Thursday, August 8, 2013

የምትገድሉት ደስታን ስለሚሰጣችሁ ነው

(ዳዊት ዳባ)
ሰውን መግደል በፊልም እንደምናየው አይነት ትሽ፤ ትሽ፤ አይነት ቀላል ነገር በጭራሽ አይደለም። እዚህ ጉዳይ ላይ የተደረጉ ጥልቅ የሆኑ ጥናቶች በሙሉ የሚያሳዩት ሆነ አጥኚዎቹ ሚስማሙበት እጅግ በጣም በጣም ከባድ ነግር መሆኑን ነው። ይህን አይነት ገጠመኝ ያላቸው ሰውች በሙሉ ህጋዊ ፖሊስ ሆነ ወታደር፤ ነብሰ ገዳይ ወይ እራስን ለመከላከል ብሎ የፈፀመው ሁሉም ተመኩሯቸው ሲናገሩ ዘግናኝና እጅግ አስፈሪ ጉዳይ እንደሆነ ነው። ብዙዎች ተመልሰው የድሮ ማንነታቸውን መግኘት እንዳልቻሉ ነው የሚመሰክሩት። አባቶቻችን ደም ያለበት ሰው የሚሉት ከመሬት ተነስተው አይደለም።
የብዙዎች ገለፃ ሰውነትህ ውስጥ ያለው ደም በሙሉ አይምሮህ ላይ ይሰባሰባል። ልብህ በርጥሶ የሚወጣ አይነት ነው የሚሰማህ። አይንህ በደም ይሞላል ማየት አትችልም።
ብዥ ይልብሀል። አይምሮህ ማሰብ ያቆማል። የት እንዳለህ ይጠፋብሀል። የሚሉ አይነት ናቸው። ለረጅም ጊዜ የሚያስከትለው ጦስም በጣም ቀላል እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት። ይህ ሁሉ ግን ለመጀመርያ ጊዜ ነው። እንደሁሉም ነገር ሲደጋገም መላመድ ይኖራል። ለተላመዱት እልም ያለ አውሬ፤ ለዛውም እብድ አውሬ ነው የሚሆኑት።
የእስልምና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያዊያንን ከዛሬ በሗላ ብሶታቸውን ባደባባይ ካሰሙ እንገላለን ብለው መንግስት ነን የሚሉ ግለሰቦች መግለጫ በዜና አውታራቸው አስለፍፈው ሰማው። መንግስት ነን ስላሉ ብቻ መንግስት ናቸው ብዬ መቀበል የለብኝም። ላላፉት ሀያ ሁለት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት የሚባል ነገር መኖሩን ለመቀበል ከሚቸገሩት ውስጥ ነኝ። የተለመደውን አይነት የለየላቸው አንባገነን መንግስት ለሚለውም ነው የማትሞሉልኝ። እኔ ብቻ ግን አይደለሁም “መንግስት የለም ወይ” የሚሉት ድምፆች እየበዙና ጎልተው መሰማት መጨመራቸው ያለ በቂ ምክንያት በጭራሽ አይደለም። ዛሬ ነን ብትሉም። መንግስት ናቸው የሚሉም ቢኖሩ። ያገር ክህደት ስለፈፀማችሁ። ለዛውም በተደጋጋሚ። ንፁሀን ዜጎችን በጅምላ የፈጃችሁ ስለሆናችሁ። ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ እንፈጃለን ብላችሁ እየፎከራችሁ ስለሆነ። ዛሬም ባይሆን ጊዜው ሲደርስና ህግ ፊት ስትቆሙ በረከት ስምኦን፤ አዳኖምና ብዙ ተጋዳላይ ተክላይ ተክሉዎች እንዲሁ ሀይለማርያም ደስ አለኝ፤ አባዱላና ደመቀ ምን አልባት ሀይሌም አስገቡኝ እያለ ነው ካስገባችሁት እራጩ ሀይሌ ጀሌ ሆነው እንደየ አስተዋጿቸሁ እንደሚሆን አያወዛግበንም።
ግን መንግስት ሆናችሁስ ቢሆን። እንደውም በአግባቡ ውክልና ያላችሁ ህዝብ ምሩን ብሎ ድምጽ የሰጣቸሁ። መንግስት ስለተሆነ በጅምላ ለመግደል፤ ለማሰርም ሆነ ለመደብደብ መብት ተሰጥቷል ብሎ የነገራችሁ ማን ነው?። በአለም ላይ ካሉም ከነበሩም መንግስታት በጅምላ የመግደልና የማሰር መብት የነበራቸው አሉንስ?። የጨፈጨፉ ቢኖሩም መብት ነበረን ብለው የሞኝ ክርክር ያቀረቡስ?። አቅርበውስ?። ፍቃድ ነበራቸው ተብለው በህግ ፊት ነጻ የወጡ ?። ወይስ መቼ ነው ከመረጣችሁን በሰኘንና ባማረን ጊዜ ሴት፤ ህፃን፤ ጎረምሳ ሳንል በጅምላ እንጨፈጭፋችሗለን፤ እናስራችሗለን ብላችሁ ነግራችሁን ዜጋች ማለፊያ ነው ያልነው። ታዲያ በምን መሰረት ነው ትክክል የሆናችሁ ወይ መብታችሁ መስሎ የተሰማቸሁ?።
“መንግስት እርምጃ ይወስዳል”። ዘረኛ ውላጅ ነብሰ ገዳይ ሁላ። እውነት እውነት እላችሗለው በምንም መመዘኛ ሆነ የህግ አንጻር በጅምላ መግደልና ለማሰር ማሰባችሁ በራሱ ወንጀል ነው። በጅምላ ንፅሀንን መግድል ሁሌም ትክክል ተደርጎ ተወስዶ አያውቅም አይደለምም። ሁሌም ማንም ያድርገው ማን ጥርት ያለ ወንጀል ነው።
ግነ ካልጨፈጨፍን የምትሉ ምን አደረጓችሁ?፤ ምን ጥፋት ፈጸሙ ብላችሁ ነው? ። እምነታችሁን ቀይሩ አትበሉን ስላሉ። ድርጅቶቻችን ከኛ ውስጥ በተውጣጣ ቦርድ ይተዳደር ስላሉ?። ምርጫችን በመስጊዳችን ስላሉ?። ወይስ እንዲመሩን የመረጥናቸውን በማን አለብኝነት ማሰራችሁ ትክክል አይደለም ስላሉ ተደፈርን ብላችሁ ነው?።
ለሁለት አመት ሙሉ ደግመው ደጋግመው ያሉት ይህንኑ ነው። ይህንኑ ቅሬታቸውን ደግሞ ፈጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መስጊዳቸው ውስጥ ሆነው ነው ያሰሙት። መቶ ጊዜ በሚጠጋ አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው። ታዲያ የትኛው ሃሳባቸው ወይ ድርጊታቸው ነው በገፍ ከልገደልናችሁ፤ ሰብስበን ካላሰርናችሁ ተኝተን አናድርም እንድትሉ ያደረጋችሁ። ይህ በዘረኝነት ላልታወረ ዜጋ በሙሉ፤ አለምም የታዘበው የሚመሰከርው እውነት ነው። ታሪክም የዘገበው ይህንኑ ነው። ታዲያ ለምን በጅምላ ልተገሉና ልታሰቃዩ ፈለጋችሁ?።
