Thursday, August 8, 2013

“ኃይሌ ፕሬዘዳንት ከሚሆን የሪዞርቱ አስዳደር ቢሆን ይሻለዋል” – አቶ ግርማ ሰይፉ

zx21111
በኢትዮጵያ ፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ የኃይሌ ገብረስላሴን ወደ ፖለቲካው ዓለም መግባትና ለፕሬዚዳንትነት እወዳደራለሁ ማለቱን ተከትሎ ለላይፍ መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ “‹‹ሃይሌ ፕሬዘዳንት ከሚሆን የሪዞርቱ አስዳደር ቢሆን ይሻለዋል›› አሉ። በመጽሔቱ የቀረበው ቃለምልልስ እንደወረደ ይኸው፦
‹‹ለሚሚ ስብሃቱ የምሰጠው ምላሽ እንኳን ብቻ ነው››
‹‹መለስ በመሞታቸው ፓርላማው ተነቃቅቷል››
የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ በታሪክ አጋጣሚ በፓርላማው ብቸኛ የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ በመሆናቸው የሁሉን ትኩረት እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡እጅግ የተጣበበ ጊዜ ያላቸው ግርማ በቅርቡ የነጻነት ዋጋው ስንት ነው? የሚል መጽሀፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ዳዊት ሰለሞን መጽሀፉን እንደመነሻ በመውሰድ ነገሮችን በተለየና በሰለጠነ መንገድ መመልከት የሚወዱትን ግርማን አነጋግሯቸዋል፡፡የፓርላማ አባሉ ጊዜያቸውን በማጣበብ ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኝነት በማሳየታቸውም ምስጋናችን ይድረሳቸው ፡፡

ላይፍ– በቅርቡ የነጻነት ዋጋው ስንት ነው የሚል መጠይቅ ያለው መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡በፓርላማ ንግግር በማድረግ፣በየሳምንቱ በጋዜጦች ላይ አርቲክሎችን ከመጻፍና አንድ ጥራዝ መጽሐፍ በማውጣት መካከል ያለው ልዮነት ምንድን ነው
ግርማ — ምንም ልዮነት የላቸውም፡፡በቀን ውስጥ ያለውን ጊዜ እንደየድርሻቸው ይከፋፈላሉ እንጂ ልዮነት የላቸውም ብዬ አምናለሁ፡፡እንደውም አንዱ ሌላኛውን ይደግፋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ላይፍ — የነጻነት ዋጋው ስንት ነው የሚለው መጽሐፍዎ በዋናነት ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት ምንድን ነው
ግርማ –ያው ሰዎች ለነጻነታቸው ምን ያህል ዋጋ እየከፈሉ እንደሆነ ለማሳየት ነው፡፡በመጽሀፉ ውስጥ በተለያየ ገጸ ባህሪ የተወከሉ ሰዎች አሉበት፡፡ነጋዴዎች፣የተማሩ የሚባሉ፣ሐይማኖተኞችና ባተሌዎች አሉበት፡፡ሁሉም በእጁ ላይ ያለውን ነጻነቱን ተደራድሮበት እየሸጠው ሳይሆን እንዲሁ እያጣው መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ልቦለድ ሳይሆን እውነተኛ ገጠመኝ ነው፡፡ሁሉም ሰው በእጁ ያለውን ነጻነት አሳልፎ እየሰጠ እንደሆነ መጽሐፉ ያሳያል፡፡በእርግጠኝነት መጽሐፉን የሚያነብ ሰው ራሱን አንድ ቦታ ያገኘዋል፡፡
ላይፍ— ‹‹እዚህ አገር ያለውን ፍርሃት 95 ከመቶ የፈጠርነው እኛው ራሳችን ነን›› የሚል መደምደሚያ ላይ በመጽሐፉ ደርሰዋል፡፡የሌለ ነገር ነው የምትፈሩት እያሉን ነው
