በዘሪሁን ሙሉጌታ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ከ33ቱ ፓርቲዎች ጋር በጋራ በመሆን በመጪው መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚወጣ አስታወቀ። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በበኩሉ ሰልፉ እንዲሳካ ከሰልፉ ዋና አስተባባሪ አንድነት ፓርቲ ባልተናነሰ ሁኔታ ንቁ ተሳታፊ እንደሚሆን ገልጿል።
የአንድነት ፓርቲ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አስራት ጣሴ እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበር አቶ አበባው መሐሪ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት ሰላማዊ ሰልፉ ዋና ዓላማ ህገ-መንግስታዊ ጥሰትን መቃወምና መንግስትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር ለማምጣት ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።
ሰልፉን በዋናነት እያስተባበረ ያለው አንድነት ፓርቲ ለአዲስ አበባ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና የህዝባዊ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ባቀረበው ቅጽ ላይ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በግምት ግማሽ ሚሊዮን (500ሺህ) ሰው እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል። በሰልፉ ላይ መጠሪያቸውን 33 ያደረጉ ወደ 23 የሚሆኑ ፓርቲዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
ቀደም ሲል የአንድነት ፓርቲ በሀገሪቱ ልዩ ልዩ ከተሞች ለሦስት ወራት ያህል ‘‘የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት’’ በሚል ርዕስ ሰላማዊ ሰልፎች ሲያካሂድ ቆይቷል። ከሕዝባዊ ንቅናቄው ዘመቻ መካከል የፀረ-ሽብር ህጉ ይሰረዝ የሚለው ይገኝበታል። ፓርቲው ይህንኑ ዘመቻ ማድረጉንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ፓርቲዎችን ማከራከሩ አይዘነጋም።
በመጪው መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም በሚካሄደው ሰልፍ ላይ ሁሉም ፓርቲዎችን የጋራ መግባባት በደረሱበት ‘‘ህገ-መንግስታዊ ጥሰትን መቃወም’’ የሚል ጥቅል ሃሳብን በማንገብ፣ የፀረ-ሽብር ህጉና ሌሎች አፋኝ ሕጎች እንዲሰረዙ፣ የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቄዬአቸው እንዲመለሱ፣ የሃይማኖት ነፃነት እንዲከበርና የኑሮ ውድነት እና የስራ አጥነት ጥያቄዎች በጎላ መንገድ በሰልፉ ላይ እንደሚንፀባረቁ ከአቶ አስራትና ከአቶ አበባው ገለፃ መረዳት ተችሏል።
‘‘የኢህአዴግ አባል መሆን ከኢትዮጵያዊ ዜግነት በላይ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል’’ ያሉት አቶ አስራት፤ ኢህአዴግ አባል ያልሆነ ብዙሃኑ የሙሉ ዜግነት መብቱን እየተነፈገ ነው ብለዋል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው በሀገሪቱ የሕግ የበላይነት ጠፍቶ ኢ-ህገመንግስታዊነት መስፈኑን የሚያረጋግጥ በመሆኑ፤ ለህግ የበላይነት ለህገ መንግስታዊነት ክብር የሚሰጥ የከተማዋና የአካባቢዋ ህብረተሰብ በሰልፉ ላይ በመውጣት ተቃውሞውን እንዲያሳይ ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የመኢአድ ፕሬዝዳንት ፓርቲያቸው ከ33ቱ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ከዚህ ቀደም በመኢአድ ጽ/ቤት ሕዝባዊ ስብሰባ ማስተባበሩን በማስታወስ መስከረም 19 ቀን በተጠራው ሰልፍ ላይ መላ አባሎቹና መዋቅሩን በማንቀሳቀስ በሰልፉ ላይ በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የሰልፉ አላማ ህብረተሰቡ ያለበትን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ችግሮች ገደባቸው እያለፉ መሆኑን በገሃድ የሚያሳይበትና መንግስትም ከገባበት ኢ-ህገመንግስታዊ አካሄድ ቆም ብሎ ወደ ውይይት እንዲመጣ ለማስገደድ እንደሆነም ከፓርቲ አመራሮቹ ገለፃ መረዳት ተችሏል።
ሰልፉን ለማስተባበርና ስኬታማ ለማድረግ በአንድነት በኩል ልዩ ግብረሃይል መቋቋሙን የጠቀሱት አቶ አስራት፤ ሕዝቡም ያለአንዳች ማወላወል ወደ አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውን እንደሚያሳይም እምነታቸውን ገልፀዋል። ከሰልፉ በኋላ መንግስትና ተቃዋሚዎች በጋዜጣና በሬዲዮ የሚያደርጉትን የአሉባልታ ዘመቻ በማቆም ወደ ህጋዊና በሁሉም ወገኖች ተአማኒነት ወደአለው የውይይት መድረክ ይመጣሉ የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።
“መንግስት አንድነት ሰላማዊ ሰልፍ በጠራበት ዕለት በተመሳሳይ በየቀበሌው ስብሰባ መጥራቱን እንዲሁም በቅርቡ ከሰማይ ወርዷል የተባለ መስቀል በአቃቂ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የገብርኤል ቤተክርስቲያን በዕለቱ ሄዶ እንዲያይ መደረጉ በሰልፉ ላይ ህብረተሰቡ እንዳይገኝ ከወዲሁ የሚደረግ ጥረት ቢሆንም በእኛ በኩል ህብረተሰቡ ያለበትን አንገብጋቢ ችግር ስለሚገነዘብ ሰልፉ ላይ ከመገኘት ወደኋላ አይልም። መንግስት ትንንሽ ምክንያቶችን ሰበብ በማድረግ መሰናክል ለመፍጠር ቢሞክርም የሰልፉ አላማ ይመታል” ሲሉ አቶ አስራት ገልፀዋል።
No comments:
Post a Comment