮሞው ማኅበረሰብ ይኖርባቸው በነበሩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ዝኆንና ሌሎች የዱር እንስሳትን እያደነ በዛ ቢባል ለሁለት ወራት ያህል ብቻ ተዘዋወረ እንጂ ያን ከፍተኛ ወጪና የተማረ የሰው ኃይል የሚፈልግ የሕዝብ ቆጠራና የዕልቂት መንስኤ ጥናት ለማካሄድ የሚያስቸለው መደላድል በነዚያን በ1990ዎቹ ዓመታት ውስጥ ፈጽሞውን ሊኖረው አይችልም፡፡
ልቦለድ ቁጥር ሁለት፡-
“… አብዛኛው ሙስሊም የኦሮሞ ሕዝብ”
ሃቅ ቁጥር ሁለት፡-
ይህ ሐረግ በጥቂት የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ዘወትር ባይሆንም ካለፍ ካገደም የሚስተዋል ነው፡፡ በመሠረቱ በኦሮሞ ሃይማኖታዊ ታሪክ ከጥንት እስከዛሬ መቼም ቢሆን ‹አብዛኛው ሕዝብ እስልምናን ተከታይ ነው› የሚባል ሕዝብ ሆኖ አያውቅም፡፡ እንደእውነቱ ክርስትናም ሆነ እስልምና ከጊዜ በኋላ የመጡ እንጂ የአያት የቅድመ አያት ጥንታዊ ሃይማኖቶቻችን አይደሉም፡፡ ለምዕተ ዓመታት ስንከተላቸው የነበሩና በትውልድ ሲወራረሱ የቆዩ ሀገር በቀል ባህላዊ እምነቶች ነበሩን፡፡ (አሁንም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡) ቀስ በቀስ ግን በተለይ የኦሮሞ መስፋፋት በተጋጋለባቸው ዓመታት እነዚህ ሁለቱ እምነቶች ወደኦሮሞው ሕዝብ ይበልጥ እየሠረጉ ገቡ፡፡ ሥርገቱም በፈቃዳችንና በተፅዕኖም እንደነበር ከታሪክ ድርሳናት እንረዳለን፡፡ በፈቃዳችን የሆነው እኛ በሰላምም ሆነ በጦርነት መልክ በሄድንባቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ ከነበረው የክርስቲያን ወይም የሙስሊም ሕዝብ ጋር ስንዋሃድ ሲሆን በተፅዕኖ የሆነው እነዚሁ ኃይሎች የኛን ግዛቶች በሚወርሩ ጊዜ በሚያሳድሩት ተፅዕኖ ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን ያን ክስተት አሁን የኋሊት ዞረን ስናየው ጉዳዩ የሁለትዮሽ እንጂ በብቸኝነት አንደኛው ሃይማኖት በሌላኛው ላይ የበላይነትን የሚጭንበት ሁኔታ ስላልነበረ አንዱ ከአንዱ ጎልቶ የወጣበትና የኦሮሞን ሃይማኖታዊ ማንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይበት ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ በዚህ ረገድ አሁን እንኳን ብናይ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ ያለው የሁለቱ ሃይማኖቶች የተከታይ ብዛት ተካካይ እንጂ ያን ያህል አፍን ሞልቶ ሊያናግር የሚያስችል የቁጥር መበላለጥ የላቸውም፡፡ (የመጨረሻው የ2000 ዓ.ም የሕዝብ ቆጠራ እንደሚያሳየው 48 በመቶ የሚሆነው ኦሮሞ የ(ማንኛውም ዘርፍ) ክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ሲሆን 47 በመቶው ደግሞ ሙስሊም ነው፡፡ እንደሚባለው ከሆነ ግን የእስልምና ሃይማት ተከታዩ ቁጥር በፍጥነት እያደገና በአንጻሩም የክርስትና ሃይማኖት እየጫጫ በመሄድ ላይ ያለ በመሆኑ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በኦሮሞዎች ዘንድ የሙስሊም ማኅበረሰብ ቁጥር ከክርስቲያኑ ሊበልጥ እንደሚችል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል፡፡
ልቦለድ ቁጥር ሦስት፡-
“ሀበሾች ኦሮሞዎችን ለማንቋሸሽ አሉታዊ ትርጉም ባዘለ ቃል ‹ጋላ› እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡”
ሃቅ ቁጥር ሦስት፡-
ይህን እብለትና ቅጥፈት የተሞላበትን የፈጠራ አባባል የሚጠቀሙበት ከፍ ሲል የተጠቀሱት መገንጠልን የሚያራምዱ የኦሮሞ ኤሊቶችና አጫፋሪዎቻቸው ናቸው፡፡ ይህን የሚያደርጉት በአባባሉ እውነትነት አምነው ሣይሆን በኦሮሞው ውስጥ የመረረ ስሜት ለመፍጠርና ሕዝቡ ሴማዊ ሀበሾችን(አማሮችን፣ ትግሬዎችንና ጉራጌዎችን) ፈጽሞ እንዲጠላ ለማድረግ ነው፡፡ ይህን በማድረጋቸው ቅራኔውን ያከረሩና በአቋራጭ የመገንጠል ዓላማቸውን ያሣኩ ይመስላቸዋል፡፡ የዚህ ቃል ጥንተ አመጣጥና ትርጉሙ ግን እንደዚህ ነው፡- ይህ አንቋሻሽ የሚመስል ‹ጋላ› የሚባል ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ላይ የዋለው በዐረቦችና በሙስሊም ሶማሌዎች ሲሆን ኦሮሞዎችን ‹ጋል› በማለት መጥራታቸው በቃሉ ትርጉም መሠረት ኦሮሞዎች ‹ሃይማኖት የሌላቸው›ና ከነሱ የተለዩ ‹ባዕዳን› መሆናቸውን ለመግለጽ ነው፡፡ በኦሮሞ መስፋፋት ወቅት ሙስሊሞች በዚህ ቃል ኦሮሞዎችን መጥራት የፈለጉት ኦሮሞዎች የነበራቸው ባህላዊ ሃይማኖት/እምነት ከተለመደው የእስልምና ወይም የክርስትና ሃይማኖቶች የሚያፈነግጥ ሆኖ ስላገኙትና ያንንም በግዑዝ ነገሮች እንደማምለክ ወይም ከነአካቴው እንደሃይማኖት የለሽነት ስለቆጠሩት ነበር ተብሎ ይገመታል፡፡ እየቆዬ ግን ይህ አሉታዊ ፍቺ እንዲይዝ ጫና የተደረገበት ‹ጋላ› የሚል ቃል የኦሮሞን ማኅበረሰብ አባላት በቡድንም ይሁን በተናጠል ለመጥራት ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ይጠቀሙበት ጀመር፡፡
ልቦለድ ቁጥር አራት፡-
“(በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ አካባቢ) ኦሮሞዎች በአፄ ምኒልክ ቅኝ አገዛዝ ሥር ወደቁ፡፡”
ሃቅ ቁጥር አራት፡-
የኦሮሞ ተገንጣይ ቡድኖች ከሚያናፍሷቸውና አንዳንድ የውጭ ጋዜጠኞችም በጭፍን ተቀብለው በተደጋጋሚ ከሚያራግቡላቸው የፈጠራ ወሬዎች መካከል አንደኛው አንድ ኢትዮጵያዊ ዘውግ (አማራ) ሌላውን ኢትዮጵያዊ ዘውግ (ኦሮሞን)በቅኝ ግዛት ሥር አስገብቷል የሚለው አስቂኝ ድራማ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ብዙውን ጊዜ “ሀበሾች ኦሮሞዎችን በቅኝ ግዛት ያዙ” ወዘተ. እየተባለ እንደመፈክር ይስተጋባል፡፡ ይህ የቅኝ ግዛት ነገር በኦነግና በመሰል የኦሮሞ ድርጅቶች እንዲሁም በአሜሪካና በአውሮፓ ሀገራት በሚገኙ የኦሮሞን ብሔርተኝነት አቀንቃኞች ዘንድ እንደእውነት ተወስዶ ለትግል ማነሳሻነትና ማነቃቂያነት ሲባል በስፋት ይወሳል፤ በሕዝብ ውስጥም ውስጥ ውስጡን ይሰበካል፡፡ በተለዬ አገላለጽና