ግርማ — የሚያስፈራራን ነገር የለም አላልኩም፡፡እኔ ሁልጊዜም 80 ከመቶ የሚሆነውን ፍርሃት የፈጠርነው እኛ ነን እል ነበር ፡፡ነገር ግን አንድ ቀን ጃዋር መሐመድ በሰላማዊ ትግል ዙሪያ ንግግር ሲያደርግ ነው ይህንን ቁጥር ያገኘሁት፡፡ማተኮር ያለብን ፐርሰንቱ ላይ አይደለም፡፡ለምሳሌ መቶ ሰዎች ቢኖሩ ሊያስፈራራው የሚችለው አንዱን ብቻ ነው፡፡ቀሪዎቹ አንዱ ሰው ላይ የደረሰውን በመመልከት የሚፈሩ ናቸው፡፡በተለያየ መንገድ ማስፈራራቱ ሊኖር ይችላል ነገር ግን ብዙዎቻችን የምንፈራው ሌሎቹን እየተመለከትን ነው፡፡በየቀበሌው የሚገኙ ሰዎች የሚበዙት ኢህአዴግ የሆነ ነገር ይጥልልኛል በማለት የተጠጉ ናቸው፡፡እነዚህ ሰዎች ናቸው ወደ የቤቱ እያመሩ ሊያስፈራሩ የሚሞክሩ፡፡ነጻነታችንን ነጻነት በሌላቸው ሰዎች እያስነጠቅን መሆኑን መመልከት አለብን፡፡እስኪ ተመልከት ከፍርሃት የወጡ አንድ ሚልዮን ሰዎች ቢኖሩን ኢህአዴግ እንዴት ነው አንድ ሚልዮኑን ሊያስፈራራ የሚችለው?
ላይፍ — በ2002 በተሳተፉበት ምርጫ ከጎንዎ ሊያገኟቸው ይፈልጓቸው የነበሩ የቅርብ ሰዎችዎን በመፍራታቸው የተነሳ ሊያገኟቸው አለመቻልዎን በመጽሐፍዎ ጠቅሰዋል፡፡እነዚህ ሰዎች መጽሐፉ ከወጣ በኋላ በአንድም በሌላ መንገድ የተናገሩት ነገር ይኖራል?
ግርማ –አይተውት ራሳቸውን ያገኙበት ይሆናል እንጂ እኔን እንዲህ አልነበረም ያለኝ የለም፡፡ደግሞም አይኖርም ምክንያቱም እውነት ነው፡፡እውነት ሲሆን እኮ ብዙም ክርክር አያስነሳም፡፡እነዚህ ሰዎች ብዙ ሚልዮኖችን የሚወክሉ መሆናቸውም መዘንጋት የለበትም፡፡
ላይፍ -ሰዎች የእኛን አገር ፖለቲካ ሲያስቡ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ሴረኝነት ነው፡፡በሴራ ፖለቲካ የተነሳ ብዙ ርቀት መጓዝ አልተቻለም፡፡እርስዎ ደግሞ ሐይማኖተኛ ለመሆንዎ በመጽሐፍዎ ደጋግመው የጠቀሷቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃላት በመመለከት መገመት አያስቸግርም፡፡ፖለቲከኛና ሐይማኖተኛ መሆን በእኛ አገር የሴራ ፖለቲካ ውስጥ ፈታኝ አይሆንም?
ግርማ — በጣም ለብዙ ሰው መናገር የምፈልገው ፖለቲከኛ ለመሆን ውሸታም ሴረኛ መሆን አለማስፈለጉን ነው፡፡ፖለቲከኛ መሆን የሚጠይቀው በመጀመሪያ ሐቀኝነትንና ሴረኛ አለመሆንን ነው፡፡እንደምታስታውሰው በፓርቲው ውስጥ ነጻ ውድድር መኖር አለበት የምለው በድርጅታዊ አሰራር ባለማመኔ ነው፡፡ድርጅታዊ አሰራር ማለት የሆነን ሰው በማንሳት የምታስቀምጥበት ነው፡፡ነገር ግን እችላለሁ የሚል ሰው ተወዳድሮ ማሸነፍ ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ያን ያህል ሐይማኖተኛ አይደለሁም፡፡ክርስቲያን ነኝ፡፡ለእምነት ክብር እሰጣለሁ፡፡ሰው ሁሉ የእኔን እምነት መከተል አለበት አልልም፡፡ነገር ግን ከማያምን የሚያምን የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ለምን ጠንቋይን አይሆንም እምነት ያለው ሰው የሆነ የሚፈራው ነግር እንዳለው አስባለሁ፡፡እግዚአብሄርን ወይም አላህን የሚያምን ሰው በጨለማ የምሰራውን ገልጦ የሚያይ አምላክ አለ ብሎ ስለሚያምን ክፉ ነገር የማድረግ ድፍረት አይኖረውም፡፡
ላይፍ– የፖለቲካ ህይወትዎን በጀመሩበት የኤዴሊ ፓርቲ ውስጥ በነበረ ሴራ ወደ ቅንጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዳይመጡ መደረግዎን በመጽሀፍዎ በማስታወስ ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴው ብመጣ ኖሮ ግን እታሰር ነበር ብለዋል፡፡ይህ በእኔ ያልተፈጸመው አምላክ ስለጠበቀኝ ነው ይላሉ፡፡ነገር በዚያ የ1997 ምርጫ ወቅት ለእስር የተዳረጉ የትግል ጓደኞችዎ እንደመሆናቸው መጠን እኔን አምላክ አስመለጠኝ ማለት ምን ያህል ተገቢ ነው?
