Thursday, September 5, 2013

ጋዜጠኛ ነኝ !

 ስለሚያገባኝ መረጃ አቀብላለሁ ፣ እጦምራለሁም!
በረጅሙ የአረቡ አለም የስደት ህይዎት በዜጎች የሚደርሰው በደል ገፍቶኝ ፣ ለዜጎቻቸው መብት መከበር የማይተጉ ተወካዮች እያበሳጩኝ መረጃ ቅበላውን የጀመርኩት ጋዜጠኛ ነኝ ። የመንግስት ሃላፊዎች ለቆሙበት ዜጎችን የመጠበቅ ሃላፊነትን ይወጡ ዘንድ የአንድ ለአቅመ አዳም የደረሰ ታዳጊ ወጣት እድሜ በሙያው የገፋሁ ጋዜጠኛ ነኝ ። የወገኖቸን በደል ፣ ስቃይ እና ሰቆቃውን በተጨባጭ መረጃ ለማሳየት የምጥር ጋዜጠኛ ነኝ ። ይህን የማደርገውም የእለት ጉርሴን ከማበስልበት ስራ ደርቤ ባለችኝ ትርፍ ሰአት በመሆኑ ሁሉንም ለመዳሰስ ብቸገርም አቅሜ በፈቀደ መጠን የግፉአኑን ድምጽ ለማሰማት የተጋሁ ኩሩ ዜጋም ነኝ ብየ አምናለሁ! ዜጎች በማይጨበጠው ህልም ተታለው አንዳይሰደዱ ፣ የመንግስት ሃላፊዎች ለከፋው አደጋ ትኩረት እንዲሰጡ የምመክር የማዘክር ጋዜጠኛ ነኝ!

እንደሚሰራ ሰው ስሰራ አልሳሳትም አልልም ፣ እሳሳታለሁ ፣ ላጠፋሁት ይቅርታ እጠይቃለሁ ! ይህን ስል ግን በሙያው ክህሎት ተክኘ የማቀርባቸው መጣጥፎች የስነ ጽሁፍ ውበት ሚዛንን መምታት አለመምታታቸው ስህተት ሆኖ ይቅርታ ቢያስጠይቅም፣የከፋ ስህተት ሆኖ አያስጨንቀኝም! ከጊዜ እጥረትና ትኩረት ካለመስጠት በመነጨ መረጃዎችን የማቀርብባቸው መጣጥፎች አልፎ አልፎ በፊደል ግድፈቶች የታጨቁ ስለመሆናቸው አስማማለሁ። ይህንን ለማስተካከልም ከይቅርታ ባለፈ በቀጣይ ለማረም ጥረት አደርጋለሁ ። ለእነኘህ ግድፈቶች ይቅርታ ብጠይቅም በስደተኛ ዙሪያ ማቀርባቸው መረጃዎች ምንጭ ግፉአን የጉዳዩ ባለቤቶቹንና የቅርብ አማኞን መሰረት ያደረጉ ናቸውና የተዛቡ መረጃዎችን ናቸውና ይቅርታ የሚያስጠይቀኝን ምክንያት ቢያንስ እስካሁን አላገኘሁም !
መረጃየ የማይጥም የማይስማማቸው ግለሰቦችንና ሹሞችን እውነቱን በመረጃ ለማስረዳት እሞክራለሁ ። እውነቱን መቀበል ለማይፈልጉት ባለጊዜዎችን ማሰረዳት ግን ከባድ ከድንጋይ ላይ ውሃ ማፍሰስ እየሆነብኝ እቸገራለሁ ። ሲቃወሙኝ መረጃን ዋቢ ሳያደርጉ የማቀርባቸው መረጃዎች " የሃገርን ገጽታ " የሚያበላሹ ናቸው ይሉኛል። እኔ በዚህ አልሰማማምና... ገጽታን የማበላሸው የዜጎች መብት ይከበር መንግስት የዜጎቹን መብት ያስከብር ስል ሃላፊዎች ሃላፊነታችሁን ተወጡ የምለው ዜጋ ሳልሆን የዜጎችን ጩኸት የማትሰሙት ፣ በተከበርንበት ስማችን ለመርከሱ ምክንያት ሆናችሁ በአረቡ መገናኛ ብዙሃን ገጽታችን የምታበላሹት አናንተ ናችሁ ...እላቸዋለሁ!
የጋዜጠኝነቱን ሙያ ከነፍሴ ጋር የተያያዘ ፍቅር ይኑረው አንጅ በአረብ ሃገር የእለት ጉርሴን ከማገኝበት ስራ ውጭ ባለኝ ትርፍ ጊዜ በሙያው የመግፋቴ ምስጢር ከመግቢያየ የገለጽኩት ነው። እርግጥ ነው በስደቱ አለም በገሃድ የማየው የመብት ረገጣና ውስጤን ሲያድማው የመንግስታችን ተወካዮች በመብት ጥበቃው አለመትጋትን አልቀበል ያልኩ ጋዜጠኛ ነኝ!!! በማቀርበው መረጃ ተገፊ ስደተኞችን ፣ አዘዋዋሪ ደላሎችን እና የመንግስት ሃላፊዎች ለመድረስ እሞክራለሁ ! በእኔና በመሰሎቸ የሚስተጋባው የወገን "የድረሱልኝ!" ጥሪ መሪር ድምጽ አልተሰማ ይሆናል! ተስፋ ግን አልቆርጥም ! "ግፍ መከራ ሰቆቃው ይቁም !" የምል ጋዜጠኛ ነኝና ነገን በተስፋ እኖራለሁ ! አዎ ጋዜጠኛ ነኝ!
ምስጋና : የውስጤን የታመቀ ስሜት ጨልፊ እንዳዎጣው ምክንያት ለሆንከው ወዳጀ ለአብርሃ ደስታ ምስጋናየ ይድረስህ !
ስለሚያገባኝ ለሐገሬ ብሩህ መጻኤ ህይዎት አልማለሁ ፣ የወገኔ የስደት መከራ ቀንበር እስኪዎርድ ለሚደርስብኝ ማናቸው አደጋ ሳልሳሳ ሰብዕና ሲዳጥ አደንደማይሻ ዜጋና ጋዜጠኛ መረጃ አቀብላለሁ! እጦምርማለሁ!
አክባሪዎ
ነቢዩ ሲራክ አባላለሁ ! ከሳውዲ አረቢያ

No comments:

Post a Comment