Wednesday, August 7, 2013

ደቂቀ እስጢፋኖስ - ድምጻችን ይሰማ

ይህ ርዕስ አወዛጋቢ ሊሆን እንደሚችል ይሰማኛል፣ ጠቅላላ ይዘቱም እንዲሁ። ደቂቀ እስጢፋኖስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስርዓት ይከበር ብለው 15ኛው ክፍለ-ዘመን የተነሱ የሀይማኖት "አህይዎና ተሀድሶ" ( Revival and Renewal or Reformation) አራማጆች ነበሩ። ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ በህግ አምላክ በሚል ርዕስ 2002 ዓም ባሳተሙት ድንቅ መጽሐፍ ስለ እስጢፋኖሳውያን ሲናገሩ፦ " አባ እስጢፋኖስና ተከታዮቻቸው ... የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የማትቀበላቸው እንዲያውም የተወገዙ አድርጋ የምታያቸው በአስራ አምስተኛው ምእተ ዓመት ያበቡ የተሐድሶ እንቅስቃሴ መሪዎች ናቸው" 
በደቂቀ እስጢፋኖስ ላይ የተፈጸመው ስቃይ በኢትዮጵያ ከሀይማኖት ጋር ተያይዞ ከተፈጸሙት ስቃዮች ሁሉ በጭካኔ መጠኑ የሚስተካከለው ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፤ እስጢፋኖሳውያን አፍንጫዎቻቸው እና ምላሶሳቸው እንዲቆረጥ በድንጋይም ተወግረው እንዲገደሉ፣ ወደ ገደልም ተወርውረው እንዲጣሉ ተደርገዋል።
ደፋሮቹና ለእምነታቸው ሟች የሆኑት እስጢፋኖሳውያን ሐያሉን ንጉስ አጼ ዘርዓ ያዕቆብን፣ በድንገት ተነስተው " ለእግዚአብሄር እንጅ ለአንተ አንሰግድም" ሲሉዋቸው እና በዙሪያቸው የተኮለኮሉትንም መነኮሳትአንዴ ከውሻ ትፋት ሌላ ጊዜ ደግሞ ከአሳማ ንጽህናጋር እያመሳሰሉ ከፍ ዝቅ ሲያደርጓቸው ሲመለከቱ ንጉሡም ክብራቸውን ( ዙፋናቸውን) ለማስጠበቅ ሲሉ አባ እስጢፋኖስንና ተከታዮቻቸውን ከምድርም ከሰማይም ገጾች ለማጥፋት ብዙ አሰቃቂ ወንጀሎችን ፈጽመዋል፤ ንጉሱን ይደግፉ የነበሩ መነኮሳትም፣ ንጉሱ ወንጀል ሲፈጽሙ አብረው ተባብረዋቸዋል። 
ደቂቀ እስጢፋኖስ መሰረታዊ በሚባለው " በአቋም ወይም በእምነት ረገድ ...ከሌሎች ገዳማት በምን እንደሚለዩ ግልጽ የሆነ ነገር" አለመኖሩን / ጌታቸው በመጽሀፋቸው ጠቁመዋል። ይሁን እንጅ እስጢፋኖሳውያኑ ሐይማኖቱን ለምድራዊው ምቾታቸው ባዋሉት መነኮሳት ላይ የትችት ናዳቸውን ከማውረድ ወደ ሁዋላ አላሉም። / ጌታቸው ስለዚሁ ነገር ሲጽፉ " በዕውቀትና በመንፈሳዊነት የታወቁ መነኮሳትም ከገዳማቸው እየወጡ የነገስቱ ባለሟሎች እየሆኑ ከነገሥቱ ችሎት ለፍርድ ይቀመጡ ነበር የፕ/ሩን አስተያየት የሚያጠናክር በአባ እስጢፋኖስ ገድል ገጽ 95 ላይ የሚከተለው ተተርጉሞ ቀርቧል፦ከዚህ በሁዋላ ንጉሡ መነኩሴዎቹ እንዲያመሰግኑት ፈለገና እነሱን፣በሉ ፍረዱአላቸው። እንዲህ ሲል ፍርድ ሰጡ፤ሞት ይገባዋል ምክንያቱም ሰንበት ሻሪ ነው፣ ለንጉሥም አይታዘዝም፣ለክብሩም አይሰግድም። 
አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ህዝቡ በደቂቀ እስጢፋኖስ ትምህርት እየተማረከ የማይሰግድላቸው ስለመሰላቸው የእምነቱን አራማጆች ለማጥፋት ታጥቀው ተነሱ። / ጌታቸው " ንጉሱም የሚደፍረው (የማይሰግድለት) ሰው ብዛት የሚያድግ ስለመሰለው ሁሉም በየበኩላቸው ( መነኮሳቱን ማለታቸው ነው) የየራሳቸውን ጥቅም ለመጠበቅ ያዋጣ የመሰላቸውን እርምጃ በህብረት ወሰዱባቸው።" ይላሉ። ( በሁለተኛው ቅንፍ ያስገባሁት ማብራሪያ የእኔ ነው።) በንጉሱና በንጉሱ ደጋፊ መነኮሳት መካከል ግልጽ የሆነ የጥቅም ትስስር ነበር ማለት ይቻላል- አንዱ ዙፋኑንና ክብሩን ለማስጠበቅ፣ ሌላው ደግሞ እንጀራውን ለመጋገር።
አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ደቂቀ አስጢፋኖስን ለማጥፋት በመጀመሪያ በክርክር፣ ቀጥሎም በንግግር ወይም በድርድር፣ አልሆን ሲልም በጉልበት ሞክረዋል። ለክርክር ይረዱ ዘንድ በርካታ መጽሀፎች በእርሳቸውና በደጋፊዎቻቸው ተዘጋጅተው ቀርበዋል፤ "ይህንን ትቀበላላችሁ አትቀበሉም?' እያሉም ራሳቸው በአዘጋጁዋቸው ሸንጎዎች ችሎት አስችለው ጭካኔ የተሞላባቸውን ውሳኔዎች በእስጢፋኖሳውያን ላይ አሳልፈዋል። 
ዛሬ በሙስሊሞች ላይ እየደረሰ ያለው በደል በደቂቀ እስጢፋኖስ ላይ ከደረሰው በደል ጋር በብዙ ነገሮች የሚመሳሰል ይመስለኛል። መንግስት፣ እንደ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን በይፋ "የድምጻችን ይሰማ ተከታዮች አፍንጫቸው ይቆረጥ" የሚል አዋጅ ባያስነገርም፣ በገሀድ እየታየ ያለው ግን ከዚያ የሚለይ መስሎ አልታየኝም። መንግስት በራሱ ጊዜ ለሙግት ይጠቅሙኛል የሚላቸውን ጽሑፎች አትሞ አሰራጨ፣ በራሱ ጊዜ የሙስሊሙ መሪዎችን እንደራደር አለ፣ በራሱ ጊዜ አስሮ ችሎት አቆማቸው፣ በራሱ ጊዜ አሸባሪ አላቸው፣ በራሱ ጊዜ ደግሞ ገረፋቸው፣ አሰራቸው፣ በጥይት ቆላቸው። ይህ ግፍ ነው! እውነት እላለሁ፣ የሙስሊሙ ጩኸት በርክቷል፤ ሙስሊም ሆኖ መኖር አስፈሪም ሆኗል፣ ሙስሊሙ በእናት አገሩ መኖር እሲኪያንገሸግሸው ድረስ እናት አገሩን ሳይወድ በግድ እንዲጠላ፣ አገር አልባነት እንዲሰማው እየተደረገ ነው። 
የድምጻችን ይሰማ መሪዎች በቀዳሚነት ያነሱዋቸው ጥያቄዎች ከመብት ( ከአስተዳደር ) ጋር የተያያዙ እንጅ የእስልምናን ሐይማኖት መሰረታዊ አቋም ( መርህ) ከመለወጥ ጋር የተያያዙ ናቸው ብየ አላምንም። "መንግስት አህባሽን በግድ አይጫንብን፣ የሀይማኖት መሪዎቻችንን ያለ መንግስት ጣልቃ ገብነት በራሳችን እንምረጥ" የሚሉት ጥያቄዎች ከሀይማኖታዊ ይዘታቸው ይልቅ አስተዳደራዊ ይዘታቸው ጎልቶ ይወጣል። የሙስሊሙን ጥያቄ ሐይማኖታዊ ይዘት ወይም የሐይማኖቱን ስርአት ለመለወጥ የአለመ አድርጎ በማቅረብ የስልጣን እድሜውን ለማርዘም ሲውተረተር የምናየው መንግስትን ነው። በደቂቀ እስጢፋኖስ ዘመን እንደታየው ጥቃቅን የአፈጻጸም ልዩነቶች በተሀድሶ አራማጆች ዘንድ ሊኖሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን እነዚህ ጥቃቅን ልዩነቶች የሀይማኖቱን ምሰሶ የሚያዛቡ አይደሉም። ደቂቀ እስጢፋኖስ የኦርቶዶክስ ሀይማኖትን መሰረታዊ አቋም ለመለወጥ እንዳልሞከሩ ሁሉ በተመሳሳይም የድምጻችን ይሰማ መሪዎች የሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች መሰረታዊ የሆነውን የሱኒ እስልምናን አቋም ለመቀየር አላማ ያደረጉ ናቸው ብየ አላስብም። ቢሆንም እንኳ በሰላም እስካስኬዱት ድረስ መብታቸው ነው። 
የአቋም ለውጥ ማካሄድ በጣም ከባድና አደገኛ ነው፤ የሐይማኖት ተቋማትን ከሁለት ሊከፍል ይችላል( በካቶሊክና በፕሮቴስታንት ወይም በሺዓና ሱኒ መካከል እንደታየው ማለቴ ነው) የድምጻችን ይሰማ ተከታዮች ጥያቄ በይበልጥ አስተዳደራዊ ይዘት ያላቸው መሆኑ ቢታወቅም መንግስት ጥያቄውን ከሀይማኖቱ አቋም ጋር የተሳሰረ አድርጎ ለማቅረብ የሚሄድበት አካሄድ አደገኛ የሆነ ውጤት ይኖረዋል። አስተዳደራዊ ጥያቄ በንግግርና መብትን በማክበር በቀላሉ የሚፈታ ነው፤ የአቋም ጥያቄ ግን በንግግር ወይም በድርድር በቀላሉ አይፈታም፣ አንዳንዴም ወደ ጦርነት ይጋብዛል። የካቶሊክ ሀይማኖትን በተቀበሉት በአጼ ሱስንዮስ ጊዜ የታየው አስከፊየሀይማኖትጦርነት በአቋም ለውጥ የተነሳ የተከሰተ ጦርነት ስለነበር አስከፊ ሆኗል። በካቶሊክና በፕሮቴስታንት ተከታይ አገሮች መካከል የተደረገው 30 አመታት ጦርነትም ( እኤአ 1618-1648) አስከፊ ተብሎ በታሪክ የተመዘገበው የአቋም ለውጥን የተከተለ ስለነበር ነው። / ጌታቸው እንዳሉት አጼ ዘርአ ያዕቆብለቤተክርስቲያኒቱ ከልቡ አሳቢ ከሆነ፣ ሲሆን ከደቂቀ ኤዎስጣጢዎስ ጋራ ያደረገውን ዕርቅ አይነት ከደቂቀ እሲጢፋኖስም ጋራ አድርጎ አብሮ ቢሰራ አለዚያም እንዳላየ ቢያያቸው ኖሮ ምናልባት በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ታአምር ይታይ ነበር።የኢትዮጵያ መንግስትም ድምጻችን ይሰማ ከሱኒ እስልምና አፈንግጠው ይወጡና የራሳቸውን አዲስ ሀይማኖት ለመመስረት እንዳሰቡ አድርጎ በማቅረብ ከሌሎቹ የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ጋር ደም እንዲቃቡ ለማድረግ የሚከተለው አካሄድ የሁዋላ ሁዋላ መዘዙ በሁሉም ላይ የሚያርፍ ይሆናል። መንግስት የአጼ ዘርአ ያዕቆብ አካሄድ ዘመን ያለፈበት አካሄድ መሆኑን የተረዳው አልመሰለኝም።
