Wednesday, August 7, 2013

ዘሩስ የወያኔ ይሁን. . . ኮትኳቹስ ጥላ ከለላውስ ማነው?

ከዮሃንስ ታደሰ አካ
ህ.ወ.ሃ.ት በታሪክ አጋጣሚ ከእጁ የገባውን ታላቋን ኢትዮጲያን የማስተዳደር (የመግዛት) ዕድል በጥንቃቄ ጉድለት ድንገት እንዳያመልጠው በማሰብ የነደፈው ስትራተጂ ኢትዮጲያ ላይ ሲዘመር የኖረውን እና የኢትዮጲያ ህዝብ በማንኛውም አጋጣሚ ዋጋ ከመክፈል ወደ ኋላ የማያፈገፍግበትን አንድነት ማጥፋት ነበር። ለዚህም መሳሪያ አድርጎ የተጠቀመው የትግራይ ህዝብን ከጎኑ ለማሰለፍ ሲል ሲያቀነቅን የኖረውን የዘር ፖለቲካ በመላው የኢትዮጲያ ምድር መዝራትን ነው።
ኢትዮጲያዊነቱን በህ.ወ.ሃ.ት. ተነጥቆ ብ.አ.ዴ.ን. ( ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ) የተሰኘው ኢ.ህ.ዴ.ን.( ኢትዮጲያ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ) በፍጥነት ፍሬ እንዲያፈራ በህ.ወ.ሃ.ት. ተዘጋጅቶ የተሰጠውን የዘረኝነት ዘር በተከለለት ምድር ላይ ዘርቷል።

ህ.ወ.ሃ.ት በ ብ.አ.ዴ.ን. እና በእድል እየታገዘ ቤተመንግስት ደጃፍ ሲደርስ በምርኮኛ ወታደሮች የተፈጠረው ኦ.ህ.ዴ.ድ.( ኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት) በተከለለት ክልል ላይ በፍጥነት ተቀባይነት አግኝቶ የህ.ወ.ሃ.ትን አላማ የሚያሳካበትን ቁመና መፍጠር እንዲያስችለው በዘሩ ባለቤት በህ.ወ.ሃ.ት. ተዘጋጅቶ የተሰጠውን ልዩ የዘረኝነት ዘር በምድሩ ላይ ዘርቷል።
ከአማራውና ከኦሮሞው ውጭ ሌሎችም ስፋት ያላቸው ጎሳዎች መኖራቸውን ቤተመንግስት ቁጭ ብሎ ያረጋገጠው ህ.ወ.ሃ.ት ያን ሁሉ ጎሳ በአንድነት ጠርንፎ ቀሪው የኢትዮጲያ ህዝብ በተለይም ነፍጠኛው አማራ “በንቀትና በጥላቻ ሲረግጥህ ኑሯል” በሚል ስብከት ደቡብ ላይ የዘረኝነት ዘሩን በደ.ኢ.ህ.ዴ.ን ( ደቡብ ኢትዮጲያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) አዘርቷል።
ፖለቲካን ከወያኔ(ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) ክስተት በኋላ የተዛመደው ወጣቱ ባለማወቅ የተሞላውን ብቻ በቅንነት በማመን፤ ለፖለቲካ ብዙም ሩቅ ያልነበረው ጎልማሳው ከጊዜው ለማትረፍ ሲል በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በመታወር በዘር ፖለቲካው ተስቦ ሳይወጋ ቆስሎ ሳይታመም አቃስቶ ያልበላውን አክኮ በገዛ ምድሩ ላይ ዘረኝነትን ዘርቶታል።
ሰርዓቱን የተቃወሙ ኢትዮጲያውያን ግማሹ ዘርን መሰረት ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመመስረትና በማደራጀት የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. የዘር ፖለቲካ በእንጭጩ እንዳይቀር ኮትኩተዋል። ውሃ አጠጥተዋል።
የዘር ፖለቲካን የተቃወሙ እና ‘ኢትዮጲያ’ ብለው የተነሱት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘርን መሰረት በማድረግ ከተቋቋሙት ተቋዋሚ ፓርቲዎች ጋር አለመግባባትን፣ አለመቻቻልን እና የርስ በርስ ጉሸማን በማዳበር የህ.ወ.ሃ.ት የዘር ፖሊቲካ ጸሃይ እነዳያጠወልገው ንፋስ እንዳይመታው ጥላ ከለላ ሆነዋል።
የተዘራውም ዘር ከላይ በተገለጸው መሰረት በተለያዩ አካላት ድጋፍና እንክብካቤ ስላልተነፈገው አብቦ አፈራ። ግለኝነትን ፣ እኔ እሻልነትን፣ የኔ ይበልጥ ባይነትን፣ የርስ በርስ ጉሸማን፣ የርስ በርስ ድቆሳን የመሳሰሉ ፍሬዎችን አፈራ ። ፍሬውም ፈክቶ ታየ።
ዘርን መሰረት አድርገው የተደራጁ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም እርስ በርስ መስማማት ተሳናቸው። ብሄርን የባሰዉን በአካባቢ በሃይመኖት ወዘተ በመሰነጣጠቅ አለመግባባቱ እንዳይከስም ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ ታዩ።
በአንድነት የሚያምኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁ በኢትዮጲያ ህዝብ ላይ በህ.ወ.ሃ.ት. እየተፈጸመ ካለው ግፍ የግለሰቦች ጉዳይ መዝኖበት ግለሰቦች በተለያዩ አጋጣሚዎች ርእስ ሲሆኑ ታዩ።
ይህ ህ.ወ.ሃ.ት. ዘርቶት የተለያዩ አካላት በማወቅም ባለማወቅም ተንከባክበው ያሳደጉት ፍሬ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ.ን ከጦር ሃይሉ በላይ ከጥቃት ይጠብቀዋል።
ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ይሆናል ብሎ ባልገመተበት ሁኔታ በ 1997 ዓ/ም የህዝብን አንድነት ክፉ በትር በማየት ተደናግጧል። ተመሳሳይ ድንገተኛ አደጋ እንዳይፈጠርም የሚችለውን ሁሉ አድርጓል።
ዛሬ ግን እድሜ እርስ በርስ ለሚዷቀሱለት ተቃዋሚዎቹ አረፍ ብሏል።
ታሪክ ነገ “በኢትዮጵያ ምድር የዘረኝነትን ዘር በመዝራት ኢትዮጲያን የከፋፈለው ህ.ወ.ሃ.ት. ነው።” በማለት ብቻ አንቀጹን አይዘጋውም። “ ህ.ወ.ሃ.ት.ስ ዘሩን ይዝራ ኮትኩቶ፣ አርሞ፣ ውሀ አጠጥቶ እና ጥላ ሁኖ በመንካባከብ ለፍሬ ያበቃው ማነው? ”  በማለት ሳይጠይቅ አያልፍም።
ለኢትዮጲያ ህዝብ ስንል የግል እልሃችንን አሸንፈን በተባበረ ክንድ ህዝባችንን ከህ.ወ.ሃ.ት ቀንበር ነጻ ማውጣት ያቀተን ሁላችንም ቢያንስ ቢያንስ የህ.ወ.ሃ.ት.ን እድሜ በማራዘም ቀዳሚ ተጠያቂዎች ነን።

No comments:

Post a Comment