‘‘ውይይትና ድርድር ደከመኝ፣ ሰለቸኝ የማይባልበት ብቸኛው የሰላምና የዴሞክራሲ አማራጭ ነው።’’
የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማኀበረሰብ አካላትና መንግስት በተለያየ መድረክ መፋጠጥ ከጀመሩ ከአስራ ስምንት ወር በላይ ሆኖታል። በአብዛኛው ከአዲስ አበባና አካባቢዋ የሶላት ስግደት ቀን የማያልፈው የመብት ጥያቄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንቅስቃሴው እየሰፋና እያደገ በመሄድ በርካታ ሙስሊሞችን ማካተት ችሏል። እንቅስቃሴውን ለመግታት መንግስት በተከታታይ በወሰደው እርምጃ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የተለያዩ ጉዳቶች ደርሰዋል። በተለይ ደግሞ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ ግጭቱ በስፋትና በቅርጽ እየጎለበተ በመሄድ ወደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በመዛመት በበርካታ ዜጎች ዘንድ አነጋጋሪና አሳሳቢ ጉዳይ ለመሆን በቅቷል።
በኢዴፓ እምነት ዜጎች በሃይማኖታዊም ሆነ በፖለቲካዊ አሊያም በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ የማንሳትና ከመንግስትና ከመንግስታዊ ተቋማት ጋር ወይም በተናጠል የመብት ጥያቄዎችን የማቅረብ፣ የመደራደርና መፍትሄ የመሻት መብታቸው ያለአንዳች ገደብ ሊከበር እንደሚገባ አጠንክሮ ያምናል። ኢዴፓ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመቃወም፣ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የማምለክና የመሳሰሉ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች እንዳይሸረሸሩ ዘብ የሚቆምላቸው አጀንዳዎቹ መሆናቸውም ይታወቃል።
በሌላ በኩል ኢዴፓ እነዚህ የመብት ጥያቄዎች በስምምነት ካልሆነ በስተቀር የሌሎችን ጥቅምና መብት በማይነኩበትና በሕገ-መንግስቱ ላይ በሰፈረው መሰረት መቅረብ፣ መደመጥና አግባብነት ያለውን ፍትሐዊ መልስ ማግኘት እንዳለባቸው ያምናል። ከዚህም በላይ ዜጎች ጥያቄዎቻችን በበቂ ሁኔታ አልተመለሱም ብለው ሲያምኑ ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱ በሕጋዊ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍ፣ የአዳራሽና ሕዝባዊ ስብሰባ በማድረግ በመንግስት ላይ ገንቢ ተጽእኖ በመፍጠር ለጥያቄዎቻቸው መፍትሄ የመሻትና የማግኘት መብታቸው ሊሸረሸርና ሊገሰስ እንደማይገባ ኢዴፓ በጽኑ ያምናል።
መንግስትና ተቋማቱ ዜጎች በሕገ-መንግስቱ ላይ የሰፈሩ መብቶቻቸው ወደ ተግባር እንዲለወጡ ሁኔታዎችን የማመቻቸትና ጥያቄዎቻቸው በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን አቅጣጫ የማሳየት፣ የማገዝና ቅራኔዎችን በሰለጠነ መንገድ በትዕግስት የመፍታት ኃላፊነት አለበት። መንግስት በአጣብቂኝ ውስጥም ሆኖ ቢሆን ከዜጎች የሚቀርቡ የመብት ጥያቄዎች እንዳይጨፈለቁ ጥበቃ ማድረግ ይገባዋል። በተለይ ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም የሚቀርቡ የመብት ጥያቄዎችን ለማስከበር የሚሄድበት ርቀት የዜጎችን የመብት ጥያቄ ለማስተናገድ የሚኖረውን ቁርጠኝነት የምንለካበት ነው። መንግስት በማንኛውም መለኪያ ዜጎች ጥያቄዎቻቸውን በነፃነት የማቅረብ መብታቸው እንዳይታፈን