ግርማ — እግዚአብሄር የሰው ልጆችን በንፍር ውሃ ባጠፋ ጊዜ በኖህ አማካኝነት በሰራው መርከብ እርሾ ማስቀረቱ አይዘነጋም፡፡መርከቡ ላይ የተሳፈሩ ሰዎች ግን በጠፉ ሰዎች ደስተኛ ነበሩ ማለት አይቻልም፡፡የእኔም እንደዚሁ ነው፡፡በመጽሀፉ ለማሳየት የሞከርኩት ይህንን ነው፡፡ሴራ የሚሰሩ ሰዎች ነበሩ፡፡እነዚህ ሰዎች ባላሰቡት መንገድ እንዲህ አይነት ነገር በመፈጠሩ ለእስር ተዳርገዋል፡፡እኔ አልታሰርኩም፡፡መቼም ብታሰር ጥሩ ነበር ይለኛል ብለህ እንደማትጠብቀኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ላይፍ –የአገሪቱ ህገመንግስት ፌደራላዊ ስርዓት መገንባቱን በማወጅ ሁለት የፌደራል ክልሎችንና ዘጠኝ ክልሎች እንዲቋቋሙ አድርጓል፡፡ስርዓቱ በብሄር ብሄረሰቦች የሚያምን በመሆኑም በዛ ያሉ ብሄር ተኮር ፓርቲዎች ተፈጥረዋል፡፡እርስዎ ደግሞ ብሄር ተኮር ፓርቲዎች ከፓርቲነት ወደ መንግስታዊ ወደልሆኑ ተቋማት እንዲወርዱ መፈለግዎን በመጻህፉ ጠቅሰዋል፡፡አባባልዎ ከነባራዊው የአገሪቱ ሁኔታ ጋር አይጋጭም?
ግርማ – እረ በፍጹም አይጋጭም፡፡በግልጽ መጽሀፉ ላይ እንዳስቀመጥኩት እነዚህ ድርጅቶች የሲቪክ ማህበራት መሆን ይችላሉ፡፡ለምሳሌ በኦሮሞ ላይ ህገ ወጥ ነገር ሲፈጸም እነዚህ ድርጅቶች ተጎዳ የሚሉትን የህብረተሰብ ክፍል በመያዝ ችግሩን ማሳየት ይችላሁ፡፡ፓርቲዎች መመስረት ያለባቸው በአስተሳሰብ እንጂ በብሄር መሆን የለበትም ምክንያቱም የኦሮሞ የአማራ የሚባል አስተሳሰብ የለም፡፡እንደዚህ ከሆነ እኮ አይሁዶች አንድ ፓርቲ ብቻ ይኖራቸው ነበር፡፡አረቦች ጋርም የምናገኘው አንድ ፓርቲ ብቻ ይሆን ነበር፡፡ኦሮሞ ላይ የሚደርስ ችግር እንዲሰማን የግዴታ ኦሮሞ መሆን አይጠበቅብንም፡፡ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡በብሄር ላይ ተመስሮቶ ፓርቲ መፍጠር የሰውን ልዮ አፈጣጠር አለመገንዘብ ነው፡፡
ላይፍ — ህብረ ብሄራዊነትን በመስበክ አንድነትን ለማጎልበት የሚጥሩት የፊውዳል ልጆችና የቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎች ናቸው ይባላል፡፡እርስዎ የፊውዳል ልጅ ይሆኑ እንዴ ?
