Wednesday, August 14, 2013

ኢትዮጵያዊቷ ወደ ቤተሰቦቿ ስልክ ከደወለች በኋላ አሰሪዋ ላይ አደጋ አደረሰች

በመስከረም አያሌው

ኢትዮጵያዊቷ የቤት ሰራተኛ በመካ ወደ ኢትዮጵያ ስልክ ከደወለች በኋላ በአሰሪዋ ላይ ጉዳት በማድረሷ በቁጥጥር ስር ዋለች።
ብሉምበርግ የሳዑዲን ጋዜጣ ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የ17 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ከአሰሪዋ ጋር ለአንድ ዓመት ያህል በሰላም የኖረች ቢሆንም ባለፈው የኢድ አልፈጥር ዋዜማ ግን ወደ ኢትዮጵያ ስልክ ደውላ ከጨረሰች በኋላ ባልታወቀ ምክንያት አሰሪዋ ላይ አደጋ አድርሳለች። ኢትዮጵያዊቷ ለፖሊስ እንደተናገረችውም የ40 ዓመቷ አሰሪዋ አብረው በኖሩበት አንድ ዓመት ውስጥ ምንም አይነት ክፉ ነገር አላደረገችባትም።
አሰሪዋ ለበዓል እቃዎችን ለመግዛት ኢትዮጵያዊቷን ይዛት ወደ መደብር በመሄድ የመደወያ ካርድ ገዝታ ለኢትዮጵያዊቷ በመስጠት ወደ ኢትዮጵያ ደውላ ቤተሰቦቿን እንኳን በሰላም አደረሳችሁ እንድትላቸው ማድረጓን የገለፀው ኦካዝ የተባለው የሳዑዲ ጋዜጣ፤ ኢትዮጵያዊቷ ስልክ ደውላ ከጨረሰች በኋላ በአሰሪዋ ላይ ጥቃቱን ማድረሷን አስነብቧል። ወደ ኢትዮጵያ የደወለችውን ስልክ አናግራ ከጨረሰች ጥቂት ሰዓታት በኋላ ከመታጠቢያ ቤት በመውጣት ላይ የነበረችው አሰሪዋ ላይ በመዝለል ጭንቅላቷን መምታት የጀመረችው ኢትዮጵያዊቷ፤ በመቀጠልም በስለት እጇን፣ ደረቷን፣ አንገቷን፣ ትከሻዋን እና ፊቷን እንደወጋጋቻት ተገልጿል።
ከኢትዮጵያዊቷ እንደምንም ብላ ያመለጠችው አሰሪዋም በክፍሏ ውስጥ ገብታ በሯን ዘግታ በተቀመጠችበት ወንድሟ ደርሶ ጎረቤቶቿ እንዲረዷት አድርጓል። ኢትዮጵያዊቷ በክፍሏ ውስጥ በመጮኽ እና በማጓራት ላይ ወደነበረችው አሰሪዋን ክፍል ለመግባት ከፍተኛ ትግል ስታደርግ እንደነበረም ተዘግቧል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ጎረቤቶች ለፖሊስ ባደረጉት የስልክ ጥሪ ፖሊሶቹ ደርሰው አፓርትመንቱን ሰብረው በመግባት አሰሪዋን ሊያተርፏት ችለዋል። በክፍሏ ውስጥ ከፍተኛ ደም ሲፈሳት የነበረችው አሰሪም በአልኑር ስፔሻሊስት ሆስፒታል ውስጥ በመረዳት ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያዊቷ አደጋውን ለማድረስ  የሚያስችል ምን አይነት ነገር ከኢትዮጵያ እንደሰማች ግን እስከ አሁን አልተደረሰበትም ብሏል ዘገባው።

No comments:

Post a Comment