በማድረግ ቁርጠኝነቱን ማሳየት ይጠበቅበታል። አጀንዳዎቹ ተጠልፈዋል ብሎ ሲያምን የችግሩ ምንጮችን ብቻ ለይቶ በማውጣት ቀሪው ዜጋ ጥያቄውን የማስተጋባት መብቱ እንዲቀጥልና መፍትሄ እንዲያገኝ በማድረግ ሕገ-መንግስታዊ ግዴታውን መወጣት አለበት። መንግስት በዚህ የመብት ጥያቄ ሂደት ውስጥ መብታቸውን በአግባቡ መጠቀም ያልቻሉ ዜጎች ቢገኙ እንኳን በዜግነታቸው ተገቢውን ሕጋዊ ጥበቃና እንክብካቤ ሳያጓድልባቸው ሕግ ፊት በማቅረብ ሳይፈረድባቸው የመወንጀል ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን በማስከበር ዋስትና መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።
ኢዴፓ ‘‘መብቶች ሁሉ ግዴታ ያዘሉ መሆናቸው’’ የምናምነውን ያህል የመብት ጥያቄዎች በቅድመ ሁኔታዎች መጨናገፍና መጨፍለቅ እንደሌለባቸው ደግሞ በጥብቅ የምንታገልለት ፍልስፍናችን ከመሆኑም በላይ ስህተት ሊሰራበት የማይገባ ጉዳይ መሆኑን ግልጽ ማድረግ ይፈልጋል።
ከላይ በዝርዝር ያነሳናቸው የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች በመርህ ደረጃ እንደተጠበቁ ሆነው። ካለፉት አስራ ስምንት ወራት ወዲህ በሙስሊሙ ማኀበረሰብ ውስጥ የተነሳውንና እስከ አሁንም የዘለቀውን የመብት ጥያቄ መፍትሄ ሳያገኝ በእንጥልጥል መቆየቱና ከነአካቴውም ስፋት እያገኘ መምጣታቸው መንግስት በተናጠል በሚወስደው የእመቃ እርምጃዎች ጥያቄዎቹ ሊፈቱ እንደማይችሉ ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው። አሁን ለመገንዘብ እንደተቻለውም የመብት ጥያቄዎቹ መልስ ሳያገኙ ለበርካታ ወራት መዝለቃቸው ቅራኔው እየሰፋና መልኩን እየለወጠ ወደ አልተጠበቀ አቅጣጫ እየተገፋ ዜጎቻችንን ለሞት፣ ለአካልና ለንብረት ጉዳት እየዳረገ መሆኑን ኢዴፓ በሃዘኔታ ለመታዘብ ችሏል።
በተለይ ደግሞ በሙስሊሙ ማኀበረሰብ የኢድ አልፈጥር በዓል ላይ የታየው ፍጥጫ፣ ድብደባ፣ መጠነ ሰፊ እስርና እንግልት በማንኛውም መስፈርት ሃይል የተቀላቀለበት ፈጽሞ ያልተገባ እንደነበረ ኢዴፓ ያምናል። በዚህ አጋጣሚም በእለቱ ጉዳት ለደረሰባቸውና ለታሰሩ የሙስሊሙ ማኀበረሰብ አባላትና ቤተሰቦቻቸው የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን መግለጽ ይወዳል። መንግስት የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማኀበረሰብ አባላትን በየበዓላቱ ቀኑ የመብት ጥያቄዎቻቸውን በመያዝ ማብቂያ በሌለው አዙሪትና ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ለሃይል እርምጃ እንዳይጋለጡ ማድረግ እንዳለበት እናምናለን። መንግስት አሁን በእስር ላይ የሚገኙት ሙስሊሞች ያሉበትን ሁኔታ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ኢዴፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
ይህ ሳይሆን ቀርቶ ጥያቄዎቹ ከዚህ በላይ እየተገፉ ከሄዱ የጉዳዩን ጥልቀት በመረዳትም ሆነ ባለመረዳት ወይም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ላልተፈለገ ግጭትና አለመረጋጋት በር መክፈቱ አይቀሬ ነው። በዚህም ምክንያት በጉዳዩ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሚመለከታቸው ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና የሃይማኖት ተቋማት አማካኝነት አጀንዳውን ወደ ውይይት መድረክ መመለስ ጉዳዩ መፍትሄ እንዲያገኝና በቅራኔ የተወጠሩ አካሄዶች እንዲረግቡ መንገድ እንደሚከፍት ኢዴፓ ያምናል። በፍጥጫና በውጥረት ውስጥ ያለን የሕዝብ ጥያቄ ማፈን ጊዜ ከመግዛት ያለፈ ፋይዳ የማይኖረው ከመሆኑም በላይ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ የአጠቃላይ ማህበረሰቡ ጣልቃ ገብነትን መጋበዙ አጠራጣሪ አይደለም።