አንድ የማይካድ ሀቅ አለ፣ የሙስሊም መሪዎች ያነሱዋቸው ጥያቄዎች ተረጋግቶና ተመቻችቶ በተቀመጠው ሥርዓት ላይ እና ሥርዓቱን ደግፈው ጥቅማቸውን በሚያስጠብቁ ሀይሎች ላይ ሁሉ አደጋ ፈጥሯል። ሙስሊሙ ያነሳው ጥያቄ ሀይማኖታዊ ገጽታ ይኑረው እንጅ መሰረቱ የፖለቲካ ( የመብት) ጥያቄ ነው። ይህ ደግሞ ተገቢና ሁሉም ዜጋ ሊደግፈው የሚገባ ነው። ሙስሊሙ ኢትዮጵያዊመሪዎቼን በነጻነት የመምረጥ መብቴ ይከበርልኝብሎ ሲጠይቅ፣መሪን በነጻነት መምረጥጀነትን ያወርሳል የሚል ህግ በቅዱስ ቁራን ውስጥ ስለተጻፈ አይደለም። መሪን በነጻነት መምረጥ ሰዋዊ መብት ነው፣ ለሙስሊሙም ለክርስቲያኑም እንደኔ ላለውም ሰው የተሰጠ የተፈጥሮ መብት። ዛሬ ሙስሊሙ በራሱ ፍላጎት መሪውን መምረጥ ከቻለ ነገ ደግሞ አርቶዶክሱ "እኔስ?" ብሎ ይጠይቃል። የሙያ የሰራተኛ የሴቶች፣ የወጣቶች ማህበራትም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ። እንዲህ እያለ የመብት ጥያቄው ከማህበር ወይም ከሀይማኖት አጥር ወጥቶ የእያንዳንዱ ዜጋ ጥያቄ ይሆናል። የእያንዳንዱ ዜጋ ጥያቄ መሆን ሲጀምር ደግሞ መንግስትም ጸጥ-ለጥ ብሎ የሚገዛለት፣ እንደፈለገ ሊከፋፍለው የሚችለው ህዝብ ስለማያገኝ ይወድቃል። መንግስት ሲወድቅ ደግሞ ከመንግስት ተጠግተው ጥቅማቸውን የሚያስከብሩ አመራሮችም አብረው ይወድቃሉ፤ እነዚህ ሀይሎች ያላቸው አማራጭ ከመንግስት ጋር ሆነው የጋራ ጥቅማቸውን ለማስከበር መታገል ነው አለዚያ ደግሞ የያዙትን ይዘው መሸሽ። በመጅሊስ መሪዎች እና በመንግስት መካከል ያለው ትስስር ይህን የሚያሳይ ነው፤ ሁለቱም የሚያሳድዱት ጥቅማቸውን ነው፣ የአንዱ መጥፋት የሌላው መጥፋት መሆኑን ያውቃሉና እስከደም ጠብታ አብረው ይጓዛሉ። 
የሙስሊሙ ትግል ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ለሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል እገዛ ያደርጋል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። ዛሬ የሙስሊሞች ጥያቄ ከተመለሰ ነገ በሌሎች ሐይማኖቶች፣ በሌሎች የሙያ፣ የጾታና የእድሜ ማህበራት ውስጥ ለሚነሱ ጥያቄዎች መንግስት መልስ መስጠቱ አያጠራጥርም።

No comments:

Post a Comment