የዕይታ አቅጣጫ ሊታይ በሚችል መልኩ ይህ አንዱ ሌላውን ለመቆጣጠር የመሻትና የመሞከርም ሁኔታ ጨርሶውን ሊካድ ባይችልም … እንደአጠቃላይ ግን የኦሮሞ ብሔር መቼም ቢሆን በሌላ (የኢትዮጵያ) ዘውግ ቅኝ ተገዝቶ አያውቅም፡፡ ይህ ዓይነቱ ወሬ ሰሚን ሣይቀር ግራ የሚያጋባ ተራ ወሬ እንጂ ቅንጣት እውነትነት የለውም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሌላው ቀርቶ አንድ የተባበረ የኦሮሞ ብሔር፣ ተለይቶ ከሚታወቅ አንድ ወጥ የኦሮሞ ግዛት ጋር በነዚያ ሩቅ ጊዜያት አልነበረም፡፡ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ የሌለባቸው የታሪክ መጻሕፍት ሁሉ የሚመሰክሩት አንድ እውነት አለ፡፡ ያም እውነት በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ቋንቋቸው አንድ በሆነ ነገር ግን የተለያዩ የጎሣ/የነገድ ስብጥር ባላቸው ማኅበረሰቦች መካከል ለዘመናት ጦርነቶች መካሄዳቸው ነው፡፡ በልማዳዊ አነጋገር የ“ሀበሾች” ሥፍራዎች ናቸው በሚባሉ የሰሜን ኢትዮጵያ ብዙ ቦታዎች ሳይቀር ኦሮሞዎች በመስፋፋት ከትግሬዎች፣ ከአማራዎች፣ ከአፋሮችና ከሌሎችም የክልሉ ነዋሪዎች ጋር በመቀላቀላቸውና በመዋሃዳቸው ይህ በአንዳንድ የዋሃን “የሀበሾች ምድር” እየተባለ አላግባብ የሚጠራው የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ራሱ የአንዱ ወይም የሌላው ብሔር ወይም ዘውግ ብቸኛ መኖሪያ ሣይሆን የሁሉም እንደሆነ በታሪክ ምሁራን ዘንድ ይታመናል፡፡ እርግጥ ነው በ1700ዎቹ ገደማ ራያ ኦሮሞዎችና የጁ ኦሮሞዎች የተወሰኑ የትግሬና የአማራ ግዛቶችን ተቆጣጥረው በነበረበት ጊዜ ለተወሰኑ ዓመታት የኢትዮጵያን ኦፊሴል ቋንቋ ኦሮምኛ አድርገው እንደነበር ከታሪክ ማኅደር መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህም ማለት በኢትዮጵያ የተለያየ ቋንቋና ባህል ያላቸው ጎሣዎችና ነገዶች እየተፈራረቁ ሥልጣን ይናጠቁ እንደነበረና በታሪክ ግምዶሽ እየተቆራኙ እርስ በርስ እንደተዋሃዱ፣ በዚህ ሂደትም ይበልጥ ጉልበተኛ የነበረው ዘውግ ለአገዛዝ አመቺ ነው ብሎ የሚያስበውን ቋንቋም (ሆነ ባህል) በሌሎች ላይ ይጭን እንደነበር መረዳት አይቸግርም፡፡ የዚያን ዘመኑ የአንድ ቋንቋ የበላይነት ግን እንደዛሬው ዘመን አጨቃጫቂና ከመጠን በላይ በተለጠጡ የቅራኔና ቁርሾ መዘዞች የታጨቀ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በንግድም ሆነ በሌላ ሥራ ከቦታ ቦታ ይዘዋወሩ የነበሩ ዜጎች ለሥራቸው ስኬት ሲሉ በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የሌሎች ጎሣዎችን ቋንቋዎች ይናገሩ ስለነበርና ቋንቋን ማወቅም ከግል ጥቅም ጋር በቀጥታ ስለሚያያዝ በዚያን ዘመን ይስተዋል የነበረው ሥነ ልሣናዊ ችግር እንዳሁኑ በፖለቲካዊ አስተሳሰቦች የተንኮል ድርና ማግ የተሸመነ አልነበረምና ያን ያህል ጎልቶ የሚታይ ለታሪክ መዝገብ ፍጆታም የሚበቃ ቋንቋ ነክ ችግር አልነበረም፡፡ ይህ እንግዲህ ኦሮሞ የሠፈረበትን ግዛት የሚጠቁመን የኋላ ታሪክ ነው፡፡ ታሪኩም የሚያሳየን ኦሮሞ ያልተዳረሰበት ኢትዮጵያዊ ሥፍራ እንደሌለና ነገር ግን በየሄደበት ባህልና ቋንቋ እየተዋጠ ከሁሉም ጋር እንደሰም ቀልጦ አንድ መሆኑን ነው፡፡ ወደኋለኛው የአፄ ምኒልክ ዘመን ስንመጣ እንግዲህ የሚስተዋል አንድ ሃቅ መኖሩን እንረዳለን፡፡ ይሄውም ብዙዎች የታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሐፍት እንደሚከራከሩበትና አሳማኝም ነው ብለው በርካቶች እንደሚቀበሉት ጉዳዩ የአማራና የኦሮሞ ዝርያ ወይም የደም ትስስር ሣይሆን አማርኛን በዋናነት የሚናገር ማኅበረሰብ ኦሮምኛን በዋናነት የሚናገርን ማኅበረሰብ በጊዜ ሂደት ሊያሸንፍ የመቻሉ ታሪካዊ አጋጣሚ መከሰቱ ነው፡፡ ይህ ሲሆን አማርኛን በሚናገረው ማኅበረሰብ ውስጥ ኦሮሞ አለ፤ ኦሮምኛን በሚናገረው ማኅበረሰብ ውስጥም አማራ አለ ማለት ነውና ትግሉ ይበልጡን የኢኮኖሚና የሥልጣን እንጂ የዘርና የቋንቋ አለመሆኑን ልብ ይሏል፤ እርግጥ ነው ግጭቶች ሁሉ የሀሰትም ይሁን የእውነት አንዳች የሚነገርላቸው ምክንያት ስለሚያስፈልጋቸው በሁሉም ወገን የሚነገሩ ግን እውነት ውሸትነታቸው ሊጣራ የሚገቡ ሰበበ-ድርጊቶች መኖራቸው የሚካድ አይደለም፡፡ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እንግዲህ በነዚህ ዓይነቶቹ የኋላ ዳፋ ሊኖራቸው በሚችል ጠንቀኛ ንግግሮችና ሰብቆች ላይ ነው፤ ምክንያቱም ‹አንድ ወሬኛ ያባረረውን ሺ ጦረኛ አይመልሰውም› እንዲሉ ተጣሞ የተነዛን ወሬ ለማቃናት አስቸጋሪ ከመሆኑም በተጨማሪ ወሬው እየተበጠሰ እየተቀጠለ ይሄድና ያልተጠበቀ ከፍተኛ ችግር ይፈጥራልና ነው፡፡ ይህ ከፍ ሲል የተገለጸው የግጭትና አንዱ ሌላውን እያሸነፈ የማስገበር ሁኔታ የሚያመለክተን አማራ ኦሮሞን ወይም ኦሮሞ አማራን የማሸነፍ ጉዳይ አለመሆኑንና ታሪካዊ አንድምታው ከዚህ የፊት ለፊት ሽፋን ረቀቅ ያለና የተለዬ መሆኑን ነው፡፡ በተቻኮለ ፍርደገምድልነት የተሳሳተ አመለካከት ከማዳበር በፊት እውነትን መረዳት ለሁሉም ይጠቅማል፡፡
ሰሜነኞቹ አማሮች ጎራ ለይተው እንደተጋጩና ለጉዳት እንደተዳረጉ ሁሉ ኦሮሞዎችም እንዲሁ ጎራ ለይተው ግጭት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ለዚህ አንዱ ግልጽ ማስረጃ የሚሆነን አፄ ምኒልክ በወጣትነታቸው ዘመን በአፄ ቴዎድሮስ ተይዘው ታስረው በነበረበት ወቅት በጎንደርና በሸዋ የአማሮች መኳንንትና መሣፍንት መካከል የታየው ፍጥጫ ነው፡፡ ወጣቱ ምኒልክ በተፈቱ ሰሞንም የኦሮሞ ነገዶች ኃይለኛ የርስ በርስ ውጊያ ላይ ነበሩ፡፡ የተቀናቃኞቻቸውን አከርካሪ በመምታት ያን ግጭት በአሸናፊነት ለመውጣት የፈለጉ የተወሰኑ የኦሮሞ ጦር ቡድኖች ከሸዋ አማሮች ንጉሥ አፄ ምኒልክ ጋር ኅብረት ፈጠሩ፡፡ ቱለማ ኦሮሞ፣ ሊሙና ሜጫ ኦሮሞ የሚባሉት የኦሮሞ ጦሮች ከሸዋው ንጉሥ ከአፄ ምኒልክ ጦር ጋር በመተባበር ሌሎችን የኦሮሞ ጦሮች በተለያዩ አስከፊ ዐወደ ዉጊያዎች በማሸነፍ ብትንትናቸውን አወጡት፡፡ ባጭሩ ኦሮሞዎች በኦሮሞነታቸው በአንድ ኦሮሞ ያልሆነ ባዕድ አካል በቅኝ ግዛት አልተያዙም፡፡ እርግጥ ነው የኦነግ መሥራች አባላት ይህን የ”ቅኝ ግዛት” ተረት ተረት ስላላመኑበት በተለይ በመጀመሪያ አካባቢ ይህን ያህል አፍ ሞልተው ሲናገሩት አልተስተዋለም፡፡ ይሁንና በ1960ዎቹ አካባቢ የኦነግ አመራሮች በግማሽ ኦሮሞ በሆኑት የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ላይ ኦሮሞዎች እንዲያምጹባቸው ለማድረግ ስሜትን የሚማርክ አንዳች የመቀስቀሻ ዘዴ መቀየስ አስፈለጋቸው፡፡ ለዚያም ሲሉ ይህችን መናኛ የ‹ቅኝ ግዛት› ካርድ በማንሣት ‹ለኦሮሚያ ነጻነት› ሁሉም ኦሮሞ በትግሉ እንዲሣተፍና “ከኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት” ራሱን ነጻ እንዲያወጣ ይቀሰቅሱበት ጀመሩ፡፡ በዚህ የኦሮሞ ነጻነት ግምባር ድንገተኛ የአቋም ለውጥ ምክንያት ከኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጋር ለበርካታ ምዕተ ዓመታት በሁሉም ረገድ ተዋህደን እንዳልኖርንና በደምና በአጥንት እንዳልተሳሰርን ሁሉ እኛ ኦሮሞዎች “በማያውቁንና በማናውቃቸው አማሮች” አማካይነት እንደከብት በቅኝ ግዛት በረት ውስጥ የመገኘታችንን ምሥጢር ኦነግ ይፋ አደረገልን፡፡ ይህ ዓይነቱ የመጨረሻ ውራጅና ከተስፋ መቁረጥ የሚመነጭ የትግል ሥልት በሌሎች ሀገሮች ውስጥ በሚካሄዱ የነጻነት እንቅስቃሴዎችም ዘንድ ሥራ ላይ ሲውል ታይቷል፡፡ የኛን ሀገር ሁኔታ በሚመለከት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የሚረዱት ገሃዱ እውነታ ግን በታሪክ ጥንቃቄ የተሞላበት ልዩ ሙያ ተዳውረው የተሸመኑት የሸዋ አማሮችና ኦሮሞዎች ለዘመናዊት ኢትዮጵያ መፈጠር ዋና መንስኤ መሆናቸው ነው፡፡ “ሸዋዎች እነማን ናቸው?” በሚለው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈ መጸሐፉ ላይ፣ የታሪክ ምሁሩና የሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪው ዶክተር ጌሪ ሳሎል ይህን የመሰለ ጠቅለል ያለ ድምዳሜ አስፍሯል፤ “ ዘር ቆጠራን በሚመለከት ሸዋ ውስጥ (ከዚያም በመላዋ ኢትዮጵያ) የፖለቲካ የበላይነትን የጨበጡትን ቡድኖች ብናይ ከአማራና ከኦሮሞ የተወለዱ ቅዩጣን ዜጎች ናቸው፡፡”
ወደማጠቃለያችን ስንመጣ እንግዲህ በዋናነት መገንዘብ የሚያስፈልገን ነገር ቢኖር ከፍ ሲል የተጠቀሱት አራት መሠረታዊ ስህተቶች የኦሮሞን ታሪክና ኦሮሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት የሚጫወተውን ሚና በሚመለከት መዘገብ የሚፈልጉ በተለይ የውጭ ሀገራት ጋዜጠኞችን በማሳሳትና እውነቱን እንዳይዘግቡ በማወናበድ እያደናቀፉ መሆናቸውን ነው፡፡ አልጀዚራን የመሳሰሉ ዕውቅ የመገናኛ ብዙኃን የኦሮሞንና የሌሎች ኢትዮጵያውያንን ችግርና እንግልት መዘገባቸው እሰዬው የሚያሰኝ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ያለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ይወጡ ዘንድ ዘገባው ሚዛናዊ እንዲሆን ተጨማሪና ከፍተኛም ጥረት ማድረግ እደሚገባቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ አለበለዚያ የሚሠሩት የተዛነፈ ሥራ በተለይ ወጣቱን ክፍል ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይመራውና ለችግሮች መፍትሔ ከማግኘት ይልቅ ችግሮች እየተባባሱ እንዲሄዱ ያደርጋል፡፡ እንደውነቱ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ እየመጡ በሚሄዱ የተለያዩ መንግሥታት አማካይነት ከፍተኛ የአስተዳደር በደልና ጭቆና የደረሰባቸውና የሚደርስባቸው ኦሮሞዎች ብቻ ሣይሆኑ ሁሉም ዜጎች ናቸው፡፡ ከዚህ አስከፊ የብረት አጥር ወጥተው ወደተሻለ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ዘመን ሊሸጋገሩ የሚችሉት ደግሞ የጎሣና መሰል ልዩነቶቻቸውን ትተው ለጋራ መብቶቻቸው መከበር በአንድነት ሲቆሙና በአንድነት ሲታገሉ ብቻ ነው፡፡ በጋራ ሲሰለፉ ደግሞ የጋራ ጠላቶቻቸው በማር ለውሰው በመሃከላቸው በረጯቸው መርዘኛ አሉቧልታዎችና የሀሰት ወሬዎች መበርገግና በነጭ ውሸት የመሠሪዎች መሠረተቢስ ወሬ መረታት የለባቸውም – ‹ተደጋግሞ የተነገረ ውሸት እንደ እውነት ይቆጠራል› የሚባለውን ምሳሌያዊ አባባል በማስታወስ የሚነገረው ሁሉ እውነት እንዳልሆነ ማጤንና ሁሉም ትኩረቱን ከባርነት አገዛዝ ነጻ ወደሚያወጣው የጋራ መንገድ ማዞር ይኖርበታል፡፡ የውጭ የመገናኛ ብዙኃንም ያልተረጋገጠ የሀሰት ዘገባ በማቅረብ በሕዝብ መሀል ጥርጣሬንና መፈራራትን ከማንገሥ ተቆጥበው ትክክለኛነቱ በሁሉም ወገኖች ዘንድ የተመሠከረለትን ዘገባ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፤ ከዚህ ቀደም ኅትመት ወይም አየር ላይ ባዋሏቸው መሰናዶዎቻቸው ላይ ስህተት ካለም ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከተው አካል ማስተካከያ መቀበልና ማስተላለፍ፣ ለቀደመ ስህተታቸውም ይቅርታን መጠየቅ ይገባቸዋል፡፡ እነዚህ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ከአሁን በኋላ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ከቀሪ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ለዴሞክራሲ፣ ለልማትና ለፍትህ የሚያደርገውን ትግል የሚያደናቅፉ ከፋፋይና መሠረተቢስ ዝግጅቶችን ከማቅረብ እንዲቆጠቡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪየን አስተላልፋለሁ፡፡
– ፈቃዱ ለሜሣ የናዝሬት ዩኒቨርስቲ የቀድሞ ፕሮፌሰርና ጸሐፊ ናቸው፡፡
ለማንኛውም አስተያየትና ሂስ የኔ አድራሻ፡- yinegal3@gmail.com
Original title of this translation:- History 101: Fiction and Facts on Oromos of Ethiopia
የኢትዮሚዲያ ምንጭ፡ Salem News

No comments:

Post a Comment