ግርማ — የፊውዳል ልጅ አይደለሁም፡፡ነገር ግን በባዮሎጂ መደራጀት የለብንም ብዬ አምናለሁ፡፡አይ መደራጀት አለብን የሚሉ ካሉም መብታቸው ነው፡፡ይህንን አከብራለሁ፡፡ሰው ከተሰጠው ነጻነት አንጻር መሳሳት መብቱ ነው የማይችለው ማሳሳት ነው፡፡እስኪ አስበው አንድ የኦሮሞ ልጅ ኦሮሞ ስለሆንኩ ምረጡኝ ቢል አያሳፍርም?፡፡አንድ አማራ እኔ አማራ በመሆኔ ልትመርጡኝ ይገባል በማለት ቢንጎማለል አያሳፍርም?፡፡ ኢትዮጵያ በጣም የተለየች ናት፡፡ኦሮሞ ወይም አማራ ስለሆንኩ ምረጡኝ ብለህ በክልልህ ብትመረጥ አገሪቱን መምራት አትችልም፡፡ኢትዮጵያን ለመምራት ኢትዮጵያዊ መሆን ያስፈልጋል፡፡እነዚህ ድርጅቶች ምንም አይነት ነገር መፍጠር አይችሉም እያልኩኝ አይደለም፡፡ነገር ግን አንድ የኦሮሞ ተወላጅ ከክልሉ ውጪ ያለውን ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ሁሉንም የሚወክል ሆኖ መቅረብ አለበት፡፡ይህን ለማድረግ ደግሞ ከብሄሩ ይልቅ የሁሉንም ልብ ሊያስገኝለት የሚችልን ሃሳብ መያዝ
ላይፍ — አሁን እርስዎ ከሚነግሩን በተቃራኒው ኢትዮጵያ ውስጥ መንደርተኝነት፣ብሄርተኝነትና ክልላዊነት እየተስፋፋ ይገኛል፡፡በዚህ ክበብ ውጪ በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ለሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ነገሮች አስቸጋሪ አይሆኑም?
ግርማ — የህብረ ብሄራዊፓርቲዎች ፈተናም ይህ ነው፡፡ሰዎች ስሜታቸው ተነክቶ የሚነሱት ሐይማኖታቸው ብሄራቸውን የተመለከቱ ነገሮች ሲነካባቸው ነው ይህ በጣም መጥፎ ነገር ነው፡፡ለምሳሌ አንተ የቡርጂ ህዝብ ተወካይ ነኝ ብለህ ብትነሳ በፓርላማው የምታገኘው አንድ ወንበር ነው፡፡ታዲያ እንዴት ነው በአንድ ወንበር በዚህች አገር ተጽእኖ ለመፍጠር የምታስበው? እኔም የወረዳ 6 ህዝባዊ ንቅናቄን በማቋቋም እንዴት ነው አገር መምራት የምችለው?፡፡ በትልቁ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ምንም ለውጥ እንደማያመጡ አልተረዱም፡፡
ላይፍ — በምክትል ፕሬዘዳንትነት የሚመሩት የፓርቲዎ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የፖለቲካ ፍልስፋና ወይም የሚከተለው ርዕዮት ምንድን ነው?