ይህ መልስ የሚሻ በጣም ትልቁ ጥያቄ ነው። ሁሉም ዜጋ አፅኖት ሰጥቶ ሊመረምረው የሚገባም ጉዳይ ነው። ለምን በጅምላ ፍጅት ለመፈጸም አሰቡ?። በትክክልም ዝግጅታችሁ ብዙ ይናገራል። ስትቋምጡ ነበር። ከሁለት አመት በሗላ አሁን ልትፈፅሙት የምትችሉ ጉዳይ ሆኖ ለምን ተሰማቸሁ? እነዚህ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው። አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ስላይደላችሁ ለጊዜው ከናንተ መልስ አናገኝም። እኛ ግን አግባብ ያለው መልስ ልንሰጥበት ይገባል። እውነተኛውን የውስጥ የአይምሯችሁን ፍርጥርጥ አድርገን ማስቀመጥ አለብን።
ዋንኛው መልስ ያለው እነማናችሁ የሚለው ላይ ነው። ስበሀት፤ በረከት፤ ሳሞራ፤ አቦይ ፀሀይዬ፤ አለማየው አቶምሳ፤ አዲሱ ለገሰ፤ ሀይለማርያም የመሳሰሉ አጫፋሪዎች ጋር አይደላችሁም?። እናንተ ናችሁ እንግዲ እርምጃ ለመውሰድ የወሰናችሁት። እርምጃ ስትሉ በገፍ ልትፈጁ ነው?። በገፍ ልታስሩና ልታሰቃዩ ነው። አሸባሪና መንግስትን በሀይል ለመጣል ስትሉ በደረደራችሁት ምክንያቶች ተነስተን የስልምና እምነት ተከታዮች ችግራቸው ከመንግስታችሁ ጋር እንደሆነ እንድናስብ ትፈልጋላችሁ አይደል?። መንግስታችሁን ለማቆየት ዜጎችን መግደል በራሱ ወንጀል ነው። በእኩል የሚያስቆጣን የምንቃወመውም ቢሆንም መግስታቸውን ለመከላከል ነው ብለን እስካሰብን ግን ችግር የለውም አይደል?። ደም ናፋቂ ልክስክስ ወሾች።
ታዲያ የምንግስታችሁ ጉዳይ ከሆነ የስልምና እምነት ተከታይ ዜጎች ባደባባይ የጠየቋችሁ ጥያቄዎች በጣም ቀላሎች ነበሩ። ጥያቄዎቹን መመለስ በደንብ ትችሉ ነበር። ብትመልሱ መንግስታችን የምትሉት ጉዳይ ላይ በየትኛውም አቅጣጫ የሚያመጣው ምንም ጉዳትም አልነበረም። ጥያቄዎቹ ቀላልና ወሳኝ ስላልነበሩ ለጊዜው መልሳችሁ ያጣችሁትን ቁጥጥርና የበላይነት በሂደት የነበረበት ማድረግስ ጠፍቷችሁ ነው?። ቀጥተኛ ባልሆን ሁኔታ ሊፈጥሩ የሚችሉት ተጽኖዎች ቢኖሩ እንኳ ለጊዜው ለዚህ እልባት ሰጥቶ በሗላ ተያያዥ ችግር ካስከተለ መፍትሄ መስራትን የምታውቁት አሰራር አይደለም። በድጋሚ ታዲያ ለምን ደም ያለበትን ምርጫ አደረጋችሁ?።
መንግስታችሁን ለመከላከል ከሆነ ሌሎችም ብዙ አማራጮች ነበሩ። የውጪ አማካሪዎቻችሁም የተሻሉትን ሌሎች አማራጮች በርግጠኛነት ነግረዋችሗል። ድሮም ሲያማክሯችሁ የነበሩ ለናንተ ቅርብ የሆኑ ሰዎች በአደባባይ አማራጮችን አሳይተዋችሗል። ሙስሊም ዜጎቻችንን እምነታችሁን ቀይሩ ነው እያላችሗቸው ያላችሁት። ይህ በቀላሉ እንደማይሆን ታውቃላችሁ። ለምን ብዙ ንፅሀንን መግደል፤ ብዙ ንፅሀንን ማሰቃየትን የሚፈልገውን መንገድ መረጣችሁ?።
ኢቲቪን ለሚያዳምጥ፤ ሰለጉዳዩ በተለያየ ጊዜ የተናገራችሁትን ለሰማን፤ ጀሀዳዊ ሀረካት፤ የአባታችንን የኑሩ ሁሴን ግድያ የተቀናበረበትን ሁኔታ። የሰጣችሁትን ያየር ሽፋን፤ የተቀደደ ባንዲራ ፖተሊካ፤ ቀድሞውንም ምርጫ ያደረጋችሁት መንገድ ደም ያለበትን መፍጀት የሚያስችሏችሁን መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው። ሌሎችም ብዙ ጠቋሚ መረጃዎች የሚያረጋገረጡት ይህንኑ ነው። ለምን ግን?።
የሰው ልጅ ስልጣን ላይ ሰለወጣ ብቻ የሰው ሂወት ቁብ የማይሰጠውና ፈጅት ፈፃሚ አይሆንም። ሁሌም የሚኖሩትን ተቀናቃኞችን ማስወገጃው መንገድ መግደል ነው ብለው የሚያስቡ ብዙ መሪዎች በርግጥ አሉም ነበሩም ። ሙት አመቱ እየተከበረለት ያለውን ሰውዬ ጨምሮ የኛዎቹ ተጋዳላይ ገዳዮች ንፁሀንን የምትፈጁብት ምክንያት ግን ለስልጣን ላይ ስላለ ስጋት በጭራሽ አይደለም።
ነብስ እንዳወቃችሁ ልትጋደሉ ጨካ ገባችሁ። ላለፉት አርባና ሀምሳ አመታት ሞት ስቃይና ሰቆቃ የበዛበት ሁኔታዎች ውስጥ ነበራችሁ። ሁላችሁም ማለት በሚቻል ሞትና ስቃይ ቀንደኛ ፈጣሪዎችም ነበራችሁ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ምን ያህል የሞተ ሰው ነው ያያችሁት፤ ስንቶቹ ጭንቅላታቸው ፈርሶ ነበር። ስንቶቹስ ደረታቸው ተከፍቶ ነበር። ስንት የተቆረጠ እግር፤የተቆረጠ እጅ ወይ የወጣ አንጎል ነበር ያያችሁት። ሰንቶቹ የምታውቋቸው ነበሩ። ስንት ሰው ተኩሳችሁ ገድላችሗል። ከገደላችሗቸው ስንቶቹ ትዋጓቸው የነበሩ ወገኖቻችሁ ናቸው። ስንቶቹ የምታውቋቸው አጋሮቻችሁ፤ ጓደኞቻችሁ፤ ዘመዶቻችሁ ነበሩ። ብዛታቸው በርግጥ በቁጥር ልታስቀምጧቸው የሚቻላችሁ ነው። የሰው ልጅ ለመሞት ሲያጣጥር ምን ይመስላል?። የሰው ልጅ ስቃይና ህመም ሲበዛበት ምን አይነት ባህሪ ነው ያለው?። ስንቴ የሰውን ልጅ ስቃይ መቋቋም አቅቶት እስኪሞት ድረስ አሰቃይታችሗል?።
አንባቢ ማወቅ ያለበት ወያኔዎች እያንዳንዳቸው ለነዚህና ይህን ለመሰሉ ሌሎች ጥያቄዎች ማስታወስ የቻሉትን ብቻ እንኳ ቢናገሩ ብዙ ደርዘን ገጠመኞችን መናገር የሚችሉ ናቸው። ተስማማንም አልተስማማን እነዚህ ሰዎች የተለዩ ናቸው። ጤናማ አይምሮ ላለን በአገራችን እየሆነ ላለው ነገር ሁሉ ትርጉም የሚሰጥ መረዳት ለመያዝ የሚቸግረን ወናው ምክንያት ይህ ይመስለኛል።
የመግደል፤ ሰቆቃ የመፈፀም፤ በጅምላ የመፍጀት ልምዳቸው የተጋድሎ ጊዜ ከሚሉት የሚነሳና እያደገ እየዳበረ የሄደ ነው። ቤተመንግስቱን ከተቆጣጠሩ በሗላ የፈጸሟቸውን ንፅሗንን መፍጀቶች በሙሉ አንድ በአንድ አውጥተን ብንመረምር አንዳቸውም እነሱ ለክፉ ደርጊታቸው የሰጡት ምክንያት አይደለም እኛ በተለያየ ጊዜ ለፍጅቶቹ ልንሰጣቸው የሞከርናቸው ምክንያቶች በበቂ ሊያስረዱት ወይ ትርጉም እንዲጥ ሊያደርጉት የሚችሉ አይደለም። ለምን?።
በበደኖ፤ በሀረር፤ በአርሲ፤ በጋንቤላ እንዲሁ የጎንደር የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ። የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ። በምርጫ 97 በሗላ በመላው አገሪቱ በይበልጥም በአዲስ አበባ የተፈጸሙትን ፍጅቶች ሌሎችንም አንባቢ አንድ በአንድ እያወጣ እንዚህ ግለሰቦች ፍጅትና ደም ያለበትን ምርጫ ሲያደርጉ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ሁኔታ በርግጥ ነበር ወይ ብሎ እስቲ ይጠይቅ?። ነበሩ የሚባሉት ችግሮች ለስልጣናቸው ወይ በግላቸው በርግጥ የሚያሰጋቸውና የዚህ አይነት ጭፍጨፋ እንዲፈፅሙ የሚያደርጋቸው ነበር ወይ?። ሌሎች አማራጮችስ አልነበራቸውም ወይ? የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አንስቶ መልስ እራስን በነሱ ቦታ አድርጎ ለመስጠት ይሞክር። የሚደረስበት እውነታ የሚገሉት ስለሚያስደስታቸው ልምድ ስላደረጉት ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ነው። በተራ በተራ እያነሳው በስፋት ያልሄድኩበት ፀሁፉን ለለማንዛዛት ነው።
ካስፈለገ ትናንሽ ሊሰኙ ነገር ግን ስለነዚህ ግለሰቦች በጣም ብዙ ሊናገሩ ከሚችሉ አስረጅ ምክንያቶችን መጨመር ይቻላል። መለስ ዜናዊን ጨምሮ ዛሬ መንግሰታችን የሚሉት ብዙዎች ከምርጫ 97 በሗላ የፈፀሙት ፍጅት ላይ በመጀመርያ የቅንጅት መሪዎች በሗላ ላይ ደግሞ
ብርቱካን ነች ንፁሃንን የፈጀችው ብለው አተካራ ከልባቸው ሲገጥሙ እናስታውሳለን። ግራ ግብት እስኪለን። በረከት ስምኦን ቅንድቡ እንኳ ሳይርገበገብ ዜናዊ አልሞተም አይኔን ግንባር ያድርገው ብሎ ሲናግርስ። እኔን ጨምሮ እርግጠኛ ነኝ ብዙዎቻችንን ይህ ሰው አልሞተ ይሆን እንዴ ብለን እንድንጠራጠር አድርጎናል። በደንብ የሚያውቁትን የቀድሞ ባልንጀራውን ጨመሮ ብዙዎችን የበረከት የመዋሸት ችሎታ አስምኗቸዋል። የዚህ አይነት ያልተለመደና አስገራሚ ድርቅና፤ ወሸት፤ ሽምጥጥ አድርጎ የመካድ ባህሪ ከየት መጣ። እጠይቃለው ለምንድነው በጅምላ ሁላችሁም በጣም በተለየ ሁኔታ ልትካኑበት ተቻላቸሁ?።
ኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ሰልፍ በቦንብ ትበትኑ ነበር፤ እስረኛ በአውሬ ታስበሉ ነበር፤ ታክሲ ላይ ወይ ጋዝ ማዲያ ላይ ቦንብ አፈንድታችሁ ንፁሀንን ፈጅታችሗል። ንፁሀንን አስራችሁ የመጨረሻው ድረስ ስቃይ ትፈፅሙና ውስጣዊ ጥንካሬያቸውን ሲሰባበር እያናዘዛችሁ መሳለቃችሁስ። ያልተለመደ አይነት የሆነው የፍቶት ፍላጎታችሁስ?። ይህን የመሰሉ ሌሎችም ብዙ ታምር ሊሰኙ የሚችሉ ጉዶችን ደራርባችሁ አሳይታችሁናል።፡ እንዴት አንድ ጤናማ አይምሮ ያለው ሰው ይህን አይነት ዘግናኝና አስገራሚ ድርጊቶችን ሊፈፅም ይችላል። ለኔ መልሱ በሽተኞች ናችሁ። የምትገሉት ደስታን ስለሚሰጣችሁ ነው። መግደልን ልምድ አድርጋችሗል።በሆነ መንገድ ልናስቆማችሁ ካልቻልን በጭራሽ እየባሰባችሁ ይሄዳል እንጂ አታቆሙም። እራሱ በመግደል የተለከፈ አስገዳይ ሲሆን እንዴትም አድርጎ ስብእና ሊሰማው አይችልም። ምኑስ ሊከብደውና ቆም ብሎ እነዲያስብ ያደርገዋል?።
ለመጀመርያም ለመጨረሻም ጊዜ እሬሳ ያሳያችሁኝ እናንተ ናችሁ። እንደገባችሁ ሰዎች እየገደላችሁ እሬሳ አይነሳ በምትሉበት ጊዜ ነው። እውነት እላችሗለው ጤናማ አይምሮ ላለን ማየቱ በራሱ በጣም ይረብሻል። የህቴ ልጅ ከካናዳ ከናቱ ጋር አገር ቤት ይሄዳል። ጊዜው የፋሲጋ በአል የሚከበረብት አካባቢ ነበር። ለበአሉ ሁለት ቀን ቀደም ብሎ በግ ተገዝቶ ነበር። ልጁ ከበጉ ጋር ጓደኝነት መስርቶ ኗራል። የበአሉ ቀን ጠዋት ከንቅልፉ ሲነሳ በጉ ሲታረድ ያያል። የአስራ ሁለት አመት ልጅ ነው። አምርሮ አለቀሰ፤ አምርሮ አዘነ። ደግሞ ደጋግሞ ልምን ትገሉታላችሁ፤ ምን አደረጋችሁ ብሎ ነበር ሲጠይቅ የነበረው። ሰጋ መብላት የጀመረው ከብዙ ጥረትና አመታት በሗላ ነው። አራጁ ልጅ ያኔ እንዳይሰማ በአማርኛ ያለው እዚህ አገር ላይ ሲያሰኛቸው ሰው የሚያርዱ የነገሱበት መሆኑን አላወክ ነበር።
ይህን ፅሁፍ የፃፍኩት ቅዳሜ ሌሊት ነበር። ሳላበጃጀው እሁድ ከሰአት የሱሳቸውን እንዳደረሱ አነበበኩ። እስከሚቀጥለው አርብ ይጀምራሉ የሚል ግምት አልነበረኝም። አላስቻላቸውም ወገኖቼን ቅዳሜ እለት ፈጆቸው። ከሰማሁበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ሀዘንና ቁጭት እየተሰማኝ ነው። ጮህን እንኳ ይውጣልን። ደምፅችንን የምናሰማበት ሁኔታ ይፈጠር። ለምን በዚህ ጊዜ አሁን ደግሞ ለምን አርሲ የሚለውም በቅድመ ዝግጅት ለመደረጉ አስረጅ ስለሆነ አመችቶኝ ብሄድበት ደስ ይለኛል።
ዳዊት ዳባ

No comments:

Post a Comment