እንደ ሙስሊምነታችን አላህ(ሱ.ወ) በቁርአኑ ዓላማችን ሊሆን ይገባል ሲል ካሳሰበን አስተምህሮት ውስጥ ለፍትህ መቆም አንዱ ነው። ሙስሊም የፍትህ እጦት በሌሎች ላይ ሲደርስ ‹‹እኔን ምን ገዶኝ›› አይልም። ይልቅስ በራሱ ላይም ሆነ በእሱ ችሎታ ስር ባለው ሁሉ ላይ ፍትህን ያሰፍናል። በእሱ ቀጥተኛ ቁጥጥር ስር በሌሉት ላይ ደግሞ ፍትህ እንዲሰፍን የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ፍትህ እንዲሰፍን እውነትን የህይወት መስመር አድርጎ ይጓዛል።በዝምድናና በጥቅም ግንኙነት ምክንያት ፍትህ እንዳይዛባ ልንታገል ይገባናል። አላህ (ሱ.ወ) በቁርዓን እንዲህ ሲል አስጠንቅቆናል፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በትክክል (ፍትሕ) ቋሚዎች ሁኑ፤ በነፍሶቻችሁ ወይም በወላጆችና በቅርብ ዘመዶች ላይ ቢኾንም እንኳ ለአላህ መስካሪዎች ኹኑ፡፡ ሀብታም ወይም ድኻ ቢኾን አላህ በእነርሱ (ከእናንተ) ይበልጥ ተገቢ ነው፡፡ እንዳታደሉም ዝንባሌን አትከተሉ፡፡
ብታጠምሙም ወይም (መመስከርን) ብትተዉ አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጥ ዐዋቂ ነው፡፡›› (አል ኒሳእ 4÷135)ሌሎች ፍትህ ሲነፈጉ ዝም ብለን፣ ፍትህን በማስፈን ላይ የበኩላችንን ሳንወጣ ቀርተን ተመሳሳይ የፍትህ እጦት እኛኑ ሲገጥመን ድምፃችንን የምናሰማ ከሆነ የቆምነው ለፍትህ ሳይሆን ለራሳችን ጥቅም ብቻ ነው ያስብላል። የተለያዩ ምክንያቶች ለፍትህ መስፈን እንዳንቆም ከማድረግ ሊያግዱን አይገባም። እኛው ራሳችን የፍትህ ያለህ ከሚሉት ወገኖች ያለን ቅራኔ፣ ጥላቻ እና ግጭት ለነኚህ ወገኖች ፍትህ እንዲሰፍንላቸው ከመስራት ከቶውንም ሊያስተጓጉለን አይገባም። አላህ (ሱ.ወ) በቁርዓን እንዲህ ሲል አዞናል፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለአላህ ቀጥተኞች በትክክል መስካሪዎች ኹኑ፡፡ ሕዝቦችንም መጥላት ባለማስተካከል ላይ አይገፋፋችሁ፡፡ አስተካክሉ፡፡ እርሱ (ማስተካከል) ለአላህ ፍራቻ በጣም የቀረበ ነው፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡›› (አል ማኢዳህ 5÷8) ከዚህ የቁርአን ትእዛዝ የምንረዳው የትኛውም ምክንያት ለፍትህ መስፈንና ፍትሃዊ በመሆን ሂደታችን ላይ ከቶውንም ጥላ ሊያጠላ እንደማይገባው ነው።አላሁ አክበር!ሰኞ መስከረም 6/2006
No comments:
Post a Comment