ፀጋው መላኩ
ከአንድ ሥጋ ቤት በተመሳሳይ ወቅት ሥጋ ገዝተው የተመገቡ የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች በህመም እየተሰቃዩ ነው። ነዋሪዎቹ ከቆየ ደንበኛቸው ሥጋ ገዝተው ለልደት፣ ለሽምግልና፣ ለሰርግ የተጠቀሙበት ሁኔታ ቢኖርም ታዳሚዎቹም ሆነ ባለቤቶቹ በሙሉ ለህመም መዳረጋቸውን ገልፀውልናል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ፀሐይ ሙላቱ ቤተሰቧ ለነበረበት የሽምግልና ፕሮግራም ከሥጋ ቤቱ 25 ኪሎ ሥጋ የገዙ መሆናቸውን ገልፃ ተጠርተው የነበሩት ወደ 60 የሚጠጉት ታዳሚዎች በዕለቱ ከምሽትና ከሌሊት ጀምሮ ለከባድ ህመም የተጋለጡ መሆናቸውን ገልፃልናለች። በአመጋገብ በኩልም የተገዛውን የከብት ሥጋ ሳይሆን ዶሮ ብቻ የተመገቡ ሰዎች ግን ያልታመሙ መሆናቸው ወጣት ፀሐይ ገልፃለች።
በተመሳሳይ መልኩ አቶ ተሾመ ሙላቱ የተባሉ በልደታ ክፍለከተማ የቀድሞው ወረዳ 5 የቤት ቁጥር 048 ነዋሪ ከሥጋ ቤቱ የተገዛውን ምግብ ተመግበው ለህመም መዳረጋቸውን ገልፀውልናል። ጌጃ ሰፈር የሚባል ነዋሪዎችም ከዚያው ተመሳሳይ ሥጋ ቤት ገዝተው ለልደት ዝግጅት የተጠቀሙ ነዋሪዎችም ለከፍተኛ ህመም የተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸውልናል። የህመሙን ሥሜት በተመለከተ የገለፁልን ታማሚዎቹ በዋነኝነት ማንቀጥቀጥ፣ ማስመለስ፣ ተቅማጥ፣ የአቅም ማነስ፣ ቁርጠት የራስ ምታትና ለመግለፅ የሚያስቸግር የህመም ስሜት የፈጠረባቸው መሆኑን ገልፀውልናል።
በልደታ ተክለ ሃይማኖት ክሊኒክ በተደረገላቸው ምርመራም ውጤቱ የምግብ መበከል የሚያሳይ መሆኑን የተገለፀ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልፀውልናል። ነዋሪዎቹ ምግቡን ከተመገቡ ቀናት ቢቆጠሩም የህመሙ ስሜት ባለመጥፋቱ የምርመራቸውን ውጤት ይዘው ወደ ክስ የሚያመሩ መሆኑን ጨምረው አመልክተዋል።
No comments:
Post a Comment