ግርማ — ይህ በግልጽ በፕሮግራማችን ላይ ተቀምጧል፡፡ጋዜጠኞች ስለማትመለከቱ ወይም ከእኔ ለመስማት ካልፈለግክ በስተቀር ማ ለት ነው፡፡አንድነት በግልጽ የሊበራል ዲሞክራሲ አራማጅ ነው፡፡ነገር ግን ይህንን የምንከተለው በኢትዮጵያ ነባራዊ እውነታ ነው፡፡ለምሳሌ ተማሪዎች በሙሉ እየከፈሉ መማር አለባቸው አንልም፡፡ይህ ቢሆን ብዙ ልጆች ትምህርት ቤት መሄድ አይችሉም፡፡ከስምምነት ዲሞክራሲም በተወሰነ ደረጃ የምንወስደው ነገር አለን፡፡እንደ አስተሳሰብ መውሰድ ያለብን ጠቃሚ የሆነውን ነገር ነው፡፡አንድነት ውስጥ በጣም ብሄርተኛ የሆነ ሰው በመግባት ፓርቲው የሆነን ብሄር ሆን ብሎ የመጨቆን አላማ እንደሌለው መመልከት ይችላል፡፡
ላይፍ — ይህንን ጥያቄ ያነሳሁት በቅርቡ የፓርቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ‹‹አንድነት ሊበራል ነኝ ካለ ችግር ይፈጠራል››በማለት በመናገራቸው ነው
ግርማ — እሱ እንግዲህ በቅርቡ ጠቅላላ ጉባዔ ስለምንጠራ ምላሽ ያገኛል፡፡በሌላ መንገድ ካልሆነ ጭልጥ ብለን ነጭ ሊበራል የምንሆንበት ምክንያት ስለሌለ እርሳቸውም የሚወጡበት ነገር የለም፡፡
ላይፍ — ወደ ፓርላማው እንመለስ፣በቅርቡ ባስነበቡን አንድ አርቲክል ፓርላማው በቀኝ ክንፍ ሲያጠቃ ዋለ ብለዋል፡፡ሌሎችም በፓርላማው ውስጥ መጠነኛ የሆነ መነቃቃት ስለመፈጠሩ ይናገራሉ፡፡ይህ መነቃቃት እውነት አቶ መለስ ዜናዊ ከሞቱ በኋላ የተፈጠረ ነው?
ግርማ — ምንም ጥርጥር የለውም እርሱ ስለመሆኑ፡፡ነገር ግን በፓርላማውም ይሁን ከመንገስት ባለስልጣናት ይህ የሆነው የእርሳቸውን ሞት ተከትሎ ነው ይላሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡እነርሱ ሊሉት የሚችሉት ባለፉት ሶስት አመታት የአቅም ግንባት ተካሂዶ በመጨረሻዎቹ ሁለት አመታት ሰራንበት ነው፡፡ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡አቶ መለስ በነበሩበት ግዜ ፓርላማው ምንም አለ ምን እርሳቸው የሚሉት ነገር ብቻ ስለሚፈጸም ለምን እናገራለሁ የሚል ስሜት ነበር፡፡እርሳቸው ከሄዱ በኋላ ግን አቶ ሃይለማርያም ፓርላማውን እንደተቋም መጠቀም ግድ ይላቸዋል፡፡ምክንያቱም እርሳቸው እንደ ቀድሞው ሁሉን ሉጠቀልሉ አይችሉም፡፡እዚህ ላይ ካነሳህው አይቀር ፓርላማው በቀኝ በኩል ሲያጠቃ ውሎ በግራ በኩል ጎል አገባ ብዬ ነበር ነገር ግን አሁን ፓርላማው ያገባው ጎል ተሰርዟል፡፡በእግር ኳስ ጎል ካገባህ በኋላ ጎሉ የሚሰረዘው አመከልክተህ ነው አይደል?እዚህ ግን ጎሉ የተሰረዘው እንዲህ አይደለም፡፡የተሰረዘው ጎል የሚያመጣው ነገር አለው፡፡ፓርላማው በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ቢወስን በግምገማ ውሳኔው የሚታጠፍ ከሆነ ፓርላማው ወደ ቀድሞ ቦታው ሊመለስ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡የአንድ የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት የሚነሳ ጥያቄው በፍትህ ሚኒስትር በኩል ነው፡፡ከዚህ በፊት የአቶ ያረጋል አይሸሹም አለመከሰስ ሲነሳ በህጉ መሰረት አልነበረም አሁንም እንዲህ ይደረግ ተብሎ ነበር ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነበር ፓርላማው የወሰነው ግን አሁን ውሳኔው እንዲታጠፍ ተደርጓል፡፡ሰውዬውም ከአገር ወጥተዋል፡፡በእውነት የ500 ካሬ ጉዳይ አይደለም፡፡አባሉም መሬቱን ከአንዱ ወስደው ለሌላ ሰጥተዋል ነው የተባለው፡፡ለማን ነው የሰጡት ከማን ነው የወሰዱት የሚለውን ነገር እንደ ጋዜጠኛ ማጣራትና ለህዝብ ማሳወቅ የእናንተ ድርሻ ነው፡፡
ላይፍ — በፓርላማው የሚያደርጓቸው ንግግሮችና የሚያቀርቧቸው ሞሽኖች ተቀባይነት አጥተው ወይም የተለየ ትርጉም ተሰጥቷቸው ሲቀርቡ ሲመለከቱ ምን አለበት ፓርላማ ባልገባሁ ብለው አያውቁም?
ግርማ – አላውቅም፡፡ምክንያቱም ከመግባቴም በፊት የማቀርበው ሃሳብ ተቀባይነትን ያገኛል ብዬ አልጠበቅኩም፡፡ነገር ግን ተናድጄ አውቃለሁ ስትናደድ ንግግር ማቋረጥ ትችላለህ እኔ ግን ለመበጥበጥ አልገባሁምና ይህንን ማድረግ አልፈለግኩም፡፡እኔ እዛ ስገባ አማራጭ እንዳለ አውቀው እንዲወስኑ የታሪክ ጨዋታ ለመጫወት ነው የገባሁት፡፡ሁሉም ነገር በታሪክ የሚመዘገብ በመሆኑ በታሪክ ተጠያቂ እንሆናለን፡፡
ላይፍ — በተለያየ አጋጣሚ ከአገር ሲወጡ በውጪ የሚያገኟቸው የሌሎች አገራት የፓርላማ አባላት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በፓርላማ መሆንዎን ሲሰሙ ምን ይልዎታል?
ግርማ — ያው መገረማቸው አይቀርም፡፡አብረውኝ የሚሄዱት የፓርላማ አባላትም እንዲህ አይነት ነገር ሲነሳ ይሸማቀቃሉ እኔ ግን አልሸማቀቅም የሚሸማቀቁት እነርሱ ናቸው፡፡በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ ኢህአዴግ ሜዳውን ክፍት በማድረግ ለመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ የሚጠቅም ነገር ያደርጋል የሚል እምነት ነበረኝ ነገር ግን ምንም ቀዳዳ ሳይፈጥር ሁሉንም አሸንፊያለሁ አለ፡፡ዝግጁነት አለመኖሩን በዚህ አሳይቶናል፡፡ስለዚህ ለ2007 ምርጫ ነጥቀን ለመውሰድ ጠንክረን መስራት ይኖርብናል፡፡እንደ አንድነትም ይህንን ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡
ላይፍ — አትሌት ሃይሌ ገ/ስላሴ በቅርቡ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት መሆን እንደሚፈልግ ይፋ አድርጓል፡፡የአትሌቱን የፕሬዘዳንትነት ፍላጎት እንዴት አገኙት?
ግርማ –ከራሱ ከሃይሌ ጋር ተነጋግሪያለሁ፡፡በመጀመሪያ ሃይሌ ፕሬዘዳንት ለመሆን የፈለገው እንደ አሜሪካ መስሎት ነው፡፡ምንም ስልጣን የሌለው ፕሬዘዳንት ሃይሌ መሆን ይፈልጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡አሁን ግን የፓርላማ አባል ሆኖ የሆነ ነገር ማበርከት ፈልጓል፡፡ነገር ግን በግሉ ተወዳድሮ ፓርላማ ቢገባ ምንም የሚጨምረው ነገር እንደሌለው ነግሬዋለሁ፡፡ሃይሌ ኢህአዴግ መሆን አይችልም ምክንያቱም አስተሳሰቡ የካፒታሊስት ነው፡፡ሃይሌ የአንድነት አባል መሆን ግን ይችላል፡፡የምችለውን በግሌ ማድረግ እችላለሁ ካለ መብቱ ነው፡፡አንዳንድ ሰዎች ሃይሌ ወደ ተቃዋሚዎች ቢመጣ በገንዘብ ይደግፋቸዋል ይላሉ ነገር ግን ይዞ መምጣት ያለበት ሊበራል የሆነ አስተሳሰቡን ነው፡፡ከዚህ ውጪ ግን ሃይሌን በኢህአዴግ መስመር ውስጥ አገኘዋለሁ ብዬ አልጠረጥረውም፡፡ ስልጣን የሌለው ፕሬዘዳንት ከሚሆንም የሪዞርቱ አስተዳዳሪ ቢሆን ይሻለዋል፡፡
ላይፍ — የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በሚል መሪ ቃል ፓርቲዎ ህዝባዊ ንቅናቄ እያደረገ ይገኛል፡፡በአጠቃላይ ተቃዋሚዎች የሚገኙበትን መነቃቃት እንዴት ተመለከቱት?
ግርማ — ብዙዎች አንድነት ንቅናቄውን የጀመረው ከሌሎች ኮርጆ ነው ይላሉ ፡፡ነገር ግን ኮርጀንም ከሆነ ችግር የለብንም፡፡አውነታው ግን ይህ አይደለም እያደረግነው ያለው በስትራቴጂክ ፕላናችን መሰረት ነው፡፡ጎንደርና ደሴ ላይ ያደረግናቸው ሰላማዊ ሰልፎች በመዋቅራችን አማካኝነት የሰራነው ነው፡፡በቀጣይም ይህንን በተለያዮ ክልሎች እናደርጋለን፡፡ሚልዮኖች ከእኛ ጋር ሆነው የሚጠይቁት የተለያዩ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ነው፡፡
ላይፍ — የፓርቲውን ንቅናቄ መጀመር ተከትሎ በዛሚ ሬዲዩ በጋዜጠኞች የክብ ጠረጴዛ ፕሮግራም ሚሚ ስብሃቱ አንድነት ይህንን ንቅናቄ የጀመረው ከውጪ በተለይም ከግንቦት 7 ከግብጽ ካገኘው ገንዘብ ፍርፋሪ እንዲደርሰው አስቦ ነው ብላለች ይህ አለመሆኑን እርስዎ በምን ሊያስረዱ ይችላሉ?
ግርማ — እንኳን ነው የምንላት፡፡በስተርጅና ሚሚ መሆኗን ከማሳየቷ ውጪ እርሷ እንዲህ ብላናለችና አይ እኛ እንዲህ ነን ማለት አንፈልግም፡፡አንድ ወቅት ላይ ሚዲያውን በተመለከተ የሆነ ካውንስል ለማቋቋም መንቀሳቀሷን በተመለከተ ለንባብ የበቃ ጽሁፍ አንብቤ ነበር፡፡ጽሁፉ ካውንስሉ መቋቋሙን ቢደግፍም የሚሚን መኖር ግን ክትፎ በፖፖ ብሎት ነበር፡፡እኔም ከዚህ ውጪ የምለው ነገር የለኝም፡፡
ላይፍ — ገዢው ፓርቲ ንቅናቄውን ከአክራሪነት እያቆራኘው ከመሆኑም በላይ ፖሊስ ወረቀት የሚበትኑ አባሎቻችሁን እያሰረ ነውና ንቅናቄው የሚሳካ ይመስልዎታል?
ግርማ — ንቅናቄው እኮ ይህንንም ለመታገል ታስቦ የተጀመረ ነው፡፡እያንዳንዱ ሰው አምባገነንነትን እምቢ ማለት አለበት፡፡ዋነኛው የንቅናቄው ግብ ከፍርሃት መውጣታችንን ማሳየት ነው፡፡ይህንንም እያደረግን እንደሆነ እናምናለን፡፡
ላይፍ –ህዝባዊ ንቅናቄው የሶስት ወር ዕድሜ እንዳለው ተነግሯል፡፡ከሶስት ወር በኋላ ምን ልታደርጉ ነው?
ግርማ — የሶስት ወሩ ንቅናቄ እንደ መነሻ ነው፡፡መስከረም ላይ ጠቅላላ ጉባዔ ይደረግና የሁለት አመት እንቅስቃሴያችን ይገመገማል፡፡ከዚያም 2007 ምርጫ የምናደርገውን ዝግጅት ህዝብን በሚያሳትፍ መልኩ እንገፋበታለን፡፡እናም ይህ የመጀመሪያ እንጂ በየትኛውም መንገድ የመጨረሻችን አይሆንም፡፡መጽሐፍስ የፈራ ይመለስ ይል የለምን?

No comments:

Post a Comment