ከዚህም በላይ እጅግ አደገኛ የሆነው መንገድ ይህንን ክፍተት በመጠቀም በክርስትያንና በሙስሊሙ ማኀበረሰቡ መካከል ልዩነትን የሚፈጥሩና ለቁርሾ የሚዳርጉ አደገኛ ዝንባሌዎች ከየአቅጣጫው እየተደመጡ መምጣታቸው የጉዳዩን አሳሳቢነትና አደገኛነት እንድንገነዘብ የሚረዳ ሆኖ አግኝተነዋል። በኢዴፓ እምነት እንደዚህ ዓይነቶቹ አደገኛ ዝንባሌዎች ምንጫቸውና ባለቤታቸው ማንም ይሁን ማን በሁላችንም የተባበረ ድምጽ ሊወገዙ እንደሚገባ ያምናል።
በመንግስት በኩል በተደጋጋሚ የሚነሳው ስጋት የመብት ጥያቄው የአክራሪ ሃይሎች ሰለባ ሆኗል የሚል ነው። ኢዴፓ ይህ ጥያቄ አሳሳቢ መሆኑን ቢያምንም፤ በተጋነነ ሁኔታ የቀረበ መሆኑን ለመረዳት አዳጋች አይደለም። ኢዴፓ፣ ኢትዮጵያዊያን የዓለም ማኀበረሰብ አካል እንደመሆናችን መጠን የጐረቤት ሃገሮችን ጨምሮ አንዳንድ ሃይሎች የውስጥ ጉዳዮቻችንንና ተፈጥሮ ልዩነቶቻንን አላግባብ በመለጠጥና በማራገብ የስግብግብ አጀንዳቸው ማራመጃ አድርጎ ለመጠቀምና ሃገራችንን ከአደገኛ ሁኔታ ጋር ለማላተም የሚተጉ ሃይሎች የሉም የሚል የዋህ እምነት ያለው ድርጅት አይደለም። ይህም ሆኖ እያለ ለእንደዚህ ዓይነቱ አደጋ አጋልጦ ወይም አመቻችቶ የሚሰጥን ምዕራፍ የሚከፈተው ውስጣዊ ችግሮቻችንን በመደማመጥና በመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለን አቅም ሲዳከም ብቻ እንደሆነ ኢዴፓ ለማሳሰብ ይወዳል።
ከዚህ መሰረታዊ ሃሳብ በመነሳት የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማኀበረሰብ አባላትን ጉዳይ መንግስት እንደገና ወደ ውይይትና ድርድር መድረክ በማምጣት መልስ እንዲገኝ ጥረት እንዲያደርግና የተጀመረውን ፍጥጫን ቅራኔ የሚያረግቡ እርምጃዎችን እንዲወስድ ጥሪያችንን እናቀርባለን። የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማኀበረሰብ አካላትም ጥያቄዎቻቸው መልስ እንዲያገኙ ወደ ውይይትና ድርድር መድረክ መመለሱ ወደ ውጤት የሚወስደው ብቸኛ መንገድ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍጥጫዎቹንና ግጭቶቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያልተገባ ዋጋ እንዳይከፍሉ የድርድርና የውይይቱን መንገድ በቁርጠኝነት እንዲገፉበት ኢዴፓ ጥሪውን ያስተላልፋል። የሃይማኖት ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሙያ ማኀበራትና ማኀበራዊ ተቋማት ይህ ጉዳይ የራሳቸው ጉዳይ መሆኑን ከወዲሁ ተረድተው ቅራኔውን ተቀራርቦ በመወያየት መፍትሄ እንዲያገኝ ገንቢ ግፊትና ጥረት እንዲያደርጉ ኢዴፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
ሰላምና ሕብረ ብሔራዊነት ዓላማችን ነው
የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ሰንደቅ ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment