‘‘በሙስሊሙ ወገኖቻችን ላይ መንግስት እያካሄደ ያለው እስር፣ ድብደባና ግድያ መንግስታዊ የሽብር ተግባር ስለሆነ አጥብቀን እናወግዛለን፣ በአስቸኳይ እንዲገታም እንጠይቃለን’’
ኢትዮጵያ የምትመራበት ሕገ መንግስት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኮንቬንሽንን የሕጉ አካል አድርጎ የተቀበለው ሲሆን ከሕገ መንግስቱ አንቀጽ 14 እስከ 29 ያሉት ሕጎችም የዜጎችን የሕይወትና የአካል ደህንነት፣ የሃይማኖት ነፃነትና የሰብአዊ መብት እኩልነት ክብርና እንዲሁም የመልካም ስምን የሕግ ጥበቃ በዝርዝር ይደነግጋል። እነዚህ በአገሪቱ የበላይ ሕግ ውስጥ የተካተቱ መብቶችን መንግስት የማክበርና የማስከበር ግዴታም እንዳለበት ጨምሮ ተደንግጓል።
የኢሕአዴግ መንግስት ግን ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እነዚህን ሕገ መንግስታዊ መብቶች ሲጥስ ይታያል። የአብዛኛው ሕዝብ ጥያቄ ኢሕአዴግ ራሱ የማያከብረውን ሕገ መንግስት ለምን አወጣው? የሚል ነው። ምክንያቱም ሕገ መንግስቱን መጣስ የዕለት ተዕለት ተግባራቱ እየሆነ መጥቷል፤ እንዲያውም ሕገ መንግስቱን የፃፈውና ያፀደቀው ለይስሙላ በዓለም አቀፍ ማኀበረሰብ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ያሰፈነ መንግስት ለመምሰል እንጂ ከምስረታው ጀምሮ ዲሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሊያሰኘው የሚችል ገፅታ እንደሌለው ግልፅ ሆኗል። የሕዝብን የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች መጣስ የጀመረው ገና ከጅምሩ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ነበር። ለአብነት ለመጥቀስም በንፁሃን የአኙአክ ዜጎች ላይ፣ ቅሬታቸውን በሠላማዊ መንገድ ለመግለፅ በወጡ የአዲስ አበባ እና የሐዋሳ ነዋሪዎች ላይ በአሳሳ፣ በዶዶላና በገርባ ሙስሊም አማኞች ላይ የፈፀማቸው የግድያ ወንጀሎች ጉልህ ማሳያዎች ናቸው። በነዚህ የግድያ ወንጀሎች እስከ ዛሬ የተጠየቀ የመንግስት አካል ወይም ባለሥልጣን የለም፤ ዛሬ ዜጎች በግፍ እየተገደሉ ደማቸው ደመ-ከልብ ሆኖ ሲቀር መንግስት የሕግ ጥበቃ ያደርግልናል የሚለው ተስፋ እየተሟጠጠ ሄዷል።
የዓለም የሰብዓዊ መብት ኮንቬንሽን በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት የፀደቁ የዜጎች መብትን በመደፍጠጥ በፀረ ሽብር ሕግ ሽፋን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ማሰር፣ ማጉላላት፣ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣ የሃይማኖት መሪዎችን በማሰር፣ የዜጎችን በነፃ አስተያየታቸውን የመግለፅ ሕገ መንግስታዊ መብት ከመጣሱም በላይ በቅርቡ በሃይማኖት ጉዳዮች መንግስት ጣልቃ እንደማይገባ የተደነገገውን በመጣስ መንግስት በሚያስተዳድረው ቀበሌ የሃይማኖት መሪዎችን ማስመረጡ፣ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ለመግባቱ ጉልህ ማስረጃ ነው። ይህን የተቃወሙትንና ድምፃችን ይሰማ ያሉ ሰላማዊ የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በሽብርተኛነት ፈርጆ ማሰሩና አሁን በሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን በኮፌሌና በዶዶላ በአሳሳ እንዲሁም በሌሎችም የኦሮሚያ ዞኖችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ያለማስረጃ በማሰርና በመደብደብ የግድያ ወንጀልም ፈጽሟል። የታጠቀ የመንግስት ኃይል ባልታጠቀ ሕዝብ ላይ እስራት፣ ግድያና ድብደባ መፈፀም መንግስታዊ የሽብር ተግባር በመሆኑ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከዚህ ኃላፊነት ከጎደለው ሕገ ወጥ ድርጊቱ ሊቆጠብና ሕገ መንግስቱን ሊያከብር ይገባል።
የእስራቱ፣ የብርበራውና የግድያው ዓላማ ሽብርተኛነትን ወይም አክራሪነትን ለማስወገድ መፍትሔ ነው ብለን አናምንም። ይልቁንም መንግስት በሕገ መንግስቱ በተደነገገው መንገድ ብቻ የዜጎችን የእምነት ነፃነት በማክበር ለሙስሊሙ ሕብረተሰብ ሰላማዊና ሕጋዊ ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ ቢሰጥ ኖሮ ይኸ ሁሉ የዜጎች ሕይወት አይጠፋም ነበር እንላለን። አክራሪነትንና ሽብርተኛነትን ምክንያት በማድረግ የዜጎችን ሕጋዊና ሰላማዊ ተቃውሞ ለመደፍጠጥ የተወሰደውን የጭካኔና ሰብአዊነት የጎደለው ተግባር በመሆኑ አጥብቀን እናወግዛለን። መንግስት በታጣቂዎቹ እየታገዘ የሚጽመው እስራትና ግድያ ለአገር ሠላምና ለሕዝብ ደህንነት እጅግ አስጊ እየሆነ ስለመጣ መንግስት ከዚህ ድርጊቱ እንዲገታ እንጠይቃለን። በዚህ አጋጣሚ ሙስሊሙ ሆነ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢሕአዴግን ኢ-ሕገመንግስታዊ ድርጊት በመገንዘብ ትግሉን በሕጋዊና ሠላማዊ መንገድ አጠናክሮ በመቀጠል አንድነቱንና ሠላማዊ የትግል ትብብሩን እንዲያሳይ ጥሪያችንን እናቀርባለን።መንግስታዊ የሽብር ተግባር በተባበረ ሕጋዊና ሠላማዊ የሕዝብ ትግል ይገታል!
ሰንደቅ ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment